Thursday, November 5, 2015

”የኢትዮጵያ ህዝብ አይንና ጆሮ ” ከድጡ ወደ ማጡ

ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም ለፕሮፈሰር ጌታቸው ሀይሌና ለሌሎችም በማለት ያስነበበውን ይቅርታ መሰል መጣጥፍ በፌስቡክ ተለቆ ስላየሁት ደጋግሜ አነበብኩት። በመጀመሪያ ”ሰው ማለት ሰው የሚሆን ነው ሰው የጠፋ እለት” እንዲሉ የፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ ምርጥና አፋጣኝ ፅሁፍ ምን ይህል ቅጥፈት ቢበዛም ቁጥራቸው ትንሽም ቢሆን ውነተኞች እንዳሉ አስመስክረዋልና ምስጋናየ ይድረሳቸው። አንባቢዋቼ ለነገሩ ግንዛቤ እንዲኖራችሁ በማሰብ መንስዔውን ለመጠቆም እሞክራለሁ።

ባለፈው የሳምንቱ እንግዳ በተባለ የኢሳት ፕሮግራም የታሪክ ተመራማሪ በሚል ሽፋን ጋዜጠኛ ፋሲል ዶክተር ላጲሶን በቃለ መጠይቅ አቅርቦ አማራን እንዳይበላ እንዳይዘራ አድርገው ይዘልፋሉ ያጣጥላሉ። እሳቸውም እንደ ታሪክ ምሁር ሳይሆን እንደ አንድ አማራን አጥብቆ የሚጠላ ጎጠኛ አማራው የሰራውን፣ ታሪኩን፣ የፃፈውን ሁሉ በማዋደቅና በማናናቅ ታሪክ አልባ ከማድረጋቸውም በላይ አዲስ ታሪክ ሊሰሩ እንዳሰቡ አሳውቀውናል። እንግዲህ የሄ የቀረበው ”የኢትዮጵያ ህዝብ አይንና ጆሮ ነኝ” በሚለው ኢሳት ነው። ያኔ ታዲያ ጋዜጠኛ ፋሲል ተጠያቂው የተጠየቁትን ትተው ማለት የፈለጉትን ሲቀባጥሩ ሁሉንም በፀጋ ተቀብሏል። ኢሳትም እንደልማዱ አማራና ኢትዮጵያዊነት ሲወቀጥ በጀ ብሎ አለፈው። ምክንያቱም እራሱን የኢትዮጵያ ህዝብ አይንና ጆሮ ነኝ የሚለው ኢሳት የግንቦት ሰባት ልሳን ብሎም በዘር የተደራጁና ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ አጥብቀው የሚተጉ ቡድኖች ጠበቃ በመሆኑ ነው። 

ስለሆነም በኢትዮጵያ አንድነት የማያምኑና አማራውን በሀሰት በጡት ቆራጭነት በበዳይነት የሚወነጅሉት እነ ተስፋየ ገብረ አብና አያሌ አገር አጥፊዎች ሲስተናገዱ ለሀገርና ለወገን የሚያስቡ ውነቱን ውነት ሀሰቱን ሀሰት በማለት የሚታወቁት እነ አቶ ጌታቸው ረዳና ዶክተር አሰፋ ነጋሽ ፕሮፌሰር ሀይሌ ላሬቦ ወዘተ የመሰሉ ምርጥ የቁርጥ ቀን ልጆች በኢሳት አካባቢ ዝር እንዳይሉ በጥብቅ ይከለከላሉ። 

ለዚህም በቂ መረጃ እንዲሆነኝ ከራሱ ከፋሲል ፅሁፍ ብነሳ፣ ፋሲል በፅሁፉ ላይ ፕሮፌሰር ጌታቸው በኢሳት የሚፈፀመውን በደል ታዝበው ትክክል አለመሆናቸውን ሲገልፁ ከታሪክ በማጣቀስ ከታሪክ ማህደር ያገኙትና በፅሁፋቸው ላይ ያሰፈሩት ” "አረሚዎች ኦሮሞዎች) የክርስቲያኑን ሀገር (ዋካትን፣ ጠጠራን፣ ምድረ በረሐን፣ መቅደላን) ሊያወድሙ ተመካክረው ከብዙ ቦታ ዋጃ ላይ ከተቱ። ምክንያቱም፣ አረሚዎች፣ (አዲስ ንጉሥ) ሲያንግሡ የነገሠው አገር የማውደም ልምድ አላቸው። በዚያን ጊዜም ዳዩ ዳባ የሚሉት ነግሦ ነበረ። አገር የሚያወድሙበትና ጦር የሚያውጁት በኅዳር ወር በሊቀ መላእክት የቅዱስ ሚካኤል በዐል ዕለት ነበር። . . . እመቤታችን ማርያም አረመኔዎቹ አገሯን ለማጥፋት ጨክነው እንደተነሡ ስታይ፥ሳያስቡት፣ ወደምድረ አዳል መርታ ጠላቶቻቸው (ሙስሊሞቹ) እጅ ላይ ጣለቻቸው። ከ12 ነገሥታት የጎሳ መሪዎች) አንድ ንጉሥ ብቻ ተረፈ፤ ከሠራዊቱም አንዳንድ ለወሬ ነጋሪ ተርፎ ይሆናል።" የሚል ይገኝበታል።

ፋሲል ታዲያ አሁንም ይህ ጽሁፍ ፕሮፌሰር ጌታቸው.ኢሳት ላይ ልናገረው ቢሉ የሚፈጥረውን አደጋ ተመልከቱ ባማለት ያስፈራራናል። ነገሩም በሁላችንም ዘንድ ሰርፆ ገብቶ እንዲዘገንነን ለማድረግ ይሞክራል። ውነተኛ ታሪክ ምኑ ነው የሚያሳፍረው? ምኑስ ነው የሚያስፈራው? አንዳንዴ ታሪክን እንደታሪክ ተቀብሎ ማለፍ የተሳነው ሁሉ ተሰብስቦ ውነት አይተንፈስ፣ ተበደልን የሚሉት ውሸትም ቢሆን ይውጣላቸው ብሎ ማጃጃል አለበለዚያም የኦሮሞ ነፃ አውጭ ነን ባይ ምሁር ተገዝቻለሁ ጠላቴ አማራ ገዝቶኛል ስላለ ሀይለኛ ንጉስ ነበራችሁ ብሎ መንገሩ የማያውቁትን መንገር አላዋቂነታቸውን ስለሚያሳይ ይቅር ማለት ይሆን? ለማንኛውም በነጋ በጠባ ምስኪን አማራ ሲፈናቀል ሲገደል ሲታረድ ከገደል ሲወረወር ገዳዩን ወዳጅ ከማድረግ ባለፈ ውነት ተድበስብሶ አጥፊዎች ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ የሚንቆለጳጰሱበት መድረክ ማመቻቸት የጥፋት መልክተኛ መሆን ይመስለኛል።

ወደጭብጤ ልመለስና ዶ/ር ላጲሶ ውነትም እንደ ስማቸው ላጲስ በመሆን ታሪኩን ሁሉ ”ራሳቸው የፃፉትን ሳይቀር” የሚፃረር የማጥፋት ዘመቻ በማካሄዳቸው ኢሳት ከውነት አንፃር ሌላ ታሪክ አዋቂ ለማቅረብ ባይሞክርም ፋሲል እንዳስነበበው ከሆነ የሚረሽ ወገኔ ሊቀመንበር አቶ ተክሌ የሻው እባካችሁ ፕሮፌሰሩ አውቀው ይሁን ሳያውቁ የሳቱዋቸው ጉዳዮች ስላሉ እነዚያ እንዲስተካከሉ ሃሳብ ልስጥ ብለው ለኢሳት የኢሜል ማመልከቻ ይልካሉ። ቀጥለውም ደግሞ የኢሳትን መልካም ፈቃደኛነት ሲያገኙ በምን በምን ላይ መልስ መስጠት እንደሚፈልጉ የሚያብራራ መልእክት ይልካሉ። 

ጋዜጠጠኛ ፋሲል የአቶ ተክሌን ፅሁፍ አስመልክትቶ የሚከተለው ይለናል። 

”ጽሁፉን አነበብኩትና የተሰማኝን ጻፍኩላቸው። አንደኛውን አስተያየት ተቀበሉት፣ ሁለተኛውን ግን " እርሱን ለኔ ተወው " አሉኝ። ይሄ ነገር አደገኛ መሆኑን ከኢዲቶሪያል ፖሊሲያችንም አንጻር ማስተላለፍ እንደማይቻል ጻፍኩላቸው። ይህንን አደገኛ የተባለውን ጽሁፍ እዚህ ላይ የማልጠቅሰው ለእርሳቸው ካለኝ አክብሮት አንጻርና እሳቸው ይፋ አድርገው ያላሉትን ማድረግ ስለሌብኝ ነው። ባልደረቦቼን አማከርኳቸው። "ቃለምልልሱን መሰረዝ" የሚለው አንድ አማራጭ ነበር፤ ይህ ደግሞ ፈጽሞ የማይሞከር ነው፤ ለሃሳብ ነጻነት የሚታገሉ ሰዎች ፣ የሰዎች ሃሳብ የሚያፍኑ ከሆነ ትግላቸው የውሸት ነው ማለት ነው ። ይህንን ንግግር ቆርጬ ባስቀረው ደግሞ "ኢሳት ሃሳባችንን አፈነ፣ ቆርጦ አስቀረ" የሚል የአፈና ዘመቻ ይከፈትበታል። ይህም ሌላ ፈተና ነውስለዚህ የነበረኝ አማራጭ በተቻለኝ መጠን ህዝብን ለግጭት የሚያነሳሳ ነገር እንዳይናገሩ መቆጣጠር ነበር። አውቀው ያደርጉታል ብዬ ባላምንም < ይህን ባይናገሩት ይሻላል" ስላቸው፣ እሱን በኔ ተወው ማለታቸው ፍርሃት ለቀቀብኝ። እውነት ለመናገር ወደ መጨረሻ አካባቢ ጣልቃ እገባ የነበረው በመጨረሻ ቅደም ተከተል ያስቀመጡትን እንዳይናገሩ እና በዋና ዋና ቅሬታዎች ላይ ብቻ አትኩረው የተነገረው ሁሉ ከውነት የራቀ ነውና መልስ ልስጥበት ስሜታዊ ወይም አነሳሽ የሆኑት ቃላትን እንዳይጠቀሙ ለማድረግ እንጅ ለሌላ አይደለም። አቶ ተክሌ ያን ጽሁፍ አስቀድመው ባይልኩልኝ ኖሮ እኔም ስጨነቅ ባልሰነበትኩ፤ እሳቸውም ያሰቡትን ተናግረው፣ እዳውን ለእኔ ትተው፣ ይጨርሱ ነበር። ዞሮ ዞሮ አደገኛ ያልኩትን ሃሳብ ቆርጨ ማስቀረቴ ስለማይቀር፣ ኢሳትም "ሃሳባቸውን ቆረጠባቸው በሚል ከመተቼት አያመልጥም ነበር ። ለነገሩ፣ ጽሁፍ አዘጋጅቶ በዚህ ቅደም ተከተል ቢሆንልኝ እመርጣለሁ የሚል መልዕክት መላኩም ትክክል አልነበረም። እንዲያውም "አቶ ተክሌ ኢሳትን አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት ብለው ነው ይህን ያጻፉት ወይስ ሌላ ምክንያት ይኖራቸው ይሆን እያልኩ ብዙ አውጥቼ አውርጃለሁ።”

 እንግዲህ ወገኖቼ ልብ በሉልኝ እኔ ከዚህ ከፋሲል ፅሁፍ የምረዳው እነ ኢሳያስ አፈወርቂን እነ ላጲሶን ሲጠይቅ ትህትና የተላበሰው ጋዜጠኛ ”ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን እውጭ ታሳድራለች እንዲሉ” የአቶ ተክሌ ባላንጣ ሆኖ መቅረቡ እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው መሆኑን ነው። ይህ ደግሞ የአማራ ጠላት በሌላ አነጋገር ”የእውነት ጠላት” አፉን በከፈተ ቁጥር ያለምንም ማስረጃ ማብጠልጠልና መወንጀል በሚፈቀድበት ኢሳት እንደ አቶ ተክሌ አይነት ይቆሙለት አላማ አማራው ከተነጣጠረበት የጥፋት ዘመቻ ለመከላከል በመሆኑ እባካችሁ ውነቱ ይኸ ነው የሚል ሰው ከኢሳት ኢዲቶሪያል ፖሊሲ አንጻር አደገኛ ከየተወገዘ መሆኑን ነው። በዚያ ቃለ ንዝንዝ ላይ ግን በጣም አስደናቂው ነገር የአቶ ተክሌ ትዕግስትና ፅናት ”ተውማ ፋሲል በዚህ ላይ ዶክተር ላጲሶ መልስ ይስጡበት አንተ የጋዜጠኛ ስራ ስራ” እያሉ በተደጋጋሚ ሲማፀኑት መስማት የአቶ ተክሌን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እውቀታቸው ጥልቅና ሁለገብ መሆኑን በብቃት ያስመሰከረ ድል መሆኑ ነው። 

በአንፃሩ ደግሞ ፋሲል እንደዛ አላስተነፍስ ብሎ የጋዜጠኝነት ስነምግባር በጎደለው መልኩ ሲነተርካቸውና ካፋቸው ሲቀማቸው የነበረው ጠፋት ሳያንስ ጥፋቱን ማረም ሲገባው ፅሁፍ አሽሞንሙኖ ማቅረቡና ልክ መሆኑን መግለፁ ቁሜለታለሁ ከሚለው ኢትዮጵያዊነት ጋር የማይጣጣም ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
 ምክንያቴም የሚከተለው ይሆናል።

  • ፋሲል በጥያቄው “የሠርቶአደር ጋዜጣ አዘጋጅ ነበሩ ይባላል። እውነት ይሁን ውሸት አላውቅም “ ብሎ የጠየቀው በቀጣይነት ከሚያቀርበው ጥያቄ ጋር ግንኙነት ስለነበረው ሳይሆን ”ደርግ” ብሎ አቶ ተክሌን ለማሸማቀቅ ነበር። ለዚህም ነው ከማስተካከያ ተብየ ፅሁፉ ውስጥ ያላካተተው። ለነገሩ ኢሳትም በአማራ ጉዳይ ይበረታል እንጅ የኢሳት እንግዶች እነ ካሳ ከበደ፥ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ፣ ዶር ላጶሶ ደርግ አልነበሩምን። ወያኔስ የነበሩት የኢሳት አባል አይደሉምን። አማራን የገደሉትና ያስገደሉት የኦነግ ባለስልጣናት፣ አሁንም አማራና ክርስቲያን በሜጫ አንገት እንቆርጣለን የሚሉት እነ ጁሀር ሙሀመድ መምነሽነሻ አደለምን! በኢሳት የደርግና የወያኔ ስራ አስፈጻሚ የነበሩ ግለሰቦች በክብርና በነፃነት በሚስተናገዱበት ኢሳት አቶ ተክሌ የሻውን የኋላ ታሪካቸውን ያለቦታው በመጎተት መጥፎና አሳፋሪ ለማስመሰል መጣር ግን ያማል። ፣

  • ፋሲል በፅሁፉ እንደገለፀው ”ይህንን ንግግር ቆርጬ ባስቀረው ደግሞ "ኢሳት ሃሳባችንን አፈነ፣ ቆርጦ አስቀረ" የሚል የአፈና ዘመቻ ይከፈትበታል። ይህም ሌላ ፈተና ነው። ስለዚህ የነበረኝ አማራጭ በተቻለኝ መጠን ህዝብን ለግጭት የሚያነሳሳ ነገር እንዳይናገሩ መቆጣጠር ነበር።” ይለናል። ይህ የሚያሳየው መልዕክቱ እንዲተላለፍ የተደረገው የኢትዮጵያ ህዝብ አይንና ጆሮ ስለሆኑ ትክክለኛውን ለማቅረብ በመፈለግ ሳይሆን ሀሜትን በመፍራትና ለኢሳት የሚገፈግፉት አማሮች ቅር እንዳይላቸውና ጥቅማጥቅሙ እንዳይቋረጥ ይመስላል። 

  •  ፋሲል ”ለነገሩ፣ ጽሁፍ አዘጋጅቶ በዚህ ቅደም ተከተል ቢሆንልኝ እመርጣለሁ የሚል መልዕክት መላኩም ትክክል አልነበረም። እንዲያውም "አቶ ተክሌ ኢሳትን አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት ብለው ነው ይህን ያጻፉት ወይስ ሌላ ምክንያት ይኖራቸው ይሆን እያልኩ ብዙ አውጥቼ አውርጃለሁ።” ይለናል። አቶ ተክሌ የሚመልሱት ዶ/ሩ በተናገሩት ጭብጥ ላይ ተመርኩዘው ስለሆነ ቅደም ተከተል ማስያዝ ግድ ይላቸዋል። ታዲያ በቅደም ተከተል አስቀምጠው የሚፈልጉትን ነጥብ ቢያሳውቁ ስተቱ ከምን ላይ ነው? በፋሲል አገላለፅ ግን ሁሉንም ነገር ሲያካብደው ጦርሜዳ ገብቻለሁ ያለው ግንቦት ሰባትም የአቶ ተክሌን ንግግር ያህል ጠላት የሚያርበደብድ አይመስልም። ይሄ ደግሞ ወያኔዎች የአማራን አከርካሪ መታን ከሚሉት ብዙም ልዩነት አላየሁበትም። 

  • አቶ ተክሌ በፅሁፍ የላኩለትን ነገር ምን እንደሆነ ሳይገልጽ ሾላ አድፍን አደገኛና ሕዝብ ከሕዝብ የሚያጋጭ በማስመሰል ቃለንዝንዙም የተደረገበት ምክንያት ከእርሳቸው ፅሁፍ እንደተረዳው መርዙ ከአፋቸው እንዳያመልጥ ነው ብሎ መቀባጠሩ ከታማኒነቱ ይልቅ በቃላት የተጠቀለለ ጥበባዊ መርዝ መርጨቱን ያሳያል።

  •  ሌላውና መዘንጋት የሌለበት የግል ማስታወሻ በሚል ርዕስ ከስር ያሰፈረው ፅሁፍ ደግሞ እራሱን እንደ ጲላጦስ ንፁህ አድርጎ አቶ ተክሌን ዘረኛ ለማስመሰል የጣረ ያስመስለዋል። ምክንያቱም እንደዛ ባያደርግ ኖሮ አቶ ተክሌ ከሞቀበት ሳያጨበጭቡ ለሚፈናቀለው ለሚታረደው ለሚሰደደው ዘር እንዳይተካ ለሚደረገውና ታዛቢ ላጣው አማራ ጠበቃ ሆኖ በስቪክ መደራጀትና መደገፋቸው ሊያስወቅሳቸው አይገባም ነበር።


 የኢትዮጵያ ህዝብ መቸስ ካጋጠመው የከፋ የወያኔ ቀንበር ለመላቀቅ የማያደርገው ጥረት የማይከፍለው መሰዋትነት የለውምና ተስፋን ስንቅ አድርጎ ቆርጨ ተነስቻለሁ ያለውን ሁሉ ለመደገፍ እውቀቱንም ገንዘቡንም ጉልበቱንም በቅንነት ይለግሳል። ከነዚህም ተስፋ ከተጣለባቸው ድርጅቶች መካከል አንዱ ”የኢትዮጵያ ህዝብ አይንና ጆሮ ”የተባለለት ኢሳት አንዱ ነው::

 ኢሳት ደግሞ አንዱን ልጅ አንዱን የእንጀራ ልጅ በማድረግ የሚያደርገው አድሎ ከወዲሁ ከልታረመ መቸም ቢሆን የኢትዮጵያ ህዝብ አይንና ጆሮ ለመሆን ከማስመሰል ባለፈ አይንና ጆሮ ሆኖ አይዘልቅም። ያው እንደተለመደው የተንሸዋረረ አይንና መስማት የተሳነው አጣርቶ የማይሰማ ጆሮ እንደሆነ ይቀራል። ኢሳቶች ደግሞ አማራን ያላካተተ ኢትዮጵያዊነት የትም አያደርስምና ከአማራው ላይ የጥፋት በትራቸውን ሊያቆሙ፣ በአማራው ላይ ጫና የሚያሳድር የተሳሳተና ከውነት የራቀ መልዕክት መተላለፉን ሊገቱ ግድ ይላል። አማራው ችሎ ችሎ በቃኝ ብሎ ፊቱን ከኢሳት ላይ እንዳያዞር ከተፈለገ መታረም ያለበት ፋሲል ብቻ ሳይሆን ኢሳት ነው። የኢሳት የጭፈን ደጋፊዎችም ያስተላለፍኩትን መልዕክት በጥሞና ተከታትላችሁ ሳትጨርሱ ለፍርድ አትቸኩሉ።

 ቸር እንሰንብት ነፃነት ናፈቀ 2015-11-03
 netsanetnafeke@hotmail.com

No comments:

Post a Comment