Sunday, October 19, 2014

ኦሮሞ እና እስልምና በ“ሕዳሴ አብዮት” መስመር ፪

(ተመስገን ደሳለኝ)
ባለፈው ሳምንት ይህንን ርዕሰ-ጉዳይ፣ በተለይም ኦሮምኛ ተናጋሪው የሚያነሳቸውን አግባብነት ያለው ቅሬታና የተንሸዋረረ የታሪክ ትንተና በተመለከተ በጨረፍታ ዳስሰን ስናበቃ፣ ከእስልምና ጋር የሚያያዘውን ክፍል ጨምሮ ጥቅል የመፍትሔ ሃሳብ መነሻን ለዛሬ በይደር አቆይተነው እንደነበረ ይታወሳል፡፡ እነሆም ተከታዩን እንዲህ እንቀጥላለን፡፡
የእስልምና ጥያቄ
በኢትዮጵያችን የረዥም ዘመን ታሪክ በተለያዩ ከባቢዎች ከተከሰቱት ጭቆናዎች እና የማንነት ጭፍለቃዎች ባሻገር፣ የእስልምና እምነት ተከታዮች የተፈፀመባቸው ሥርዓታዊ በደሎችና ጭካኔዎች፣ አንዳንዴም ጅምላ ጭፍጨፋንም ሳይቀር እንደሚጨምር በደም የተጻፉት ትርክቶች ያስረግጣሉ፡፡ የነገሥታቱ የሥልጣን እርካብ በ‹‹ስዩመ-እግዚአብሔር›› ላይ የተደላደለ በመሆኑ፣ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና በቀር ሌሎች እምነቶች በመዓት-አይን (በጠላትነት) ይታዩ ዘንድ መግፍኤ እንደነበረ ‹‹ዜና መዋዕል››ዎቻቸውን ብቻ በመመርመር መረዳቱ አያዳግትም (በኦርቶዶክስ በሚበየኑት ቅባት እና የፀጋ ልጅ ተከታዮች ላይ የደረሰባቸውን ዘግናኝ እልቂት እዚህ ጋ ማስታወስ ይቻላል)፡፡ በ14ኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ጦረኛው አምደፅዮን ወደዙፋን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ እስከ አፄ ዮሐንስ 4ኛ ድረስ እስልምና ላይ የደረሰው ጭፍለቃ አልፎ አልፎ በሠይፍ የታገዘ የግዴታ ጠመቃንም ስለማካተቱ ድርሳናቱ ያወሳሉ፡፡ ፕ/ር ባሕሩ ዘውዴ የአፄ ዮሐንስን የ1871 ዓ.ም የቦሩ-ሜዳ ውሳኔን ተከትሎ የወሎ ሙስሊም ቀን ቀን ‹‹እግዚአብሔር››፣ ማታ ማታ ደግሞ ‹‹አላህ›› ለማለት መገደዱን ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ›› በሚለው መጽሐፋቸው ማብራራታቸውም የሙግቱን አውድ ያጠናክረዋል፡፡ ዜና መዋዕሎቹም በእምነቱ ተከታዮች ላይ የደረሰውን እንዲህ አይነቱን ሥርዓታዊ የኃይማኖት ጥቃት፣ ማገለል፣ የማምለክ ነፃነትን መገፈፍ እና መሰል የጭካኔ ድርጊቶችን ነገሥታቱ ለአገራቸው የፈፀሙት ውለታ እና አኩሪ ተጋድሎ እንደሆነ በድፍረት መተረካቸው ማሳያ ተደርጎ ሊወስድ ይችላል፡፡
በጥቅሉ በዘመኑ ሥልጣንን ቅቡል ለማድረግ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ ግድ ከማለቱ በተጨማሪ፣ ነገሥታቱ ለክርስትና ያላቸው መታመን እና የሥርዓቱ መተዳደሪያ ሕግ ፍትሐ-ነገሥት መሆኑ ለእስልምና መጨፍለቅ እንደዋነኛ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ የዛሬውን ‹‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ነች›› አይነት ስሁት ፖለቲካ አምኖ የሚቀበል ወንድም-እህት መፍጠሩ አንሶ፣ አንዱ ክፍል ራሱን ‹‹ዜጋ››፣ ሌላውን ‹‹እንግዳ›› አድርጎ ወደማየቱ ጠርዝ ገፍቶታል፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ ክርስትናም ሆነ እስልምና እትብታቸው የተቀበረው በመካከለኛው ምስራቅ አገራት እንጂ አክሱም አሊያም ሐረር ውስጥ አለመሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ግና፣ ቀድሞ ወደሀገር የገባው የበላይ፤ ተከታዩ ደግሞ የበታች እንዲሆን የሚያስገድድ አንዳችም አመክንዮ ማቅረብ በማይቻልበት በዚህ ስልጡን ጊዜም ሳይቀር ሙግቱ አልፎ አልፎ ሲነሳ እየተሰማ በመሆኑ፣ በ‹‹ሕዳሴው አብዮታ››ችን በግንባር ቀደምትነት ፈውስ ሊያገኝ ይገባል ብዬ የማስበው ጉዳይ ሆኗል፡፡
በ1966ቱ አብዮት ንጉሣዊው አገዛዝ ለመጨረሻ ጊዜ ተንኮታኩቶ ከወደቀ ወዲህ መንግስት እና ኃይማኖት በአዋጅ መለያየታቸው ቢደነገግም፤ ግራ-ዘመሙ ወታደራዊው አስተዳደር በስውር ክንዱ ሁሉንም የእምነት ተቋማት ለመቆጣጠር በነበረው ህልም፣ በመንፈሳውያን መሪዎች ላይ አያሌ መከራ ስለማድረሱም ሆነ ተቋማቱን አቅም-አልባ ስለማድረጉ በህይወት ያሉ የዓይን ምስክሮች እልፍ አእላፍ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡
ደርግን በ1983 ዓ.ም ወርሃ-ግንቦት ከቤተ-መንግስት አባርሮ በእግሩ የተተካው አብዮታዊ ግንባሩ መጀመሪያ አካባቢ በተለይም የእስልምና እምነት ተከታዮች በአንፃራዊነት ከቀድሞ በተሻለ መልኩ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው አድርጎ እንደነበረ ይታወሳል (ሥርዓቱ ይህንን መብት የፈቀደ የመሰለው፣ በዋናነት ለመጨፍለቅ ያሰበው የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት አንዱ ወካይ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት በመሆኑ፣ በ66ቱ አብዮት ያበቃለትን የእምነቱ የበላይነት አለቅጥ በማጎን እና ከመቶ ዓመታት በፊት የተከሰቱ ታሪካዊ ስህተቶችን በማስጮህ ለማድቀቅ የሄደበት ርቀት እንደነበረ ጉዳዩን ያጠኑ ምሁራን ይከራከራሉ) ለዚህም ነው በዘመነ-ኢህአዴግ የኃይማኖት ነፃነት ከአፋዊነት አልፎ በተግባር ሊረጋገጥ ያልቻለው፡፡ ጣልቃ ገብነቱም ለኦርቶዶክስ ክርስትና ‹‹ፓትርያርክ›› እስከ መሾም፣ መጅሊሱም የካድሬዎች መፈንጪያ እንዲሆን እስከማስገደድ ድረስ ለመዳፈሩ የሁለቱም እምነት ተከታዮች የተቃውሞ ድምፅ ዛሬም ተግ አለማለቱ አስረጅ ነው፡፡ ከ2004 ዓ.ም ወርሃ-
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
2
ታሕሳስ አንስቶ ሕዝበ-ሙስሊሙ በመላ አገሪቱ እያደረገው ያለው ሰላማዊ፣ ነገር ግን ጠንካራና የተደራጀ የተቃውሞ ንቅናቄም ይህንን ሁነት ፍንትው አድርጎ ያሳያል ብዬ አምናለሁ፡፡
በነገራችን ላይ ለረዥም ጊዜ በመካሄድ ላይ ያለው የሕዝበ-ሙስሊሙ ‹ድምፃችን ይሰማ› እንቅስቃሴን በተመለከተ፣ ሌሎች እስካሁን ያሳዩት ዝምታ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ እዚህ ጋ ሊነሳ የሚገባው ዓብይ ጉዳይ ነው፡፡ መእምናኑ ለመፍትሔ አፈላላጊነት የወከሏቸው የኮሚቴ አባላት ለግፍ እስር ከመዳረጋቸው በተጨማሪ፤ የእምነት ነፃነት መብቶቻቸው እንዲከበር እና ታሳሪዎቹ መንፈሳውያን እንዲፈቱ በሠላማዊ መንገድ መጠየቃቸው እንደ ወንጀል ተቆጥሮ፣ ‹‹ፀጥታ›› አስከባሪዎች የተከበረው ቤተ-አምልኮ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሳይቀር በድፍረት ሰተት ብለው በመግባት እየወሰዱት ያለው ዘግናኝ የኃይል እርምጃ እና ተደጋጋሚ ጭካኔ የተሞላበት ድብደባ፣ እስር፣ እንግልት… የማናችንንም ልብ የሚሰብር ቢሆንም፣ አስፈሪው ዝምታችንን ግን ሊገራው አለመቻሉ እጅጉን ግራ አጋቢ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት በአንዋር መስጊድ የተፈፀመው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት (የንቅናቄው አራማጆች ‹‹ጥቁር ሽብር›› ብለውታል) ያለአንዳች የኃይማኖት እና የብሔር ልዩነት ከሕዝበ-ሙስሊሙ ጎን መቆምን አማራጭ አልባ ማድረጉን አምኖ መቀበሉ ከዘገየ ፀፀት ይታደጋል፡፡ በተለይም በሀገሪቱ ፖለቲካ የዳበረ የተሳታፊነት ልምድ ያላቸው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ለዘብተኝነት ያበቃ ዘንድ ወቅቱ ግድ ማለቱን ማስተዋል ብልህነት ነው (በርግጥ የተቃውሞ እንቅስቃሴው በመስጊድ ብቻ መገደቡ ለትብብሩ አንድ እንቅፋት መሆኑን አልዘነጋሁም)፡፡ እዚህ አስፈሪ ‹‹የነርሱ ጉዳይ ነው›› አይነት ገለልተኛ አቋም ላይ ለመድረሳቸው ገፊ-ምክንያት ተብሎ የሚታመነው፣ በፕ/ር ሀጋይ ኤርሊክ ‹የግራኝ ስጋት› (Syndrome) በሚል የተገለፀው አደንዛዥ ስነ-ልቦና ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ክርስቲያኖች አህመድ ኢብን አልጋዚ የሄደበትን የፖለቲካ ስልጣን ፍለጋ አውዳሚ የጦርነት መንገድ፤ በክርስትና መቃብር ላይ የእስልምናን የበላይነት ለማንበር እንደተሞከረ ተደርጎ ለሚቀርበው መላምት መታመናቸው ወደዚህ ጠርዝ የገፋቸው ይመስለኛል፡፡ ይህንን መሰሉ አካሄድም በማኪያቬሊያዊ አስተምህሮ የተዋቀረውን ሥርዓት ዕድሜ ከማራዘም በቀር ቅንጣት ፋይዳ የሌለው በመሆኑ፣ ስጋቱን አራግፎ መጣል አገሪቱን ወደፊት ለመውሰድ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል (በአልነጃሺ/አርማህ መሀከል ያለውን የሚታረቅ የማይመስል ቅራኔ ሳንዘነጋ)፡፡ እየተነጋገርንበት ባለው የ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› ሀቲት፣ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ላይ ቆመን፣ ከአራት መቶ ዓመታት በፊት በተከሰተ (ሊያውም ስምምነት ላይ ሊያደርሱ ያልቻሉ ትርክቶች ባሉበት ሁነት) ይህን ዘመን መቃኘት ረብ የለሽ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ወደፊት ለመራመድ የክርስቲያኑ ቀዳሚ የቤት ስራ መሆን ያለበት፣ በሕዳሴው የምትፀነሰው ኢትዮጵያ ከሙስሊም ጋር በብቻነት መዋረስ እንደሌለባት ሁሉ፤ እስከአሁን እንደተሸከመቻቸው የሚታሰቡትን ኦርቶዶክስ ቀመስ ትዕምርታዊ እሴቶችንም ለመግራት መፍቀድን ይጠይቃል፡፡
ከእስልምና ልሂቃን አንዱ ኡስታዝ ሀሰን ታጁ፣ ለዚህ አይነቱ አንድነት የሚያግዙ ሦስት ነጥቦችን ያነሳል፡፡ ‹‹ሰይፉን ፍለጋ›› በሚል ርዕስ በቅርቡ ባሳተመው ድርሳኑ፣ ሙስሊም በቀደሙ ጊዜያት በኦርቶዶክስ በዓላት ላይ የመሳተፍ የግዴታ ቀንበሩን መጣሉ አለመቻቻል ተደርጎ መቅረብ እንደሌለበት በአንደኝነት ይጠቅሳል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዞ፣ ባለፉት ሁለት አስርታት የተመለከትነውን የእምነቱ ተከታዩን ‹‹እስልምናን ወደ ማፅደቅ›› መመለስ እንዳለመቻቻል፤ አልያም ሌላ ድብቅ ዓላማ እንዳለው በማስመሰል በጥርጣሬ ማየቱ አደገኛ ስለመሆኑ አጽንኦት ሰጥቶበታል፡፡ ‹‹…‹ቴዎድሮስ ጨፍጭፎናል፣ ዮሐንስ አርዶናል፣ ዘርአያዕቆብ እምነታችንን አንቋሽሿል›… መሰል የታሪክ እውነቶችን መካድ የትም አያደርሰንም›› ሲልም ያስታውሳል፡፡ እነዚህን የኡስታዙ ምክረ-ሐሳቦች የጠቀስኩት፣ ቢያንስ የታሪክ ተዋስኦ ላይ የተፃረሩ ሙግቶች የሚቀርቡባቸውን ኩነቶች ትተን፣ በሕዳሴቷ ኢትዮጵያ በሚበጀው ብያኔ ውስጥ ሙስሊሙን ለመቀላቀል በእጅጉ እንደሚጠቅመን ከልብ በማመን ነው፡፡
ሌላው መሰረታዊ ጥያቄ ደግሞ፣ ከሕዝበ-ሙስሊሙስ ምን ይጠበቃል? የሚለው ነው፡፡ እንደ ሐሰን ታጁ ትንተና አንዱ አስፈላጊ ጉዳይ፣ ኃይማኖቱም ሆነ ተከታዮቹ በተለይም በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ መሪዎች ተረግጠው መቀጥቀጣቸው የማይስተባበል ሀቅ ቢሆንም፣ ባለፉት የታሪክ ሁነቶች ላይ ተመስርቶ ጦር መወራወርን ትተው ወደፊት በሚወስዱን ጭብጦች ዙሪያ ለመነጋገር ከመፍቀድና ከመድፈር ውጪ የቀረ ምርጫ አለመኖሩን መገንዘብ እንዳለባቸው ነው፡፡ የሆነው ሁሉ የተነገረውን ያህል ቢሆንም/ባይሆንም፣ አሁን ያለንበትም ሆነ የነገ ዕጣ ፈንታችን በማይበጠሱ ክሮች መገመዱን ተቀብሎ በሕብረት መነሳት ወደመታደሳችን የሚያደርሰን ብቸኛው መንገድ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ኡስታዝ ሐሰን ከላይ ባወሳሁት መጽሀፉ፤ ዶ/ር እንድሪስ ሙሐሙድ ለፒኤችዲ ካዘጋጀው የጥናት ጽሑፍ ላይ የጠቀሰውም ይህንን ሐቅ በሚገባ ያጠናክረዋል፡-
‹‹የአሁኑ ትውልድ ላለፉ ግፎች እና መድሎዎች እውቅና በመስጠቱ በአስተሳሰቡም ሆነ በተግባር የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ፤ እንዲሁም ጥላቻን ዘርቶ ከማብቀል መታቀብ ይኖርበታል፡፡ በታሪካዊ ጭቆናዎች ምክንያት የተፈጠሩ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባሕላዊ መበላለጦች የሚካሱበት መንገድም ሊኖር ይገባል፡፡ ምናልባትም በንዲህ አይነት ልባዊ ጥረቶች ያለፉ ቁስሎች ሊሻሩና መጪው ዘመን ጤናማነቱ ሊረጋገጥ ይችል ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጪ እውነታውን በመድፈቅና በማድበስበስ ጤናማና ጠንካራ ማሕበረሰብ መገንባት አንችልም፡፡›› (ገፅ 388)
3
ዛሬ በአሰቃቂው ቅሊንጦ እስር ቤት የሚገኘው የመፍትሔ አፈላላጊው ኮሚቴ አባል አሕመዲን ጀበልም ‹‹ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከ615-1700 የጭቆናና የትግል ታሪክ›› በሚል ርዕስ በ2003 ዓ.ም ለንባብ ባበቃው ቅጽ አንድ መጽሐፉ መግቢያ ላይ የታሪክን ፋይዳ እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-
‹‹ታሪክ ትናንትን ለማወቅ፣ ዛሬን ለመረዳትና ለነገ ለማቀድ ያግዛል፡፡ ታሪክ ያለው ሕዝብ በአግባቡ ከተጠቀመበት ታሪክ ይሰራል፡፡ ወደፊት መጓዝ የፈለገ መጀመሪያ ወደኋላ ተመልሶ ታሪኩን ይፈትሻል፡፡ የአባቶቹንና የአያቶቹን ገድል ሲረዳ በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳለፉ ግልጽ ብሎ ይታየዋል፡፡ የዛሬው እርሱነቱ የበርካታ ሂደቶች ውጤት መሆኑን ይረዳል፡፡ የአባቶቹንም ስህተት አይደግምም፡፡ የነርሱ ጠንካራ ተሞክሮ ኃይል ይሆነዋል፡፡›› (ገፅ 19)
አብዱልከሪም ታጁ ባለፈው ሳምንት በዚሁ በ‹‹ፋክት›› መጽሔት ላይ ‹‹ወደጥንቱ መመለስ!?›› በሚል ርዕስ ላስነበበን ጽሑፍ መደምደሚያ ያደረገውን ሃሳብ ማከልም ሙግቱን ያጠነክረዋል፡-
‹‹የነ እማሆይ ወተት፣ የነ ሲቲ መይሙና አገር፡፡ የነ የኔታ፣ የነ አብዋ፣ የነ አባዬ፣ የነ ጌትዬ፣ የነ አባ ገዳ አገር፡፡ የነ አብርኸት (የመጀመሪያው ኢትዮጲያዊት ሙስሊም)፣ የነ ድል ወንበራ፣ የነ ምንትዋብ፣ የነ እትዬ ጣይቱ፣ የነ እትዬ መነን አገር፡፡ የነ ኢዛና፣ የነ ነጃሺ፣ የነ ፋሲለደስ፣ የነ አባ ጂፋር፣ የነ ሐሰን አንጃሞ… አገር፡፡ የክርስትና፣ የእስልምና፣ የዋቄፈታና የሌሎች ባሕላዊ ኃይማኖቶች ሀገር፡፡ እነዚህ ሁሉ ናቸው እንግዲህ ማንነታችን የተገመደባቸው ልዩ፣ ጠንካራና ቀለመ-ብዙ ክሮች፡፡ ባሕላችን የተሸመነባቸው ድርና ማጎች፡፡››
…በኢሕአዴግ ስር ያለፍናቸው ዓመታት እንዳስረገጡት ጭቆናው ሙስሊሙን ለይቶ የተተገበረ ካለመሆኑ አኳያ፣ በመጪው የ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› ኢትዮጵያን ከውድቀት ለማዳን ወደ መሀከለኛው ፖለቲካ መምጣት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም ሕዝበ-ሙስሊሙ (ልክ እንደ ኦሮምኛ ተናጋሪው ሁሉ) ቀዳሚው አዋጪ መሆን የሚኖርበት፣ ኢሕአዴግ ላይ በእምነትና በጥርጣሬ መካከል ሲዋልል የከረመበት አካሄድ አሁን እንዳየነው ኃይማኖቱን በመጨፍለቅ መደምደሙን በግላጭ መመልከቱ ነው፡፡ የክሽፈቱ ሂደት የሚነግረን አንድ እውነትም፣ መምጣቱ አይቀሬ ነው ብለን በምንከራከርለት የመታደስ አብዮት ይህ የማሕበረሰብ ክፍል ከፊት ለመሰለፍ ካንገራገረ፣ ወደ ጨፍላቂነት ሊያፈገፍግ የሚችል ሥርዓት የሚመጣበትን ዕድል ዳግም መፍቀድ እንደሆነ መገንዘብ እንደሚያሻው ነው፡፡
ፖለቲካው የዘነጋው ማሕበረሰብ
አንድ ማሕበረሰብ በደምም ሆነ በስምምነት መገንባቱን የዓለም ታሪክ ይናገራል፡፡ ግንባታው በደም በተቀባ ታሪክ መካከል የማለፉ አጋጣሚም በራሱ አገሪቱን ባቢሎን ለማስባል ምክንያት አይሆንም፡፡ ‹ይሁን› ከተባለ ግን ኢትዮጵያን በዓለማችን ብቸኛዋ አገር ልናደርጋት እንገደዳለን፡፡ ቀደምት አባቶች ማሕበረሰብን ለዘለዓለም በአንድነት ለማፅናት ከጠብ-መንጃ በተጨማሪ ቋንቋ፣ ባሕል፣ መልከዓ-ምድርና መሰል ጉዳዮችን ለማስተሳሰር ይሞክሩ እንደነበረ ይታወሳል፤ ብዙውን ጊዜም ከሰላማዊው ስምምነት ይልቅ፣ በኃይል ማስገበርን ይመርጡ ነበር፡፡ በኢትዮጵያችን ይህ መንገድ ካስገኘው ትልቁ ውጤት በተቃርኖ፣ ታሪክን ዘመኑን የመበየኛ ‹‹ፖለቲካ›› በማስመሰል የልዩነት በርን ለማስፋት ለሚሞክሩ ሥልጣንን የሚያሰሉ ኃይሎች የመጫወቻ ካርድ ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ ግና፣ እነስፓርታና ትሮይ በኃይል መገበራቸው የዛሬዋን ሄለናዊ ግሪክ መፍጠር መቻሉን እንጂ፤ በዚህ ዘመን መነፅር ተቃኝቶና ለብይን ቀርቦ የ‹‹እንገነጠላለን›› ጥያቄ ስለማስነሳቱ ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ የአገርን የመጨረሻ ቅርፅ ያበጁ ማሕበረሰባዊ ውሎች ከፖለቲካዊ ፍቺ ይልቅ፣ አንድነትን ለማፅናት ያላቸውን አስተዋፅኦ ያህል፣ ሂደቱ የዜጎችን እልቂት፣ የማንነት ጭፍለቃን፣ የኃይማኖት ድፍጠጣን፣ የባሕል ወረራን… የማድረሱን አይቀሬነትም በቅንነት መረዳትን ይጠይቃል፤ ሙግቱም ከዚህ አውድ ሊርቅ አይገባውም፡፡
ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ማሕበረሰባዊ እሴቶችን ዘንግተው ጊዜያዊ ትርፍን ብቻ ታሳቢ ካደረጉ ከትውልድ ትውልድ በቀላሉ የማይቋጭ ከባድ የቤት ስራ ሰጥቶ የሚያልፍ ጠባሳ መተዋቸው አከራካሪ አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ በኦሮሚያ ከማንነት ጭፍለቃ፣ በታሪክ ከመዘንጋት እና የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ በትክክል ካለመተግበሩ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ተከትሎ፣ ዝነኛው የቃሊቲ ማጎሪያ ለቋንቋው ተናጋሪ ወጣቶች ሌላኛው የሲኦል ቤት የሆነበትን ኩነት ማስተባበል አይቻልም፡፡ የብሔሩ ልሂቃን ባላጠሩት ወይም በከፋፈሏቸው መሰረታዊ ልዩነቶች መንስኤነት ወክለነዋል የሚሉት ማሕበረሰብ የስቃዩ ገፈት ቀማሽ እንዲሆን መግፋታቸውን ሳንዘነጋ ማለት ነው፡፡ በርግጥ ወደዚህ ድምዳሜ የሚያደርሰን ‹ጥያቄዎቹ ከመገንጠል በመለስ ሁነኛ ምላሽ የላቸውም› የሚሉትን ያህል፤ ‹ስርየቱ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ብቻ ነው› የሚሉ፤ አሊያም ሀገሪቱን እስከወዲያኛው በብቸኝነት በመግዛት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ኃይሎች በአንድ ብሔር ጥያቄ አፈታት ላይ የተያዙ አቋሞች የመሆናቸው እውነታ ነው፡፡ ከእነዚህ ፖለቲካዊ ምላሾች መካከል መገንጠል ወይም በብቸኝነት የሥልጣን ይገባኛል ጥያቄ ተግባራዊ የሚሆንበት አጋጣሚ ቢፈጠር፣ የሀገር ህልውናን የተሸከሙ አዕማዶች ፈራርሰው፤ ዘመናትን የተሻገረው ማሕበራዊ ትስስር ተበጣጥሶ አገር-አልባ የተበታተነ ትውልድ መውለዳቸው አይቀርም፡፡ ኦሮሚያን ከተቀረው የአገሪቱ አካል መገንጠል፣ ዛሬም ክልሉ በተዋቀረበት መልከዓ-ምድራዊ ቅርፅ ውስጥ ሌሎች ህዳጣኖችን ማስተናገድ የሚያስችል ሥርዓት ማበጀት እንደማይቻል (በብሔር ፌደራሊዝሙ ትግበራ ያየናቸው ጉድለቶች እንደማይከሰቱ ተገንጣይ ልሂቃኑ በቂ
4
መከራከሪያ እንኳ ሲያቀርቡ አልሰማንም) እና የተዳፈኑ ሌሎች ጥያቄዎች ፈንቅለው ከመውጣትም ሆነ በማያቋርጡ አዳዲስ ችግሮች የቋንቋውን ተናጋሪ ከመናጥ አይታደግም፡፡ በብቸኝነት የመግዛት ጥያቄም ቢሆን (ኦሮሞ ብዙ ከመሆኑ አኳያ ሁሉም የቋንቋ ተጋሪውን ልሂቅ ብቻ ይመረጣል ከሚል ምክንያተ-አልቦ መነሻነት) የበላይ ልሁን ባይነትና ኢ-ዲሞክራሲያዊ ከመሆኑም ባሻገር የዘመኑን መንፈስ የሚፃረር ነው፡፡
ወደድንም ጠላን ኦሮምኛ ተናጋሪው እንደከዚህ ቀደሙ የልሂቃኑን ያልተፈተነ ፖለቲካዊ የመፍትሔ ሃሳብ ብቻ አንጠልጥሎ፣ ከወንድምና እህቶቹ ጋር ለዘመናት የገነባውን ሁለንተናዊ ትስስር ጥሎ እንዲነጉዱ የሚገፉበት እኩይ ቀመር የሚያከትምበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ስለምን ቢሉ? ያለፈው ታሪካችን በደም መገንባቱ ባይካድም፣ ዛሬም ዕጣ-ፈንታችን በዚህ ሊደመደም አይቻለውምና ነው፡፡ እነዚህን ችግሮችም በማያዳግም ሁኔታ ለመፍታት፣ በቀዳሚነት ኦሮምኛ ተናጋሪው ክፍል እና የአንድ ጠቅላይ ኢትዮጵያ አቀንቃኝ ሆነው የምናገኛቸው ወገኖቻችን መካከለኛውን የመቻቻል መደላድልን ለመፍጠር በሰጥቶ መቀበል መርህ የተቃኘ መፍትሄን አምነው የመተግበር ተነሳሽነት ሊኖራቸው እንደሚገባ አምናለሁ፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ይህንን መንገድ መከተሉ አዋጭ እንደሆነ የገለፁት እንዲህ ሲሉ ነው፡-
‹‹ብዙዎቹ የዛሬ 30 እና 40 አመታት ብቻ ሳይሆን፣ የዛሬ 130 እና 140 አመታት በፊት የነበረውን ጭምር የታሪክ ሂሳብ እንተሳሰብ የሚሉ ይመስሉኛል፡፡ የኦሮሞ ልሂቃን ዋና ችግራቸው የጋራ የፖለቲካ አጀንዳ ለመቅረፅ ከመጣር ይልቅ ለብቻቸው የሚደረገው ትግልን የመንግስት ሰማያት አስተማማኝ መንገድ አድርገው ማምለካቸው ነው፡፡ የአማራው ልሂቅ ዋና በሽታው በዋናነት በአማራ ልሂቃን የተፈጠረች የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እንደዛው ትቀጥል ነው፡፡ እምነታቸው መቀጠልም ትችላለች ነው፡፡ ባለፉት አርባ ዓመታት የሀገሪቱ ፖለቲካ ዋናው ቀውስ ምንጭም እንደነበረች መቀጠል ያለመቻሏ መሆኑን በውል መገንዘብ ያቃታቸው ይመስለኛል፡፡›› (ገፅ 261-262)
የ‹‹ሕዳሴው አብዮታ››ችን ዋነኛ ግብም በዴሞክራሲያዊ አንድነት የፀናች፣ የጠነከረችና የታደሰች ኢትዮጵያን መፍጠር እንጂ፣ በቀላሉ ሊታረቁ በሚችሉ ልዩነቶቻችን ላይ እሳት ለኩሶ የመበጣጠስን አደጋ መጋረጥ አለመሆኑን ማስታወሱ አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ሌሎች የዓለም አገራትም ይህን መሰሉን የብሔር ጥያቄ (ቅራኔ)፣ ያለደም መፋሰስና መበታተን የተሻገሩበትን ጥበብ ብንፈትሸው እውነተኛ ዲሞክራሲን በማስፈን እንደነበረ እንረዳለን፡፡ ‹ከቡድን መብት ውጪ ሌላ ነገር አያሳየኝ› የሚል ግትር አቋም ይዞ የሚንገታገተው ኢህአዴግን ጨምሮ በተአማኒ ምርጫ ለሥልጣን የሚወዳደሩ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› ግለሰብን-እንደግለሰብ እውቅና እንዲሰጡ የመገደዳቸው እውነታም ሆነ በዲሞክራሲያዊው መንገድ የሚመሰረተው ሥርዓት በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም የአገሪቱ ክልል የሚነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎችን በብቃት የመመለስ አቅም እንዲኖረን የሚያስችለው መተማመኛችን ያሳለፍናቸው የመከራ እና የልዩነት ዓመታት ሁነኛ ተሞክሮዎች በመሆናቸው ነው፡፡
የ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› ተዋስኦ
በተከታታይ ክፍሎች የተነጋገርንበት የ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› በጠንካራ ትውልዳዊ መሰረት ይገነባ ዘንድ፤ በተነሱት ሃሳቦች ዙሪያም ሆነ ተለጣጭ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ አሀዱ የሚባሉ የአደባባይ ውይይቶች በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ይህም የአብዮቱ ተግባሮት ቀዳሚ ጅማሮ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ገጾች በማደስ ይበየናል የምለው የሕዳሴው አብዮት፣ ካለምሁራዊ ተዋስኦ የምንፈልጋትን ከራሷ ጋር የታረቀች ኢትዮጵያን እንደማያመጣልን አምናለሁ፡፡ የመንግስታችንም ሥርዓት በዘውግ ተኮር ልባሶች የሚቀነቀኑ ፖለቲካዊ ግቦችን የማዘል አዝማሚያ እንዳለው እረዳለሁ፡፡ ይህም፣ ማሕበረሰባችንን ለተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ ከማሳተፍ ይልቅ፣ ወደኋላ እንዲንሸራተት አስተዋፅኦ ማድረጉ ግልፅ ነው፡፡ የሚመጣው አብዮት፣ የኢትዮጵያን የቁልቁለት ጉዞ በመግታት፣ እንደሀገር መቀጠል እንድትችል ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉንም ፍላጎቶች የሚያካትት ይሆን ዘንድ፣ በዚህ መንፈስ የተቃኘ የአደባባይ ሙግት አይነተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ በተዋስኦ ጅማሮም፣ ክብደት ልንሰጣቸው የሚገቡትን ጭብጦች ከዚህ ቀደም በሕዳሴ መምህርነት ከጠቀስኳቸው ልሂቃን ክርክሮች መነሳት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ የመስፍን ወልደማሪያምን የክሽፈት ኃልዮት ማሕበረ-ባሕላዊ እና ሥርዓታዊ ምንጮች መፈተሽና ማብራራት፤ የመሳይ ከበደን የሀገሪቷ የቀደሙ ስልጣኔዎች መገታት ለመሻገር ዘመናዊነትን ከልማዳዊ ማንነቶቻችን ጋር በመለንቀጥ እንደገና አቧራውን ማራገፍ ይቻላልንም ሆነ፤ የተከሰተ ነጋሽን የትምህርት ሥርዓታችንን በሀገረኞቹ አማርኛ እና ኦሮምኛ ቋንቋዎች ሙሉ ለሙሉ መቀየር የሚለውን ሙግት ጨምሮ፣ ከዚህ ቀደም ኦሮሚያን ለመገንጠል ይታትሩ የነበሩት ሌንጮ ለታ በቅርቡ በመሰረቱት ድርጅታቸው (ኦዴግ) ‹‹የፖለቲካ ፕሮግራሜ›› ብለው የዘረዘሯቸው ነጥቦች የመታደሰቸው ምልክት በመሆኑ፤ እንዲሁም የሐሰን ታጁ የመቻቻል ትርጓሜና የአንድነት የመፍትሔ ሃሳብ (በተለይም የታሪክ ወቀሳና ሮሮ ላይ ማተኮሩን ማለዘቡ ከተሳካለት) የሕዳሴው ተዋስኦ አዕማዶች ሊሆኑ የሚችሉ ይመስለኛል፡፡
በዚህ መንፈስ ይገራል ብዬ የምታመንለት ተዋስኦ፣ ከዚህ ጽሑፍ አንፃር የሚያተኩርባቸው ዕሴቶች ይኖሩታል፡፡ በኦሮሞ ጥያቄ እና በሙስሊሙ ጉዳይ ላይ የሚኖረን ክርክር፣ ያለፉትን አሟጋች የታሪክ ኩነቶችንና ሰብዕናዎችን ለአካዳሚው ክበብ
5
በመተው፤ ሁለቱ የማሕበረሰብ ክፍሎች ኢትዮጵያን ዳግም በመበየን እና በአብዮቱ ሊኖራቸው የሚገባ ሚና ዋነኛ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከኃይማኖቱም ሆነ ከኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪው ማሕበረሰብ ለሕዳሴው እውናዊነት የሚበጁ የዘነጋናቸውን ዕሴቶችን መመርመር እና እነርሱንም በተዋስኦው ውስጥ አጥብቆ መግፋት፣ አንዱ ቀጣይ የቤት ስራችን ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ …እነሆም በማሕበረሰባዊ ክፍሎች መሀከል ብዙ ፈታኝ አደጋዎችን ተሻግሮ የመጣው ሁለንተናዊ ትስስራችን በአብዮቱ ዳግም ይታደስ ዘንድ፣ የአገሬ ልጆች ነቅተው እንዲጠብቁት በጥብቅ እመክራለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com

ኦሮሞ እና እስልምና በ“ሕዳሴ አብዮት” መስመር

ተመስገን ደሳለኝ)
በወርሃ-ግንቦት ላይ ለዘመናት የተንሰራፋውን ሀገራዊ ደዌ ይፈውሳል ብዬ ተስፋ ስለማደርግበት “የሕዳሴ አብዮት” በሶስት ተከታታይ ክፍሎች ለመዳሰስ መሞከሬ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ መጪው የ “ሕዳሴ አብዮታችን” መፍትሔ ሊሰጥባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መሀል በዋነኝነት የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪው ማሕበረሰብ እና የእስልምና እምነት ተከታዮች የመብት ጥያቄን በተመለከተ በጥቅሉ ጠቃቅሼው አልፌ ነበር፡፡ ሆኖም ‘ሰፋ ብሎ ቢዳሰስ’ የሚሉ በተለያየ መንገድ የሚቀርቡ ጎትጓች ድምፆች መበራከታቸው የመነሻ ሃሳቡን ፈታ አድርጌ እንዳቀርብ አስገድዶኛል፤ እንግዲህ ይህ ጭብጥም የዛው ተከታይ መሆኑ ይሰመርልኝ፡፡
የኦሮሞ ጥያቄ
በኢትዮጵያችን ከሚገኙ በርካታ ብሔሮች መካከል አብላጫውን ቁጥር የሚይዘው ኦሮምኛ ተናጋሪው ቢሆንም፣ ለዘመናት ይደርሱበት ከነበሩ ሥርዓታዊ በደሎች እና የባሕል ጭፍለቃዎች ዛሬም በምልአት ነፃ እንዳልወጣ በቂ ማሳያዎች አሉ፡፡ በ1960ዎቹ አጋማሽ የአገሪቷ አደባባዮች የዘመኑን መንፈስ በተረዱ ቁጡ ወጣቶች መጥለቅለቁን ተከትሎ፣ ‹በንጉሣዊው አገዛዝ ግብዓተ-መሬት ላይ የመጨረሻዋን ድንጋይ ለማስቀመጥ› በሚል ሰበብ ቤተ-መንግስቱን መቆጣጠር የቻለው ወታደራዊው ደርግ፣ ህልቆ መሳፍርት በሌለው መስዋዕትነት የተገኘውን ወርቃማ ዕድል ከጅማሮው አጨናፍጎታል፡፡ በግልባጩ አብዮቱን ካጋሙት ገፊ-ምክንያቶች ዋንኞቹ ለሆኑት የብሔርና የሕዝባዊ መንግስት ምስረታ ጥያቄዎች፣ መፍትሄ ይስጥ አይስጥ እስኪረጋገጥ ድረስ መታገስ ያልፈለገው ህወሓት፣ ጉዳዩ በደም መፋሰስ ብቻ እንደሚፈታ አውጆ ጫካ ሲገባ አዲሱ መንግስት ገና የ6 ወር ጨቅላ እንደነበረ አይዘነጋም፡፡ ይሁንና ታሪክ በአስከፊ መልኩ ራሱን ሲደግም ያስተዋልነው ወታደራዊውን መንግስት መንፈቅ-ዓመት ያህል እንኳ መታገስ ያልፈቀደው ይህ ቡድን፣ ለጥያቄዎቹ መልስ ሳይሰጥ ከሁለት አስርታት በላይ ያለመንግራገጭ በሥልጣን ለመቆየት ባለመቸገሩ ነው፤ ርግጥ የእኔ ትውልድም የእድሜውን እኩሌታ በትግስት መጠበቁ የአደባባይ እውነታ ቢሆንም፣ ተጨማሪ የቻይነት ዓመታት ይኖራሉ ብዬ ግን አላስብም፤ አብዮቱን ምኩንያዊ የሚያደርገውም ይህ ነው፡፡ …እነሆም ከአራት አስርታት በላይ ሲንከባለሉ የቆዩት የኦሮሞ ጥያቄዎች በ“ሕዳሴ አብዮት” ይፈቱ ዘንዳ፣ ሊተኩርባቸው የሚገቡ አንኳር አጀንዳዎችን በሁለት አውድ ከፍለን እንመለከታለን፡፡
ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ጥያቄዎቹን ከወረቀት ድንጋጌ (ከአፋዊነት) እና ከፕሮፓጋንዳ ሽንገላ ባለፈ፣ እውነተኛ መፍትሔ በሚያስገኝ መልኩ እልባት ሊያበጅላቸው አልፈቀደም፤ ባለፉት ሃያ ሶስት ዓመታት ‹‹አነበርኩት›› የሚለው ቋንቋ ተኮር ፌዴራሊዝም የይስሙላ ስለመሆኑ ለመገንዘብ፣ ዛሬም ከደርዝን በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች የራስ አስተዳደር ጥያቄን አንግበው በትግል መድረክ መገኘታቸውን ማየቱ በቂ ነው፡፡ የክልሉ ‹‹ገዥ›› እንደሆነ የሚነገርለት ኦህዴድም ቢሆን፣ የህወሓቱ የአማርኛ ክንፍ እንደሆነው ብአዴን ሁሉ፣ የኦሮምኛ ክንፍ ከመሆን አለማለፉን፣ የብሔሩ ልሂቃንን ጨምሮ የፌደራል ሥርዓቱን አወቃቀር ያጠኑ በርካታ ምሁራን ማስረጃ እያጣቀሱ ያጋለጡት እውነታ ነው፡፡ ሕዝቡም በየጊዜውና በየአጋጣሚው የሚያነሳው ጥያቄ አሁንም ተግ አለማለቱ የልሂቃኑ ማስረጃ መሬት መርገጡን ያስረዳል፡፡ በቅርቡ አፈ-ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ስለሕጋዊነቱ በድፍረት የደሰኮረለት የማስተር ፕላኑ ጥያቄ በኃይል መጨፍለቅም በገዥው በኩል ሕገ-መንግስቱ አፈር ለብሶ እንዳበቃለት ተናግሮ አልፏል፡፡ በተጓዳኝ የክልሉ ነዋሪ በተፈጥሮ ሀብቱ ተጠቃሚ እንዳይሆንና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዳይኖር ከመደረጉ ባሻገር፤ ከሕዝቡ ቁጥር ብዛት አኳያ ኦሮምኛ በሁለተኛ ብሔራዊ የሥራ ቋንቋነት እንዲያገለግል ኦህዴድ ተፅእኖ የሚፈጥር አልሆነም፤ ሌላው ቀርቶ ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ያነሱ ፖለቲከኞች ‹‹ኦነግ›› ተብለው የምድር ፍዳቸውን ሲቀበሉ የታደጋቸው የለም፡፡ የዚህ እኩይ ድርጊት ተጠያቂም ጉልበተኛው ህወሓት ብቻ ነው ማለት ገራገርነት ይመስለኛል፤ የገዛ ወገኑን አሳልፎ የሰጠው ኦህዴድም ጭምር የድርሻውን መውሰዱ አይቀሬ ነውና፡፡ ይህም ሆኖ ከአንዳንድ ምልክቶች በመነሳት ጥያቄዎቹ መልስ እስካላገኙ ድረስ፣ የቱንም ያህል የእስር ቤት ደጃፎች ከዚህም በላይ ቢጨናነቁ፣ የቱንም ያህል የእስረኞቹ ሰቆቃ እያደር ቢበረታ ከእንግዲህ በኦሮሚያ ምድር በፍርሃት ዝም-ጭጭ ብሎ የሚተኛ ሊኖር እንደማይችል ዛሬ ላይ ቆሞ መናገሩ ‹‹ሟርተኛ›› አያስብልም፡፡
የኦሮምኛ ተናጋሪውን ያደረ ቅራኔ በመፍታት የአንድነት ዘብ ለማድረግ፣ የሀገሪቱ ታሪክ እና ባሕል በዳግም ብያኔ መታደሱ ግድ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የክልሉ ማሕበረሰብ በዘመናዊው መንግስት ምስረታም ሆነ ከባእድ ወረራ መታደጉ ላይ ታላቅ አበርክቶ ቢኖረውም፣ በሀገሪቷ ታሪክ ውስጥ ሚናው ደብዝዞ መገለፁ ጎምዛዛ እውነት ነው፤ የቋንቋው ተናጋሪ ያልሆነው አብዛኛው ኢትዮጵያዊም ይህንን አምኖ ሊያርመው ቀርቶ፣ እውቅና ሊሰጠው እንኳ አለመፍቀዱ፣ ጉዳዩን ወደሰሞነኛው ‹‹ውጡ ከሀገራችን›› አይነቱ አስደንጋጭ ኩነት ገፍቶታል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው በጥቂት የብሔሩ ልሂቃን የሚንፀባረቀው (ሀገርን ለፍርሰት ሊያጋልጥ የሚችለው) ሸውራራ የታሪክ አረዳድን እና የቅኝ አገዛዝ ትርክትን ማጥራት ሌላው ወሳኝ የቤት ሥራ ሆኗል፤ ምክንያቱም ከጥያቄው ጋር ተያይዘው የሚነሱ የተቃውሞ ድምፆች ማጠንጠኛ ‹ባሳለፍነው መቶ ዓመት ለቅኝ አገዛዝ ተዳርገናል፣ ሥርዓታዊ በሆነ መዋቅር የሥልጣን ባይተዋር ሆነን ቆይተናል፣ ከሌላው ሕዝብም በተለየ መልኩ ከሰብአዊ ፍጡር በታች ተቆጠረን ተረግጠናል…› የሚል መንፈስ እንዲይዝ እየተለጠጠ ነው፡፡ ይህ የታሪክ ትንተና ስሁት መሆኑን የምንረዳው በየትኛውም መንግስታዊ ሥልጣን ጊዜ (ሀገሪቱ በጦር መሪዎችም ሆነ
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
2
በነገሥታቱ ጠንካራ መዳፍ ስር በተያዘችበት ዘመን) በግንባር ቀደምትነት በመንበሩ ላይ ይፈራረቁ ከነበሩት አማርኛና ትግርኛ ተናጋሪዎች የማይተናነስ እኩል ሚና እንደነበራቸው የቋንቋው ተናጋሪ ምሁራን በማስረጃ አስደግፈው ባዘጋጇቸው ድርሳኖቻቸው ያተቱትን ስናስተውል ነው፡፡
ለማሳያም ‹‹የጎንደር ዘመን›› ተብሎ ከሚጠቀሰው (እ.ኤ.አ ከ1636-1769 ዓ.ም ድረስ የዘለቀው) ማዕከላዊ መንግስት ውድቀት በኋላ የተተካውና ‹‹ዘመነ መሳፍንት›› እየተባለ የሚጠራው አገራዊ የአስተዳደር ዘይቤ ጠንሳሽና ተግባሪ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንደነበሩ ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ በወቅቱ የመንግስቱ መቀመጫ ከሰሜን ጎንደር ወደ ደብረታቦር የተዘዋወረ ሲሆን፣ የግዛት ወሰኑ ደግሞ ጎንደርን፣ ወሎን፣ ጎጃምን፣ ከፊል ሸዋንና ትግራይን የሚያካትት እንደነበር መዛግብቱ ያወሳሉ፡፡ በዘመኑ ሥልጣኑን የጠቀለሉትና ‹‹የጁ (ወራ-ሼክ) ስርወ-መንግስት›› በሚል ስም የሚጠሩት የአሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንደነበሩ የብሔሩ ምሁራን ነግረውናል፡፡ እያገባደድነው ባለው በዚህ ዓመት ‹‹የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች›› በሚል ርዕስ ዳጎስ ያለ ጥራዝ ያሳተሙት ታቦር ዋሚ ‹‹በኢትዮጵያ ታሪክ ዘገባዎች አላግባብ ዘመነ መሳፍንት ሲባል የቆየው የየጁ ዘመንና ታሪካዊ ሚና›› በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር በርካታ መጽሐፍትና የጥናት ጽሑፎችን በመጥቀስ ሥልጣኑ በኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እጅ እንደነበረ በስፋት አብራርተዋል፡፡ ታቦር በትርክታቸው ‹‹የጁ ከሰሜን ኢትዮጵያ የኦሮሞ ነገዶች አንዱ እንደሆነና ቀስ በቀስም ይህ ስም የጎሳው ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ የሰፈረበት አካባቢ ጭምር መጠሪያ እንደሆነ በርካታ ጸሐፍት ይመሰክራሉ›› (ገፅ 287) ሲሉ በአባሪ ማስረጃዎች አስደግፈው አቅርበዋል፡፡ ሥርወ-መንግስቱ በሥልጣን ላይ የቆየበት ጊዜያትንም ‹‹ከጎንደር ዘመነ-መንግስት ማብቂያ እስከ አፄ ቴዎድሮስ መነሳት ድረስ የነበሩትን ዓመታት ሁሉ ያካትታል›› (ገፅ 293) በማለት ገልፀውታል፤ ይህንን በአሃዝ እናስቀምጠው ብንል ደግሞ ወደ 86 ዓመት ገደማ ልንቆጥር እንገደዳለን፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ‹‹የኦሮሞ ታሪክ›› የተሰኘው መጽሐፍ ጸሐፊ እሸቱ ኢረና ዲባባም መከራከሪያውን እንዲህ ሲሉ ያጠናክሩታል፡-
‹‹ጎንደር የሃበሻ መንግስት (አቢሲኒያ) ማዕከል በነበረችበት ወቅት የኦሮሞ ህዝብ በአካባቢው ሰፍሮ ይኖር እንደነበረና ወሳኝ ሚና ለረጅም ጊዜ ነበረው፤ እ.ኤ.አ. ከ1853-1854 በጎንደር በእስር ላይ የነበረው ጀርመናዊ ሰዓሊ በሰራቸው ምስሎች ኦሮሞ በወቅቱ በአካባቢው ገዢ እንደነበር እርሱም ከአካባቢው ኦሮሞ ሴት እንዳገባ፤ ምስልዋንም ሰርቶ እነዚህ የስዕል ስራዎቹ እ.ኤ.አ. በ1868 ዓ.ም በለንደን ከተማ በመጽሐፍ መልክ ታትሞ ወጥቶ ይገኛል፡፡ በአካባቢው ሰፍረው ይኖሩ ከነበሩት የኦሮሞ ጎሳዎች ውስጥ የቦረና ኦሮሞ አንዱ መሆኑን ኤች ሙሬይ በ1830ዎቹ ባሳተመው ጽሑፍ ውስጥ ከጠቀሰ በኋላ ኦሮሞ እንደ ሕዝብ በደንቢያ በጎጃም፣ በዳሞትና በአንጎት አካባቢዎች ሰፍሮ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡›› (ገፅ 83-84)
ራሱ የክልሉ መንግስትም፣ በባሕልና ቱሪዝም ቢሮው በኩል ‹‹የኦሮሞ ታሪክ እስከ አስራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን›› በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፍ ‹‹…‹ወራ-ሼክ› የሚለው የቤተሰቡ መጠሪያ በየጁ ኦሮሞዎች ዘንድ ታላቅ ዝና ከማግኘቱም በላይ በአጠቃላይ የየጁ ኦሮሞዎች ቀደምት መንግስት መነሻ ወይም አባት ተደርጎ እስከመቆጠር ደረሰ ይባላል›› (ገፅ 281) ሲል ገልጿል፡፡
በግልባጩ የአፄ ምኒሊክ ፈረስ ሐረርና አርሲ መርገጡን ‹‹የቅኝ-ግዛት ወረራ›› አድርገው የሚያቀርቡ ዘመነኛ ‹‹ፖለቲከኞች››፣ ይህ አይነቱን ጥሬ ሀቅ ለመቀበል ቀርቶ ለመስማት አይፈቅዱም፡፡ የጠቀስኳቸው ድርሳናትም የሚነግሩን ኦሮሞ ከሌላው ብሔር ጋር ትንቅንቅ ገጥሞ በለስ ቀንቶት ድል ባደረገ ቁጥር መንግስታዊ ሥልጣን መጠቅለሉን ብቻ አይደለም፤ በሀገሪቱ ታሪክ ጭቆና እንጂ ቅኝ አገዛዝ የሚባል ነገር አለመኖሩንም ጭምር ነው፡፡ ከኤርትራ እስከ ሞያሌ፤ ከጋምቤላ እስከ ሶማሌ በተዘረጋው ሰፊ የኢትዮጵያ ግዛት ላይ በተደጋጋሚ ከተቃጡ የባዕዳን ወረራዎች በቀር፣ ቅኝ-ገዢም ሆነ ቅኝ-ተገዢዎች ስለመኖራቸው የሚያትት አንድም የታሪክ መረጃ ተፈልጎ ታጥቷል፡፡ መቼም ‹‹ድሮ ነፃ ሀገር ነበረን›› በሚል ዛሬ ላይ የመገንጠልን ጥያቄ ሲያነሱ፤ አሊያም አንድ ብሔርን በነፍጠኛነትና በወራሪነት ሲኮንኑ የምናደምጣቸው ጠርዘኛ ልሂቃን ‹የኦሮሚያ የግዛት ወሰን ጎንደርን እና ትግራይን ያጠቃልል ነበር› ስለማለታቸው ሰምተን አናውቅም፡፡ መቀመጫውን ደብረታቦር ላይ አድርጎ ከትግራይ እስከ ሸዋ ያስተዳድር የነበረ ሥርወ-መንግስት፣ የበለጠ ጉልበተኛ ተነስቶበት፣ በተራው ከመንበሩ በኃይል ሲገለበጥ ቅኝ-አገዛዝና ኢ-ሰብአዊ ብሎ ለመኮነን መሞከሩ ውሃ የሚያነሳ ሙግት ሊሆን አይችልም፡፡ እዚህ ጋ ሊዘነጋ የማይገባው ጉዳይ፣ በተለይም ከአፄ ምኒሊክ መንገሥ ወዲህ የኦሮሞ ማሕበረሰብ ቋንቋውን ጨምሮ የባሕል እሴቶቹ ተውጠው፣ የአገሪቱ ወካይ እንዳይሆኑ መጨፍለቃቸውን ነው፤ እንደምሳሌም የገዳ ሥርዓት ምንም እንኳ ሁሉንም የቋንቋው ተናጋሪ ያቀፈ ባይሆንም (የ‹‹ጊቤ ግዛት›› ተብለው የሚታወቁት፡- ጅማ፣ ሊሙ፣ ጎማ፣ ጉማ እና ጌራ ከገዳ ይልቅ በንጉሣዊ ሥርዓት ሲተዳደሩ፤ ወለጋና ኢሊባቡርን የመሳሰሉ አካባቢዎችም በ‹‹ሞቲ›› ይመሩ ስለነበር) የአክሱም ሐውልትን ወይም የጎንደር ግንብን ያህል በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቦታ አለማግኘቱ አይካድም፡፡ እንዲሁም በሌላ ቋንቋ ተናጋሪው ዘንድ ‹‹ጣኦት ማምለክ›› ተደርጎ የሚቆጠረው የኢሬቻ ክብረ-በዓል አረዳድ ስሁት ስለመሆኑ ቢረፍድም የመስከሩ ጠቀሜታ የጎላ ነው፡፡ ይህ የምስጋና ሥነ-ስርዓት በአገሪቱ ታሪክ ተገቢውን የክብር ስፍራ ሳያገኝ መገፋቱን በማመን፣ ሚዛንን ማስተካከል ግድ ይላል፡፡ በጥቅሉ ምግቡ፣ አለባበሱ፣ ሙዚቃውና መሰል እሴቶቹ በትልቁ የታሪካችን ገፅ በበቂ ደረጃ አለመወከላቸውን ዛሬም ለማድበስበስ መሞከሩ መፍትሔውን ከማራቅ፤ አሊያም ልዩነትን ከማስፋት ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ መቼም በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ የመገንጠል ጥያቄ ያነሱ ቡድኖች መኖራቸው ደብቀን የምናስቀረው ሚስጥር አይደለም፤ ከኦሮሚያ እስኪ ኦጋዴን፤ ከጋምቤላ እስከ ቤንሻንጉል ድረስ ይህን ለማስፈፀም የሚተጉ የታጠቁ ኃይሎች ተፈጥረዋልና፡፡ በርግጥ እነዚህ ኃይሎች የቆሙበት መሰረት ማሕበረሰቡን የሚወክል ነው ወይስ የራሳቸውን የሥልጣን ጥማት ብቻ የሚያረካ? የሚለው ገና ያልጠራ፣ አሁንም አጥጋቢ መልስ ያላገኘ ጥያቄ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ፖለቲካዊው ፍላጎት ማሕበራዊ ውሉን የዋጠው ይመስላል፡፡ ኤርትራን ያጣንበት ምክንያትም ከዚህ ብዙም እንደማይርቅ ጥርጥር የለውም፡፡ አሁንም የዚህን ጥያቄ ውል ከሳትን ሌላ የምናጣው ክፍለ-አካል መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህም ነው በ‹‹ሕዳሴው አብዮት›› እንደ አዲስ በምትገነባው ኢትዮጵያችን ጥያቄዎቹ በቀዳሚነት ምላሽ ሊያገኙ ይገባል ብዬ የምከራከረው፡፡ በለውጡም፣ እነዚህ ጎታች የፖለቲካ አቋሞች እና አቀንቃኞቹ ዘላቂ መፍትሔ አግኝተው የአንድነት ዘመን አብሳሪ እንደሚሆኑ አልጠራጠርም፡፡
3
በተቀረ በኦሮሞ ላይ አንድ ብሔር በተለየ መልኩ በደል አድርሷል፣ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ፈፅሟል… መሰል ትርክቶች ጭራና ቀንድ ተሰክቶባቸው ግብረ-ሂትለርና ፋሽስታዊ ድርጊቶች ተመስለው የሚቀርቡበት አውድ ከተራ ጊዜያዊ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳነት ያለፈ፣ በዕውን ለመፈፀማቸው ምንም አይነት የታሪክ ሰነድ አልተገኘም፡፡ ከጥቂት ሳምንት ቀደም ብሎ በዚህ ርዕሰ-ጉዳይ ዙሪያ ከታሪክ ምሁሩ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ጋር ስንወያይ ‹‹ወደ አኖሌ (አርሲ) ከዘመተው የአፄ ምኒሊክ ሠራዊት መካከል አብላጫው ኦሮሞ ነው›› ሲሉ መግለፃቸውም፣ ከዶ/ሩ የትምህርት ደረጃ፣ ከረዥም ዓመት የሥራ ልምዳቸው እና ከቋንቋው ተናጋሪ አብራክ የተገኙ ከመሆናቸው አኳያ ችግሩን ወደ አንድ ብሔር ማላከኩ ስህተት ለመሆኑ ሁሉንም የሚያስማማ ይመስለኛል፡፡ ታቦር ዋሚም ከላይ በጠቀስኩት መጽሐፍ (ከገፅ 275-278) ከአማራው ነገስታቶች ጋር ጋብቻ የፈፀሙ ኦሮሞ ንጉስና ንግስት በማለት በስዕላዊ መግለጫ አስደግፈው ያቀረቡት የቋንቋው ተናጋሪ ንጉሦችና ነገስታት ስም ዝርዝር እንደተጨማሪ ማስረጃ ሊወሰድ ይችላል፡፡ 

ጸሐፊው ለማሳያነት ከጠቀሷቸው ውስጥ የአፄ ቴዎድሮስ-እቴጌ ተዋበች፣ የአፄ ምኒሊክ-ጣይቱ ብጡል፣ የንግስት ዘውዲቱ-ወሌ ብጡል፣ የአፄ ኃይለስላሴ-እቴጌ መነን፣ የምኒልክን እህት ያገቡት-ንጉስ ሚካኤል… የኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት እንደነበሩ አትተዋል፡፡ ከዚሁ ጋርም አያይዘው በተለያየ ጊዜ በሀገሪቷ የተከሰቱት የኃይል ግጭቶች አሰላለፍ በብሔር ከመቧደን ይልቅ፣ በሥልጣንና በጥቅመኝነት ላይ የተመሰረቱ እንደነበረ ፈራ-ተባ እያሉም ቢሆን እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል፡-
‹‹በጣም የሚገርመው ከሣህለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ እስከ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ድረስ በኦሮሞው ላይ ሲካሄዱ ለነበሩት ዘመቻዎች ሁሉ ግንባር ቀደም ተዋናዮቹ በተለያዩ ምክንያቶች ከነገሥታቶቹ ጋር ጊዜያዊና ዘላቂ ዝምድና የፈጠሩ እራሳቸው ኦሮሞዎች መሆናቸው ነው፡፡ …(ራስ ጎበና) እኚህ የኦሮሞ መስፍን የታወቁ ፈረሰኛ፣ ጀግና፣ ተዋጊና ወታደራዊ ስትራቴጂስት ከመሆናቸው በላይ በኦሮሞ የውጊያ ስልትና በኦሮሞ ሥነ-ልቡና ላይ የጠለቀ እውቀት ነበራቸው፡፡ ይህንን ብቃት ሙሉ በሙሉ ለምኒሊክ አገልግሎት አውለውታል፡፡ ከሁሉም በፊት ምኒልክ ሳይሆኑ የኦሮሞን ግዛት ያሸነፉት ራስ ጎበና ነበሩ፡፡›› (ገፅ 499-500 እና 503)፡፡

ይህን መሰሉ የኃይል ትንቅንቅ ከአርሲና ባሌ በፊት ቤጌምድርና ትግራይ ውስጥ በተከሰተበት ወቅት ኦሮምኛ ተናጋሪው በአሸናፊነት በመውጣቱ ለ86 ዓመት ያህል ሥልጣን ይዞ መቆየቱን ከላይ አይተናል፡፡ መቼም የጁዎች፣ ጎንደሮችን ድል አድርገው ሥርወ-መንግስታቸውን ደብረ ታቦር ላይ የመሰረቱት በምርጫ ካርድ (ያለነፍጥ) ነበር ካልተባለ በቀር፣ አንዱን ወገን ለይቶ በሂትለርነት መኮነኑ ፍትሃዊ ካለመሆኑም ባለፈ፤ የሚጠቅመው ከመከራ ነፃ እንዲወጣ የምንዋትትለትን ሕዝብ ሳይሆን፣ የአገዛዙን ዕድሜ ለማራዘም ነው፡፡ በተጨማሪም በራሱ በቋንቋው ተናጋሪዎች ብቻ ከተዘጋጁ ድርሳናት የጠቀስኳቸው እነዚህ ሁነቶች፣ በማስረጃ ያልተደገፈውን (አፈ-ታሪኩን) የአኖሌ ጡት ቆረጣ ትርክት ተአማኒነት ያሳጡታል፡፡ ከዚህ ባለፈ የተሸነፈ ሠራዊትን እጅ-እግር መቁረጥ ምኒሊክም ሆኑ ከእርሳቸው በፊት የነበሩ ገዥዎች ይፈፅሙት የነበረ ጭካኔ መሆኑ አይስተባበልም፤ እንዲያውም በአንድ ወቅት አፄ ቴዎድሮስ፣ በሸዋ ላይ ሾመውት የነበረው የምኒሊክ አጎት አቤቶ ሠይፈ ‹‹ሸፍቶብኛል›› በሚል አንኮበር ድረስ መጥተው ወግተው ድል ካደረጉት በኋላ ሠራዊቱ በሙሉ አንድ እጅና አንድ እግሩ እንዲቆረጥ ማድረጋቸውን ተከትሎ፡-
“አፄ ቴዎድሮስ እጅግ ተዋረዱ
የሸዋን ሰው ሁሉ እጅ ነስተው ሄዱ”
ተብሎ መገጠሙ የጉዳዩን እውነታነት ለማሳየት በቂ ነው፡፡
(የእስልምና እምነት እና የኦሮምኛ ተናጋሪው ማሕበረሰብ ጥያቄዎች፣ በ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› የሚኖራቸውን የመፍትሔ ሃሳብ በተመለከተ ሳምንት እመለስበታለሁ)
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
July 23, 2014

ለኢትዮጵያ ከወያኔዎች የተለየ ተመሳሳይ በጎ ራእይ ላላቸው ተቃዋሚ ቡድኖች

ጌታቸው ኃይሌ
እንደምሰማውና እንደማነበው ከሆነ፥ ከአንድ ዓመት በኋላ በሚደረገው ምርጫ የወያኔ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው ይሳተፋሉ። ይኸ እንዴት እውነት ሊሆን ይችላል? ባለፉት ምርጫዎች ምን እንደሆነ ረሥተነዋል እንዳንል፥ ለመርሣት የሚያበቃ ጊዜ የለንም። ምርጫ 97 ላይ ቅንጅቶች፥ “አንዳንድ ቦታ ተጭበርብረናል፤ ይመርመርልን፥ ወይም እነዚያ ቦታዎች ምርጫው ይደገምልም” ሲሉ፥ ወያኔዎችም፥ “እኛም ተጭበርብረናል፤ መመርመሩንና ድጋሚውን ምርጫ እኛም የምንመኘው ነው” ብለው፥ ሁሉም ተመረመረ፤ ምርጫውም ተደገመ። በሁሉም ቦታ፥ የነሱ ተወዳዳሪ የተሸነፈበትንና ቅንጂት ያሸነፈበትን አውራጃ ሳይቀር፥ ወያኔዎች ወሰዱት። ሕዝቡም ቢቆጣ፥ ከቁም ነገር የቈጠረው አልነበረምና የማታ ማታ ቁጣውን ዋጥ አድርጎ ተኛ።

የተቃዋሚ ቡድኖች በሚቀጥለው ምርጫ ለምን ለመሳተፍ እንደወሰኑ ከመሪዎቻቸው የሰማሁት ነገር የለም። ስገምተው ግን፥ እርግጥ ለመሳተፍ ከወሰኑ ምክንያታቸው ከሁለት አንዱ ወይም ሁለቱም መሆን አለበት፤ ወይ እንዲሳተፉ የሚያስገድዳቸው ወያኔያዊ ተጽዕኖ አለባቸው፥ ወይም ወያኔዎቹ ምርጫውን ነፃና ፍትሐዊ ሊያደርጉት ይችላሉ የሚል ተስፋ አድሮባቸዋል። እኔ ግን ለውጥ አለ ብዬ ለማመን እቸገራለሁ። ምክንያቱም መለስ ዜናዊ የሞተው ፖሊሲው እንዳይለወጥ ኀይለ ማርያም ደሳለኝን አደራ ብሎ ነው። እንደሰማሁት ኀይለ ማርያም ደሳለኝ ክርስቲያን ስለ ሆነ፥ በአደራ-በላነት አይጠረጠርም።

ለማንኛውም፥ በምርጫው የሚሳተፉ ከሆነና በምርጫው ተስፋ ከጣሉበት፥ ተመሳሳይ ራእይ ያለቸው ቡድኖች በአንድነት ለመሥራት ፈጠን ብለው መስማማት ይኖርባቸዋል። እስካሁን አዲስ አሳብ አላቀረብኩም። እንዲያውም ቅንጅት የተወለደው በዚህ ምክንያት ነበር። አሁንም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና እንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) አንድ አማራጭ ኀይል ሆነው ለመገኘት የሚያስማማቸው የቅድመ ውሕደት የመግባቢያ ሰነድ በይፋ ወጥቷል። የሰማያዊ ፓርቲ ራእይ መሪ ያሰማቸውን ቃለ ምልልሶች እንዳዳመጥኩት ከሆነ፥ ከነዚህ ሁለት ፓርቲዎች ለኢትዮጵያ የተለየ ፍላጎት የለውም። ሁሉም በኢትዮጵያ አንድነትና በሙሉ የዲሞክራሲ መዋቅሮችና መቆሚያዎች ያምናሉ። የጎሳዎች የባህል መብት መከበርን ተቀብለው፥ የጎሳ ፖለቲካን ያወግዛሉ። እነዚህ ቡድኖች በሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ ለማስወገድ የተዘጋጁት በእነዚህ ባነሣኋቸው መሠረታዊ ነጥቦች ስለሚለያዩ ነው።

የምተቻቸው ተቃዋሚ ቡድኖች ከወያኔዎች ጋር በሌላም ነገር እንደሚለዩ ተስፋ አለኝ። ወያኔዎች የመጡት ሲገዙ ለመኖርና ራሳቸውን ለመጥቀም ነው። የተቃዋሚዎቹ ጥረት ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመጥቀም ነው። ነፃና ፍትሐዊ በሆነ ምርጫ ወያኔዎች ቢሸነፉ፥ ሽንፈቱን አይቀበሉም፤ እነዚህ ቡድኖች ግን ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ መሆቱ በገለልተኛ አስመራጭ ድርጅት ከተረጋገጠላቸው ሽንፈታቸውን በደስታም ባይሆን በጸጋ ይቀበሉታል።
2
የተቃዋሚዎቹ ራእይ እንደ እምነቴ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመጥቀም ከሆነ፥ በፍጥነት አንድ ግምባር ለመፍጠር ቢነሡ፥ ብዙ ችግር ሊገጥማቸው አይችልም። ከልብ ካለቀሱ ዕንባ አይገድም እንዲሉ፥ ከልብ ከጣሩ የአንድነት መንገድ አይገድም። ለምሳሌ፤
1. አባሉ ሕዝብ መሪውን ስለሚከት መሪዎቹ ብቻ የዝግ ስብሰባ አድርገው አንድ አመራርና አንድ የፓርቲ ስም ሊፈጥሩ ይችላሉ፤ ሕዝቡም በውሳኔያቸው የማይስማማበት ምክንያት አይኖረውም። ለኢትዮጵያ የሚያስብና ውገናን የሚኮንን “የእኛ እገሌ ይምራን” አይልም። ዲሞክራሲ በሰፈነበት ሀገር የሚደረገውን ስናይ፥ ፓርቲዎች በመሪ ፍለጋ ላይ ብዙ ይጥራሉ።

2. ይኼ ካልሆነ፥ መሪዎቹ የዝግ ስብሰባ አድርገው፥ ወደ አንዱ ፓርቲ ይጠቃለሉ። ለኢትዮጵያ የሚያስብና ውገናን የሚኮንን ድርጅት “ወደእኛ ፓርቲ እንጠቃለል” ብሎ አያስቸግርም። “በሥሩ ብንጠቃለል የበለጠ ኀይል ያገኛል የሚሉትን” አለዚያ በዕጣም ቢሆን አንዱን ይምረጡ። ዲሞክራሲ በሰፈነበት ሀገር የሚደረገውን ስናይ፥ አንድ ተወዳዳሪ መዳከሙን ሲያይ፥ ተከታዩን ሕዝብ “ወደ እገሌ ሂዱ ብሎ” አስናብቷቸው ይወጣል። እርግጥ፥ እምቢ የሚልም አለ፤ ግን እሱ መሰሉን ፓርቲ ይጐዳና ሲወቀስ ይኖራል።
3. ይኼም ካልሆነ፥ ፓርቲዎች እርስ በርሳቸው የሚወዳደሩበት ቀዳሚ ምርጫ ያድርጉ። ይኸንን አሜሪካ “Primary election” ይሉታል። ቡድኖች በየምርጫው ቦታ የራሳቸውን ተወዳዳሪ አቁመው ያወዳድሯቸው። አንዱ ማሸነፉ አይቀርም። በጠቅላላው ምርጫ ጊዜ የፓርቲዎቹ ሁሉ ተወዳዳሪ ያ በቀዳሚ ምርጫ ያሸነፈው ይሁንና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁሉ ይደግፉት።

ለኢትዮጵያ ተመሳሳይ ራእይ ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአድነታቸውን ዐዋጅ ሲያሰሙ የሚደርሳቸው የሞራልና የገንዘብ ድጋፍ ፥ የአባልነት ማመልከቻን ጨምሮ ሲጎርፍ ይታየኛል።

የአገርን ዉጥረት በአገር መፍታት

ተስፋዬ ደምመላሽ

ተለዋዋጭ ሁኔታዎችንና ፈታኝ ችግሮችን ተቋቁመዉ ማንነታቸዉን፣ ቀጣይነታቸዉን፣ ማረጋገጥ የማይሳናቸዉ ጥልቅ የታሪክ ሥር ያላቸዉ አገሮች የታደሉ ናቸዉ። ዛሬ በዉጥረት የተያዘችዉ ኢትዮጵያ ከነዚህ እድላማ አገሮች አንዷ ናት። ተብትቦ የያዛትን የጭቆና ሥርዓት ሰባብራ ራሷን ነፃ ማዉጣት የሚያስችላት፣ የለዉጥና እድገት እምቅ ችሎታ ያላነሰዉ፣ ጽኑ ብሔራዊ ህልዉና አላት። ኢትዮጵያ የማህበረሰብ፣ የባህል፣ የቋንቋና የእምነት ብዙሃንነትን ያካተተች ብትሆንም ህልዉናዋን የተጠናወቱት የዛሬዎቹ ሞገደኛ ገዢዎቿ እንደሚያዩዋት “የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” ጥርቅም ሳትሆን የተዋለደና የተሳሰረ አንድ ሕዝብ ተደጋግፎና ተከባብሮ በሰላም የሚኖርባትአንድ አገር ናት።

ይህን እዉነታ በእምነትም በተግባርም በመላ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ማረጋገጥ ከገዢዉ “የትግሬ ህዝብ ነፃ አዉጪ” ከተባለ ቡድን በስተቀር ለማንም ከማይበጅ አገር ከፋፋይ የአምባገነን አገዛዝ ለመላቀቅና ብሔራዊ ህልዉናችንን ለማደስ እኛ ነገደ ብዙ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት መዉሰድ ያለብን ወሳኝ እርምጃ ነዉ። ዘረኛ “ነፃ አዉጪ” የአገዛዝም ሆነ የተቃዉሞ ፖለቲካ ጐዳና ለጊዜዉ ጠባብ አራማጆቹን የሚጠቅም ቢሆንም ለዘለቄታዉ የትም የማያስኬድ፣ መዉጫ የሌለዉና መዳረሻዉ ፍሬ ቢስ መንገድ እንደሆነ፣ ይልቅስ የጋራ ብሔራዊ ህይወታችንን በጋራ መወሰን የማናመልጠዉ እጣ ፈንታችን መሆኑ ዛሬ ብዙ የማያከራክር ሃቅ ነዉ። ይህን ሃቅ ሶስት አስርተ አመታት በፈጀ ጦርነት ያገኙት “ብሔራዊ ነፃነት” መራራም ጣፋጭም የሆነባቸው፣ የዚያ ሁሉ ትግልና መስዋዕትነት መጨረሻ ዉጤት በአስከፊ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ስር መማቀቅ ሆኖ ያገኙት ከመረብ ወንዝ በላይ ያሉ ኢትዮጵያዊነታቸዉን የጣሉ ብዙ ትግሬዎች ዛሬ በይፋ ባይገልጹትም በልባቸዉ የሚክዱት አይመስለኝም።

ኢትዮጵያ ከምሽት ወደ ንጋት እንዴት ?
ኢትዮጵያ ዛሬ ጨልማለች። አለምላሚ ሳይሆን አጠዉላጊ በሆነ ብርሃን የራቀዉ የጐሳ ፖለቲካ ተሸንሽና፣ በጐጥ ተመትራ የምትገኝ አገር ናት። ለመረዳት አዳጋች በሆነ መንገድ በታዋቂ ንጉሧ የአፄ ዩሃንስ ዘሮች ሴረኛነትና አድራጊ ፈጣሪነት ከዉስጧ ተኖ የተነሳ አጨላሚ የመከፋፈል ደመና ያንዣብብባታል። ዘመኑ አገራዊ ሉዓላዊነታችን ያልተረጋገጠበት፣ አንድነታችን አስጊ ሁኔታ ዉስጥ የወደቀበት ጊዜ ነዉ። ዉጥረቱ ብዙ ሳይዉል ሳያድር ዘላቂ መቋጫ እንደሚያስፈልገዉ ግልጽ ነዉ፣ ምንም እንኳን ያቆጫጩ አኪያሄድ በቀላሉ ባይታየንም። የጋራ ብሔራዊ ህይወታችን፣ ኢትዮጵያዊነታችን፣ ወሳኝ መስቀለኛ መንገድ ላይ ደርሷል። የሞት ወይስ የሽረት አቅጣጫ፣ ለሁላችንም አደገኛ የሆነ ጠማማና ጠባብ የመለያየት መንገድ ወይስ ቀና፣ ሰፊ የአንድነት ሕዳሴ ጐዳና?
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ዉጥረት ዉስብስብ የሚያደርገዉ ከኤርትራ ጋር ያለን ማለቂያ የሌለዉ የተንዛዛ መፋጨት ነዉ። የኢትዮጵያና የኤርትራ “መለያየት” እድሜ ልክ ቀጣይ በሆነ መጥፎ፣ አጨቃጫቂ፣ የባልና ሚስት ፍቺ ይመሰላል። ከመረብ ወንዝ በታች ባሉ ወያኔ ትግሬዎች የተቋቋመዉና ዛሬ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት ግራ በሚያጋባ መንገድ የሚያምስ ዘረኛ አምባገነናዊ አገዛዝ ራሱ ከጽንሱ የኤርትራ እጅ አለበት። ከዛሬ አመራሩ ዉስጥም የኤርትራ ትግሬዎች አሉበት። ሆኖም ከመረብ በላይ ባሉ የትግሬ ፖለቲካ ሊህቃንና ከመረብ በታች ባሉ የጐሳና የፖለቲካ አቻዎቻቸዉ መካከል ነባር፣ ባመዛኙ የጣሊያን ቅኝ አገዛዝ የፈጠረዉ ልዩነት፣ አለመጣጣምና መናናቅ አለ። እንዲሁም ሁለቱ ገዢ ወገኖች ጊዜዉ የፈጠራቸዉ፣ ሰሞኑን የኢሳያስ አፍወርቂ ቅጥረኞች የሚመስሉ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች “እናስታርቅ” ብለዉ የተነሱባቸዉ፣ የብሔርተኝነት ቅራኔዎችና “ልማት” ከሚሉት ከኢትዮጵያ የዉስጥና የዉጭ ብዝብዛ አጀንዳ ጋር የተያያዙ ስልታዊ ልየነቶችም አሏቸዉ። በተጨማሪ አንዱ ገዢ ወገን ሌላዉን ከሥልጣን በትጥቅ ትግል ለማዉረድ የተነሱ ተቃዋሚ ሃይሎችን በቁጥጥሩ ሥር “ደግፎ” በፖለቲካ መሣሪያነትና ወካይ ጦር ተዋጊነት ይዟል። ይህ ሁሉ ዘባዝንኬ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ዉጥረትና መፍቻዉን ዉስብስብ አድራጊ ነዉ።
የኤርትራ አምባገነናዊ አገዛዝ ከኢትዮጵያ ጋር በቀጥታ የጦር ግጭት ከማድረግ ቢቆጠብም (አቅም አንሶት ወይም በባድመ ዉጊያ የደረሰበትን አይነት ሽንፈት ፈርቶ) ብሔራዊ ጐናችን ዉስጥ በቋሚነት ተሰክቶ ቀሰ በቀስ የሚያደማን ጋሬጣ ከመሆን ጋብ የሚል አይመስልም። ብሔራዊ ነፃነት የተቀዳጀሁ፣ ራሴን የቻልኩ አገር ነኝ ባይ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጉያ የማዉጣት ወይም የማራቅ ፍላጐቱም ችሎታዉም የለዉም። ሆን ብሎም ይሁን ሳያሰላ ብሔራዊ ዉጥረታችን ዉስጥ የራሱን እኩይ ፀረ ኢትዮጵያ ሚና ይጫወታል፣ በተለይ አጋሮቹም ተቀናቃኞቹም የሆኑት ወያኔዎች ስልጣን ላይ እስከቆዩ ድረስ። ይህን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለኤርትራ ህዝብም የማይበጅ፣ ሲበዛ ጨቋኝ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ማስወገድ የተጨቋኙ ህዝብ ራሱ ሥራና ሃላፊነት ቢሆንም አገዛዙ የኢትዮጵያ ገዳዮች ላይ ያለዉን ቀጥታና ተዘዋዋሪ ጐጂ ተጽእኖ የብሔራዊ ህይወታችን ሕዳሴ ትግል በሚገባ መተንተን፣ መገንዘብና መቋቋምና ያለበት ነገር ነዉ። ይህ ካልሆነ ኢትዮጵያና ኤርትራ በሰላም ተለያይተዉም ሆነ ተዋህደዉ ሊኖሩ አይችሉም።
2
እንግዲህ ከተያዝንበት የተወሳሰበ ብሔራዊ ዉጥረት መዉጣት የምንጀምረዉ እንዴት ነዉ? ከየት ወይም እንዴት ነዉ የምንነሳዉ? ጥያቄዉ ይህ ነዉ። የገጠመን የመንግሥት ወይም የፖለቲካ ለዉጥ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ይህ አይነት ለዉጥ ለአገር ማዳን ትግሉ አሰፈላጊና ወሳኝ ቢሆንም በቂ አይደለም። ጥያቄዉን በዝች ጽሑፍ በቅጡ ለመመለስ የሚሞከርም ባይሆን ለመልሱ አስተዋጽዎ የሚሆኑ ጥቂት አወያይ ሃሳቦች መሰንዘር ይቻላል። “እንዴት” የሚለዉን ጉዳይ ሳነሳ የሚያስፈልገንና የሚበጀን ዘላቂ የሆነ ሰላማዊ የለዉጥ ዘመቻ ነዉ ወይስ የትጥቅ ትግል በሚል የተለመደ “የአማራጮች” አቀራረብ በመገታት አይደለም፣ በግሌ አነዱ ወይም ሌላዉ መንገድ ይበልጥ ያስፈልጋል የሚል እምነት ቢኖረኝም እንኳን።

ጉዳዩ በሰፊዉ ሲታይ በተለያዩ መስኮች፣ ረድፎችና ደረጃዎች የተለያዩ የትግል ዘዴዎችና አቅሞች (የነፍጥንም ጨምሮ) እየገነቡ በመጠቀም በጀግንነት የሚንቀሳቀሱ አገር ወዳድ ዜጐችና ተቃዋሚ ሃይሎች ዘንድ አግባብነት አለዉ። እንደ አገር ያለንበት ዉጥረት በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጉዳዮች፣ ለምሳሌ በዜግነትና አገራዊ ሉዓላዊነት፣ በኢኮኖሚና ማህበረሰባዊ ኑሮ፣ በመንፈሳዊ ሕይወት፣ በትምህርትና ባህል መስክ፣ በመንግሥት ሥልጣን አያያዝ፣ አገሪቱ ከጐረቤት አገሮች፣ በተለይ ከሱዳንና ከኤርትራ (ኤርትራ ራሱን የቻለ ለኢትዮጵያ “የዉጭ” አገር ነዉ ከተባለ) ጋር በተከተተችባቸዉ ጐጂ፣ የተዛቡ ግንኝነቶች ይታያል። በተለይ ደግሞ ቀኖናዊ ለሆኑ አራማጆቹ የተወሰነ ስነልቦናዊ እርካታ ከመስጠቱ ባሻገር ምንም ያህል ገንቢ የሆነ አካባባዊም ሆነ አገራዊ ጐን በሌለዉ ጐሳ “ነፃ አዉጪ“ ፖለቲካ በአገሪቱ መስፋፋት ይከሰታል።

በነዚህ ሁሉ መስኮች በአንጻር ራሳቸዉን የቻሉ ግን የተያያዙ አገር አዳኝ እንቅስቃሴዎች በተለያዩ ነገደ ብዙ የኢትዮጵያዊያን ስብስቦችና ወገኖች ሊኪያሄዱ ይችላሉ። አስፈላጊነታቸዉም አጠያያቂ አይደለም። ነገር ግን ከላይ ያነሳሁትን ጥያቄ በሚመለከት የማጐላዉ የታጋይ ወገኖችን የየብቻ ወይም የጋራ አድራጊ ፈጣሪነት ሳይሆን ትግላቸዉን በቅንብር የሚያነሳሳ፣ የሚያካትት፣ የሚደግፍና ከፍ የሚያደርግ፣ መልሶም በትግላቸዉ የሚጠናከር ጠቅላላ የኢትዮጵያ ራስን አዳኝ ብሔራዊ ተንቀሳቃሽነት ላይ የሚያተኩር ነዉ። ከዚህ ትኩረት ጀርባ ከአገራዊ ባህላችንና ልምዳችን እይታ ጋር የተያያዘ ቅድመ ግንዛቤ አለኝ። ይኸዉም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ልምድ የራሱ ሕይወትና ተጽእኖ የሌለዉ፣ ዝም ብሎ ሲገፉት የሚገፋ በደልና ጥቃት ተቀባይ፣ በቀላሉ የኛን (የዜጐችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የምሁራንን) መታደግ ጠባቂ ሆኖ የሚታይ ሳይሆን ለለዉጥና እድገት ክፍት የሆነ፣ ራሱ ተንቀሳቃሽ ሃይል መሆኑ ወይም ሊሆን መቻሉ ነዉ።

ይህ ግንዛቤ በመሠረቱ ትክክል ከሆነ (በዝርዝር ሊያከራክር ቢችልም) ከተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን ጀምሮ በተቃዋሚም ሆነ በገዢ አብዮተኞችና ፖለቲከኞች ዘንድ መንጸባረቅ አካቶ ያላቋረጠ የአገር እይታ ተለምዶን መክላትና በምትኩ የተሻለ፣ ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ተሐድሶ አስፈላጊና ተገቢ የሆነ አመለካከት ማዳበር ያሰችለናል። ተለምዶዉ የጋራ ብሔራዊ ህይወታችንን፣ ኢትዮጵያዊነትን፣ በጅምላ አሉታዊ በሆነ መንፈስና አቀራረብ “የችግሮች” ምንጭና ድምር ብቻ አድርጐ አይቶ፣ በእዉንም ሆነ በምናብ ለታዩ ችግሮች የአገራዊ ህልዉናችን ተቀናቃኝ የሆኑ የፖለቲካ “መፍትሔዎች” ያራባ ነዉ። ልምዱ ኢትዮጵያን ከሃያ አመት በላይ የገዛዉና ዛሬም በገዢነት ላይ እያለ ራሱን “የትግሬ ህዝብ ነፃ አዉጪ” እያለ የሚጠራ ወገን ኢትዮጵያዊነትን የሚያፍን አደገኛ ዘረኛነት ጨምሮ የሚከተለዉ ነዉ።
ስለዚህ ዛሬ ባለንበት የዉጥረት ሁኔታ የጋራ ብሔራዊ ህይወታችን የራሱ ተጽእኖ ያለዉ ተንቀሳቃሽ ሃይል ነዉ ማለት አጠያያቂ ሊሆን ይችላል። በመላ የአገሪቱ ጉዳዮች ዉስጥ ቦርቡሮ የገባና በላያቸዉ ላይም የተስፋፋ አምባገነናዊ የጐሳ ብሔርተኝነት አገዛዝ በሰፈነበት ባሁኑ ዘመን፣ የአገሪቱ ሰፊ ህዝብ ጥቅሞችና “ልማት” ከሥር እስከ ቅርንጫፋቸዉ ለተወሰኑ የዉስጥም የዉጭም ተቀራማቾች ተመቻችተዉ በቀረቡበት ጊዜ፣ እንዴት ብሎ ነዉ ሃቀኛ ኢትዮጵያዊነት የራሱ ተጽእኖ ሊኖረዉ የሚችል? ጥያቄዉ ተገቢ ነዉ፣ መልሱም ስላለንበት ብሔራዊ ዉጥረትና ስለ ፍችዉ ያለንን ግንዛቤ ያዳብርልናል። በይበልጥ ጠቃሚነትም ለዚህ ጥያቄ የምናበጀዉ መልስ ከዉጥረቱ ለመላቀቅ እንደ አገር የምናደርገዉን ጥረት ሊያበረታታና ሊያግዝ ይችላል።

ለጥያቄዉ የኔ ምላሽ የሚከተለዉ ነዉ። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ጠንካራ ታሪካዊ ሥር ባላቸዉ አገሮች ዉስጥ ብሔራዊ ዉዝግብና ሽብር፣ አብዮት የሚያመጣቸዉን ፖለቲካዊ፣ ህብረተሰባዊና ብሔራዊ ዉጥረቶች ጨምሮ፣ አገራዊ ህልዉናን ጨርሰዉ የሚያወድሙ ወይም እንዳልነበረ የሚያደርጉ አይደሉም። ለምሳሌ ቻይና በቀዳሚዉ የሃያኛዉ ክፍለ ዘመን ግማሽ የደረሰባትን፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ካለችበት አስጊ ሁኔታ የከፋ፣ ከባድ ብሔራዊ ዉጥረት መጥቀስ ይቻላል። እንደ ፈረንጆች ዘመን ቀመር 19ኛዉ ምእተ አመት እየተገባደደ 20ኛዉ ክፍለ ዘመን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 1940ዎቹ መጨረሻ ቻይና የሄደችበት የዉጥረት መንገድ ምን ይመስል ነበር? ጥንታዊ ንጉሠ ነገሥታዊ የአገዛዝ ሥርዓቷን መፍረስ፣ በአዉሮፓ አገሮች በቅርምት መያዝንና መበዝበዝን፣ በጃፓን መወረርንና በወረራዉ የህዝቧን በአረመኔያዊ ጭፍጨፋ ማለቅንና መሰቃየትን (ናንኪንግ እሚባል ከተማዋ ብቻ ከ250,000 የሚበልጡ ሰላማዊ ዜጐቿ ተገለዋል)፣ እንዲሁም ከዉስጧ የጦርነት ባላባቶችን ዉዝግብና በብሔርተኞችና በኮሚንስቶች መካከል የተደረገ የእርስ በርስ ግጭትንና አብዮታዊ ትግልን ያካተተ ጐዳና ነበር። ቻይና እነዚህን ብሔራዊ ህልዉናዋን ከባድ አደጋ ላይ የጣሉ ከዉስጥም ከዉጭም የመነጩ ተፈራራቂና ተደራራቢ ዉጥረቶች ሁሉ አሸንፋ ነዉ ዛሬ ላለችበት ከፍተኛ የልማትና የሃየለኛ አገርነት ደረጃ የበቃችዉ።
እንግዲህ ኢትዮጵያ ከቻይና ባልተናነሰ ደረጃም ባይሆን የማንሰራራትና የሕዳሴ እምቅ ችሎታ አላት። አንድ የዘርፌ ከበደን መንፈሳዊ መዝሙር ቃላት ለመዋስ፣ ቢመሽም ለኢትዮጵያ ቀን አለ። እንደ ኢትዮጵያና ቻይና ያለ ጠንካራ ታሪካዊ መሠረት ያለዉ ብሔራዊ
3
ልምድ ለተወሰነ ጊዜ ከዉስጥ ሊበጠበጥና ሊናወጥ ይችላል። የዉጭ ጠላት ሃይሎች ወይም በዝባዦች በዉስጥ ተባባሪዎች፣ በዉጨኞች መጠቀሚያዎችና ተጠቃሚዎች፣ እየተረዱ ልምዱን ሊያናጉትና ሊያዳክሙት ይችላሉ። በዚህ አይነት ጊዜያዊ ሄደት የአገር ሉዓላዊነት ከባድ ወጥረት ያጋጥመዉ ይሆናል። የሆነ ሆኖ ግን አገሩ ከገጠመዉ ዉጥረተ ለመዉጣት ተንገዳግዶም ቢሆን የሚነሳዉ አካቶ ካልወደመዉ ከራሱ ታሪካዊ ህልዉና ነዉ። ራሱን ለማዳን የሚንቀሳቀሰዉ፣ ከጨለማ ወጥቶ ብርሃን የሚላበሰዉ፣ ከደረሰበት ጥቃትና ጉዳት በተረፈ ብሔራዊ ህይወቱ ነዉ። የራሱን ብሔራዊ አቅሞችና ፀጋዎች አድሶ፣ አሰባስቦና አጠናክሮ ነዉ።
አገር በዚህ የሕዳሴ አነሳሱና እንቅስቃሴዉ ከሌሎች አገሮች ወይም ከዓለም አቀፍ ምንጮች እዉቀት፣ መረጃዎች፣ ሃሳቦችና ቴክኖሎጂዎች ቢያገኝም እነዚህን መሣሪያዎች በሚገባ ለመጠቀም ከራሱ ጋር ማዛመድና ማዋሃድ ይኖርበታል። መሣሪያዎቹ አገራዊ ባህልን በጅምላ መንቀፊያና ማፍረሺያ ወይም መተኪያ አይሆኑም፣ ይልቅስ ማደሻና ማሻሻያ ነዉ መሆን ያለባቸዉ ። ይህ ነጥብ በተለይ ዘመናዊ ፖለቲካ ሃሳብ የዛሬዉ የኢትዮጵያ ራስን አዳኝ ብሔራዊ ትግል ዉስጥ ያለዉን አገባብ ይመለከታል። ስለዚህ በወቅቱ የኢትዮጵያ የለዉጥ ትግል ሂደት ሃሳቦች ላይ የተመሰረተ ፖለቲካችንና ራሱ ተንቀሳቃሽ የሆነ ብሔራዊ ህልዉናችን ያላቸዉን ወይም ሊኖራቸዉ የሚገባን ግንኙነት ቀረብ ብሎ መቃኘቱ ይጠቅማል።

የፖለቲካ ሃሳብና ብሔራዊ ባህል በትግል ትስስር ይህ ንዑስ ርእስ የሚነሳበትን ግንዛቤ ከጅምሩ ግልጽ ላድርግ። ዘመናዊ የሚባሉ የፖለቲካ ሃሳቦች (ለምሳሌ “ዲሞክራሲ”፣ የማህበረሰቦች ወይም ያካባቢዎች “ራስ ገዝነት”) እና ባህላዊ ብሔርተኝነታችን ወይም አገር ወዳድነታችን በተናጠል የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ህልዉና ለዘለቄታዉ በብቃት አያካትቱም፣ አያረጋግጡም። ትስስራቸዉ አስፈላጊ ነዉ። ጉዳዩ በዛሬዉ የለዉጥ ትግል ዉስጥ ግንኙነት አላቸዉ ወይስ የላቸዉም ሳይሆን የግንኙነታቸዉ ቅርጽና ይዘት ነዉ። ለምሳሌ ዛሬ በአገራችን ያሉ የተለያዩ እምነታዊና ባህላዊ ማንነቶችን እኩልነት በመርህ ስንደግፍ ለዚህ መርህ ወያኔዎች የሰጡትን በመሠረቱ ስታልናዊ የሆነ የአምባገነን ፖለቲካ ቅርጽና ትርጉም ዉዳቂነት ተገንዝበንና አስገንዝበን ነዉ የሚሆነዉ። ለመርሁ በኢትዮጵያ ህዝብ ይበልጥ ተቀባይነት ያለዉ የተሻለ አማራጭ ፍቺ፣ መዋቅርና አፈጻጸም ሰጥተን ነዉ።

ሆኖም ፖለቲካ ሃሳባችንና ብሔራዊ ልምዳችን ስላላቸዉ ትስስር በቅጡ ለመወያየት መጀመሪያ አንጻራዊ ልዩነታቸዉን በግልጽ ማስቀመጥ ያስፈልጋል።ፖለቲካ ሃሳብ ስል የአገርና የህዝብ ጉዳዮችን ሆን ብለንና አትኩረን የምናስተዉልባቸዉንና የምንቀርጽባቸዉን ፈርጆች፣ መርሆች፣ እምነቶችና ጽንሰ ሃሳቦች፣ እንዲሁም ዲስኩራዊ የትንተና፣ የክርክርና የትችት እንቅስቃሴዎች በመመልከት ነዉ። እነዚህን ዘመናዊ የፖለቲካ ንቃተ ህሊናችን ፈጠራዎች ወይም ዉጤቶች ራሳቸዉንም ሆነ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ገዳዮች ዉስጥ ያላቸዉን እዉን አገባብ መፈተሽ፣ መገምገም፣ መለወጥና ማሻሻል እንችላለን። ብሔራዊ ባህል የምለዉ በታሪክ ሂደትም አጋጣሚም ሥርና ቅርጽ የያዘ፣ የተፈተነ፣ በዝግመት እያደገና እየዳበረ የመጣዉን የኢትዮጵያን ማንነት ወይም አገርነት ልምድ ለመለየት ነዉ። ባህሉ ከጊዜ ወደጊዜ ተቋማዊና ቴክኖሎጂያዊ ዘመናዊነትን በጨረፍታ ያስተጋባ ቢሆንም በመሠረቱ ታሪካዊ ሂደት ያፈራዉ፣ የምንኖረዉ ልምድ እንጂ ትናንት የመጣ የፖለቲካ ሃሳብ የፈጠረዉ አይደለም። የማህበረሰብ፣ የባህልና የቋንቋ ብዙሃንነት የተመላበት ብሔራዊ ህልዉናችንን “መሥራች አባቶች” ሆን ብለዉ በረቂቅ ሃሳቦች አልነደፉትም።

ፖለቲካ ሃሳብ ሥር ነቀል ቅርጽና ይዘት ቢኖረዉም፣ ተራማጅ ቢባልም፣ የግድ ብሔራዊ ህልዉናን ተጻራሪና አፍራሽ አይደለም። ለምሳሌ የ18ኛዉን ምእተ አመት የፈረንሳይ አብዮትና የ20ኛዉን ክፍለ ዘመን የቻይና አብዮት መጥቀስ ይቻላል። አብዮት አንድን አገር ወይም ህዝብ አንድነቱንና ሉዓላዊነቱን ጠብቆ የራሱን መሠረታዊ ለዉጥና እድገት ማኪያሄድ የሚያስችል ሃይል ሊሆን ይችላል ማለት ነዉ። ነገር ግን አገራችን ዉስጥ ፈሩን በለቀቀ የተማሪዎች ግራ ክንፈኛ ንቅናቄ ተጀምሮ በወያኔዎች ጐሳዎችን “ነፃ አዉጪ” ነኝ ባይ አገር ከፋፋይ አምባገነናዊ አገዛዝ የተገባደደዉ አብዮታዊ ሂደት የኢትዮጵያ የራሷ የለዉጥ ትግል ሳይሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአመዛኙ የአገሪቱን ህልዉና ተጠናዉቷል፣ ምንም እንኳን ትግሉ እህብረተሰቡ ዉስጥ አጀማመሩ አገራዊ የነበረ ቢሆንም።
ይሁን እንጂ የፖለቲካ ሂደቱ በጅምላ “የኢትዮጵያ አብዮት” ተብሎ ተፈርጇል። የዚህን ፍረጃ አጠያያቂነት አጉልቶ የሚያሳይ አንድ ከጥቂት አመታት በፊት ገብሩ ታረቀ በተባለ ደራሲ በእንግሊዝኛ የተጻፈ መጽሐፍ አለ። መጽሐፉ ባመዛኙ ያጠነጠነባቸዉ ጉዳዮች የኤርትራና የትግሬ ጐሰኛ ብሔርተኞች በትጥቅ ትግል እንዴት የኢትዮጵያን “አብዮታዊ ጦር ሠራዊት” አሸንፈዉ ራሳቸዉን ነፃ እንዳወጡ የሚያትቱ ናቸዉ። የመጽሐፉ ርዕስ ግን The Ethiopian Revolution ነዉ። እዚህ ብዙዉን ጊዜ የማይነሳ አወያይ ጥያቄ አለ። ይኸዉም አብዮታዊ የተባሉ የኢትዮጵያ ጦር ሃይሎች የተሸነፉበት ብቻ ሳይሆን አካተዉ የወደሙበትና በመጨረሻም አገሪቱ ከዉስጧ ለተነሱ ግን ከፋፋይ የቅኝ ገዢነት መንፈስ ላላቸዉ ደመኞቿ ተገዥ የሆነችበት አኪያሄድ የኢትዮጵያ አብዮት የተባለዉ፣ የአገሪቱ የራሷ ለዉጥ የሆነዉ እንዴት ነዉ?
4
ይህን ሰፊ ታሪካዊና ጽንሰ ሃሳባዊ ትንተና የሚጠይቅ ጉዳይ እዚህ ልሄድበት አልሞክርም። ያነሳሁት ዘመናዊ፣ አገር ለዋጭ፣ ፖለቲካ ሃሳብና በታሪክ ዝግመት የዳበረ ብሔራዊ ህልዉና ያላቸዉን ወይም ሊኖራቸዉ የሚችልን ግንኙነት በሚመለከት የተራማጅነት ባህላችን የፈጠረዉን፣ በርዝራዥ ዛሬም ያልተለየንን፣ መሠረታዊ ዉዝግብ ለመጠቆም ነዉ። አክሎም ከዛሬዉ የለዉጥ ትግል አኳያ አበዮታዊ ልምዳችንን ለተሟላ መልሶ ማስተዋልና ማመዛዘን ከፍተን ከልምዱ ጋር ያለንን የርዕዩት አለምና የፖለቲካ ሂሳብ መዝጋት የሚያስፈልገን መሆኑን ለማመልከት ነዉ።

እንግዲህ በዛሬዉ የኢትዮጵያ የለዉጥ ትግል፣ ሃሳቦች ላይ የተመሠረተ ስልታዊ የፖለቲካ ሥራን ከጋራ ብሔራዊ ህይወታችንና እንቅስቃሴያችን ጋር የምናዛምደዉ እንዴት ነዉ? በኔ ግምት ጉዳዩ በአንድ በኩል የብሔራዊ ልምዳችንን ተገቢ ግንዛቤ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሃሳቦችን አቀራረባችንና አያያዛችን ይመለከታል። የማዛመዱ ሥራ መነሻችን አገራዊ ህልዉናችን እንጂ ረቂቅ ርዕዩተ ዓለም አይደለም። የተለያዩ የዘር ብሔርተኝነት እቅዶች ወይም ጐሳ “ነፃ አዉጪ” የፖለቲካ ዉጥኖችም አይደሉም። የነፃነትና የዲሞክራሲ ጉዳዮች፣ የአካባቢ፣ የባህልና የእምነት እኩልነት ጥያቄዎች፣ የኢኮኖሚ ልማትና የማህበረሰባዊ ኑሮ እንቅስቃሴዎችና የሌሎችም ጉዳዮቻችን መነሻና መዳረሻ የምንጋራዉ ብሔራዊነታችን፣ ኢትዮጵያዊነታችን ነዉ።
የጋራ ብሔራዊ ባህላችንን ከዘመናዊ ሃሳቦች ተነስቶ መመዘን፣ መተንተንና መገምገም፣ ለመላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ በሚጠቅም መልክ የሚለወጥበትንና የሚሻሻልበትን መንገድ መፈለግ አንድ ነገር ሲሆን፣ ባህሉን ከሥር እስከ ቅርንጫፉ በጅምላ ተቃርኖ በጥላቻ በተዋጠ ተራ ዘረኛነትም ሆነ በከፊል የረቂቅ ርዕዩተ ዓለም ፈጠራ በሆነ ጐሰኛ ብሔርተኝነት አማካኝነት እንዳልነበረ ለማድረግ መሞከር ግን ጨርሶ ሌላ ነገር ነዉ። የኋለኛዉን አደገኛ፣ በእምቁ አገር አፍራሽ፣ አዝማሚያ የዛሬዉ የለዉጥ ትግል በቆራጥነትና በዘዴ ሊቋቋመዉና ቢያንስ ጥግ ሊያስይዘዉ ይገባል።

አገራዊ ልምዳችንን በሚመለከት “ተራማጅ” የፖለቲካ ሃሳባችን ሳይጨብጠዉ የቀረ ወይም ሊረዳዉ ያልቻለ አንድ ዋና ነገር አለ። ይኸዉም ልምዱ ለትችትም ሆነ ለተጨባጭ ምርምርና የእዉቀት ክትትል ክፍት የሆነ እዉነታ ቢሆንም እንደማንኛዉም ከታሪካዊ ማንነት ጋር የተሳሰረ ብሔራዊ ልምድ ስለራሱ አግባብ ያለዉ የራሱ ግንዛቤ፣ አመኔታና ያነጋገር ዘይቤ አለዉ። ለተመዘገቡ ተጨባጭ ታሪካዊ ሁነቶች፣ ክንዉኖችና የታላላቅ መሪዎች ድርጊቶች (ለምሳሌ የአፄ ምኒልክ) የራሱ ፍቺና እሴት ሰጪ ትረካ፣ የራሱ አተረጓጐም፣ እምነትና የአነጋገር ዘይቤ አለዉ። ቁም ነገሩ ይህን የብሔራዊ ባህላችን ህያዉ ቅርጽ አስተዉሏችንና አቀራረባችን ነዉ።
በዚህ አገራዊ ማንነትና እመነት ገንቢ በሆነ ጐኑ ብሔራዊ ባህላችን ተጨባጭ ታሪካዊ እዉነታዎችን ዝም ብሎ ቃል በቃል ዘጋቢና ገላጭ ስላልሆነ አብዮተኞቻችን ያለማመዛዘን እንዳደረጉት ባህሉን ላይ ላዩን የሳይንስ ቋንቋ በሚናገር ዘመናዊ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና አይን አይተን እዉነት አይደለም፣ ዉሸት “የአፈታሪክ” ፈጠራ ነዉ ብለን የምናጣጥለዉ አይደለም። አለበለዚያ አንድን የእምነት ባህል፣ ለምሳሌ የክርስትናን ወይም የእስልምናን አመኔታ ከነአለም አፈጣጠር ትረካ ልምዱ፣ በተመሳሳይ ጥራዝ ነጠቅ “ሳይንሳዊ” እይታ ዝቅ አድርጐ እንደመገመት ይሆናል። ቅኔን ወይም ግጥምን እንደ ተራ ድርሰት ማንበብ ይቆጠራል።

ብሔራዊ ባህላችን አላግባብ በእዉነታ ዘጋቢነት ብቻ ታይቶ አፈታሪክ ነዉ ቢባልም እንኳን በዚህ ሁኔታዉ በአበዮቱ ሳቢያና በድህረ አብዮቱ ዘመን በአገራችን ከሰፈነዉ ተራማጅ የተሰኘ የፖለቲካ አስተሳሰብ ባህል አይለይም። ዘመናዊዉ አብዮታዊ ተብዬ የፖለቲካ አስተሳሰባችን ራሱ በተራ አፈታሪክ የተሞላ ነዉና። ይህን ለማየት ብዙ ሐታታ ዉስጥ ሳንገባ በድህረ አብዮቱ ዘመን የተፈለፈሉ፣ ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ያልተገናኙ ብቻ ሳይሆኑ ምንም ያህል ጽንሰሃሳባዊ ይዘትም የሌላቸዉ የርዕዩተ አለማዊ ቃላትን ጥርቅም፣ ለምሳሌ “ዲሞክራሲን” እና “የህግ የበላይነትን”፣ ከደርግና ከወያኔ አምባገነናዊ አገዛዞች ጋር ማነጻጸር ይበቃል። አብዮታዊም ተባለ ልማታዊ ከወያኔ “ዲሞክራሲ” የበለጠ እዉን ሁኔታን ገላጭና ጨባጭ ነኝ ባይ ግን ጨርሶ ከእዉነታ የራቀ ግልብ አፈታሪክ የት አለ? በዛሬዉ አገር አዳኝ ትግል እንግዲህ የጋራ ብሔራዊ ልምዳችን ያለዉን የራስ ግንዛቤና አመኔታ በተገቢ ቦታዉ የምንቀበለዉና በተሳትፎ የምናንጸባርቀዉ ዉስጣዊ የማንነታችን ገጽታ ነዉ፣ ህያዉ አነሳሽና አንቀሳቃሽ ሃይላችን ነዉ። ከዉጩ ሆነን ባልተመዛዘነ ረቂቅ ሃሳባዊና ፖለቲካዊ አቀራረብ ልንተነትነዉና ልንተቸዉ ስንሞክር ከግጥም ወደ ስድ ንባብ ዝቅ እናደርገዋለን፣ ህያዉነቱን፣ አነሳሽ ሃይሉን እናሳጣዋለን። በዚህ መንገድ ራሳችንንም ለገዛ ብሔራዊ ባህላችን ባይታወር በማድረግ፣ ራሳችንን በማዳከም፣ በቀላሉ የዉስጥና የዉጭ ፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ግፊትና በደል ተቀባይ ሆነን እንቀጥላለን። በዚህ ሁኔታ የምናጠነጥነዉ የፖለቲካ ሃሳብ ደግሞ ለተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ስብስቦች በመለስተኛ ደረጃ እንቅስቃሴ ማሰላሰያ፣ ማደራጂያና መምሪያና ከመሆን አልፎ የሚኖረዉ ሕዝብ አነሳሽ፣ አወያይና አታጋይ ሰፊ አገራዊ ትርጉም ወይም ራዕይ ዉስን ሆኖ ነዉ የሚቀረዉ። ተቃዋሚ ወገኖች ራሳቸዉ ብሔራዊ ልምዳችን የሚሰጠዉን አነሳሽ መንፈስና አንቀሳቃሽ ሃይል ጠልቀዉ ሳያካትቱ በፖለቲካ ሃሳቦችና ግቦች (ፍትህ፣ ድሞክራሲ ወ.ዘ.ተ) ዙሪያ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እነሱንም ሆነ አገራዊ ትግሉን ሩቅ አይወስድም። የትግል ጉዟቸዉ አገር ነፃ ማዉጣት የሚያደርስ ለዘለቄታዉ በቂ “ነዳጅ” አይኖረዉም።
5
ይችን መጣጥፍ ከማገባደዴ በፊት በዛሬዉ የለዉጥ ትግል ብሔራዊ ልምዳችንን በሚመለከት ሊኖረን ስለሚገባ ግንዛቤ የምለዉን እዚህ አቁሜ በትግሉ ዉስጥ ሃሳቦችንና መርሆችን በአግባብ ከማካተት ወይም ከመከታተል አኳያ መወጣት ያለብንን ተግዳሮቶችና ችግሮችም ባጭሩ ልሂድባቸዉ። በቅድሚያ መጨበጥ ያለብን ነገር የዛሬዉ የሃሳብ ክትትል እንቅስቃሴያችን ከየት እንደሚነሳ ነዉ። ለአገር የሚበጅ፣ በመላ የኢትዮጵያ ዜጐችና ማህበረሰቦች ዘንድ ይበልጥ ተቀባይነት ሊኖረዉ የሚችል ወደ ፊት ተራማጅ የፖለቲካ ሃሳብ በአዲስ መንፈስና ሁኔታ ለማዳበር በአስተሳሰብ ልምዳችን የት እንደነበርንና ዛሬ የት እንዳለን ማስተዋል ግድ ይላል። እዚህ ላይ ጉዳዩ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በቅርቡ በጻፈዉ መጽሐፉ (ዴሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ) እንደሚያየዉ ወደ ኃላ ተመልሶ ርዕዩተ አለማዊ ክርክር ለማድረግ መፈለግ ወይም አለመፈለግ አይደለም። ብርሃኑ ራሱ እንደሚረዳዉ ዛሬ የገጠመን ከባድ ተግዳሮት ያለፈዉን፣ ግን በወያኔ አገዛዝ ከሞላ ጐደል ቀጣይነት ያገኘዉን፣ አምባገነናዊ የፖለቲካ አስተሳሰብና አሠራር ሥርዓት መቋቋምና መስበር፣ ከሥሩ መመንገል ነዉ። አያይዞም ሥርዓቱ ዛሬ የጋራ ብሔራዊነታችንን ተጠናዉቶ አገራዊ አንድነታችን ላይ ብቻ ሳይሆን አካባቢያዊና ማህበረሰባዊ ራስ ገዝነታችን ላይ ያሳረፈዉን ጐጂ ተጽእኖ ለማስወገድ ነዉ። ይህ ሥራ ርዕዩተ አለማዊ ክርክር ቢያስነሳም ክርክሩ አስፈላጊ ነዉ።

ከዚህ በፊት በሌላ ጽሑፍ እንዳልኩት፣ በአብዮቱ ጊዜና በድህረ አብዮቱ ዘመን፣ በተለይ በወያኔ አገዛዝ፣ በአገሪቱ የተስፋፋዉን በጥልቅ እንከናማ የሆነ ግራ ክንፈኛ የፖለቲካ አስተሳሰብና እምነት ባህል መልሰን ሳንፈትሽና ሳናርም አዲስ “እዉነተኛ” ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማቋቋም መሞከር ሙጃ የዋጠዉ ያልተጐለጐለ እርሻ መሬት ላይ ዘር በትኖ ሰብል ለማምራት እንደመጣር የሚቆጠር ነዉ። የወያኔ አገዛዝ ነገ ቢወገድም አስተሳሰቡ በቀላሉ ባንዴ አብሮ የሚወገድ አይደለም። እምነቱ ከአገዛዙ ዉጭ በተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ጐሰኛ ብሔርተኞች፣ መልሰዉ ባልታነጹ “ተራማጆች” እና አልፎ አልፎም ጉዳዩን ጠለቅ ብለዉ በሂሳዊ አይን ባላዩ ገራገር ዜጐች ዘንድ ከሞላ ጐደል የሰፈነ ነዉ።

እንግዲህ በዉጥረት ዉስጥ የሚገኘዉን ብሔራዊ ህይወታችንን ለማዳን በፖለቲካ ሃሳብ መስክ ላይ ስንታገል መስኩን ራሱን አዙረን እያየንና የአረም ማጽዳት ዘመቻ እያኪያሄድን ነዉ የሚሆነዉ። ምክንያቱም ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ የፖለቲካ ቋንቋ ሙስና መረን ለቆ የተስፋፋበት ነዉ። ጊዜዉ ህዝብን አደንዝዞና አፍዝዞ መግዣ የሆኑ፣ ምንም ተጨባጭ አወንታዊ ትርጉም ወይም ዋጋ የሌላቸዉ የተደጋጋሚ ቃላት ጥርቅም (“ነፃነት”፣ “ዲሞክራሲ”፣ “እኩልነት”፣ “ህገ መንግስት”፣ “የራስን ዕድል በራስ መወሰን” ወ.ዘ.ተ) በመሠረቱ አስቀያሚ የሆነ ጐሰኛ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝን ተገቢና ህጋዊ አስመስሎ ማስጌጫ እርካሽ ጌጣ ጌጦች ሆነዉ የሚያገለግሉበት ዘመን ነዉ። ገዢዎቻችን አንዴ ብቻ እንኳን ቢሉት እዉን ዲሞክራሲያዊ ትርጉም ወይም ፌደራላዊ ይዘት የሌለዉን ስታልናዊ “የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ነፃነትና እኩልነት” ዲስኩር ከሃያ አመት በላይ ሌት ተቀን እየደጋገሙ ሲያሰሙን የዘመኑን የፖለቲካ ቋንቋ ሙስና እያስፋፉ ነዉ። ይህ አይምሮ አደንዛዥ ዲስኩር ከጅምሩ (በተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን) የረባ ፍቺ ነበረዉም አልነበረዉም ዛሬ ከመጠን በላይ ከመደጋገሙ ብዛት ለዛዉን ጨርሶ ያጣ፣ ትርጉሙ ተሟጦበት ብቅት ያለዉ፣ የቸከ አፈትረካ አባባል እንጂ ከአገዛዝ መሣሪያነቱ ባሻገር ምንም ያህል ሃሳባዊና መርሃዊም ሆነ ተግባራዊ ፋይዳ ያለዉ አይደለም።
ባጭሩ፣ ያለንበት ጊዜ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ሃቀኝነት በራቃቸዉ አስመሳይ ርዕዩተ አለማዊ፣ ባህላዊና ተቋማዊ ማንሜናዎች፣ በተልካሻ የላይ ላይ እምነቶችና የታይታ ድርጊቶች፣ ገዢዉ ወግን እንዳሻዉ ለራሱ ጥቅም መጠበቂያ በፈጠራቸዉ አገር ከፋፋይ የጐሳ ማንነቶችና ክልሎች፣ እንዲሁም ረክሰዉ የጋራ ብሔራዊ ባህላችንን ያረከሱ ሌሎች የፖለቲካ ፍጆታ ሸቀጦች የተጥለቀለቀበት ዘመን ነዉ። በአገር ተሐድሶ ትግሉ የሃሳብና ባህል ማጥራት ዘመችዉ ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል።

የፖለቲካ ሃሳብ በቋንቋ ሙስና ሳይጣመምና ሳይረክስ፣ የቃል በቃል አቀራረቡ በተግባራዊ ትርጉሙ ሳይሰረዝ፣ ያለዉን ወይም ሊኖረዉ የሚችለዉን በጐ ፍቺ እንኳን በዛሬዉ አገር አዳኝ ትግል ዉስጥ በቅጡ መጨበጥና ተፈጻሚ ማድረግ ቀላል አይደለም። አብዛኛዉን ጊዜ ሃሳባዊ ይዘቱም ሆነ ተግባራዊ የሚሆንባቸዉ እዉን ሁኔታዎች ተገቢ ትንተና፣ ግንዛቤና አስተዳደር ያስፈልጋቸዋል። ትርጉማቸዉ በአግባብ ሳይስተዋልና ሳይጨበጥ በቃል መደጋገም የተለመዱ፣ በአመዛኙ ህይወት የሌሽ ቀኖና ወይም ያነጋገር ዘይቤ ብቻ ሆነዉ የቀሩ የፖለቲካ ሃሳቦች (በተለይ “ዲሞክራሲ”) የተሻለ፣ ከብሔራዊ ህልዉናችን ጋር የሚግባባ፣ ህያዉ አተረጓጐምና አፈጻጸም ይፈልጋሉ። ባጭሩ የአገሪቱን ብሔራዊ ጉዳዮች በዉስጠ ሁኔታቸዉና በአካባቢያቸዉም ሆነ በአገራዊ ትስስራቸዉ በአማራጭ መንገድ ለመጨበጥና ለማስተዳደር ምን አይነት ጠቅላላ የአስተሳሰብ፣ የስልትና የእንቅስቃሴ ሂድት ተፈላጊና ተመራጭ ነዉ የሚል መሠረታዊ ጥያቄ በዛሬዉ የለዉጥ ትግል ዉስጥ መነሳትና መመለስ ያለበት ይመስለኛል። ይህ ሁሉ ሥራ ደግሞ በተለያዩ መስኮችና ደረጃዎች የተቀናበሩ ምሁራዊ፣ ፖለቲካዊና ድርጅታዊ አቅሞች ይጠይቃል።
አገርን ከአደገኛ ዉጥረት ለማዉጣት እንደ አገር መነሳትና መታገል ስንል የፖለቲካ ሃሳብ ወይም እንቅስቃሴ ራሱ በጠቅላላ የጋራ ብሔራዊ ህይወታችን ዉስጥ የሚኖረዉን ተገቢ ቦታ እግምት በማስገባት ነዉ። ግምቱ የሚያስፈልገን ከተማሪዎች ተራማጅ ንቅናቄ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ የወያኔ አገዛዝ ዘመን ድረስ አብዮታዊ ልምዳችን በሚያሳዝን መልክ ከአሳየን የተዛባ አገር ጐጂ የፖለቲካ አኪያሄድ አሉታዊ ትምህርት ስለወሰድን፣ ማለትም ምን ማድረግ እንደሌለብን ስለተረዳን ነዉ። እንደምናዉቀዉ አኪያሄዱ የተወሰነ ርዕዩተ አለምን እንደ ጣኦት አምልኮ ከአገርና ከህዝብ በላይ የቀረጸና ያዋቀረ፣ ለዚሁ አምባገነናዊ የርዕዩተ አለም “አምላክ” ያለማመዛዘን፣
6
በጭፍኑ፣ የሰገደና የታዘዘ ነበር። ወያኔዎች የራሳቸዉን ጠባብ የዘረኛነት አምልኮ ያክሉበት እንጂ ከሞላ ጐደል በዚሁ “የተራማጅነት” አኪያሄድ ነዉ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ የበቁት።
እንግዲህ የዛሬዉ አገር አዳኝ ፖለቲካ ዋና ሥራ ከራሱ ዉስጣዊ እምነቶች፣ ግቦችና ክርክሮችና የመነጩ አንድ ወጥ የሆኑ ወይም የተለያዩ ሃሳቦችንና ፖሊሲዎችን በቅድሚያ መፍትሔዎች አድርጐ ማንደርደር ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ብሶትና ፍላጐት በጥሞና ተገንዝቦ፣ ብሔራዊ ልምዳችን ካለበት አስጊ ሁኔታ መዉጣት የሚያስችሉት የራሱ ሃይሎችና አቅሞች የሚታደሱበትንና የሚጠናከሩበትን መንገድ ማመቻቸት ነዉ። እዚህ ላይ አገር ፈዋሽ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በሰዎች ጤና ጥበቃ ሥራ ይመሰላል። ሕመም የያዘዉን ሰዉ ሰዉነቱ በዉስጡ ያለዉን ራስ አዳኝ አቅም ቀድሞና ችላ ብሎ በዘመን አመጣሽ የመድኃኒቶች፣ የስቃይ ማስታገሻዎችና የተክኖሎጂ መሣሪያዎች ብዛት በሽታዉን መቆጣጠር ለታማሚዉ ዘላቂ ፈዉስና ጤንነት የማያስገኝ መሆኑ በጤና ባለሙያዎችና አዋቂዎች ዘንድ እያደገ የመጣ ግንዛቤ ነዉ። በማመሳሰል የኢትዮጵያን “ሕመም” ከአገሪቱ ከራሷ የማንሰራራት፣ የማገገምና የመጠናከር አቅሞች አርቀዉ የሚቀርቡ ዘመናዊ የፖለቲካ “መፍትሔዎች”፣ ጐሰኛ ብሔርተኝነትንም ጨምሮ፣ ለዘለቄታዉ የጋራ ሕመማችንን የማይፈዉሱ ብቻ ሳይሆኑ ለማንኛዉም የአገሪቱ ማህበረሰብ አይበጁም። አገር በጠቅላላ ጤና አጥቶና ተጐድቶ፣ የአገር አካላት የሆኑ ማህበረሰቦች በርቀት ሂደት ጤናማ አይሆኑም፣ አይጠቀሙም። የማን አገር ፈርሶ የማን ክልል ሊለማ?
ይህን ዉይይት ለመደምደም፣ ዛሬ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ሁኔታ አስጊነት፣ የምትሄድበት የፖለቲካ አቅጣጫም አደገኛነት፣ በእርግጥ አሳሳቢ ነዉ። ይሁን እንጂ አገርን እንደ አገር ተነስቶ ለማዳን ከመታገል አኳያ ስጋታችን ራሱ (ሲጋነን) የማይበጅ ጐን አለዉ። በአገር ወዳድ ዜጐችና ተቃዋሚ ድርጅቶች ዘንድ አንዳንዴ የሚታይ ችግር አለ። ይኸዉም የመለያየት ስቃይ ፍራቻ ከመለያየት ሕመም ራሱ ማየሉና ይህም ፍራቻ ብሔራዊ ተነሳሽነታችንን፣ እንደ ኢትዮጵያዊያን በራሳችን መተማመንን የሚያዳክም መሆኑ ነዉ። አገራዊ ልምዳችንን እያደስን እያጠናከርንና እያሰፋን በሙሉ ልብ በመንቀሳቀስ የተለያዩ የአገር ወገኖችና ክፍሎችንና በቅንብር ከመሳብና ከማሰባሰብ ይልቅ ከኢትዮጵያ ጥቅምና ከኢተዮጵያዊነት ጋር ሲያንስ አጠያያቂ ግንኙነት፣ ሲበዛ ደግሞ ተጻራሪነት ካላቸዉ ስብስቦችና ሃይሎች ድጋፍ ወይም ትብብር መፈለግ በራሳችን ያለመተማመን መገለጫ ይመስላል። የተወሰነ ድርጅታዊና ታክቲካዊ የትግል ቀመር ቢኖረዉም የሩቅ ሂደት ብሔራዊ ራዕይና ስልታዊ አስተዉሎ ይጐለዋል።

ይህን ያመኔታ፣ የራዕይና የስልት ጉድለት በዛሬዉ የለዉጥ ትግል ለማሟላት በብሔራዊ ልምዳችን የሚኖረን እዉን ተሳትፎ ወሳኝ ነዉ። ልምዱ ወደ ፊት ተመልካች ፖለቲካ ሃሳባችን ተቀባይነት የማይነፍገዉና በተለያዩ ግን የተሳሰሩ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ረድፎች (ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ መንፈሳዊ፣ ምሁራዊ፣ ኪነጥበባዊ፣ ወ.ዘ.ተ) ተገቢ ቦታ ያለዉ ስለሆነ ተሳትፏችንም እንዲሁ ልዩ ልዩ ቅርጾች አስተባብሮ ሊይዝ ይችላል። በዚህ ሁለንተናዊ አገር መልሶ ገንቢ ትግል የፖለቲካ እንቅስቃሴያችንና ብሔራዊ ህይወታችን አይጋለሉም። አንጻራዊ ረድፋቸዉን ወይም ነፃነታቸዉን ጠብቀዉ እርስ በርስ ይመጋገባሉ፣ ተደጋግፈዉ ወደ ፊት ይሄዳሉ። በድግግፍ ሂደታቸዉም ኢትዮጵያ ትታደሳለች። እንደ አገር ከምሽት ወደ ንጋት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን እንሻገራለን።
Email: tdemmellash@comcast.net
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
February 6, 2014

እስረኛው ጠ/ሚ ኃ/ማ ደሳለኝ በምግብ ራሳችን ችለናል ማለቱ ከምኑ ላይ ነው ስህተቱ?!!

በጌታቸው ፏፏቴ
መግቢያ
ህወሃት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያዊ የሆነ አጀንዳ እንደሌለውና ሊኖረውም እንደማይችል ከተቋሙ መሠረታዊ ፕሮግራም በመነሳት ግንቦት 20/1983 በሚል ባቀርብኳት ጦማሬ አስረግጨ አሳውቄ ነበር። እነዚህን የምልበት ምክንያት ከባዶው ተነስቼ ሳይሆን ድርጅቱ ከፈጸማቸውና እየፈጸማቸው ካለው ፀረ-ሕዝብና አሰቃቂ ዘግናኝ ተግባሮቹ በመነሳት እንደሆነ እንዲታወቅልኝ እወዳለሁ።የዚህ ድርጅት መነሻውም ሆነ የመጨረሻ ግቡ ከተቻለ የህወሃት/ኢህአዴግ ትውልዶች ብቻ የሚኖሩባት ኢትዮጵያን መፍጠር አለዚያም ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚያምነውን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነገድ ተራ በተራ እያዘናጉ መጨረስና አገሪቱንም ለባእዳን እንዳወጣች ሸጦ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንዳልነበረች ማድረግ እንደሆነ ለማንም ስውር ሊሆንበት አይገባም።
ድርጅቱ ቀደም ሲል ጫካ ውስጥ በትግል በነበረበት ወቅትም ሆነ የመንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላ የፈፀማቸውና እየፈፀማቸው ያሉት አፀያፊ ድርጊቶች ታይተው ያማያውቁ የኢትዮጵያዊነት ሞራልና ስብእና የጎደላቸው ስለመሆናቸው ብዙ የተባለ ሲሆን አንድ ግልጽና ቀላል አስረጅ መጥቀስ የበለጠ እውነታውን ያሳያል ብየ አስባለሁ።

የፌደራል መንግሥት እየተባለ የሚጠራ የይስሙላ መንግሥት ቢኖርም የመንግሥትንም ሆነ የድርጅትን ሥራ ጠቅልሎ የሚያከናውነው ህወሃት/ኢህአዴግ ነው። በግንባሩ ውስጥ የተካተቱት ድርጅቶች የመወሰንና መመሪያ የማውጣት ሥልጣን ባይኖራቸውም በህወሃት በጎ ፈቃድ የሌሎችን ነፃ ተፎካካሪዎች እድል ለመዝጋት የግል ባንኮችን ኮታው እንዲሸፍኑ ተደርጎ በሥራቸው የሚያንቀሳቅሱት ባንክ አላቸው።እነዚህ ባንኮች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሥራ ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ ሆን ብሎ የታቀደ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረው ሊሰሩ ያሰቡትን ተግባር እንዳያከናውኑ የሚያደርግ ተንኮለኛ ሴራ ነው።ከነዚህ ከተጠቀሱት የህወሃት አዳማቂ ድርጅቶች ባንክ ብድር ተበድሮ ኢንቨስት ለማድረግ ቢታሰብ ደግሞ አይሞክሩትም እንጅ የግድ መሟላት ያለበት አንድ ነገር አለ። ይኸውም የህወሃት/ ኢህአዴግን የአባልነት ካርድ መያዝ ይኖርባቸዋል ማለት ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እንቅስቃሴን ለመግታትና የውጭ ምንዛሬ እንዳያገኝ ከማድረጉ አልፎ ባንኩ ራቁቱን እንዲቀር ያደረጉ ሌሎች የተቀነባበሩ ተንኮለኛ ተግባሮችም ተፈጽመዋል እነሱም ከባለ ሥልጣናቱ ቀጭን ትእዛዝ እየተሰጠ የግንባሩ አባላትና ደጋፊዎች በኢንቨስትመንት ስም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ እንዲበደሩ ይደረጋል። ገንዘቡን ወስደው ከተጠቀሙ በኋላ ለባንኩ መክፈል የሚገባቸውን የተጠቀሙበትን የአገልግሎት ዋጋ(interst) መክፈል ይገባቸዋል ነገር ግን ይህ ሊሆን ይቅርና ዋናውን ብድርም አሻፈረን አንከፍልም ብለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኪሳራ እንዲደርስበት አድርገዋል።ይህችን ትንሽ ምሳሌ ያቀረብኩት የሌሎቻችሁንም ስሜት ለመቀስቀስ እንጅ ወንጀሉማ ስፍር ቁጥር የለውም እያልኩ ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ልግባ።

አዎ! አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም በግንቦት 20 ንግግሩ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን መቻሏን ተናግሯል።ንግግሩን ሰምቸዋለሁ።ነገር ግን ስለማን እንደተናገረ ለማወቅ ለኔ ጊዜ አልወሰደብኝም።የኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና ወይም የልማታዊ መንግሥቱ መርህ ህወሃት/ኢህአዴግን፤ የግንባሩ አባላትንና ደጋፊዎችን ብቻ የሚመለከት እንጅ ሌላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመለከት ጉዳይ አይደለም።ወደፊትም እንዲኖር የሚታሰበው ትውልድም በዚህ ዘረኛ ድርጅት ፕሮግራም ተኮትኩቶ የሚወጣን ትውልድ እንጅ ሌላ ኢትዮጵያዊ ትውልድ እንዲሆን በፍጹም አይታሰብም ይህን ነው ማወቅ ያለብን።

ቀደም ሲል በአንድ ጹሑፌ ላይ ደርግ ከወደቀ በኋላ በሠራዊት ግንባታና አደረጃጀት ጉዳይ ላይ የተፈጸመ አሳዛኝ ድርጊት ጠቅሸ ነበር። ይኸውም ህወሃት አሰልፎት የነበረው ሠራዊት ከፍተኛ ቁጥር የነበረው መሆኑና የአዲሱ የሠራዊት አደረጃጀት ደግሞ ክልሎች ባላቸው የሕዝብ ብዛት ነው ስለሚል የህወሃትን ሠራዊት ላለመበተን ሲባል የተወሰደው እርምጃ አማርኛ የሚችለው የህወሃት ሠራዊት የመከረኛውን አማራ ሕዝብ ኮታ እንዲሸፍን ማድረግ ነበር ። የቀረውን በትግራይ ሕዝብ ባዛት መጠን ማሰለፍና ኢትዮጵያዊነት መንፈስ የተላበሱትን ደግሞ መዳረሻቸውን በማጥፋት ህወሃት ዓላማውን ስኬታማ ለማድረግ ችሏል።አሁን ደግሞ የህወሃት አባላት የኦሮምኛ ቋንቋ እንዲማሩና የኦሮሞውን ክልል በቁጥጥር ሥር ለማዋል የተወሰደውን አቋምና በየዐረብ አገሩ በዐረብኛ ቋንቋ የሰለጠኑ ወጣቶች ለማፍራትና በየኮሚኒቲውና ኤምባሲው ለመሰግሰግና የስለላ ተግባራትን ለማካሄድ ሲባል የሀገሪቱ ሀብት(ገንዘብ)ለዚህ ወጭ መሸፈኛ እየተመዘበረ ያለበት መሠረታዊ ምክንያት (አንድምታው )ህወሃት ወለድ የሆነ አዲስ ትውልድን የመገንባትና የመትከል አባዜ ነው።

ህወሃት ጫካ ውስጥ በነበረበት ወቅት ወደ ፊት ድርጅቱ ወደየት እንደሚሄድ የሚያሳይ ማኒፌስቶ በ1976 ዓ/ም ማውጣቱ ይታወቃል።ከ1983ዓ/ም ከደርግ መውደቅ በኋላ ግን ህወሃትን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ድርጅት በመቁጠር ሕዝቡ የተዘናጋበት ጉዳይ ቢኖር የህወሃትን የመጨረሻ ግብ መርሳቱ ነው።ህወሃት ለ23 ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ ያደረገው ቆይታ ኢትዮጵያዊ በመሆን ሳይሆን እንደ ጣሊያንና ድርቡሽ(የመሐዲስት) ወራሪ ኃይል በኢትዮጵያ ውስጥ መጥፋት ያለበትን ለማጥፋት ሊዘረፍ የሚችለውን የሀገሪቱ ሀብት ለመዝረፍና ኢትዮጵያን በታትኖ በማጥፋት ለትውልደ ህወሃት የሚሆነውን አዲሱን የህወሃት ሥርዎ መንግሥት ለማመቻቸት ነው።

ከአፋር ጀምሮ የኤርትራን አጎራባች ድንበሮች እያጠቃለለ ከሰሜን ወሎ የማይጨው አውራጃን እንዳለ በመውሰድ ሰሜን ጎንደር ጠልምት ወልቃይት ጠገዴን፤አርማጭሆን እያጠቃለለ መተማን ሙሉ በሙሉ ካርታው ውስጥ ያስገባና ሽንፋና ቋራን ዘልቆ እስከ ጋምቤላና ቤንሻንጉል እየመረሸ ወለጋንም ሸረፍ በማድረግ በመውሰድ ”ታላቋን ትግራይ ሪፐብሊክ” መገንባት ነው።ይህ ተግባር ባሳለፍናቸው የህወሃት 23ዓመታት ሲተገበር ቆይቷል። አሁንም ዋናው ግብ እሱ በመሆኑ ሰላዮችን ካድሬውንና የህወሃትን የመከላከያ ሠራዊት እንዲሁም በውጭ ያደራጁትን የህወሃት አባል “ከሱዳን ተመላሽ ወገን”በማለት እያሰፈሩ ይገኛሉ። እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል ይህን መሬት ለሱዳን ሰጥተውት የለም ወይ?የሚል ሊሆን ይችላል።አስቀድሞ ማለቅ ያለበት ተግባር ስለ አለ እንጅ በህወሃት ሰፍሳፋ ተፈጥሮ ይህን የመሰለ ለምና ውሃ ገብ መሬት ለሱዳን? እንዴት ብሎ? ወደ ፊት በሰፊው እናየዋለን።
አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም፦ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደማይወክልና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የቆመ አለመሆኑ ግልጽ ቢሆንም ቢያንስ ሲወራ ሊሰማ ይችላል ብየ እገምታለሁ እዛው ከመዲናችን አዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ በየሆቴሉ የቆሻሻ መጣያ የተጣለ ትራፊ ምግብ ለማግኘት የሚደክሙትን፤በየትምህርት ቤቱ በርሃብ ጠኔ የሚወድቁትንና መማር አልችል ያሉ ወጣቶች በሞሉባት አዲስ አበባ ፤ከሀገሪቱ ሕዝብ 2/3ኛው ቁጥሩ ከ85ሚሊዮን የማያንስ የኢትዮጵያ ሕዝብ በርሃብ አደጋ ላይ ያለ መሆኑን ዓለም አውቆትና የውጭ እርዳታ እየተጠበቀ ባለበት ወቅት «በምግብ ራሳችን ችለናል» ብሎ መናገር ምንያል ቅጥፈት የተሞላበት ንግግር እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው? አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም መለስ ዜናዊ የስኳርን ውድነት ችግር ሲያስረዳ ስኳር ቀምሶ የማያውቀው አርሶ አደር ስኳር በመቅመሱ እንደሆነ በህዝብ ላይ ያለውን ንቀት እያላገጠ ተናግሯል።አንተም የጤፍን ዋጋ ያስወደደው አርሶ አደሩ ጤፍን በመመገብ ያስከተለው የዋጋ ውድነት እንደሆነ ልታስረዳን ሞከርክ የሁለታችሁም መጥፎ አገላለጽ አንድ ጤና ካለው ሰው የሚጠበቅ ባይሆንም የሁለታችሁ ንግግርም ሆነ በጠቅላላ የካቢኔው ስብስብ ጤና የጎደለው በመሆኑ የሚገርም አይደለም።ታዲያ በምን ሂሳብ ነው ህወሃት/ኢህአዴግ የአርሶ አደር መንግሥት ነው የሚባለው?ረግጦና አስርቦ ለመግዛትም እኮ የሚገዛና የሚረገጥ ሕዝብ መኖር አለበት።

የእናንተው ከርስ እንዳይጎድል ደግሞ ማምረት አለበት።ይህ ይገባችኋል ወይ?ወይስ ሁሌ በደፈረሰ አእምሯችሁ ለመቀጠል ነው ያሰባችሁት?አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም፦ ህወሃት/ ኢህአዴግና የፌደራል መንግሥትን ምንነት ገና የገባው አለመሆኑን የሚያመላክቱ ብዙ ነገሮችን ሲናገር ተስተውሏል።ከኤርትራ ጋር ስለሰላም ለመመካከር ዝግጁ መሆኑንና በሌላ ወገን ደግሞ ኤርትራን የአሸባሪዎች ደጋፊ ናት የሚል ክስ መስል ነገር ሲናግርም ተደምጧል ሁለቱ የሚቃረኑ ሃሳቦች መሆናቸውን መመርመር አልቻለም።መራሾቹ ነብሰ ገዳዮች ስብሃት ነጋ ፤ ስዩም መስፍን ፤ አባይ ፀሐየ ፤ አዲሱ ለገሰ ፤ ብረከት ስምኦን ፤ አርከበ እቁባይ ፤ሕላዊ ዮሴፍ፤ታደሰ ካሣ፤ ደብረጽዮንና ቴዎድሮስ አድሃኖም አንብብ ብለው የሚሰጡትን ጹሑፍ ከማንበቡ በፊት ቢያነበው ቢያንስ ለያዘው ሥልጣን የሚመጥን ሀሳብ ባገኘ ነበር ።ነገር ግን ከዚህ በላይ የጠቀስኳቸው የጠቅላይ ሚንስትሩ የካቢኔ አባላትና የጡረታ አማካሪዎቹ እሱን እያጋፈጡ የውስጥ ፍላጎታቸውንና የተነሱበትን ዓላማ እያስፈጸሙ ይገኛሉ።

አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም የህወሃት ጠቅላይ ሚንስትር ሁሌ ስለአንተ የሚጻፉ ጹሑፎችን አንብባቸው አንድ ቀን ልብ ትገዛና ወደ ሰውነትህ ትመለስ ይሆናል።አንድ መረሳት የሌለበት ጉዳይ ቢኖር ደርግ ከፈፀማቸው ፋሽስያታዊ ድርጊቶቹ ዋነኛው ክቡር ፀሐፊ አክሊሉ ሀብተወልድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር የመሳሰሉትን መግደሉ ሲሆን በክቡር አቶ አክሊሉ ሀብተወልድ የተፈጸሙ ተግባራትን የተለያዩ ሰዎች የፃፉ ሲሆን በራሳቸው የተጻፉ” የአክሊሉ ማስታዎሻዎች” ብዙ ጠቃሚ ሀገራዊ ጉዳዮችን ያካተተ ጹሑፍ ስለሆነ ያን ማንበብና ኦ! ለካስ እኔም መለስም እሳቸው ከነበሩበት መቀመጫ ነው ያለነው የነበርነው እንድትል ይጠቅማሃል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ስህተቱ ከምኑ ላይ ነው በሚል ርእስ የገባሁት ስህተት አልተናገረም ለማለት ሳይሆን ጹሑፌ ትኩረት እንድትስብ በማሰብ ነው እንጅ ስህተቱንማ ከቁመቱ በላይ በሚደርስ አዘቅት ተዘፍቆበታል። አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም ወደታች ወርዶ በቀበሌ የሚኖረውን የከተማውንም ሆነ የገጠሩን ነዋሪ ኢትዮጵያዊ የሚያይበት እድል ቢኖረው ምን ሊለን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ዳሩ ግን እሱ ራሱ በግዞት ላይ ያለ እስረኛ ስለሆነ ያሳዝነኛል።

የህወሃት እንባ ጠባቂዎች በትክክል በልተው ያድራሉ ። ምክንያቱም ሕሊናቸውን ለሆዳቸው ሲሉ ሸጠውታልና።አባላቱ ሁሉ በእጃቸው ሁሉ በደጃቸው ስለሆነ ምን አጥተው? እንኳን ሦስት ጊዜ አስር ጊዜስ ቢበሉስ ምን ጎድሎባቸው? እላይ ያለው ቱባ-ቱባ ባለሥልጣን በልቶ ማደር ብቻ ሳይሆን ከሚፈለገው በላይ የጠገቡና የጥጋብ ቁምጣናቸውን በአረቄ ለማወራረድ ሲደፈርሱ የሚያድሩ፤ ሰማይ ውረድ የሚሉ ጥጋበኞች፤ ሰማይ ጠቀስ የሆኑ ፎቆች ያላቸው፤ሀብት ተብሎ የሚቆጠረው ሁሉ የነሱ ያደረጉ፤ መሬትን የነሱ ያደረጉ፤ የበርካታ ሆቴሎች ባለቤት፤ልጆቻቸው ከፍተኛ ወጭ እየተከፈለላቸው ውጭ አገር ተልከው የሚማሩ፤ የፓርቲ ልብስ የሚገዙት ውጭ አገር ነው፤ ጉንፋን በያዛቸው ቁጥር የሚታከሙትም ውጭ አገር በሚገኙ ሆስፒታሎች ነው።ይህ ሁሉ የሚደረገው ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት እየተዘረፈ ነው።

የአቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም የግንቦት 20 ቆርፋዳ ንግግር ቢያንስ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ያለበትን ደረጃና ሁኔታ አለማወቅ ራሱን ችሎ ኢትዮጵያ በምን ዓይነት ድናቁርቶች እየተመራች መሆኗን ከማሳየቱም በላይ አምራችና መሬት እንዳይገናኙ የተደረገበትን መሠረታዊ ምክንያት አለማወቁ የግለሰቡን ጥሬነት ያሳያል።ለባዕዳን የተሸጠው መሬት እንዳለ ሆኖ የቀረው መሬት ላይ ኢትዮጵያዊ ኢንቨስተሮችና አርሶ አደሩ ለማምረት እድሉ ቢፈጠርላቸው ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ሌሎችን የጎረቤት አገሮች ሊመግብ የሚችል ምርት ማምረት ትችል ነበር።
አብዛኛው ከደቡብ እስከ ምዕራብ ያለውን የሀገሪቱን ክፍል ወስደን ብንመለከት ለም ድንግልና የተለያዩ አዝእርቶችን ሊያመርት የሚችል መሬት እንዳለ ይታወቃል።ከደርግ መውደቅ በኋላ ከ1985 እስከ 1987ዓ/ም በነበረው ወቅት የነበረውን የሕዝቡ ተነሳሽነትና በምእራብ ጐንደርና ምእራብ ጐጃም ብቻ የነበረው የምርት ውጤት ሲታይ ተስፋ ሰጭ ነበር። ሁመራና መተማ ተከማችቶ የነበረውን ማሽላ፤ ሰሊጥና ጥጥ ለማጓጓዝ የነበርውን የተሽከርካሪና የመደብር እጥረት አስታውሳለሁ።ያን ተነሳሽነት ግን ገዥዎቻችን ቀልጥፈው አጠፉት። የመሬት መጠቀሚያና የእርሻ ግብር ክፍያውን እላይ ሰቀሉት ኢንቨስተሩም የሥራ ፈቃዱን መመለስ ጀመረ። ህወሃትን እሰየው አሰኘ ታይቶ የነበረው ተስፋ ጨለመ።

አድንቁረህና አስርበህ ግዛው መሆኑንንም አሳዩን።ያን ተስፋ የተጣለበትን የደቡብ ምእራብና ሰሜን ምእራብ መሬትም ለሱዳን አስረክበው ዛሬ የሱዳን ገበሬዎች በህወሃት የመከላከያ ሠራዊት እየታጀቡ አባቶቻችን ደም አፍስሠው አጥንታቸውን ከስክሰው ውድ ሕይወታቸውን ገብረው ያቆዩትን መሬት እያረሱት ይገኛል።አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም ለማወቅ የተሳነው እንዲህ አይነቱን ሀቅ ነው።በዚህ የኢትዮ-ሱዳን ድንበር በቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ዘመነ መንግሥት በነበረው ፓርላማ ውስጥ እንስጥ አንስጥ በሚል ሃሳብ ተነስቶ አብዛኛው የፓርላማ አባል ለዚህ ቆላማ መሬት ብለን ወዳጅነትን ከሱዳን ከምናጣ ይውሰዱት ሲል ጥቂት የፓርላማ አባላት በድርጊቱ ተቆጥተው ፓርላማው ውስጥ በወንበር መደባደብ እንደተጀመረና ወዲያውኑ ለሱዳን ይሰጥ የሚለው ውሳኔ ተሽሮ ድንበሩ እስከ አሁን የኛው ዘመን ድረስ በጦር ኃይል ሳይሆን በህዝብ የጎበዝ አለቆችና በራሱ ትጥቅ ተከብሮ የኖረ መሬታችን ነው ዛሬ ለሱዳን የተሰጠው።

አሁን ያለው ፓርላማ ፓርላማ ነው ለማለት እንደማይቻል ይታወቃል።የካድሬ ስብስብና እጅህን አውጣ ሲባል ብቻ እጁን እያወጣ ድምጽ የሚያስቆጥር እንጅ በኢትዮጵያዊነት ስሜትና ወኔ ለሀገር የሚጠቅም ሃሳብ ያመነጫል ተብሎም ተስፋ የሚጣልበት ፓርላማ አይደለም። ለግልጥቅሙና ለሆዱ የተሰለፈውን ህወሃት ከየትም ለቃቅሞ የሰበሰበው ጥርቅም ነው። አንድ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ ግን»- እንደ ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ላይ የጥፋት መርዙን የተከለ አልነበረም እሱ ወደ መጨረሻው ከተጓዘ በኋላም ዛሬ እየገዙን ያሉት እኩያን “ በመለስ ራእይ” ስለሆነ እነዚህን ስንኩሎች ነቅለን ካልጣልን እፎይ የምንልበት፤በኢትዮጵያ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚተከልበት፤የሕግ የበላይነት የሚሰፍንበት፤ኢትዮጵያውያን ተፋቅረውና ተከባብረው በጋራ በእኩልነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያን ማሰብ አይቻልም።

መፍትሔ አልባ የሚፈጠር ችግር የለም። እኛን ለገጠመን ድቅድቅ የጨለማ ዘመን ደግሞ መፍትሔ አለው ብየ አስባለሁ።”የፀደይ አብዮት”በመባል የሚታወቀው የሕዝብ አመጽ የቱኒዚያን፤የግብጽን፤የየመንን፤የሊቢያን፤የሶርያን አሁን ደግሞ የኢራንን መሬቶች እንዳንቀጠቀጠና እያንቀጠቀጠ እንደሚገኝ ይታወቃል።አዎ! ብዙ መስእዋትነት ተከፍሎበታል ቢከፈልበትም ትርጉም ያለው ውጤት ደግሞ አስገኝቷል።በእኛም አገር ትግሉ አፈና የበዛበት ቢሆንም አላቋረጠም።ዳሩ ግን የተከፈለው መስእዋትነትና የተገኘው ውጤት ሲመዘን ብዙ ጎደሎዎችን አሳይቷል።አንደኛ ትግሉ ከየግል ፍላጎት የሚነሳና የተናጠል መሆኑ ፤ሁለተኛ ሁሉንም የሕ/ሰብ ክፍል በአንድ ጊዜ ያነቃነቀ አለመሆኑ፤ሦስተኛ በሳምንት አንድ ጊዜ ወይም አንድ ቀን ብቻ የሚደረግ ትእይንተ ሕዝብ እንጅ ቀጣይነት የሌለው መሆኑ፤አራተኛ በሕዝብ የሚደረጉት ትእይንተ ሕዝቦች ታክቲክ ለገዥው ቡድን የተጋለጡ መሆናቸው ነው።
የማይሳሳት ቢኖር የማይሰራ ወይም የማይንቀሳቀስ ብቻ ነው።እኛ ኢትዮጵያውያን ህወሃትን ለማስወገድ በተመቸው መንገድ ሁሉ አንድ እርምጃ ወደፊት ተጉዘናል።ስንጓዝ ደግሞ ስህተቶች ተፈጽመዋል ስለሰራን ተሳስተናል ትልቁ ጉዳይ ግን ከስህተት መማርና ከዚያ አደጋ የመውጣቱ ቅልጥፍና ጉዳይ ነው ወሳኙ።አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ከችግር ጋር ያጋፈጠንን ህወሃትን ጡንቻው እንዲያብጥና ጠንካራ ጠላታችን እንዲሆን አብቅተነዋል። ምክንያቱም የጠላትን ጠንካራና ደካማ ጎን መገምገም አልቻልንም። የህወሃት ጠንካራ ጎን እርስ በርሳችን እንድንባላ ማድረጉ ሲሆን ይህን አሜን ብለን ተቀብለነዋል።እስከ መቼ? ደካማ ጎኑ ህወሃት የማይወደው “ሕብረት ወይም አንድነት ስንፈጠር ነው”ካልተሳሳትኩ ቁልፉ እዚህ ላይ ነው ያለው።ወደዚህ እንዳንመጣ ያደረገው ደግሞ ከሥልጣን ጥማት ጋር የተያያዘና እኔ ከሁሉም የላቅሁ ነኝ የሚል ኋላ ቀር አስተሳሰብ ነው። በዚህ ላይ የሕዝብን ሉዓላዊነት የሚፈልገውን የመሾም የማይፈልገውን የመሻር ሥልጣኑን የማይቀበል አመለካከት ተሸክመን በመጓዛችን ምክንያት ነው።
ስለዚህ በኢትዮጵያ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ተቻችሎ አንድነትን መገንባት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጎች በመተሳሰብ በፍቅር በጋራና በእኩልነት ለመኖር የሚያስችል ራእይ ይዞ መታገል አግባብ ነው ብየ አስባለሁ።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላዓለም ትኑር!!!
እያንዳንዳችን ራሳችን ነፃ ለማውጣት እንታገል!!

ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
June 27, 2014

ዐባይን ያላቅም

በዶ/ር ከፍያለው አባተ
1. መግቢያ
የዐባይ ነገር በተነሳ ቁጥር የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቃትና ሀዘን የሚሰማው ይመስለኛል። ያገራችን ነገር (በብዙ መልኩ) “እያዩ ማዘን” ነው። ሕዝብ በፍትህ እጦት እንዳሻሮ ሲታመስ እያዩ ማዘን፣ ወገን በርሀብና በበሽታ ሲማቅቅ እያዩ ማዘን፣ ያገር ልጅ በድርቅና በጦርነት የተነሳ እንደ ቅጠል ሲረግፍ እያዩ ማዘን፣ ሰው ሀገሩን ጥሎ ሲሰደድ እያዩ ማዘን፣ ዐባይ ያለ አንዳች ጥቅም አገር አቋርጦ ሲሄድ እያየን ማዘን። አቅም የሌለው ሰው እያየ ከማዘን ሌላ ምን ሊያደርግ ይችላል? የኢኮኖሚ አቅም የለን፣ ወታደራዊ አቅም የለን፣ የተማረና የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅም የለን፣ እንዲያው ሁሉንም በአርምሞ እያየን ማዘን ነው ልምዳችን። የሚገርመው፣ አቅመቢስነታችን የምናባብሰው እኛው እራሳችን ነን።
ከታሪካችን መማር አንችል፣ ተጣልተን መታረቅ አንችል፣ ተከራክረን መተማመን አንችል፣ ሙያችን እንዲሁ መነታረክ ብቻ ሆነ። ለስልጣን ስንል እርስ በርሳችን ስንራኮት፣ ስንዋጋና ስንጨፋጨፍ አቅማችን ልንገነባ ቀርቶ ይበልጥ ስናዳክመው ኖርን። ያቅመቢሶች ባላቅም፣ የጡንቻቢሶች ባለጡንቻ፣ የስልጣን-የለሾች ባለስልጣን፣ የደካሞች አውራ፣ የዐይነ ስውሮች አንድ-አይና መሪ ለመሆን ስንል፣ ሀገራችን አቅም-የለሽ፣ ኋላ-ቀር፣ የተናቀችና ለጥቃት የተጋለጠች ሀገር አደረግናት። የዐባይ ወንዝ አጠቃቀም ጉዳይም አቅመ ደካማነታችንና ለጥቃት የተጋለጥን መሆናችን የሚያንጸባርቅ አንድ ጉልህ ማስረጃ ነው።
የዐባይን ወንዝ በተመለከተ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስር የሰደደ የረዥም ጊዜ ሀዘን፣ እሮሮና ቁጭት አለበት። ዐባይ ግብጽን የመሰለች፣ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት የከፈተች፣ አጼ ዮሐንስን ከጦር ጀኔራላቸው ከራስ አሉላ ዕቁቢ (አባ ነጋ) እና ከሰራዊታቸው ጋር እረፍት አሳጥታ ስታንከለክል የኖረች፣ ብዙ ንብረትና የሰው ሕይወት መስዋእትነትን ያስከፈለች ባላጋራ የፈጠረብን ወንዝ ነው። የዐባይን ወንዝ የመጠቀም አቅም እንዳይኖረን (ለኢትዮጵያ ጠላቶች ከለላ በመሆን፣ የውስጥ ብጥብጥንና መከፋፈልን በመፍጠር፣ ብጥብጡ እንዳይበርድ በማራገብ፣ ለውጭ ጠላቶቻችን ድጋፍ በመስጠት፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ስውር ደባ በመፈጸም ወ.ዘ.ተ) ድክመትና ውድቀታችን ስትመኝ የምትኖር፣ አብሮ መጠቀምና መተባበር እማይታያትን፣ ግብጽን የመሰለ አውራ ባላጋራ ያፈራብን ወንዝ ነው። ዐባይን ባስጠቂነቱ እንጂ በጠቃሚነቱ አናውቀውም።
አጼ ዮሐንስን ሲያሳስቱና ሲያታልሉ1 የኖሩት እንግሊዞች በ1882 ዓ.ም2 ግብጽን ሲቆጣጠሩና፣ በ1898 ዓ.ም ደግሞ ሱዳንን እንደገና ሲይዙ ያነጣጠሩት ዐባይ ውሀ ላይ ነበር።
የእንግሊዞች ዓይነተኛ ዓላማ በግብጽና በሱዳን የተንጣለለ የዐባይ ሸለቆ ላይ (ለእንግሊዞች የጥጥ ፋብሪካዎች ፍጆታ የሚሆን) ካመት እስካመት ጥጥ የሚመረትበት ሰፊ የመስኖ እርሻ ማልማት ነበር። ይህ ጥጥ የበጋና የክረምት ወራት ሳይጠብቅ ያለማቋረጥ እንዲለቀም፣ የዐባይ ውሀ መጠን ከፍና ዝቅ እንዳይል፣ እስከመነሻው (እስከጣና ሀይቅ ድረስ) በቁጥጥራቸው ስር አድርገው የወንዙን ውሀ መጠንና አወራረድ መቆጣጠር (regulate) ነበረባቸው። በዚህም የተነሳ እንግሊዞች በኢትዮጵያዊያን ላይ ከትውልድ እስከ ትውልድ ሊፋቁ የማይችሉ (በኋላ በተደጋጋሚ የፈጸሙብን በደል ሳይቆጠር) ሦስት ግዙፍ በደሎችን ፈጸሙ።
በደል1. በ1902 ዓ.ም ከአጼ ምኒልክ ጋር የድምበር ውል ሲዋዋሉ፣ ላቀዱት የጥጥ እርሻ ሲሉ ሰፊ ደልዳላ መሬት ወደቅኝ ግዛታቸው (ወደሱዳን) ክልል ውስጥ እንዲገባ አደረጉ። ወደ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የገባው (ከቀጭን/ከጠባብ ደልዳላ መሬት በስተቀር) ተራራማውና ለመስኖ ስራ አመቺ ያልሆነው ወጣ ገባው መሬት ነበር።
በደል 2. በዚያው ዓመተ ምህረት (በ1902 ዓ.ም) ግንቦት ወር ውስጥ በሱዳንና በግብጽ ውስጥ ለማምረት ላሰቡት የጥጥ ምርት በቂ ውሀ ለማግኘት ሲሉ፣ የእንግሊዝ መንግሥትና የሱዳን መንግሥት ካልፈቀዱ
1 ሀ) በጦር መሳሪያና በወታደራዊ ስልጠና አታ(ል)ለው፣ ለኢትዮጵያ ክብር ሲሉ አንገታቸውን የተቀሉት አጼ ዮሐንስ፣ በእንግሊዞችና በኢትዮጵያ (በአጼ ቴዎድሮስ) መካከል በተፈጠረው ወሳኝ ጦርነት ላይ የሚያስወቅስ አቋም እንዲይዙ አድርገዋቸዋል። ለ) ግብጾችን ከምጽዋ እናስወጣልሀለን እያሉ አጼ ዮሐንስን እንደ ሕፃን ልጅ ሲያታልሉ ቆይተው፣ ከጣሊያኖች ጋር ተመካክረው፣ ግብጾች ከምጽዋ እንደወጡ ምጽዋን ጣሊያኖች እንዲይዟት አድርገዋል። ሐ) በሔዊት ውል (Hewitt treaty) ሱዳን ውስጥ በመሐዲስቶች የተከበበውን የእንግሊዝ ሠራዊት ብታስለቅቅልን፣ ግብጽን አስወጥተን ቦጐስ(ከረን?) በኢትዮጵያ ግዛት ስር እንዲሆን እናደርጋለን፣ በምጽዋ በኩልም የምታስገባውን የጦር መሣሪያ በነፃ/ያለቁጥጥር ታስገባለህ ብለው ከተዋዋሉ በኋላ፣ ውላቸውን አፍርሰው ቦጐስ ለግብጾች እንዲሆን ሲያሳስቧቸው፣ አጼ ዮሐንስ በመገረም የተሰማቸውን ቅሬታ በደብዳቤ ገልጸውላቸዋል። ምጽዋንም አፄ ዮሐንስ በነፃ ሊጠቀሙባት ቀርቶ ከነአካቴው ጣሊያን ወደ ኤርትራ ደጋ እየዘለቀ ለአፄ ዮሐንስና ለጦር ጀኔራላቸው ለራስ አሉላ አባ ነጋ ራስ-ምታት ሲፈጥርባቸው ቆይቷል።
2 ይህ ዓመተ ምህረትና በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የሚገኙ ዓመተ ምህረቶች ሁሉ የአውሮፓዊያን አቆጣጠር ናቸው።
በስተቀር በጥቁር ዐባይ፣ በጣናና በሶባት ወንዝ ላይ የወንዞቹን ውሀ ‘የሚያስቀር’ (arrest the flow of their waters) ምንም ዓይነት ስራ እንዳይሰራ ከአፄ ምኒልክ ጋር ተዋዋሉ3።
በደል 3. እንግሊዝ በ1929 ዓ.ም ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበት የዐባይን ውሀ ለግብጽና ለሱዳን የሚያከፋፍል የውል ስምምነት4 አዘጋጅታ ሁለቱን ሀገሮች (ግብጽንና ሱዳንን) አፈራረመች።
ታዲያ ይህ ሁሉ ደባና ጥቃት እየተሰማው ይመስለኛል፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ በዐባይ እንዳዘነ ይኖራል። የዐባይ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር በንዴት ከንፈሩን የሚመጠው ዜጋ ብዙ ነው። በዐባይ ላይ እማይሸለል ሽለላ፣ እማይቅራራ ቀረርቶ፣ እማይዘፈን ዘፈን፣ እማይገጠም ግጥም የለም። የዚሁ ሕዝብ ውስጣዊ ስሜት ተካፋይ የነበሩት እንደነሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ያሉ ታዋቂ ገጣሚዎች ሳይቀሩ “ዐባይ አቫይ” እያሉ ዐባይን ይወቅሱታል።
ተገንዝበነው እንደሆነ ወይም አልተገነዘብነው እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም እንጂ፣ በዐባይ ላይ የሚሰነዘረው ሀዘንና ወቀሳ ሁሉ በመንግሥቶቻችን (በፓለቲካ ባለሥልጣኖቻችን) ላይ ያነጣጠረ ይመስለኛል። ዐባይማ ግዑዝ ነውና ቆም ብሎ ሀዘንና እሮሮ አይሰማ! አቤቱታ አይቀበል! በየተራ የመንግሥት ስልጣን ይዘው የነበሩት ገዢዎቻችን ካለፈው ጥቃት ተምረው የኢኮኖሚና የጦር ኃይል ጡንቻችን እንዲፈረጥምና በባላጋራዎቻችን እንድንታፈር አላደረጉም። ከኢኮኖሚውና ከተደራጀው የጦር ኃይል በተጨማሪ፣ በተለያዩ መድረኮች ላይ የግብጽ ኃይል ሚዛን እንዳያደፋ፣ በኛ በኩል የሚሰለፍ የተማረ/የሰለጠነ የሰው ኃይል አላፈሩልንምና በኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሰነዘረው ወቀሳ፣ ሀዘንና እሮሮ ሁሉ በገዢዎቻችን ላይ ያነጣጠረ ይመስለኛል።
ሀገራችን አቅመ-ደካማ በመሆኗ፣ በድምበሯ ውስጥ ከሚፈ(ስ)ሰው የዐባይና የገባሮቹ ውሀ ድርሻ እንዳይኖራት በተፋሰሱ ታችኛ ክፍል የሚገኙት ሀገሮች (በተለይ ግብጽ) ዓይናቸውን አፍጥጠው ይጠብቋታል። ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከሯታል። የዐባይን ውሀ አጠቃቀም በተመለከተ በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ክርክር ረዘም ያለ ጊዜ የፈጀ ነው። አሁንም ክርክሩ እንደቀጠለ ነው።
ላንባቢዎች ለማስታወስ ያህል፣ በዐባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ የኢትዮጵያና የግብጽ የክርክር አቋም ባጭሩ እንደሚከተለው ነው።
2. የኢትዮጵያና የግብጽ አቋም በዐባይ አጠቃቀም ላይ
2.1. የኢትዮጵያ አቋም፡ ኢትዮጵያ የያዘቺው የክርክር አቋም በ1966 ዓ.ም በወጣው የሄለስንኪ ደምብ (Helsinki Rules) በመባል በሚታወቀው የሀገር አቋራጭ ወንዞች አጠቃቀም ድንጋጌን የተመረኮዘ ነው። የኢትዮጵያ አቋም የዐባይን ወንዝ ውሀ ‘ሚዛናዊ’ (equitable distribution) በሆነ መልኩ ‘ተዛዝነን’ (fairly) እንጠቀምበት የሚል ነው። ዐባይ ወንዛችን ነውና (ለግብጽ የሚያስፈልገው ውሀ ሳይዛባ) እኛም ተጠቃሚዎች መሆን ይገባናል። በሀገራችን ክልል ውስጥ የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት እንዳንጠቀም መከልከል የተባበሩት መንግሥታት ያጸደቀውን ያንድን ሀገር ሉዐላዊ መብት መጋፋትና መድፈር ነው። ስለዚህ የሱዳንንም ሆነ የግብጽን ሕዝብ ጥቅም በማያናጋ መንገድ ወንዛችን እንጠቀምበታለን የሚል ነው። የዐባይን ወንዝ (ለግብጽም፣ ለሱዳንም፣ ለኢትዮጵያም) ሚዛናዊና ተመጣጣኝ (equitable) በሆነ መልኩ እንድንጠቀም ግብጽ ፈቃደኛ ካልሆነች፣ ኢትዮጵያ (የግብጽን አወንታ ሳትጠብቅ) በግሏ ትወስናለች ወይም እርምጃ ትወስዳለች (unilateral decision) የሚል ነው የኢትዮጵያ አቋም።
2.2. የግብጽ አቋም፡ የግብጽን የመከራከሪያ አቋም በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል።
ሀ) ከ5,000 ዘመናት በላይ ከኢትዮጵያም ሆነ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ተነስቶ ወደግብጽ የሚፈሰው (የጥቁር ዐባይና የነጭ ዐባይ) ውሀ ታሪካዊ ተጠቃሚ ነኝ። አሁንም ዋናዋ ተጠቃሚ (primary user) እኔ ነኝ፣ የውሀው ታሪካዊ ባለቤትም እኔ ነኝ ባይ ናት። ግብጽ ይህን ታሪካዊ ተጠቃሚነት መከራከሪያ የምታደርግበት ምክንያት፣ በተባበሩት መንግሥታት ተቀባይነት ያለው “ዓለም አቀፍ የሕግ ኮሚሽን” (International Law Commission/ILC) ካወጣቸው ሕግጋት አንዱ “መጀመሪያ የውሀው ተጠቃሚ የሆነ፣ የውሀው ባለመብት ይሆናል። በኋላ የመጣው የመጀመሪያውን ተጠቃሚ መብት ሊገስስ አይችልም”5 ስለሚል ነው። እንደዚህ ያለውን ባለመብትነት በእንግሊዝኛ acquired rights or prior appropriation እያሉ ይጠሩታል። ግብጽ ይህንን ደምብ ተንተርሳ፣ በስተላይ ካሉት የተፋሰስ ሀገሮች አዲስ የሚወጠን ፕሮጀክት ሁሉ ታሪካዊ ጥቅሜን ማዛባቱ አይቀርም (leads to ‘appreciable’ harm) ትላለች። በዐባይ ተፋሰስ ላይኛው ክፍል (upper catchments) የሚታቀድና የሚወጠን የልማት ስራ ሁሉ ታሪካዊ ጥቅሜን ስለሚነካ፣ እኔ ያየሁት/ያወቅሁት፣ ያመንኩበት፣
3 አንዳንድ ምንጮች እንደሚጠቁሙት ይህ ውል (የቋንቋ አተረጓጐም ውዝግብ በማስከተሉ) በኢትዮጵያ በኩል አልተፈረመም/አልጸደቀም (not ratified) ይላሉ።
4በ1929ኙና በ1959ኙ የውል ስምምነቶች ሌሎቹ የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮችም አልተሳተፉበትም። ምክንያቱም ኮንጐ በቤልጅየም ስር ነበረች። ሌሎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች በሙሉ ነፃነት ያልነበራቸው፣ የራሷ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች ነበሩ።
5 ------ Whoever uses the water first thereby establishes a claim or right to it. Any use or user coming second in time cannot legally diminish the right that the first user has claimed.(Waterbury 2002, 28).
የተስማማሁበትና ያጸደቅሁት ካልሆነ በስተቀር፣ የሚታቀደው የልማት ስራ ተፈጻሚነት ወይም ተግባራዊነት አይኖረውም የሚል ነው። ስለዚህ ግብጽ የያዘቺው አቋም ባጭሩ፣ በዐባይ ተፋሰስ ውስጥ ለሚታሰቡና ለሚወጠኑ ፕሮጀክቶች ሁሉ ፈቃጅና ከልካይ፣ ሰጪና ነሺ እኔ ነኝ የሚል ነው።
ለ) በእንግሊዞች አማካይነት በ1929 ዓ.ም፣ በኋላ ደግሞ በ1959 ዓ.ም በግብጽና (በእንግሊዞችና በግብጽ ጣምራ ግዛት ስር /Anglo-Egyptian Condominium በነበረቺው) በሱዳን ከተፈረመው የዐባይ ውሀ አጠቃቀም ስምምነት ውጪ፣ ከዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ጋር ሌላ ድርድር አልደራደርም፣ ሌላ ውል አልዋዋልም፣ ሌላ ፊርማም አልፈራረምም የሚል ነው።
3. የ1929ኙና የ1959ኙ ውሎች ባጭሩ
የአንባቢዎቼን ትውስታ ለመቀስቀስ ያህል፣ የዐባይ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር የ1929 ዓ.ም እና የ1959 ዓ.ም የውል ስምምነቶች በየመድረኩ በተደጋጋሚ (በተለይ በግብጾች) የሚነሱ ናቸውና ባጭር ባጭሩ እንደሚከተለው ላቅርብላችሁ።
ሀ) የ1929ኙ የዐባይ ውል ተፈራራሚዎች፣ 1) ከቅኝ ተገዢነት ነፃ የወጣች ቢሆንም በብዙ መልኩ (በተለይ በመንግሥት አስተዳደር ዘርፍ) ገና በእንግሊዞች ተጽእኖ ስር የነበረቺው ግብጽ ናት። 2) በእንግሊዝና በግብጽ ጣምራ ተገዢ የነበረቺው ሱዳን ናት። አድራጊ ፈጣሪዋ እንግሊዝ ብትሆንም የ1929ኙ የውል ስምምነት (በተለምዶ) ግብጽና ሱዳን የተስማሙበት ውል እንደሆነ ተቆጥሮ ነው የሚወሳው። የ1929ኙ ውል ባጭሩ የሚከተለውን ይመስላል።
 በዚያን ጊዜ በእንግሊዞች አማካይነት ግብጽና ሱዳን በተማመኑበት መሠረት በያመቱ በጠቅላላ 80 ቢሊዮን ሜትር ኩብ (cubic meters) ውሀ ግብጽ/አስዋን ይደርስ ነበር። ከዚህ 80 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ ውስጥ ግብጽና ሱዳን በዚያን ጊዜ ሊጠቀሙበት ይችላሉ ተብሎ የተተመነው የውሀ መጠን (utilizable water) 52 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ነበር። ይህም ማለት (80 – 52 = 28) ወደ 28 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ ከግብጽ ተርፎ ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር እንደሚገባ ነበር የታመነበት።
 ግብጽና ሱዳን ሊጠቀሙበት ይችላሉ ከተባለው 52 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ (cubic meters) ውስጥ ሱዳን 4 ቢሊዮን ሜትር ኩብ (7.7%) ውሀ እንድትጠቀም፣ ግብጽ ደግሞ 48 ቢሊዮን ሜትር ኩብ (92.3%) ውሀ እንድትጠቀም ተስማሙ።
 በበጋው ወቅት (ከጥር መጨረሻ እስከ ሐምሌ አጋማሽ ድረስ/January 20 to July 15) የሚፈስሰው የዐባይ ውሀ ግን ሙሉ በሙሉ ለግብጽ ጥቅም ብቻ እንዲውል ተስማሙ።
 በላይ በኩል የሚገኙትን የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ለመቆጣጠር (monitor) የግብጽ መብት የተጠበቀ ስለመሆኑ ተስማሙበት።
 በላይ በኩል ያሉትን የተፋሰሱን ሀገሮች ፈቃድ ሳታገኝ (without the consent of upstream riparian states) በዐባይ ላይና ከዐባይ ጋር የሚገናኝ ማንኛውንም ፕሮጀክት ለመስራት የግብጽ መብት የተጠበቀ መሆኑን ተስማሙበት።
እንግዲህ አንባቢዎች እነዚህን ውሎች አይታችሁ የየራሳችሁን ሚዛናዊ ፍርድ ስጡ። እነዚህ ውሎች በሁለቱ ሀገሮች መካከል ብቻ መፈረማቸው ልክ ነውን? በነዚህ ውሎች የማን መብት ተጠበቀ? የማን መብት ተደፈረ? ከውሎቹ እንደምትረዱት ይህ ውል የዐባይን ተፋሰስ ሀገሮች6 በሙሉ የሚመለከት ነው። ተደራዳሪዎቹና ተፈራራሚዎቹ ግን ‘ግብጽና’ ‘ሱዳን’ ብቻ ናቸው። የላይኞቹ የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ከዐባይ ወንዝ ውሀ የተተወላቸው ድርሻ የለም። በኔ እይታ ይህ ውል በላይ በኩል ያሉትን የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ሉዐላዊነት ገፍፎ፣ መብታቸውን ደፍሮ፣ አድራጊ ፈጣሪዋ ግብጽ ብቻ እንድትሆን ያደረገ ውል ነው።
ለ) የ1959ኙ የዐባይ ውል ስምምነት ሱዳን ከእንግሊዞች ቅኝ ተገዢነት ነፃ ከሆነች በኋላ (ማለትም በሁለት ነፃ ሀገሮች) በግብጽና በሱዳን መካከል የተደረገ ስምምነት ነው። የስምምነቱ ዋና ዋና ነጥቦች ባጭሩ የሚከተሉት ናቸው።
 አስዋን ላይ ለሃምሳ ዓመታት ያህል ተለክቶ የተገኘ ነው በማለት ጠቅላላው የዐባይ ውሀ 84 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ነው ብለው ተመኑ። ከዚህ 84 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ ውስጥ 10 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በትነትና (surface evaporation) በስርገት (seepage) ሊጠፋ/ሊባክን ይችላል ተብሎ ተገመተ።
6 ሕጋዊ ታዋቂነት ያላቸውና የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች በመባል የሚታወቁት ሀገሮች፡ግብጽ፣ ሱዳን፣ ዩጋንዳ፣ ኮንጐ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ታንዛኒያ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ ናቸው።
 ቀሪውን 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ ግብጽና ሱዳን ላገልግሎት ያውሉታል ተብሎ ታመነበት። ይህ ተመን ከ1929ኙ ተመን የ22 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ ብልጫ ያሳያል። በዚህ ተመን መሠረት ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር የሚገባ የዐባይ ውሀ የለም።
 ይህንን 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ፣ ሱዳን 18.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ (25%) ውሀ እንድትጠቀም፣ ግብጽ ደግሞ 55.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ (75%) ውሀ እንድትጠቀም ተከፋፈሉ።
 ሱዳን ነፃ ከወጣች ከሁለት ዓመት በኋላ (በ1958 ዓ.ም) የተስማሙበትን፣ የዐባይን ወንዝ ውሀ ሙሉ በሙሉ ይይዛል ብለው ያመኑበትን፣ የአስዋንን ግድብ ግብጽ እንድትገነባ ስምምነታቸውን አጸደቁ።
 ሱዳን የውሀ ኮታዋን እስካላለፈች ድረስ ሮሲዬርስ (Roseires Dam) የተባለውን ግድብ ጥቁር ዐባይ ላይ ገድባ ለኃይል ማመንጫና ለመስኖ አገልግሎት እንድትጠቀምበት ተስማሙ።
 ሱዳን ከግብጽ ጋር በመስማማት የዐባይን ውሀ ፍሰት እሚያጠነክሩ (ወደ ሱድ/Sudd ረግረግ እየገባ በትነት የሚባክነውን ውሀ የሚቀንሱ) በኋላ እንደተወጠኑት እንደነ ጆንገሌይ ቦይ (Jongelei Canal) የመሳሰሉ ፕሮጀክቶች አውጥታ መስራት እንደምትችል፣ ይህ ዓይነቱ ስራ በሚያስከትለው ወጪና ገቢ ግብጽ ተሳታፊ/ተካፋይ እንደምትሆን ተስማሙ።
 በስተላይ ከሚገኙ የተፋሰሱ ሀገሮች የሚሰነዘር አቤቱታ ቢኖር ጉዳዩን ግብጽና ሱዳን በጋራ ሊያዩትና፣ በጋራ ሊያስተናግዱት ስምምነት አደረጉ።
 ከሁለቱ ሀገሮች (ከሱዳንና ከግብጽ) ውጪ የዐባይ ውሀ ይገባኛል የሚል፣ በተፋሰሱ ውስጥ የሚገኝ ሀገር ቢነሳ፣ የቀረበው ጥያቄ በግብጽና በሱዳን ከታመነበት፣ አስዋን ግድብ የሚደርሰው የዐባይ ውሀ ተለክቶ በሚገኘው የውሀ መጠን መሠረት፣ ለጠያቂው ሀገር ተቀንሶ የሚሰጠውን ውሀ ግብጽና ሱዳን እኩል ሊካፈሉ ተስማሙ።
 ቴክኒካዊ የሆኑ የውሀ ልማት ስራዎችንና ትብብሮችን የሚያከናውን ቋሚ የጋራ የቴክኒክ ኮሚሽን (Permanent Joint Technical Commission/PJTC) እንዲቋቋም ተስማምተው አቋቋሙ።
እነዚህን ውሎች ነው ግብጽ በድፍረት የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች የጋራ ውሎች በማስመሰል በያጋጣሚው በተደጋጋሚ መከራከሪያ ነጥብ እያደረገች የምትጠቅሳቸው። በነዚህ የውል ስምምነቶች እኛ አልተሳተፍንባቸውም በማለት ሌሎቹ የተፋሰሱ ሀገሮች (riparian states) ቢወተውቱም፣ ግብጽ በአዲስ መልክ በሚረቀቅ ሌላ የውሀ አጠቃቀም ወይም ክፍፍል ላይ ለመደራደር ፈቃደኛ አለመሆኗን እስካሁን እንዳጸናች ነች።
በ1995 ዓ.ም የግብጽ የውጭ ጉዳይ ምንስቴር ረዳት ሚኒስትር የነበሩ (ማርዋን በድር/Marwan Badr) የተባሉ ግብጻዊ “የሕዝባቸው ቁጥርና ኢኮኖሚያቸው እያደገ የመጣው የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች የውሀ ጥያቄ፣ ፓለቲካ ብቻ ሳይሆን እውን እየሆነ ነውና ግብጽ ከ1959ኙ የውሀ ኮታ ለየት ባለ የውሀ ድርሻ ላይ ለመደራደር መዘጋጀት አለባት” የሚል (ካንድ ግብጻዊ ባለስልጣን እማይጠበቅ) ሀሳብ በማቅረባቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባቸዋል። የግብጾች ግትር አቋም በ1959 ዓ.ም ከሱዳን ጋር ተደራድረን ካገኘነው (55.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ) የተለየ መደራደሪያ ሀሳብ አንቀበልም የሚል ነው።
4. ያገር አቋራጭ ወንዞች አጠቃቀም ተመክሮ
ወንዞች የተፈጥሮ ፀጋ ናቸው። ወንዞቹ በሚፈስሱበት አቅጣጫ የሚገኙ ሀገሮች ሁሉ ሊጠቀሙባቸው ይገባል። አጠቃቀሙ ግን ካገር አገር መለያየቱ የማይቀር ነው። ምክንያቱም የተለያየ የውሀ አቅርቦት አማራጭ (ዝናም፣ ሀይቅ፣ ምንጭ፣ የከርሰ ምድር ውሀ፣ ሌላ ወንዝ) ያለው ሀገር አለ። እንደ ግብጽ ያለው ደግሞ ከወንዝ ውሀ በስተቀር ሌላ አማራጭ የሌለው (primary user) ሀገር አለ። በእድገት ደረጃው ከፍተኝነት ምክንያት የውሀ ፍላጐቱና ፍጆታው ከፍተኛ የሚሆንበት ሀገር አለ። ኋላ-ቀርና ብዙ ውሀ እማይጠቀም (እማያስፈልገው) ሀገር አለ። ኋላ-ቀር የነበረው ሀገር በኢኮኖሚ እያደገ ሲሄድ የውሀ ፍላጐቱና ፍጆታውም እየጨመረ ስለሚሄድ የውሀ ድርሻው/ኮታው በየጊዜው መታየት ይኖርበታል። ባጭሩ ለማስቀመጥ ያህል የውሀ ፍላጐትና ፍጆታ ከጊዜ ጊዜ ይለዋወጣል። የውሀ ክፍፍልም እንደዚሁ በየጊዜው እየተጠና መስተካከል አለበት። አንድ ጊዜ የተመደበ የውሀ ኮታ ለዘላለም ቋሚ ሁኖ መኖር የለበትም። ግብጽ ይህንን ሁሉ አላጣቺውም፣ ግን ልትቀበለው፣ ሊዋጥላት አልቻለም።
ይህንን (የወንዝን ውሀ) የመሰለ የተፈጥሮ ሀብት በድርድር መከፋፈል እንደሚገባ የዓለም ሕዝብ ያምንበታል። የተባበሩት መንግሥታት ያጸደቃቸው የድምበር አቋራጭ ወንዞች አጠቃቀም ደምቦችና ሕግጋት አሉ። በጋራ ወንዞቻቸው አጠቃቀም ላይ
የተለያዩ ሀገሮች (ባፍሪካ ውስጥም ካፍሪካ ውጭም) ስምምነት7 እየተፈራረሙ ሲጠቀሙባቸው እናያለን። ለናሙና ያህል ጥቂቶቹን ልዘርዝርላችሁ።
ምዕራብ አፍሪካ፡
- ሴኔጋል ወንዝ (Senegal River) እሚፈስባቸው ሀገሮች (ማሊ፣ ሞሪታኒያ፣ ጊኒና ሴኔጋል) የወንዙን አጠቃቀምና እንክብካቤ በሚመለከት ተደራድረው የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል። ማሊ ውስጥ የሚገኘው ማናንታሊ (Manantali Dam) የተሰኘው ግድብ በተፋሰሱ ሀገሮች ኅብረት በትብብር የተሰራ ነው። ግድቡ ማሊ ውስጥ ቢሆንም የተፋሰሱ ሀገሮች በሙሉ በጋራ ባለቤትነት የሚያ(ዝ)ዙበት፣ የሴኔጋል ሸለቆ ባለስልጣን (OMVS/ Office de Mise-en-Valeur du Vallee du Senegal) ብለው ባቋቋሙት ቢሮ የሚተዳድር የኅብረት ግድብ ነው።
- የናይጀር ወንዝ (Niger River) ተፋሰስ ማሊን፣ ናይጀሪያን፣ ኒጀርን፣ ጊኒን፣ በርኪናፋሶን፣ ካሚሩንን፣ ቤኒንን፣ አይቮሪኮስትን፣ ቻድን ያጠቃልላል። እነዚህ የናይጀር ወንዝ ተፋሰስ ሀገሮች የውል ስምምነት ተፈራርመው የተፋሰሱን ውሀ በጋራ ይጠቀሙበታል። ባንዳንዶቹ የተፋሰሱ ሀገሮች ቅሬታ መሰንዘሩ ባይቀርም እንደ ዐባይ ጐልቶ የወጣ ችግር የለባቸውም።
መካከለኛው አፍሪካ፡
- የዛምቤዚ ወንዝ (Zambezi River) ተፋሰስ ዛምቢያን፣ ዚምባቡዬን፣ ሞዛምቢክን፣ ማላዊን፣ አንጐላን፣ ናሚቢያን፣ ቦትስዋናን፣ ታንዛኒያን ያካትታል። ከነዚህ ሀገሮች መካከል ዛምቢያና ዚምባቡዬ የጋራ አጠቃቀም ስምምነት ተፈራርመዋል። እንዲያውም ካሪባ ግድብ (Kariba Dam) የሚባለውን ከአፍሪካ ታላላቅ ግድቦች አንዱ የሆነውን ግድብ በጋራ ነው የገደቡት። የዛምቤዚን ወንዝና የግድቡን አጠቃቀም የሚከታተልና የሚያስተዳድር (Zambezi River Authority የሚባል) ባለስልጣን መስሪያ ቤትም በጋራ አቋቁመዋል። ሌሎቹ የዛምቤዚ ተፋሰስ ሀገሮች በወንዙ ውሀ አጠቃቀም ላይ እምብዛም ስለሆኑ፣ በተፋሰሱ አጠባበቅ ግዴታ ውስጥ መግባት ስላልፈለጉ ይመስላል የስምምነቱ ተሳታፊ አልሆኑም።
- ካጌራ ወንዝ (Kagera River) ሩዋንዳና ቡሩንዲ የሚነሳ ወደ ቪክቶሪያ ሀይቅ የሚገባ ትልቅ ወንዝ ነው። በዚሁ ወንዝ ሩሱሞ ፏፏቴ (Rusumo Falls) ላይ የኃይል ማመንጫ ግድብ ገድበው የኤሌትሪክ ኃይሉን ለታንዛኒያ ለመሸጥ ፕሮጀክት ወጥነው ነበር። የገንዘብ አቅማቸውን ለማጐልበት ከሩዋንዳና ከቡሩንዲ በተጨማሪ ታንዛኒያንና ዩጋንዳን አስተባብረው (አባል አድርገው) የካጌራ ሸለቆ የልማት ድርጅት የሚባል አቋቁመው ነበር። ነገር ግን በመካከል አካባቢው በጦርነት ስለተመሰቃቀለ ፕሮጀክቱ በውጥን ቀርቷል።
አውሮፓ፡
- የዳኒዩብ ወንዝ (Danube River) ተፋሰስ ሀንጋሪን፣ ዩጐዝላቪያን፣ ሮማንያን፣ ኦስትርያን፣ አልባኒያን፣ ፓላንድን፣ ጣሊያንን፣ ስዊትዘርላንድን፣ ቡልጋሪያን፣ ስሎቫኪያን፣ ጀርመንን፣ ቼኮዝለቫኪያን፣ ራሽያን (የድሮውን ሶቪዬት ኅብረት) ያካተተ ነው። እነዚህ ሀገሮች ሁሉ በተፋሰሱ አያያዝና አጠቃቀም ላይ ተፈራርመው ወንዙን በጋራ ይጠቀሙበታል።
- የራይን ወንዝ (Rhine River) ደግሞ ቤልጅዬምን፣ ኔዘርላንድን፣ ኦስትሪያን፣ ፍራንስን፣ ስዊትዘርላንድን፣ የሚያስተሳስር ስለሆነ በዚህ ወንዝ አያያዝና አጠቃቀም ላይ እነዚህ ሀገሮች የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ሰሜን አሜሪካ፡
- ኮሎራዶና ሪዮ-ግራንድ (Colorado and Rio Grande) አሜሪካንና ሜክሲኮን ስለሚያስተሳስር ሁለቱ ሀገሮች የስምምነት ውል ተፈራርመዋል።
- ኮሎምቢያና ታላላቆቹ ሀይቆች (Columbia and the Great Lakes) ካናዳና አሜሪካ በጋራ ስለሚጠቀሙባቸው ስምምነት ተፈራርመዋል።
ደቡብ አሜሪካ፡
- ፕሌት ወንዝ (Plate or La Plata) የሚባለው ብራዚልን፣ አርጀንቲናን፣ ፓራጉዋይን፣ ኡራጉዋይን፣ ቦሊቪያን ያስተሳስራል። ስለሆነም እነዚህ ሀገሮች በዚህ ወንዝ ውሀ አጠቃቀም ላይ የውል ስምምነት ተፈራርመዋል።
- አማዞን ወንዝ (Amazon River) ፔሩን፣ ኢኳዶርን፣ ኮሎምቢያን እና ብራዚልን የሚያስተሳስር፣ በዓለም ከታወቁት ታላላቅ ወንዞች አንዱ ነው። የአማዞን ተፋሰስ ሀገሮች (በጆግራፊያዊ አቀማመጣቸው የተነሳ) ከሚፈልጉት በላይ ከዓመት እስከ ዓመት ዝናም ያገኛሉ። ስለሆነም የመስኖ ውሀ አያስፈልጋቸውም። የገንዘቡን አቅም ካገኙት ከአማዞን ገባር ወንዞች ለኃይል ማመንጫ የሚሆኑ ግድቦች ሊገድቡ ይችላሉ። ስለዚህ በአማዞን ተፋሰስ ውስጥ ከላይ እስከታች ውሀ እንደልብ ስለሚገኝ የውሀ ክፍፍል ውል አልተፈራረሙም። በአማዞን ተፋሰስ ውስጥ ያለው ችግር የድንግል ጫካዎች አጠባበቅና አያያዝ ጉዳይ ነው። ወደዚያ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ አልገባም።
7 ስምምነት ተፈራረሙ ማለት የሆነ ያጠቃቀም ስርዐት በጋራ አውጥተዋል ማለት ነው እንጂ ፈጽሞ ከችግር ነፃ ናቸው ማለት አይደለም።
እስያ፡
- ኢንዱስ ወንዝ (Indus River) ፓኪስታንና ሕንድ በጋራ የሚጠቀሙበት ወንዝ ስለሆነ ሁለቱ ሀገሮች በዚሁ ወንዝ አጠቃቀም ላይ ውል ተፈራርመዋል።
- ሜኮንግ ወንዝ (Mekong River) ቻይናን፣ ካምቦዲያን፣ ላዎስን፣ ታይላንድንና ቪየትናምን ያስተሳስራል። ስለሆነም ከቻይና በስተቀር ሌሎቹ የሜኮንግ ተፋሰስ ሀገሮች የውል ስምምነት ተፈራርመዋል።
- ቲግሪስና ዩፍራጥስ (Tigris and Euphrates) ቱርክን፣ ሲሪያንና ኢራቅን ያስተሳስራል። ቱርክ የሁለቱም ወንዞች መነሻ ነው። ሲሪያ ከዩፍራጥስ ወንዝ ወገብ (መካከል) ላይ ነች። ኢራቅ ደግሞ ሁለቱ ወንዞች ተገናኝተው ከሚወርዱበት ዝቅተኛው፣ ደልዳላውና በረኻማው ክፍል ላይ ይገኛል። በዩፍራጥስ ወንዝ ላይ በሲሪያና በቱርክ መካከል ለብቻ አንድ ስምምነት ተደርጓል። በሲሪያና በኢራቅ መካከል ደግሞ ሌላ ስምምነት ተደርጓል። በኢራቅና በቱርክ መካከል ግን የተደረገ ስምምነት የለም።
አንባቢዎቼ ዝርዝሩ ረዥም ነው። ለማስረጃ ያህል ይህ የሚበቃ ይመስለኛል። በዐባይ ወንዝ ላይ ግን (በ1929 ዓ.ም እና በ1959 ዓ.ም) ግብጽና ሱዳን ተፈራረሙ ከሚባለው ውል በስተቀር ሌላ ውል የለም። የግብጽ አቋም ግልጽ ነው። ደጋገምኩባችሁ እንጂ፣ የግብጽ አቋም የዐባይን ውሀ ከተፋሰሱ ሀገሮች ጋር ለመካፈል አልደራደርም ነው።
ግብጽ ወደ ድርድር ለመቅረብ የማትፈልግበት ምክንያት ግልጽ ነው። አዲስ ድርድር ከተጀመረ ሚዛኑ ወደ ብቸኛ ተጠቃሚነቱ (sole acquired rights) ሳይሆን ይነስም ይብዛም ለሌሎቹ የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮችም ድርሻ ይኑራቸው (equitable distribution) ወደሚለው ማድፋቱ አይቀርም። ሌሎቹ የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ድርሻ ከተሰጣቸው፣ ግብጽና ሱዳን በብቸኝነት ሲጠቀሙበት የቆዩት የውሀ መጠን መቀነሱ የማይቀር ነው። ግብጽ አዲስ ድርድር የምትጠላውም ለዚህ ነው።
ዘመን ከመቆጠሩ በፊት ጀምራ እስካሁን ድረስ ከሚገባት/ከድርሻዋ በላይ የዐባይን ወንዝ ስትጠቀም የኖረች ስለሆነች፣ ለአዲስ የውሀ አጠቃቀም ድርድር አልሰለፍም በማለት ጸንታለች። እናንተ ውሀ ሲጠማችሁ የወንዝ ውሀ በመዳፋችሁ ያለዚያም በእንስራና በቅል ቀድታችሁ ከመጠጣት በስተቀር ሌላ የውሀ አጠቃቀም ታሪክ የላችሁምና፣ ከዚያ የተለየ አዲስ አመል አታምጡ ማለቷ ይመስላል።
አንባቢዎቼ፣ የውሀ አጠቃቀም በጥንታዊነትና በታሪክ ቢሆንማ ኑሮ፣ የትግሪስንና የዩፍራጥስን ወንዝ የጥንቱ ሜሶፓታሚያ ስልጣኔ ምንጭና እምብርት የሆነቺው ኢራቅ ብቻ ትጠቀምበት ነበር። የውሀ አጠቃቀም ግን ከታሪክና ከጥንታዊነት ጋር ሳይሆን ከኢኮኖሚ ጥንካሬና ከኃይል ሚዛን ጋር ወይም ከአቅም ጋር የሚሄድ ስለሆነ፣ የቲግሪስና የዩፍራጥስ ውሀ ባለ ሙሉ መብት ተጠቃሚ ቱርክ ሁናለች።
ቱርክ 1.6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማትና የውሀ ኃይልም ለማመንጨት፣ አናቶሊያ ግድብ (Anatolia Dam) የሚባል በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተወዳዳሪ የማይገኝለት ትልቅ ግድብ ስትገነባ፣ ሲሪያና ኢራቅ8 ተቃውመው ነበር። በ1992 ዓ.ም የቱርክ ፕሬዚደንት የነበሩት ሱሌማን ደሚረል (Suleiman Demirel) “በሳውዲ አረቢያ የነዳጅ ሀብት ማንም ጣልቃ እንደማይገባ ሁሉ፣ በቱርክ የውሀ ሀብትም ማንም ጣልቃ ሊገባ አይችልም፣ የፈለግነውን እናደርግበታለን” በማለት በሀገራቸው ድምበር ውስጥ የሚገኘው የዩፍራጥስ ወንዝ ውሀ ብቸኛ ባለሙሉ መብት መሆናቸውን ተናገሩ።
ግብጽ ኢትዮጵያን ለማዳከም ለረዢም ጊዜ ስታደርገው እንደኖረቺው ሁሉ፣ ሲሪያም የቱርክን ኢኮኖሚ ለማዳከምና የግድቡን ስራ ለማደናቀፍ ስትል፣ የኩርድ ሽምቅ ተዋጊዎችን (Kurdish guerrilla fighters) እያሰለጠነች ወደቱርክ ማስገባትና ፀጥታ ማደፍረስ ጀምራ ነበር። ይህንን የሲሪያን ተንኮል የተገነዘበቺው ቱርክ የጦር ሠራዊቷን አንቀሳቅሳ ሲሪያ ድምበር ላይ ስታሰፍር፣ ሲሪያ (ቱርክን የመቋቋም ወታደራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ አቅም/ጥንካሬ ስላልነበራት) አንገቷን ደፍታ ቁጭ አለች። ቱርክም “በሀገሯ ክልል ውስጥ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት የወንዙን ውሀ ጭምር ያለማንም ፈቃድ ሙሉ በሙሉ መጠቀም ትችላለች” የሚል ዛቻ ስታሰማ ከቆየች በኋላ፣ በ1987 ዓ.ም በሲሪያ የውሀ ባለመብትነት ሳይሆን፣ በቱርክ ሰብአዊነት ወይም በርኅራሄ፣ ለሲሪያ በየሰከንዱ 500 ሜትር ኩብ (cumsec) ውሀ የምትለቅ መሆኑን ገለጸች። ሲሪያም በተራዋ ቱርክ ‘በርኅራሄ’ ከምትለቅላት የዩፍራጥስ ውሀ ሀምሳ ስምንት ከመቶ (58%) የሚሆነውን ለኢራቅ እንደምታስተላልፍ ገለጸች። ይህ ታዲያ የኃይል ሚዛንን ነው እሚያሳየው? ወይስ ጥንታዊ ተጠቃሚነትን? በጥንታዊ ተጠቃሚነት ቢሆንማ ኑሮ፣ ከላይ እንዳልኩት፣ የቲግሪስና የዩፍራጥስ ወንዝ ዋና ተጠቃሚ መሆን የነበረባት ኢራቅ ነበረች።
በንጹሕ ኅሊና እንደምናስበው ቢሆን ኑሮ፣ የዮርዳኖስን ወንዝ ሲሪያ፣ ሌባኖስ፣ ጆርዳን፣ ፍልስጤምና እስራኤል ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ተከፋፍለው ሊጠቀሙበት ይገባ ነበር። ነገር ግን ከ1950ዎቹ ጀምሮ ዋናዋ ተጠቃሚ (በአሜሪካ ተገንነት የምትተማመነው ባለጡንቻዋ) እስራአኤል ነች። እስራኤል ከሚገባት በላይ የወንዙ ተጠቃሚ ሁናለች በማለት (ሲሪያ) ከዮርዳኖስ ገባር ወንዞች መካከል ትልቅ ከሚባለው ያርሙክ ወንዝ (Yarmouk River) ውሀ ጠልፋ ለመስኖ ለመጠቀም ስትሞክር፣ ለመስኖ ውሀ መጥለፊያ የገነባቺውን ግድብ እስራኤል በቦምብ ደብድባ አፈራርሳባታለች።
8 ኢራቅ የቲግሪስና የዩፍራጥስ ወንዞች ታችኛ ሀገር ስለሆነች፣ እንደ ግብጽ የወንዞቹ ጥንታዊ/ታሪካዊ ባለመብት ነኝ ማለት ትችላለች(acquired rights/ prior appropriation)። ይህ መብት ግን በኢራቅ ላይ ሲሰራ አይታይም።
በ1975 ዓ.ም ሕንድ ጋንጀስ ወንዝ (Ganges River) ላይ ፋራቃ (Farrakka Barrage) የሚባል ግድብ ገደበች። የግድቡ ዓላማ በበጋ/በደረቅ ጊዜ ከትልቁ ጋንጀስ ወንዝ ውሀ ተጠልፎ ሁግሊ (Hoogli River) ወደሚባለው አንስተኛ ወንዝ እንዲቀላቀልና የወንዙ ውሀ፣ ብክለት የሚበዛበትን የካልከታን ወደብ እንዲያጸዳው፣ ወይም ደለሉንና ቁሻሻውን አጣጥቦ ወደሕንድ ውቅያኖስ እንዲወስደው ለማድረግ ነበር። ነገር ግን ይህ ጋንጀስ ወንዝ ላይ የተገደበ (ፋራቃ (Farrakka) የተሰኘ) ግድብ ከታች በኩል ሩዝ አምራች የሆኑትን የባንግላዲሽ ገበሬዎች ውሀ አስቀረባቸው። በዚህም የተነሳ ባንግላዲሾች እስከ 1977 ዓ.ም ችግሩን ከሕንድ ጋር በድርድር ለመፍታት ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ከሕንድ ጋር የመፎካከር አቅም ስለሌላቸው፣ አድማጭ አጥተው፣ አንጀታቸው እያረረ ጥቃታቸውን ‘ተቀብለው’ ይኖራሉ። ሕንድም እንዳሰበቺው በበጋ ጊዜ ከጋንጀስ ወንዝ እየጠለፈች (ጸድቶ እማይጸዳ ወደቧን) ካልከታን ታጸዳለች።
ቻይና ሜኮንግ (Mekong River) በተሰኘው ወንዝ ደጋማው ክፍል ላይ ትልቅ የኃይል ማመንጫ ግድብ ስትገድብ የታችኞቹን ሀገሮች (ካምቦዲያን፣ ላዎስን፣ ታይላንድን፣ ቪዬትናምን) አላማከረችም፣ አላሳወቀችም። በራሷ የግል ውሳኔ ብቻ ሜኮንግ ወንዝ ላይ ትልቅ ግድብ ገድባለች።
አንባቢዎቼን ያሰለቻል እንጂ በደቡብ አሜሪካም ሌሎች ምሳሌዎችን መጨማመር ይቻል ነበር። ኃይል ያለው የፈለገውን ማድረግ እንደሚችል፣ ደካማው ጥቃት ቢደርስበትም አድማጭ/ተቆርቋሪ እንደማያገኝ ለማሳየት ያህል ያቀረብኳቸው ምሳሌዎች የሚበቁ ይመስለኛል። የዓለም አቀፍ ሕግ ኮሚሽን (International Law Commission) ደምብ፣ አንድ የተፋሰስ ሀገር ሌሎች ሀገሮች በሚጋሩት ወንዝ ላይ ፕሮጀክት የሚነድፍ ከሆነ ለሚመለከታቸው የተፋሰሱ ሀገሮች ማሳወቅ ይገባዋል የሚል ቢሆንም፣ የተፋሰሱ ሀገሮች የኃይል ሚዛን/አቅም ከሞላ ጐደል ተመጣጣኝ ካልሆነ ተፈጻሚነት ወይም ተግባራዊነት እንደማይኖረው ያቀረብኳቸው ምሳሌዎች ያሳያሉ። ተጨባጩ ሁኔታ እንደሚያሳየን ከሆነ የድምበር አቋራጭ ወንዞችን አጠቃቀም አስመልክተው የወጡ ዓለም አቀፍ ሕግጋት ብቻቸውን ፋይዳ የላቸውም፣ አይሰሩም። ፋይዳ የሚኖራቸውና የሚሰሩ የሚመስሉት የኃይል ሚዛን/አቅም ሲጨመርባቸው ብቻ ነው።
የወንዝ ተጠቃሚዎቹ ሀገሮች የኃይል ሚዛን ከሞላ ጐደል ተመጣጣኝ በሚሆንበት ጊዜ የውሀ አጠቃቀሙም ከሞላ ጐደል ተመጣጣኝ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል የኢንዱስን ወንዝ (Indus River) አጠቃቀም በሚመለከት ሕንድና ፓኪስታን (ሁለቱም ባለኒዩክሊየር ሀገሮች በመሆናቸው ይመስላል) በዓለም ባንክ አደራዳሪነት፣ የኢንዱስን ወንዝ ገባር ወንዞችም ሆነ የዋናውን ኢንዱስ ወንዝ እኩል ተካፍለው ለመጠቀም በ1960 ዓ.ም ተፈራርመዋል። በዚያው ውል መሠረት እስካሁን ድረስ ወንዙን በጋራ ይጠቀሙበታል። በወንዙ አጠቃቀም የተነሳ ሕንድና ፓኪስታን ሲጋጩ ተሰምተው አያውቁም። ኔፓልና (Nepal) ባንግላዲሽ (Bangladesh) ግን የጋንጀስንና የብርሀማፑትራን (Brhamaputra River) ወንዞች ከሕንድ ጋር እንዴት እንደሚከፋፈሉ የተፈረመ ውል የለም። ሕንድ እንደፈለገች ብቻዋን ውሳኔ የምትወስን ዓይነተኛ ተጠቃሚ ነች።
የዐባይን ወንዝ አጠቃቀም በተመለከተ ደግሞ ፈላጭ ቆራጯ ግብጽ ነች። ከ1970ዎቹ ጀምራ የተፋሰሱን ሀገሮች ሳታማክር በዐባይ ውሀ (በቱቦ ሱዊዝ ካናልን አሻግራ የሰላም ካናል/”Peace Canal” የተባለ ትልቅ ቦይ/ካናል በመቅደድ) ሲናይ (Sinai) ውስጥ ሕዝብ ለማስፈርና የመስኖ ልማት ለማስፋፋት የያዘቺውን እቅድ በመከታተል ላይ ነች። ይህ ግዙፍ እቅድ የሲናይን በረሃ ለማልማት ብቻ ሳይሆን፣ ለእስራኤል ውሀ ለመሸጥም ጭምር የተወጠነ ፕሮጀክት እንደሆነ ይታማል።
ይህ እንደተሰማ፣ ሀ) ግብጽ የዐባይን ወንዝ ከተፈጥሮ ተፋሰሱ ውጪ በቱቦና በካናል ስባ ልትወስድና ልትጠቀም አይገባትም፣ ለ) የግብጽ እርምጃ ሌሎቹን የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ሳታሳውቅ በግል ብቻዋን የወሰነቺው ነውና አግባብ አይደለም በማለት ኢትዮጵያ ተቃውማ ነበር። ተቃውሞዋን ጆሮ የሰጠው፣ ያዳመጠው የለም። ከግብጽ ባለስልጣኖችም የተሰጠው መልስ “ከተፋሰሱ የመጨረሻ ታችኛ ስለሆንን የማሳወቅ ግዴታ የለብንም” የሚል ነው። ግብጾች ይህን የሚሉት ያለምክንያት አይደለም። ለትልልቅ ፕሮጀክቶች ብድር በመስጠት ተጽእኖ በማሳደር የማይናቅ ሚና የሚጫወተው የዓለም ባንክ፣ የተፋሰሶችን ላይኛ ሀገሮች ፕሮጀክት ሲወጥኑ ለተፋሰሱ ታችኛ ሀገሮች ማሳወቅ እንዳለባቸው ሲደነግግ፣ የታችኞች ሀገሮች ግን ለላይኞች ሀገሮች እንዲያሳውቁ ግዴታ አልጣለባቸውም።
በዚህ የሰላም ካናል/”Peace Canal” ላይ ኢትዮጵያ ለሰነዘረቺው ተቃውሞ ግብጾች ሲያፌዙ/ሲያሾፉ “የዐባይ ወንዝ በጥንት ጊዜ ሲናይ ድረስ ይፈስ ስለነበር የሰላም ካናል ፕሮጀክታችን ከወንዙ የተፈጥሮ ተፋሰስ ውጪ አይደለም” ይላሉ። የኢትዮጵያ ፓለቲከኞች የጅኦሎጂ እውቀት ውሱን ሁኖ ነው እንጂ፣ ከብዙ ሚሊዮን ዓመታት በፊትማ ዐባይ አዋሽ በሚፈስበት አቅጣጫ ይፈስ ስለነበር ኢትዮጵያ የዐባይን ወንዝ አቅጣጫ ወደ አዋሽ ወንዝ ትቀይራለች በማለት ፌዙን በፌዝ መመለስ ነበረባቸው።
ከዚህም በተጨማሪ፣ ግብጽ ውስጥ ከዐባይ ሸለቆ በስተምእራብ በኩል የሚገኙትን የበረሃ ገነቶች (oases) በዐባይ ውሀ ሊያለሙ መዘጋጀታቸውን ፕሬዚደንት ሙባረክ በ1996 ዓ.ም ይፋ አድርገዋል። ይህ ፕሮጀክት የአዲሱ ሸለቆ ፕሮጀክት (New Valley Project or Toshka Project) ወይም ቶሽካ ፕሮጀክት በመባል ይታወቃል። የአስዋን ግድብ ከመጠን በላይ በሚሞላበት ጊዜ ትርፉን ውሃ ለማፍሰስ (spill way) የሚረዳ ነው ብለው ከግድቡ መኻል ወገብ ላይ ወደምእራብ አቅጣጫ ቶሽካ (Toshka) በሚል መጠሪያ የሚታወቅ የውሀ መሄጃ ቆፍረው ነበር። ያንን አስፋፍተው ወደ ውሀ ማጠራቀሚያነት በመለወጥ ከዐባይ ወንዝ በስተምእራብ 70 ኪሎ ሜትር ርቆ እስከሚገኘው የበረሃ ገነት ድረስ የመስኖ እርሻ ለማስፋፋት ማቀዳቸውን ገልጸዋል። በዚህ እቅድ በያመቱ ካስዋን ግድብ 5 (አምስት) ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ እየጠለፉ 200,000 (ሁለት መቶ ሺህ) ሄክታር መሬት ሊያለሙ ማቀዳቸው ታውቋል። ይህ የልማት እቅድ በዐባይ ሸለቆ ዳርና ዳር ተጣ(ብ)ቦ
ከሚኖረው ሕዝብ መካከል 7 (ሰባት) ሚሊዮን ሰው ተቀንሶ ባዲሱ የልማት ሸለቆ እንዲሰፍር ታቅዷል። ይህ ፕሮጀክት ቀስ በቀስ የሚካሄድና በሃያ ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ነው። ይህ የግብጽ የግል ውሳኔ (በ1997? ዓ.ም) ይፋ ሲደረግ፣ የወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር (ስዩም መስፍን) ለዓለም ባንክ ፕሬዝደንት (James Wolfensohn)፣ ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጽሐፊ (Kofi Annan)፣ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና ጽሐፊ (Salim Ahmed Salim) ተቃውሟቸውን በደብዳቤ ገልጸዋል። አቶ ስዩም መስፍን ተቃውሟቸውን ካስመዘገቡ ካንድ ዓመት በኋላ የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር (አቶ ተቀዳ ዓለሙ) የ1959ኙ የሱዳንና የግብጽ ስምምነት እንዲሰረዝ በአፍሪካ አንድነት ስብሰባ ላይ ጥሪ አቅርበዋል።
ነገር ግን የኢትዮጵያ ተቃውሞ እስካሁን ድረስ ያስከተለው/ያሳየው ውጤት የለም። የዐባይን ወንዝ አጠቃቀም በተመለከተ ኢትዮጵያ ባገኘቺው መድረክ ሁሉ ተቃውሞዋን ከመግለጽ ተቆጥባ አታውቅም። ግን ባዶ ተቃውሞ ነው። ተቃውሟቸውን በተግባር ሲገልጹ፣ በተለያየ ጊዜ (ከኃይለ ሥላሴ ጀምሮ እስካሁን ድረስ) በዐባይ ተፋሰስ ውስጥ ባስጠኗቸው ፕሮጀክቶች ላይ ስራ በመጀመር ባለመብትነታቸውን ለማረጋገጥ ሲሞክሩ ታይተው አይታወቁም። እንዲያውም አድማጮች “ዐባይ በተነሳ ቁጥር ኢትዮጵያዊያን” ተቃውሞ ማቅረብ ልማዳቸው ነው” ሳይሏቸው አይቀሩም። ባዶ ተቃውሞ፣ ጉልበት የለሽ ተቃውሞ፣ አቅም የለሽ ተቃውሞ ሰሚ የለውም። አቅመ ደካማ አቅሙን ገምብቶ የራሱን ማንነት ካላሳየ/ካላስመሰከረ በስተቀር ጩኸቱ አድማጭ አያገኝም።
ኢትዮጵያ አቅሟን ሳትገነባ (ባቅመ ደካማነቷ) እኔም ባለመብት ነኝና በዐባይ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ በምትልበት ጊዜ ከግብጽ የሚሰነዘረውን ተቃውሞ በሚገባ ልናጤነው ይገባል። ከውግዘት ለመዳንና ጥፋተኛ ላለመምሰል፣ ከሆነላትም ዲፕሎማሲያዊና የሞራል ድጋፍ ለማግኘት፣ ግብጽ የዓለም አቀፍ ሕግጋትን አክባሪ መስላ ለመታየት ከመጣር አትቆጠብም። ይህንኑ የፓለቲካ ስራ በሚገባ ሊሰሩ የሚችሉ፣ ብዙ ልምድ ያካበቱ፣ የበሰሉ ፓለቲከኞች፣ ምሁሮች፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ ወ.ዘ.ተ. አሏት። ያም ሆኖ ግን ግብጽ የምትመካውና የምትተማመነው በዓለም አቀፍ ሕግጋት አይደለም። ግብጽ የምትመካው በጉልበቷ (በተፋሰሱ ውስጥ ባላት የኃይል ሚዛን) ነው። ግብጽ የምታቅደው እቅድ፣ የምትሰነዝረው ተቃውሞ፣ የምታቀርበው ሀሳብ አድማጭና ድጋፍ እሚያገኘው በተፋሰሱ ውስጥ ባላት አንጻራዊ ጥንካሬ (ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል) ብቻ መሆኑን ጠንቅቃ ታውቃለች።
አቅመ-ደካማዋ ኢትዮጵያማ እንግዳው፣ እኔም ወንዞቼን ለመስኖና ለኃይል ማመንጫ እጠቀምባቸዋለሁ ባለች ቁጥር፣ ከግብጽ የሚሰነዘረው ተቃውሞ የጦርነት ማስፈራሪያ ነው። ጉዳዩ የአቅም ጉዳይ፣ የኃይል ሚዛን ጉዳይ ነውና፣ ያለግብጽ አወንታ የዐባይን ውሀ (የግብጽን ጥቅም በሚነካ መልኩ) ለመጠቀም የሚሞክር የዐባይ ተፋሰስ ሀገር ቢኖር፣ ሙከራው ወደጦርነት የሚያመራ እንደሚሆን የግብጽ ባለሥልጣኖች ደጋግመው አስጠንቅቀዋል። ይህ የተደጋገመ የጦርነት ዛቻ የሚሰነዘረው በተለይ በኢትዮጵያ ላይ ነው።
ለምሳሌ ያህል፣ “ኢትዮጵያ በእስራኤል ድጋፍ ዐባይ ላይ ግድብ ልትገድብ ነው” ከሚል ወሬ ተነስተው፣ የግብጽ ፕሬዝደንት የነበሩት አኑዋር ሳዳት፣ በ1979 ዓ.ም በግንቦት ወር (May 30) ባደረጉት ንግግር፣ ከዐባይ የምናገኘውን ውሀ ለመጠበቅ ስንል (ከኢትዮጵያ ጋር) ጦርነት እንከፍታለን ሲሉ ተናግረዋል። በዚያው ንግግራቸው ላይ የግብጽ ብቻ ሳይሆን የሱዳንም የውሀ አጠቃቀም (በኢትዮጵያ) ቢነካ ግብጽ ጦርነት ታስነሳለች፣ ምክንያቱም ሱዳን ስትነካ ግብጽም መነካቷ አይቀርምና በማለት ዝተዋል (J. Waterbury, 2002, 71)። በኋላም (በ1991 ዓ.ም) የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጽሐፊ የነበሩት ግብጻዊ ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ፣ ኢትዮጵያ የዐባይን ውሀ ከነካች “ጦርነት” የግድ ነው ብለዋል። ቡትሮስ ጋሊ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች በውሀ ኮታ (ክፍፍሎሽ) ላይ ከሚነታረኩ ይልቅ፣ ከዐባይ ውሀ ሌላ አማራጮችን በማፈላለግ፣ ተፋሰሶችን በመንከባከብ፣ የምርምር ጥናቶችን በማጠናከር፣ በመጓጓዣ፣ በቱሪዝም፣ በጤና፣ በፀጥታ አጠባበቅ፣ ወ.ዘ.ተ. ላይ ቢያተኩሩና ቢተባበሩ የተሻለ ነው፣ አስተባባሪነቱንም ግብጽ ልትወስድ ትችላለች በማለት የተፋሰሱን የውሀ ድርሻ/የኮታ ጥያቄ ለማስወገድ ጥረት ያደርጉ ነበር።
በ1995 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ የግብጽ ፕሬዝደንት በነበሩት በሆስኒ ሙባረክ ላይ በተቃጣው የግድያ ሙከራ የሱዳን እጅ አለበት በመባሉ ግብጽና ሱዳን ተቃቅረው ነበር። “ወንጀለኞቹን ለመያዝ በቂ ክትትል አላደረገችም” በሚል ግብጽ ኢትዮጵያንም ከሱዳን ጋር አብራ ስትወቅስ ነበር። በዚያ መቃቃር የተነሳ ባመት አራት ጊዜ በሚሰበሰበው (በሱዳንና በግብጽ በ1959 ዓ.ም በተቋቋመው) የቴክኒክ ኮሚሽን (Permanent Joint Technical Commission/PJTC) መደበኛ ስብሰባ ላይ ሱዳን ሳትገኝ ቀረች። ሱዳን ለስብሰባው ተሳታፊ አለመላኳ ብቻ ሳይሆን፣ የተፈጠረውን መቃቃር ምክንያት በማድረግ፣ “እንዲያውም ከነአካቴው ወደግብጽ የሚወርደውን የዐባይን ውሀ እቀንሰዋለሁ” የሚል ጉራ መንፋት ጀምራ ነበር። በዚያን ጊዜ (በ1995 ዓ.ም) የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አምር ሙሳ (Amr Musa) “የዐባይን ውሀ መነካካት ውጤቱ ጦርነት ነው” በማለት አስጠንቅቀዋል። አሁንም በሕዳሴ ግድብ የተነሳ በግብጽ ባለስልጣኖች የሚሰነዘረው ማስፈራሪያ “ጦርነት” ነው።
ባጭሩ ለማስቀመጥ ያህል ኢትዮጵያ በዐባይ ወንዝ ላይ የሆነ ሀሳብ አስባለች፣ ውጥን ወጥናለች በተባለ ቁጥር ከግብጽ ባለስልጣኖች አፍ የሚወጣው ቃል “ጦርነት” ነው። ጦርነትን በማስፈራሪያነት በመጠቀም ከየትኛውም የተፋሰሱ ሀገሮች የተሻለ ኃይል እንዳላቸው ደጋግመው ከሚያስታውሱ በስተቀር፣ ግብጾች በዐባይ ወንዝ ውሀ አጠቃቀም ላይ መደራደር አይፈልጉም።
አንዳንዴ ሁኔታውን በጥሞና ስናስተውለው የሚደራደሩበት ምክንያት እንደሌላቸው እንገነዘባለን። ድርድር እኮ የሚመጣውና እውን ሊሆን የሚችለው በኃይል ሚዛን ተመጣጣኝ ሁኖ ሲገኙ ብቻ ነው። ሩቅ ሳንሄድ ታህት፣ የኤርትራ ነፃ አውጭ ግምባር እና የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግምባር ባንድነት ተሰልፈው አቅማቸውን ባያጠናክሩ ኑሮ በኸርማን ኮኸን ‘ሸምጋይነት’ ሎንዶን ላይ ከደርግ ጋር ለድርድር መሰለፍ ይችሉ ነበር? ወይም በተቃራኒው ደርግ አቅም ባያጣ ኑሮ ከነታህት ጋር ለድርድር ይቀርባል ተብሎ ይታሰብ ነበር? አይታሰብም። ደካማና ኃይለኛ እንዴት ሁነው በእኩልነት ይደራደራሉ? አይደራደሩም። ለድርድር ቢቀርቡም እንኳን ድርድሩ መሳ ለመሳ የሚካሄድ አይሆንም። ድርድሩ የሚካሄደው ኃይለኛውና ጉልበተኛው በሚፈልገው አቅጣጫ ነው። የኃይለኛው ፍላጐት ተፈጻሚነት ሲያገኝ፣ የደካማው ድምጽ አድማጭ ሲያጣ ነው ስንታዘብ የኖርነው። በተለይ በፖለቲካው ዓለም ይህ የማይታበል ሀቅ ነው።
4. የላይኛው ዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች አቅምና የትብብር ተስፋ
የላይኛው ዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች በሙሉ አቅመቢሶች ስለሆኑ ከግብጽ ጋር (በኢኮኖሚ፣ በወታደራዊ ኃይል፣ በተማረና በሰለጠነ የሰው ኃይል) በእኩልነት ሊሰለፉ የማይችሉ፣ ለግብጽ ዓይን የማይሞሉ ደካሞች ናቸው። ዩጋንዳ? ኬንያ? ታንዛኒያ? ኤርትራ? ሩዋንዳ? ቡሩንዲ? ኮንጐ? ኢትዮጵያ? ከነዚህ ሀገሮች መካከል ግብጽን የመመዘን አቅም ያለው ሀገር የትኛው ነው? መልሱ ግልጽ ይመስለኛል። የትኛቸውም ሚዛን የሚደፉ አይደሉም። ስልጣን ለመጨበጥ ሲሉ ለዘመናት እርስ በርሳቸው (በጐሳ፣ በዘውግ፣ በምን? -----) ሲጨፋጨፉና ሲገለባበጡ፣ በኢኮኖሚ ግምባታ፣ በወታደራዊ ድርጅትና በሰለጠነ የሰው ኃይል ወደኋላ የቀሩ፣ አንዳንዶቹም ከወደቁበት ለመነሳት ያልቻሉ፣ ገና በመንፈራፈር ላይ ያሉ ናቸው። በዚሁ የስልጣን አያያዝና ተቃዋሚ ቡድኖችን በማስጠጋት የተነሳ እስካሁን ድረስ ሩዋንዳ ከኮንጐ ጋር፣ ኮንጐ ከዩጋንዳ ጋር፣ ዩጋንዳ ከሱዳንና ከሩዋንዳ ጋር ከመናቆር ያልተቆጠቡ ናቸው። ስለዚህ አንድ ጠንካራ ግምባር ፈጥረው ግብጽ ለአዲስ ድርድር እንድትሰለፍ አስገዳጅ ሁኔታ የሚፈጥሩ አይደሉም።
ከዚህም በተጨማሪ ዐባይን በተመለከተ የሁሉም የተፋሰሱ ሀገሮች ችግር፣ አንድ ወጥ ያልሆነና እኩል ክብደት የሌለው ስለሆነ፣ የግብጽን እብሪት ለማርገብ እስካሁን ድረስ አንድ ህብረት ወይም ግምባር አልፈጠሩም። ቢፈጥሩም በችግሮቻቸው መለያየትና በመካከላቸው በየጊዜው በሚፈጠረው ፖለቲካዊ ፍትጊያ የተነሳ የሚፈጥሩት ህብረትና ግምባር ጠንካራ ይሆናል የሚል እምነት የለም። የዐባይን ውሀ አጠቃቀም በተመለከተ፣ ችግራቸውና ፍላጐታቸው የተለያየ መሆኑን ለማየት እንድንችል ባጭር ባጭሩ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ።
1. ኮንጐ፡ አብዛኞቹ ወንዞቿ ወደራሷ ክልል የሚፈስሱ ናቸው። የገንዘብ አቅሙ ካላቸው የፈለጉትን የኃይል ማመንጫ ግድብ በፈለጉት መጠን መገንባት ይችላሉ። ሞቡቱ ሴሴሴኮ “ኢንጋ” የተባለውን ትልቅ ግድብ በኮንጐ ወንዝ ላይ ሲሰሩ፣ (ወንዙም ግድቡም ከኮንጐ ድምበር ውስጥ ስለሆኑ) ከየትኛውም ሀገር ጋር አላጋጫቸውም። እንዲያውም ኮንጐ ብዙ ኃይል ሊያመነጭ የሚችል የውሀ ኃይል ስላላት፣ በ1989 ከግብጽ ጋር ተነጋግራ (ተሻርካ) ለምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች፣ ለሱዳን፣ ለግብጽ፣ ለቱርክና ለደቡብ አውሮፓ ሀገሮች የውሀ ኃይል ለመሸጥ አስባ ነበር። ይህንንም ሀሳብ ግብጽ ትደግፈው ስለነበር ኮንጐና ግብጽ የቅርብ ወዳጆች እንጂ በዐባይ የተነሳ የሚፎካከሩ አይደሉም።
2. ዩጋንዳ፡ ነጭ ዐባይ ከሚወጣበት ከቪክቶሪያ ሀይቅ ጫፍ፣ ጂንጃ (Jinja) ከሚባለው ቦታ ላይ ከሚገኘው ኦውን (Owen Falls) ፏፏቴ ላይ ኦውን የሚባል(Owen Dam) ግድብ ገድባ በቂ የኤሌትሪክ ኃይል ታገኛለች። እንዲያውም ከራሷ አልፋ ተርፋ የኤሌትሪክ ኃይል ለኬንያ ትሸጣለች። ዩጋንዳ ይህን ግድብ (ኦውን ግድብ) በመገደቧ ከግብጽ ተቃውሞ አልተሰነዘረባትም። እንዲያውም ከግብጽ ድጋፍ ታገኛለች። በ1947 ዓ.ም ቅኝ ገዢዎች በነበሩት እንግሊዞች አስተናባሪነት፣ ዩጋንዳዊያን የኦውንን ግድብ በአንድ ሜትር ከፍ ቢያደርጉ፣ ግብጽ ለዩጋንዳ አንድ ሚሊዮን ስተርሊንግ ፓውንድ (£1,000,000) እንደምትከፍል ተስማምታለች። ክፍያውም ያንዴ ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት እንደሚኖረው ተዋውለዋል። ግብጽ ይህን ውል የተዋዋለችበት ምክንያት፣ በሱዳንና በግብጽ በረሃ በትነት የሚባክነውን ውሀ ለመቀነስ፣ ማለትም የቪክቶሪያን ሀይቅ እንደ ውሀ ማጠራቀሚያ ገንዳ አርጋ ለመጠቀም ስለፈለገች ነው። የዩጋንዳ ምድር አብዛኛው ከዓመት እስከ ዓመት በቂ የዝናም መጠን የሚያገኝ ስለሆነ ዩጋንዳዎች የዐባይን ውሀ ለመስኖ ስራ አይጠቀሙበትም፣ አይፈልጉትም። ስለዚህ ከዐባይ የሚያጡት ጥቅም የለም። በዚህም ምክንያት ዩጋንዳዊያን ዐባይን በተመለከተ (ከግብጽና ከሱዳን መገላገያ ለማግኘት ያህል አንዳንዴ ከሚያንገራግሩ በስተቀር) ብዙውን ጊዜ ገለልተኞች ናቸው።
3. ኬንያ፡ ከኬንያ ምእራባዊ ከፍተኛ ቦታዎች (Western Highlands) ተነስተው ወደ ቪክቶሪያ ሀይቅ የሚገቡ አጫጭር ወንዞች አሉ። እነዚህ ወንዞች የረባ የኤሌትሪክ ኃይል ሊያመነጩ የሚችሉ አይደሉም። በነዚህ ወንዞች ምክንያትም ኬንያዊያን ቀረብን የሚሉት ጥቅም የለም። ይሁን እንጂ የቪክቶሪያ ሀይቅ እሩቡ (1/4th) ያህል በኬንያ ክልል/ድምበር ውስጥ ነውና፣ ከቪክቶሪያ ሀይቅ ውሀ ጠልፈን ለመስኖ መጠቀም እንፈልጋለን ብለው ሱዳንንና ግብጽን፣ ዩጋንዳንም ጭምር ማስፈራራት ይችላሉ። ዩጋንዳ የምትፈራበት ምክንያት የውሀ ኃይል የምታመነጭበት ግድብ ውሀው የቪክቶሪያ ሀይቅ ስለሆነ፣ የቪክቶሪያ ሀይቅ ሲቀንስ የግድቡ ውሀ ስለሚቀንስባት ነው። ያም ሆነ ይህ እስካሁን እንደታየው ኬንያዊያን በሽምግልና ከሚሰለፉ በስተቀር የዐባይ ውሀ አጠቃቀም እምብዛም ደንታ አይሰጣቸውም።
4. ሩዋንዳና ቡሩንዲ፡ ከሩዋንዳና ከቡሩንዲ ተራራማ ቦታዎች ተነስተው ወደቪክቶሪያ ሀይቅ የሚገቡ ወንዞች አሉ። ወደቪክቶሪያ ሀይቅ ከሚገቡት ወንዞች መካከል ትልቁ ከሩዋንዳ ከፍተኛ ቦታዎች የሚነሳው ካጌራ (Kagera River) የሚባለው ወንዝ ነው። ሩዋንዳና ቡሩንዲ ካመት እስካመት በቂ ዝናም የሚያገኙ ሀገሮች ስለሆኑ የካጌራንና የሌሎቹንም ወንዞች ለመስኖ የመጠቀም ፍላጐት የላቸውም። ይሁን እንጂ ኃይል ለማመንጨት የካጌራን ወንዝ ለመገደብ የተጠና ጥናት አላቸው። ገንዘቡ ተገኝቶ የካጌራ ወንዝ ለኃይል ማመንጫ ቢገደብም ሱዳንንና ግብጽን ስጋት ላይ የሚጥል አይደለም። ምክንያቱም፣ ሀ) የኃይል ማመንጫ ግድብ ስለሆነ ወደቪክቶሪያ ሀይቅ የሚገባውን የውሀ መጠን አይለውጠውም፣ ለ) የኃይል ማመንጫው ግድብ በዝናማማውና በደጋማው አካባቢ ስለሆነ (ወደ ሱዳንና ወደ ግብጽ ሲደርስ) በትነት መልክ የሚባክነውን ውሀ ይቆጥባል። ሩዋንዳና ቡሩንዲም በዐባይ ውሀ ክፍፍል ላይ ከመነታረክ ይልቅ፣ የካጌራን ወንዝ ለመጠቀም ከሌሎች አጐራባች ሀገሮች ጋር በጣምራ መስራት ይሻላል በሚል ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ቡሩንዲና ዩጋንዳ በአባልነት የሚገኙበት የካጌራ ሸለቆ ድርጅት (Kagera Basin Organization) የተሰኘ ድርጅት አቋቁመው የድርጅቱ አባል ሀገሮች የጋራ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ብልሀት በማፈላለግ ላይ ናቸው። ስለዚህ የግብጽን እብሪት ለመግታት ከኢትዮጵያና ከሌሎቹ የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ጋር ህብረት ለመፍጠር የሚገፋፋቸው ችግር የለም።
5. ታንዛኒያ፡ አብዛኛው (2/3 ያህል) የቪክቶሪያ ሀይቅ በታንዛኒያ ክልል ውስጥ ነው። ታንዛኒያ (የጀርመን ቅኝ ግዛት በነበረችበት ጊዜ) በቅኝ ገዢዎቿ አማካይነት የቪክቶሪያን ሀይቅ ውሀ ጠልፋ በቦይ (canal) ወደ መሀል ታንዛኒያ በመውሰድ የመስኖ እርሻ ለማስፋፋት አቅዳ ነበር። ግብጽም ያንን የድሮ ቅኝ ገዢዎች ጅምር ስለምታውቅ፣ በንቃት በዓይነ ቁራኛ የምትከታተለው (ከኢትዮጵያ ቀጥላ) ታንዛኒያን ነው። ያንን የቅኝ ገዢዎች ውጥን እገፋበታለሁ ካለች፣ የቪክቶሪያን ሀይቅ ውሀ፣ ብሎም ወደ ዐባይ የሚገባውን ውሀ በጣም የሚቀንስ/የሚያዛባ ስለሚሆን፣ የግብጽን ብቻ ሳይሆን የነጭ ዐባይን ተፋሰስ ሀገሮች ሁሉ ቀልብ የሚስብ ይሆናል። እስካሁን ግን የግብጽን ትዕቢትና ለትብብር አለመዘጋጀት እያስተዋለች ግብጽን ከምትተች በስተቀር፣ ግብጽን ስጋት ላይ የሚጥል ፕሮጀክት አልወጠነችም። የጥንቱን ውጥኗንም አልቀሰቀሰችም።
6. የቪክቶሪያ ገበቴ ሀገሮች ተሰባስበው የቪክቶሪያ ገበቴ ቡድን (Lake Victoria Basin Group) የተሰኘ ድርጅት አቋቁመዋል። የተቋቋመው ቡድን አትኩሮቱ በሀይቁ አጠቃቀምና አጠባበቅ ላይ እንጂ፣ ከሱዳንና ከግብጽ ጋር በቀጥታ የሚያነካካ አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ ቡድኑ የሚያተኩረው በቪክቶሪያ ሀይቅ ላይ በሚንሳፈፈው ቅጠል/አረም (water hyacinth)፣ በሀይቁ ብክለት (pollution)፣ በሀይቁ ላይ ስለሚካሄደው የአሳ ማጥመድ ጉዳይና በሀይቁ የመጓጓዣ ጉዳይ ላይ ነው።
ባጭሩ ለማጠቃለል ያህል የምስራቅ አፍሪካ (የዐባይ ተፋሰስ) ሀገሮች በግብጽና በሱዳን የውሀ ድርሻ ላይ ህብረት/ግምባር የሚያስፈጥር ጥብቅ ችግር የለባቸውም ማለት ይቻላል። ፊታቸውን ወደ ሶቪየት ኅብረት ያዞሩትን የግብጹን ገማል አብደል ናስርንና የሱዳኑን ጀኔራል አቡድን ቂም ለመወጣት ብለው፣ እንግሊዞች (ከ1959 ዓ.ም እስከ 1961 ዓ.ም ድረስ) የምስራቅ አፍሪካ የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ግምባር (ኅብረት) እንዲፈጥሩ ለማስተባበር ሞክረው ነበር፣ ግን አልተሳካላቸውም። ከእንግሊዞቹ ጅምር በመነሳት የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ያለባቸውን ትንሽ የመቆጨት አዝማሚያ በመጠቀም ግምባር እንዲፈጥሩ በማግባባቱ፣ በመቀስቀሱና በመጐትጐቱ በኩል መታገል የነበረባት ኢትዮጵያ ነበረች። አቅም (የኢኮኖሚም ሆነ የተማረና የሰለጠነ ሰው) የላትምና፣ በአቅመቢስነቷም የተነሳ ተደማጭነት የላትምና አላደረገቺውም። ኢትዮጵያ የማስተባበር አቅም እንደሌላትም ግብጾች ጠንቅቀው የሚያውቁ ይመስለኛል።
ቀደም ብየ እንደጠቀስኩት እነዚህ የምስራቅ አፍሪካ/የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች፣ ሀ) ለግብጽ ዓይን የማይሞሉ (በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በጦር ኃይል) ደካሞች ናቸው። የዐባይን ችግር በሰላማዊ መልክ በድርድር ካልፈታሁ፣ ያለኔ ተሳትፎ የራሳቸውን እርምጃ ይወስዳሉ የሚባሉ አይደሉም። ለ) አብዛኞቻቸው የዐባይ ወንዝ ውሀ ቀጥተኛ በሆነ መልኩ ስለማይነካቸው አይቆረቁራቸውም። ከግብጽና ከሱዳን ጋር የሚያፋጥጥ ጉዳት አልደረሰባቸውም።
በግብጽ በኩልም ሲታይ፣ እነዚህ ሁሉ ሀገሮች ተደማምረው ለግብጽ ከሚደርሰው የዐባይ ውሀ ከ5% እስከ 14% ብቻ ነው አስተዋጽኦ የሚያደርጉት። ስለዚህ ግብጽ ከምስራቅ አፍሪካ (የዐባይ ተፋሰስ) ሀገሮች የምታገኘው የውሀ ድርሻ ከፍ እንዲልላት፣ ወዳጅነት እየፈጠረች (ለምሳሌ፣ የዩጋንዳዎችን ግድብ ከፍታ በመጨመር፣ የአልበርትን ሀይቅ በማስገደብ፣ ወደ ሱድ ረግረግ የሚሄደውን የነጭ ዐባይ ውሀ እንደ ጆንገሌይ ቦይ በመሳሰሉት) ከነጭ ዐባይ ተጨማሪ ውሀ ለማግኘት ከምትጥር በስተቀር፣ በቀንደኛ ባለጋራነት የምትሰለፍበት ጉዳይ የላትም።
5. የግብጽ አትኩሮት በኢትዮጵያ ላይ
ከሁሉም የተፋሰሱ ሀገሮች የበለጠ ግብጽ እምታተኩረው ኢትዮጵያ ላይ ነው። የኢትዮጵያ ጉዳይ ከላይ ከዘረዘርኳቸው የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ (የዐባይ ተፋሰስ) ሀገሮች በጣም የተለየ ነው። ኢትዮጵያ እንደሌሎቹ የዐባይ (ላይኛው) ተፋሰስ ሀገሮች ሁሉ አቅመ ደካማ ብትሆንም፣ ለግብጽና ለሱዳን የምታበረክተው የውሀ መጠን በጣም ብዙ ነው። ከሀገራችን
ጠቅላላ ስፋት 32%9 (ወይም 365,449 km2) የሚሆነው ለግብጽ ውሀ የሚያቀብል ነው። ከዚህ ሰፊ መሬት (365,449 km2) ላይ የሚዘንመው የዝናም ውሀ ሁሉ በጥቃቅን ገባር ወንዞች አማካይነት ወደ ጥቁር ዐባይ፣ ወደ አኮቦ-ባሮና ወደ ተከዜ ተቀላቅሎ በመጨረሻ ወደዋናው ዐባይ10 የሚገባ ነው። ሦስቱ ትልልቅ ተፋሰሶች ከነስፋታቸው እንደሚከተለው ቀርበዋል።
የተፋሰስ ስፋት (km2)
የተፋሰስ ስም በኢትዮጵያ ድምበር ውስጥ
1. የጥቁር ዐባይ ተፋሰስ 201,346
2. የባሮና ያኮቦ ተፋሰስ (የሶባት ተፋሰስ) 74,102
3. የተከዜ (ያትበራ) ተፋሰስ 90,001
ድምር 365,449
ዩጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲና ከስምጥ ሸለቆ በስተምእራብ የሚገኘው የኬንያ ክፍል ባንድ ላይ ቢደመሩ ጠቅላላ ስፋታቸው ከነዚህ ሦስት ተፋሰሶች ስፋት አይደርስም። ይህን ያህል ስፋት ባለው መሬት ላይ ነው ኢትዮጵያ ውሀ ነክ ልማት እንዳታካሂድ ግብጽ የምትቃወመው።
እነዚህ ተፋሰሶች ግብጽ ከሚደርሰው የዋናው ዐባይ ውሀ ከ86% እስከ 95% የሚሆን አስተዋጽዖ ያደርጋሉ። ሦስቱ ተፋሰሶቻችን በያመቱና በክረምት ወራት ግብጽ ለሚደርሰው የዐባይ ውሀ የሚያደርጉት አማካይ አስተዋጽኦ ከነጭ ዐባይ ጋር ሲነጻጸር (ግምታዊ አሀዙ/estimate) በሚከተለው ሰንጠረዢ ላይ የሚታየውን ይመስላል።
የተፋሰሶች ስም
ግብጽ ለሚደርሰው የዐባይ ውሀ
የሚያደርጉት አስተዋጽዖ በ(%)
ጥቁር ዐባይ
ያመት አስተዋጽዖ
የክረምት (የዝናም) ወራት አስተዋጽዖ
59
68
ባሮና አኮቦ (ሶባት)
14
5
ተከዜ (አትበራ)
13
22
የኢትዮጵያ አስተዋጽዖ በጠቅላላ/ድምር
86
95
ነጭ ዐባይ
14
5
Source: Waterbury, J. (2002) The Nile Basin: National Determinants of Collective Action, Yale University Press, London.
ሰንጠረዡ እንደሚያሳየው የነጭ ዐባይ አስተዋጽዖ (ከባሮና ካኮቦ ያልተሻለ) አንስተኛ ነው። በተለይ በክረምት ወራት ግብጽ ለሚደርሰው የዐባይ ውሀ፣ የነጭ ዐባይ አስተዋጽዖ 5% ብቻ ነው። ስለዚህ ነው የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ተባበሩም አልተባበሩም፣ የግድብና የመስኖ ፕሮጀክቶች ሰሩም አልሰሩም ለግብጾች አሳሳቢ እማይሆነው። ኢትዮጵያ ግን ካመት እስካመት ግብጽ ከሚደርሰው የዐባይ ውሀ ባማካይ 86%ቱን የምትሰጥ የግብጽ ህልውና የተመሰረተባት ናት። በክረምት ወቅት ደግሞ (በተለይ በነሐሴና በመስከረም) ግብጽ ከሚደርሰው የዐባይ ውሀ ከመቶ ዘጠና አምስቱ እጅ (95%) ከኢትዮጵያ የሚሄድ ነው። ከሦስቱ የኢትዮጵያ ተፋሰሶች ውስጥ አብዛኛውን (ያመቱ 59%፣ የክረምቱ 68%) ውሀ ለግብጾች የሚወስድላቸው ጥቁር ዐባይ ነው (ሰንጠረዡን ይመልከቱ)። ግብጾችም ከሁሉም አብልጠው አይናቸውን አፍጥጠው በንቃት የሚጠብቁት ይህንኑ ጥቁር ዐባይን ነው።
ከነዚህ ሦስት ተፋሰሶች እየተነሳ ወደግብጽ የሚሄደው ውሀ በርካታ ሁኖ ሳለ፣ በተፋሰሶቹ ውስጥ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ግን በተደጋጋሚ የድርቅ ሰለባ ይሆናል። እነዚህ ሦስት ተፋሰሶች የአማራን ክልል፣ የጋምቤላን ክልል፣ የቤኒሻንጉል-ጉሙዝን ክልል እና የትግራይን ክልል ከሞላ ጐደል ይሸፍናሉ ብንል (በ2012 ዓ.ም በተገመተው የሕዝብ ብዛት መሠረት) ወደ ሀያ ሦስት ሚሊዮን (22, 508, 807) የሚጠጋ ሕዝብ ይገኝባቸዋል። ይህም ከጠቅላላው (ከ92 ሚሊዮን) የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 25% ይሆናል። በአማራና በትግራይ ክልል ባማካይ በያንዳንዱ ኪሎሜትር ካሬ መሬት ከ105 እስከ 115 የሚሆን ሕዝብ
9 ይህ ስሌት የተሰላው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ስፋት 1.127 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ካሬ (km2) ነው በማለት ነው።
10 በዚህ ጽሑፍ “ዋናው ዐባይ” እያልኩ የምጠራው ሱዳንን አቋርጦ ወደ ግብጽ የሚፈስሰውን የነጭ ዐባይን፣ የጥቁር ዐባይንና የተከዜን ድምር ወንዝ ነው።
ይኖርበታል። የትግሬውና የአማራው ክልል ባመዛኙ የመሬቱ አምራቺነት በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ እያንዳንዱ ኪሎ ሜትር ካሬ ከ105 እስከ 115 የሚሆን ሕዝብ የመያዝ አቅም የለውም። የመሬቱ አምራችነት ዝቅተኛ በሆነው አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ በተቀናጀ ሁኔታ ወደ ደልዳላው አካባቢ ሂዶ በመስኖ እንዳይጠቀም ያለግብጽ ፈቃድ የረባ የመስኖ ስራ መስራት አይቻልም። (አለመቻሉን በ1996 ዓ.ም ግብጽ ለኢሕአዴግ የሰፈራ እቅድ የሰጠቺውን ምላሽ ዝቅ ብለው ያነቡታል)።
በግምት ወደ ሰማኒያ አምስት በመቶ (85%) የሚሆነው የሦስቱ ተፋሰሶች ነዋሪ በግብርናና በከብት እርባታ የሚተዳደር ነው። ግብርናውም ከብት እርባታውም በዝናም ውሀ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው። ይህ ሕዝብ በነዚህ ሰፊ ተፋሰሶች ውስጥ ከሚያልፉት ወንዞች የረባ የኤሌትሪክ ኃይልም ሆነ የመስኖ አገልግሎት ሳያገኝባቸው አልፈውት ወደግብጽ ይወርዳሉ።
የዐባይን ውሀ ለመስኖ ባለመጠቀሟ ኢትዮጵያ ባጉረመረመች ቁጥር ከግብጾችና ከደጋፊዎቻቸው ከሚሰነዘሩት መልሶች አንዱ “ኢትዮጵያ አማራጭ አላት” የሚል ነው። አማራጭ የተባለው “ዝናም” ነው። ኢትዮጵያ ዝናም ይዘንምላታል፣ የዝናም ወቅት እየጠበቀች ስታመርት የኖረች ነች፣ ያንኑ የዝናም አጠቃቀም ዘዴ እያሻሻለች ትቀጥል ለማለት ነው። ነገር ግን የኢትዮጵያ ዝናም እንደ ኮንጐ፣ እንደ ሩዋንዳ፣ እንደ ቡሩንዲ፣ እንደ ዩጋንዳና እንደ ምእራብ ኬንያ አይደለም። ቀደም ብየ እንደገለጽኩት እነዚህ የምስራቅ አፍሪካ (የዐባይ ተፋሰስ) ሀገሮች በጅዖግራፊያዊ አቀማመጣቸው የተነሳ ካመት እስካመት በመጠንም፣ በስርጭትም በቂና አስተማማኝ የሆነ ዝናም ያገኛሉ። የዝናሙ ውሀ በቂ ስለሆነ የወንዞቻቸውን ውሀ ለመስኖ አይፈልጉትም። ስለዚህም ነው ወደ ነጭ ዐባይ የሚፈሰው የወንዞቻቸው ውሀ ደንታ እማይሰጣቸው።
የኢትዮጵያ ዝናም መጠን፣ ጸባይና ስርጭት ግን ከዚህ በላይ ከጠቀስኳቸው ሀገሮች በጣም የተለየ ነው። ከባሮ ተፋሰስ በስተቀር በሌሎቹ ተፋሰሶች የሚዘንመው ዝናም አስተማማኝ አይደለም። በቂ ዝናም በማይገኝበት ጊዜና አንዳንዴም ጨርሶ በሚጠፋበት ጊዜ ከእጅ-ወደ አፍ ኑሮ የሚኖረው አርሶ-አደርና አርብቶ-አደር ሕዝብ ለርሀብና ለስደት ይጋለጣል። በተፋሰሶቹ አካባቢ የሚዘንመው ዝናም ተለዋዋጭ ነው። ያለወቅቱ ይመጣል፣ ያለወቅቱ ይሄዳል(ያቋርጣል)። አንዴ ያንሳል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከመጠን በላይ ይበዛና አፈሩ፣ ቡቃያው፣ እንስሳው፣ ሰው ከነንብረቱ ለጐርፍ ይጋለጣል። አርሶ አደሩ ሕዝብ ይህንን የማያስተማምን ዝናም እየጠበቀ የሚያመርተው ምርት ለዓመት ቀለቡ አይበቃም። ስለዚህ ኢትዮጵያን በተመለከተ ዝናምን የመስኖ ምትክ ወይም አማራጭ አርጐ ማቅረብ ዓይን ያወጣ ብልጣ ብልጥነት ነው።
ሕዝባችን ለዝናም እጥረት መደጐሚያ እንኳን የሚሆን የመስኖ ውሀ (supplemental irrigation) የለውም። ድርቅ በሚሆንበት ጊዜ፣ ወይም ዝናሙ በቂ በማይሆንበት ጊዜ እንዲጠቅም ተብሎ በማሟያነትና በመጠባበቂያነት የተቀደደ፣ በሀገርና በክልል ደረጃ ቀርቶ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ እንኳን የሚታወቅ ዘመናዊ ቦይ የለም። በዝናም ብቻ ተማምነን የምንኖር በመሆናችንም የተነሳ በ1970ዎቹና በ1984-85 ዓ.ም በዐባይና በተከዜ ተፋሰሶች ውስጥ11 በርሀብ ያለቀውን በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ እናስታውሳለን። አሁንም ቢሆን በነዚህ ተፋሰሶች ውስጥ የሚኖረው (ከጠቅላላው የሀገሪቱ ሕዝብ 25%) ኢትዮጵያዊ አብዛኛው በድህነትና በችግር የሚቆላ ነው። በየጊዜው ከውጭ በሚመጣ የምግብ ምጽዋት እየተደጐመ የሚኖር ሕዝብ ነው። የሀገሪቱን የምግብ ፍላጐት ለማሟላት በመስኖ ሊለማ የሚችለውን መሬት፣ አቅም ያላቸው ዜጐችና ድርጅቶች አልምተው ለገበያ ለማቅረብ ይችሉ ነበር። ዳሩ ግን ወንዞቻችን ከሱዳንና ከግብጽ ጋር ስላቆራኙን፣ በልበ-ሙሉነት/በድፍረት በዐባይ ተፋሰስ ውስጥ በውሀ ላይ የተመሠረተ የረባ ወይም ከቁጥር የሚገባ የመስኖ ልማት ስራ የሚጀምርና የሚያካሂድ የለም። ከጐረቤቶቻችን ጋር ለሚያነካኩን ወንዞች ጀርባችን እየሰጠን፣ እስካሁን ድረስ ስንረባረብ የቆየነው በአዋሽ ወንዝ ላይ ብቻ ነው።
በመስኖ ሊለማና ችግራችን ሊቀርፍ የሚችል ምን ያህል መሬት ያለጥቅም እንደተቀመጠ በግልጽ እንዲታያችሁ አንዳንድ ምንጮች የሚሉትን አጠር አጠር አድርጌ ልዘርዝርላችሁ።
 ዋተርበሪ/Waterbury (2002) የኢትዮጵያ አንድ ሦስተኛ (ወደ 33 ሚሊዮን ሄክታር) የሚሆን በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት አላት ይላሉ።
 የማእከላዊ ፕላን ብሔራዊ ኮሚቴ (1990) 3.5 ሚሊዮን ሄክታር ለመስኖ የሚያመች መሬት እንዳለን ይገልጻል። በመስኖ የለማው ግን 200,000 ሄክታር ወይም ወደ ስድስት በመቶ (5.7%) ብቻ መሆኑን ይኸው ብሔራዊ ኮሚቴ ያብራራል።
 የአሜሪካ ጠፍ-አቅኚ? ቢሮ (US Bureau of Reclamation) በ1964 ዓ.ም ያቀረበው የጥናት ሪፓርት የሚከተለውን በመስኖ ሊለማ የሚችል ግምታዊ (estimate) የመሬት ስፋት ያሳየናል።
11 የዐባይና የተከዜ ተፋሰሶች ከሞላ ጐደል የሚከተሉትን አካባቢዎች ያጠቃልላሉ። ሰሜን ሸዋን ከእንጦጦ ጀምሮ፣ አብዛኛውን ወሎ፣ ትግራይን፣ ጐንደርን፣ ጐጃምን፣ ሰሜናዊውን ወለጋ።
1) ከዲንደር ወንዝ እስከ ተከዜ ወንዝ ድረስ 230,000 ሄክታር መሬት በመስኖ ሊለማ ይችላል። (ከዲንደር ወንዝ በስተደቡብ የሚገኘው የበለስ ወንዝ ተፋሰስ እስከ ወለጋ ድምበር ያለው ደልዳላ መሬትና የተፋሰሱ ላይኛ ክፍል እዚህ ግምገማ ውስጥ አለመግባቱን ያስተውሉ)።
2) በአንገረብ ተፋሰስና በተከዜ ተፋሰስ ውስጥ 300,000 ሄክታር መሬት በመስኖ ሊለማ ይችላል።(ይህ አካባቢ እነሰቲት ሁመራንም ይጨምራል)።
3) ይኸው ያሜሪካ (ጠፍ-አቅኚ) ቢሮ ባኮቦ-ባሮ ተፋሰስ ውስጥ 335,000 ሄክታር ለመስኖ ሊውል የሚችል መሬት አለ ሲል፣ ታምስ-ኡልግ (TAMS-ULG) የተሰኘ ቡድን ግን በ1995 ዓ.ም ባካሄደው ግምገማ በዚሁ (ባኮቦ-ባሮ) ተፋሰስ ውስጥ 1.1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ሊለማ ይችላል ይላል።
እነዚህ የተለያዩ ቡድኖች የሰጡት ቁጥር ቢለያይም፣ የተጠኑት አካባቢዎች ምናልባት ሊደራረቡ (overlap) ቢችሉም፣ የሁሉም ግምገማ በማያሻማ ሁኔታ የሚያሳየን በመስኖ ሊለማ የሚችል፣ ገና ያልነካነው ሰፊ መሬት ያለን መሆኑን ነው።
ከሌሎች ምንጮች ደጋግመን እንደምናገኘው ከተፋሰሶቻችን ሁሉ የሚበልጥ12 (በግምት ከ760,000 ሄክታር በላይ የሆነ) ሰፊ ለመስኖ የሚውል መሬት ያለው ተፋሰስ ጥቁር ዐባይ ነው። በግብጽ እብሪትና በኛ/በራሳችን አቅመቢስነት የተነሳ ወንዞቻችንም ሆነ ለመስኖ የሚሆነውን መሬታችን ለመጠቀም አልቻልንም። “እያዩ ማዘን” ማለት ይህ አይደለም? ውሀና መሬት ይዘን አርሰን የማንጠቀም፣ ከንፈራችን እማይወዛ ጦም አዳሪዎች፣ የግብጽን ጡንቻ እያየን፣ ወንዞቻችን የመጠቀም መብታችን ተገፍፈን ተሸማቅቀን የምንኖር ደካሞች ነን።
ግብጽም የምትፈልገው ደካማነታችን እንዲቀጥል ነው። ትንሽ ጠንከር ካልን ወንዞቻችን ካሁኑ በተሻለ ሁኔታ መጠቀማችን እማይቀር ነው። ትንሽ ጠንከር ካልን ግብጾችን በተለያዩ መድረኮችም ሆነ በወታደራዊ ኃይል እንቋቋማለን ማለታችን እማይቀር ነው። ይህ እንዳይሆን ግብጾች በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ያደርጋሉ። የተለያየ ዘዴ እየፈጠሩ በስውርም በግልጽም ይወጉናል፣ ያዳክሙናል።
ብዙዎቻችን “ጦርነት እንከፍታለን” የሚለውን የግብጾችን ማስፈራሪያ ደጋግመን ስለምንሰማ፣ ብዙውን ጊዜ ሀሳባችን እሚያዘነብለውና እሚያተኩረው ወደ ወታደራዊ አቅማችን ነው። ስጋታችን የግብጽን ወታደራዊ ኃይል የሚመጥን ወታደራዊ ዝግጅት ይኖረን ይሆን? የሚል ነው። አዎ! ተገቢ ስጋት ነው። እኔ በበኩሌ ግብጽን የሚቋቋም ወታደራዊ ድርጅት አለን ብየ አላምንም። ግብጽም የለመደቺውንና ወደፊትም ለመጠቀም ያቀደቺውን የውሀ መጠን የሚቀንስ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ብትጀምር (ሌላ የምትፈራው የኢትዮጵያ ተገን/patron ካልኖረ በስተቀር) ግብጽ ጦር ከማስነሳት ትቆጠባለች ብየ አላምንም። ትልቁና ግብጽ ስትጠቀምበት የኖረቺውና ወደፊትም የምትጠቀምበት የጦርነት ዘዴ ግን በተለያዩ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች/መድረኮች ውስጥ የምታካሂድብን ጦርነት ነው። በአቅመ ደካማነታችን ላይ የዲፕሎማሲና የሞራል ተጽእኖ ከታከለበት ይበልጥ እየደከምን፣ ይበልጥ አቅም እያጣን፣ ይበልጥ አድማጭና ሰሚ እያጣን፣ ይበልጥ ለጥቃት እየተጋለጥን እንሄዳለን።
ግብጽ በተባበሩት መንግሥታት ልዩ ልዩ ቅርንጫፍ ድርጅቶች (FAO, UNDP, UNEP, ECA, WMO, WHO, UNESCO, etc.)፣ በዓለም ባንክ፣ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF)፣ በሌሎችም ትልልቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ፣ በአህጉራዊ ልማት ባንኮች ውስጥ ስር የሰደዱ፣ ቁልፍ ቁልፍ ቦታ ይዘው የሚሰሩ ዜጐች አሏት (Waterbury 2002, 11)። እነዚህ በተለያየ የትምህርት መስክ የሰለጠኑ ታላላቅ ግብጻዊያን፣ ተናግረው የሚያሳምኑ፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተጽእኖ ሊያደርጉ የሚችሉ፣ ውለታ ላደረገላቸው ውለታውን መመለስ የሚችሉ፣ ውሳኔ ሊያስቀይሩ የሚችሉ ዜጐች ናቸው (እንደላይኛው)። በተለይ በውሃ ጥናት መስክ (hydrological studies) የነጠሩና በብዙ ትልልቅ ድርጅቶች ውስጥ ባማካሪነት የሚሰሩ የግብጽ ባለሙያዎች አሉ (እንደላይኛው)። እነዚህ በየቦታው የተሰገሰጉ ግብጻዊያን የኢትዮጵያ አቤቱታና ጩኸት እንዳይሰማ ግልጽ ባልሆነ መንገድ መሰናክል ሊፈጥሩ ይችላሉ።
በኢትዮጵያ ተረ(ቅ)ቆ የሚቀርብ ፕሮጀክት ቢኖር ውድቅ እንዲሆን ሊያደርጉ ይችላሉ። ለቀረበው ፕሮጀክት ብድር ሊያስከለክሉ ይችላሉ። የትልልቅ ውሀ ፕሮጀክት ተቋራጮች እንዲሸሹ ሊያደርጉ ይችላሉ። የሕግ አማካሪዎችንና ባለሙያዎችን ሊያግባቡ ይችላሉ። በውሀ ክፍፍል ስምምነቶችና ውሳኔዎች ላይ ኢትዮጵያ እንድትገለል ሊያደርጉ ይችላሉ። በዐባይ ውሀ ላይ ኢትዮጵያን የማግለሉ ጉዳይ ከዚህ በፊት በ1989 ዓ.ም. በማያሻማ ሁኔታ ተከስቷል። የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) እና የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን (ECA) በ1989 ዓ.ም ያቋቋሙት፣ ሮጀር በርተሎት (Roger Berthelot) በተባለ ሰብሳቢ የተመራ አጥኚ ቡድን (fact finding mission) ኢትዮጵያን በጥናቱ ሳያስገባ፣ በቪክቶሪያ ሀይቅ ዙሪያ በሚገኙት የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ብቻ በመመርኮዝ የዐባይ ውሀ አጠቃቀም ባለበት
12 ላኮቦ-ባሮ የተሰጠው ግምት (1.1 ሚሊዮን ሄክታር) እውነት ከሆነ ለዐባይ የተሰጠው ግምት (760,000 ሄክታር) ትክክል አይመስልም። በኔ ግምት ካኮቦ-ባሮ ይልቅ ጥቁር ዐባይ የበለጠ ለመስኖ የሚውል መሬት የሚኖረው ይመስለኛል።
እንዲቀጥል ወስኗል። ይህም ማለት “እንደ ድሮዋ ኢትዮጵያ የዐባይን ውሀ ሳትጠቀም ትቀጥል” ማለት ነው። ይህ የጥናት ቡድን የሱዳንንና የግብጽን ጥቅም ላምስጠበቅ የተሰለፈ ሁኖ መታየቱን ወተርበሪ (Waterbury, 2002) ይገልጻሉ13።
የተለያዩ ሰበብ አስባቦችን (መረጃ አልተሟላም ማለትን ጨምሮ) በመጠቀም ውሳኔ በማዘግየት (በማጉላላት) ተስፋ እሚያስቆርጥ ሁኔታ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ። ባንጻሩ ለግብጽ ሁኔታዎችን ሁሉ ሊያመቻቹ፣ ቅድሚያ ሊሰጡና ሊያሰጡ ይችላሉ። ይህ ጦርነት በውሀዎች አጠቃቀም ዙሪያ ብቻ የሚያካሂዱት ጦርነት ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ጠንካራ ሀገር እንዳትሆን በሌሎች መስኮች ሁሉ ሊከፍቱብን የሚችሉት ጦርነት ነው። ይህ በየቢሮውና በየመድረኩ የሚካሄደው ስውር ጦርነት ሲካሄድ የኖረ ነው፣ አሁንም በመካሄድ ላይ ነው። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊም በግብጽ የሚካሄደው ኢትዮጵያን ለዘለቄታው በኢኮኖሚ ደካማ የማድረግ አሻጥር ገብቷቸው ነበር። ያቶ መለስን አባባል በግርጌ ያንብቡ14።
ታዲያ ይህን የመሰለውን ጦርነት ለመቋቋም ኢትዮጵያ ምን ይህል ዝግጁ ነች? በኔ ግምት ሀገራችን በኢኮኖሚም፣ በተማረ ሰው ኃይልም ገና እንደ ሕፃን የምታንቧችር ሀገር ነች። ከግብጽ ደረጃ ለመድረስ ብዙ ይቀራታል። ኢትዮጵያ በኢኮኖሚና በወታደራዊ ድርጅት ግብጽን የሚመጥን አቅም እንደሌላት ሁሉ፣ በተማረና በሰለጠነ የሰው ኃይልም አቅም የላትም።
በኢትዮጵያ ላይ ከሚሸረበው ደባና አሻጥር በተጨማሪ ሀገራችን አቅም በማጣቷ የተነሳ ስንት ውጥኖች ተወጥነው፣ ፍጻሜ ላይ ሳይደርሱ መክነው ቀርተዋል። እነዚህ በውጥን የቀሩ የልማት ፕሮጀክቶች የአቅመ-ደካማነታችንና የተጠቂነታችን ነጸብራቆች ናቸው። ጥቂቶቹን ልዘርዝርላችሁ።
6. በዐባይ ተፋሰስ መክነው የቀሩ ውጥኖች (በከፊል)
የአሜሪካ ጠፍ-አቅኚ ቢሮ (US Bureau of Reclamation, Department of the Interior) ከ1958 ዓ.ም እስከ 1963 ዓ.ም ድረስ በዐባይ ተፋሰስ ላይ ያጠናው ጥናት፣ በ1964 ዓ.ም በ17 ቅጾች ታትሞ ወጥቷል። በዚህ የጥናት ሪፓርት እንደሚታየው፣ ከጣና ሀይቅ ጀምሮ እስከ ሱዳን ጠረፍ ድረስ ባለው 900 ኪሎ ሜትር እርቀት ውስጥ፣ ለመስኖና ለኃይል ማመንጫ ሊውሉ የሚችሉ 26 ግድቦች (reservoirs) ሊገደቡ እንደሚችሉ ይገልጻል። ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።
ሀ) ሜጀር (በኋላ ኮሎኔል) ችዝማን (Cheesman) የተባሉ እንግሊዛዊ? በ1930 ዓ.ም ጣና-በለስ የተሰኘ፣ ጥናቱ የተጠናቀቀ የልማት ፕሮጀክት እንደነበር ይገልጻሉ። ከጣና ደቡባዊ ምእራብ በኩል ስፋቱ 5 ኪሎ ሜትር ብቻ የሆነውን ሸንተረር ቀ(ድ)ዶ/በስቶ (tunnel) የጣናን ውሀ ከበለስ ወንዝ ጋር አቀላቅሎ፣ ውሀው ለኃይል ማመንጫ አገልግሎት ከዋለ በኋላ በበለስ ወንዝ አማካይነት ወደ ዐባይ ወንዝ እንዲገባ ለማድረግ ታቅዶ ነበር ይላሉ። ይህ የጣና-በለስ እቅድ ኃይል ለማመንጨትና 65,000 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት የታቀደ ነበር። ከዚሁ እቅድ ጋር አያይዘው አሜሪካኖቹም በዚሁ በበለስ ወንዝ ተፋሰስ ሌላ ለኃይል ማመንጫ የሚውል ጥናት አጥንተው ነበር።
በ1982 ዓ.ም የኢትዮጵያ መብራትና ኃይል ባለስልጣን ይህንን የጣና-በለስ ፕሮጀክት ከዲዴሳ ፕሮጀክት ጋር ቀላቅሎ ይከታተለው ነበር። በ1986 ዓ.ም ወደ በለስ የሚወሰደውን ውሀ መጠን ለመቆጣጠር የሚያስችለው ስራ ጣና ላይ ተጠናቅቆ ነበር። በ1990 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሸለቆዎች ባለስልጣን (EVDSA-WAPCOS) በበለስ ሸለቆ/ተፋሰስ ብቻ 5 ግድቦችን ቀስ በቀስ መገደብ እንደሚቻል አምኖበት ነበር። በ1990 ዓ.ም ይህንኑ የጣና በለስ ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ የደርግ መንግሥት ቸሊኒ (Celini) ከተባለ የጣሊያን ተቋራጭ ኩባንያ ጋር ተዋውሎ፣ ተቋራጩም ለእቃው ማመላለሻ የሚያገለግል ያየር ማረፊያ ከጠረገ/ካዘጋጀ በኋላ ስራው (ባልታወቀ ምክንያት) በውጥን/ተቋርጦ ቀርቷል። በደርግ የተጀመረው የጣና-በለስ ፕሮጀክት በድርቅ የተጐዳውን ሕዝብ በምእራብ ኢትዮጵያ አስፍሮ 150,000 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ነበር።
ለ) የአሜሪካ ጠፍ-አቅኚ ቢሮ ከጣና ሀይቅ ሰሜናዊ ምስራቅ በኩል የሚገኝ የመገጭ ልማት (Megech Scheme) በተሰኘ፣ 25,000 ሄክታር መሬት በመስኖ ማልማት እንደሚቻል ታምኖበት እንደነበር ይገልጻል።
13 The stable front established by Egypt and the Sudan over the years has carried over into multilateral organizations and external funding agencies. Their position is not only taken as unassailable; it is sometimes argued more strenuously by third parties than by the two countries themselves. In 1989, Economic Commission for Africa (ECA)/UNDP fact finding mission, led by Roger Berthelot, is almost caricatural in its argumentation in support of the status quo in the basin. ------- Ethiopia was not included in this study (Waterbury, 2002, 132-133).(emphasis mine).
14 --- We hoped that the 1993 agreement would signal Egypt’s willingness to accommodate the interests of a new, friendly but economically weak neighbor in the basin. Three years later we felt Egypt had been at best politely obstructionist; and in the long term interested in keeping Ethiopia economically weak and diplomatically isolated (Waterbury, 2002, 83-84)
ሐ) ይኸው የአሜሪካ ጠፍ-አቅኚ ቢሮ ዲዴሳ ወንዝ ላይ 4 ግድቦችን መገደብ እንደሚቻልና ከወንዙ በታች በኩል ከሚሰራው ግድብ ላይ ኃይል ማመንጨት እንደሚቻል አጥንቶ ነበር።
መ) ዲንደርና ረሀድ በተሰኙት ወንዞች ከሱዳን ጋር የሚዋሰነውን የጐንደርና የሰሜናዊ-ምእራብ ጐጃምን ደልዳላ መሬት በመስኖ ማልማት እንደሚቻልና የውሀ ኃይልም ማመንጨት እንደሚቻል አሜሪካኖቹ ሪፓርት አድርገዋል።
ሰ) ካራዶቢ (Karadobi) የተሰኘ ጉደር ወንዝና የዐባይ ወንዝ ከሚገናኙበት ትንሽ ከፍ ብሎ እንዲገነባ የተጠና ትልቅ የኃይል ማመንጫ ግድብ ነበር። ይህ ቦታ ትልቅ የኃይል ማመንጫ ግድብ ለመገደብ በጣም አመቺ መሆኑንና በትነት ብዙ ውሀ እንደማያባክንም ገልጸዋል።
ረ) የድምበር ግድብ (Border Dam) የተሰኘ፣ ከሱዳን ድምበር ወደ ኢትዮጵያ 21 ኪሎ ሜትር ያህል ገባ ብሎ ከሚገኝ ቦታ ላይ፣ 11 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ ሊይዝ የሚችል፣ 6.2 ሚሊዮን ኪሎዋት አወርስ (KWh) የሚሆን ኃይል ማመንጨት የሚችል ግድብ እንዲሰራ ሀሳብ ቀርቦ ነበር። ይህ ግድብ ምናልባት አሁን “ሕዳሴ” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይመስለኛል።
ከዚህ ሁሉ የተጠና ፕሮጀክት ውስጥ፣ ጭስ ዐባይ ላይ ካለቺው አንስተኛ የኃይል ማመንጫና መጠነኛ ከሆነው የፊንጫ የኃይል ማመንጫ በስተቀር በተግባር የተተረጐመ የልማት ስራ የለም። አሜሪካኖቹ በዘመኑ አሉ በተባሉት ሳይንሳዊ የጥናት ዘዴዎች ተመርኩዘው ካገኙዋቸው 26 የግድብ ቦታዎች መካከል ሃያ አራቱ (24) መክነው የቀሩ ናቸው።
የፊንጫ ግድብ ስራ በተጀመረበትም ጊዜ ግብጽ ተቃውሞ አቅርባ በስንት ውጣ ውረድ (ባሜሪካኖች ተጽእኖ) ከዓለም ባንክ መጠነኛ-ከፊል ብድር ተገኝቶ ሊሰራ ችሏል። የፊንጫ (ፊንጫ-አማሪቲ ፕሮጀክት) ግድብ የተጠናው ለመስኖና ለኃይል ማመንጫ ቢሆንም፣ የሆነ ያልሆነ ምክንያት በመፍጠር፣ ዛሬ ነገ በማለት፣ ግድቡ እስካሁን ድረስ ለመስኖ ስራ እንዲያገለግል አልተደረገም። ከግድቡ የሚወጣው ውሀ ለመስኖ አገልግሎት ሳይውል ሙሉ በሙሉ ወደ ዐባይ ወንዝ የሚቀላቀል ነው። የመስኖው ስራ ያልተካሄደበትና ያልተስፋፋበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? ከጥርጣሬ በስተቀር ማስረጃ ስለሌለኝ አንባቢዎች ማስረጃ ካላችሁ አካፍሉን። ያለዚያ ግን ሴራ ስታሴርብን የኖረችና የምትኖር ሀገር ነችና ግብጽን በመጠርጠር አጅቡኝ።
ይህንኑ ጀምሮ የመተው ልማዳችን የታዘበው “የድምበር ዘለል ወንዞች ድርጅት” (International Rivers Network) በቅርብ ጊዜ በሕዳሴ ግድብ ገምጋሚዎች (Panel of International Experts) ከቀረበው የግምገማ ሪፓርት ተነስቶ ሲጽፍ፣ ------ በተፋሰሶች ውስጥ ታቅደው ተግባራዊ ያልሆኑ ፕሮጀክቶች ዘይንተረፍ ናቸው ሲል በኛ ላይ የቀረብ ሽሙጥ ሁኖ ይሰማኛል። የሕዳሴ ግድብ ጥናት የሚጐድለው የችኮላ ስራ ነውና በግድቡና ግድቡ በሚያስከትለው አካባቢያዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተጨማሪ ጥናት ይካሄድበት ማለቱም፣ (ነገር ጠምዛዥ አትበሉኝ እንጂ) የግብጾችን ልማዳዊ የማሰናከያ ዘዴ የሚያንጸባርቅ የመልእክተኛ አነጋገር ሁኖ ይሰማኛል።
ተጨማሪ መረጃና ተጨማሪ ጥናት መጠየቅን ግብጽ የማሰናከያ ዘዴ አድርጋ የምትጠቀምበት መሆኑን ለማሳየት ያህል፣ ገና የሽግግር መንግሥት በነበረበት ጊዜ (በ1993 ሐምሌ ወር) ከግብጽ ወይም ከሙባረክ ጋር የወዳጅነት ፊርማ በተፈራረመው በዚህ (በኢሕአዴግ ወይም በአቶ መለስ) መንግሥት ላይ የሆነውን ላስታውሳችሁ።
ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ የበተነውን የኢትዮጵያ ሠራዊት/ወታደር፣ ከራሱ (ከኢሕአዴግ) ጋር የመጡትንና ከስራ የተባረሩትን ሽምቅ ተዋጊዎች፣ በድርቅና በጦርነት ምክንያት ካካባቢያቸው ተፈናቀለው መተዳደሪያ ያጡትን ኢትዮጵያዊያን (በተለይ የትግራይ ተፈናቃይዎችን) በግብርና ስራ ለማሰማራት አንድ ፕሮጀክት ነድፎ ነበር። በዚያ ፕሮጀክት በዐባይ ተፋሰስና በተከዜ ተፋሰስ ውስጥ 10, 000 (አስር ሺህ) ሄክታር መሬት ለማረስ ታስቦ ነበር (Waterbury 2002, 83)። ከአስሩ ሽህ ሄክታር መሬት ውስጥ አንድ ሦስተኛው (ወደ 3,333 ሄክታር የሚሆን መሬት) ከዐባይና ከተከዜ ተፋሰሶች ውሀ ተጠልፎ በመስኖ እንዲታረስ ነበር የታሰበው። ከሁለቱ ተፋሰሶች ለመስኖ የሚጠለፈው ውሀ ባመት 37 ሚሊዮን ሜትር ኩብ እንደሚሆን ተገምቶ ነበር። ያ ውሀ ከጠቅላላው አማካይ የዐባይ ውሀ 0.004% እንደሚሆን ነበር የተሰላው።
ይህንን ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ “መልሶ ማቋቋምና ማህበራዊ ተሀድሶ?”15 (Ethiopian Relief and Social Rehabilitation Fund) የተሰኘ ገንዘብ አሰባሳቢ ድርጅት ተቋቁሞ ከዓለም ባንክ ገንዘብ ተጠየቀ። የዓለም ባንክም በፕሮጀክቱ አምኖበት ለፕሮጀክቱ ስራ የሚውል $70 ሚሊዮን ዶላር መደበ። በዓለም ባንክ ሕግ መሠረት በድምበር አቋራጭ ወንዞች ላይኛ ክፍል ላይ ያለ ሀገር ፕሮጀክት ሲወጥን፣ የሚመለከተውን የታችኛ የተፋሰስ ሀገር ማሳወቅ ግዴታ ነውና፣ ኢትዮጵያ ያቀደቺውን የሰፈራ ፕሮጀክት ለግብጽ እንድታሳውቅ የዓለም ባንክ ጠየቀ። በዓለም ባንክ ጥያቄ መሠረት ኢትዮጵያ ለግብጽ ስታሳውቅ ግብጽ ፕሮጀክቱን ልታውቅ/ልትቀበል አልፈለገችም።
15 ስሙ የራሴ ትርጉም ነው። ትክክለኛ ስሙ ሌላ ሊሆን ይችላል። የተጠቀምኩበት ምንጭ በእንግሊዝኛ የተጻፈ ስለሆነ እንግሊዝኛውን የሚተካ የመሰለኝን የአማርኛ ስም ሰጥቸዋለሁ። የአማርኛ ስሙን የምታውቁ ከሆናችሁ የእንግሊዝኛ ስሙን በቅንፍ ውስጥ ስላስቀመጥኩላችሁ ስለምን እያወራሁ እንደሆነ ሳትረዱት አትቀሩም።
የግብጽ ምላሽ “ተጨማሪ ጥናት ይደረግበት”፣ “ተጨማሪ መረጃ ይሰጠን” የሚል ነበር። በዚህም የተነሳ ፕሮጀክቱ በተግባር ላይ ሳይውል ረዢም ጊዜ ወሰደ። የዓለም ባንክም የግብጽን መልስ ሲጠብቅ ለፕሮጀክቱ የመደበውን $70 ሚሊዮን ዶላር ሳይለቅ እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ ቆየ። በመጨረሻ ግን (ምናልባት በአሜሪካና በእንግሊዞች አግባቢነት?) የዓለም ባንክ ለዚህ ፕሮጀክት የመደበውን $70 ሚሊዮን ዶላር በ1997 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ለቀቀ። ግብጽም ማቋረጫ የሌለውን የመረጃና የጥናት ጥያቄ እንደቀጠለች ፕሮጀክቱን ሳታውቅ/ሳትቀበል ቀረች።
የዓለም ባንክ በማን/በነማን አግባቢነትና ተጽእኖ ለኢትዮጵያ ገንዘብ ለመስጠት እንደወሰነ ግብጽ ባትረዳ ኑሮ ብዙ ጩኸት፣ ብዙ ማስፈራሪያ ታሰማ ነበር። የኢሕአዴግ ፕሮጀክትም ዓለም ሁሉ በንቃት የሚከታተለው ትልቅ መነጋገሪያ ዜና ይሆን እንደነበር እገምታለሁ። ያም ሆነ ይህ በእቅድ የተያዘው፣ ወደ 3,333 ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት ጉዳይ ተግባራዊ የሆነ አልመሰለኝም። የዓለም ባንክ የሰጠው $70 ሚሊዮን ዶላርም ለታሰበላቸው ሰዎች እንዴት እንደተሰጣቸው አላውቅም። ዋናው ላስተላልፈው የፈለግሁት መልእክት ኢትዮጵያ በዐባይ ተፋሰስ ውስጥ የመስኖም ሆነ የኃይል ማመንጫ ስራ ስትወጥን፣ ተጨማሪ ጥናትና ተጨማሪ መረጃ መጠየቅ የግብጽ የማደናቀፊያ ዘዴ መሆኑን ነው።
ይህንን ታሪክ ያመጣሁት የሕዳሴን ግድብ አስመልክቶ የ‘ድምበር ዘለል ወንዞች ድርጅት’ (International Rivers Network) ተጨማሪ ጥናትና ተጨማሪ መረጃ እየጠየቁ የልማት ፕሮጀክቶችን ማወሳሰብና ተጨናግፈው እንዲቀሩ ማድረግ ከግብጽ የተዋሰው አሰራር መስሎ ስለታየኝ ነው።
7. ወሳኝ አቋም በሕዳሴ ግድብ ላይ
ስለሕዳሴ ግድብ ዝርዝር መረጃ የለኝም። ሂጀም አልጐበኘሁትም። ትልቅ ግድብ መሆኑን እሰማለሁ። ለሌሎች ሀገሮች የሚሸጥ የውሀ ኃይል (hydro-electric power) እንዲያመነጭ መታቀዱን ሰምቻለሁ። ከሱዳን ድምበር 20 ኪሎ ሜትር ወደ ኢትዮጵያ ገባ ብሎ በኢትዮጵያ መሬት (በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል) ውስጥ፣ በዐባይ ወንዝ ላይ መጀመሩን አውቃለሁ።
ከ1958 ዓ.ም እስከ 1963 ዓ.ም በአሜሪካኖች በተካሄደው የዐባይ ተፋሰስ ጥናት እዚሁ አካባቢ፣ ማለትም ከሱዳን ድምበር 21 ኪሎ ሜትር ወደ ኢትዮጵያ ገባ ብሎ 11 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ ሊይዝ የሚችል፣ ቆቃን ሰባት ጊዜ የሚበልጥ፣ የግብጾችን አስዋን ግድብ ሁለት ሦስተኛ የሆነ (⅔) ትልቅ ግድብ እንዲገደብ በአሜሪካኖቹ አጥኚ ቡድን ሀሳብ ቀርቦ እንደነበር አንብቤአለሁ።
ኢትዮጵያ ወደ ኮሚዩኒስቱ ዓለም ጭልጥ ብላ ገብታ በነበረበት ጊዜ፣ በ1984 ዓ.ም ምእራብ-ዘመም (pro-west) በነበሩት የሱዳን መሪ ጃፋር አልኒሜሪ (Ja’afar al-Nimeiry) የሱዳንን የኤሌትሪክ ኃይል ችግርና የመስኖ ችግር እንዲያጠና ያሜሪካ ጠፍ-አቅኚ ቢሮ (US Bureau of Reclamation) ተጋብዞ ነበር። ይህ የአሜሪካ አጥኚ ቡድን ሱዳን ውስጥ ጥናት ሲያካሂድ፣ ቀደም ሲል (ከ1958 ዓ.ም እስከ 1963 ዓ.ም) ኢትዮጵያ ውስጥ ካጠናቸው ግድቦች አንዱን (ከሱዳን ድምበር 21 ኪሎ ሜትር እርቆ ኢትዮጵያ ውስጥ ተጠንቶ የነበረውን) ግድብ (Border Dam) ለኒሜሪ አንስቶላቸው ነበር።
የድምበር ግድብ (Border Dam) የተባለውን ሱዳን መጠቀም ብትችል፣ የካርቱምን፣ የዋዲመዳኔን፣ የአትበራን ከተሞች የኤሌትሪክ ኃይል ፍላጐት በቀላሉ ማሟላት እንደምትችል፣ የሮሲየርስን ግድብ (Roseires Dam) የውሀ ከፍታ መጨመር እንደምትችል፣ ከሶባት ወንዝ ጀምሮ በኢትዮጵያና በነጭ ዐባይ መካከል ያለውን የተንጣለለ ሰፊ የሱዳን መሬት እስከ አትበራ ድረስ ያለምንም ችግር ካመት እስካመት በመስኖ ልታለማ እንደምትችል የአሜሪካው አጥኚ ቡድን ለኒሜሪ ገልጾላቸዋል። የድምበር ግድብ (Border Dam) የተባለው፣ ሮሲየርስ ግድብ (Roseires Dam)፣ ስናር ግድብ (Sennar Dam) እና ካሽም-አል-ጊርባ ግድብ (Khashm al-Girba) የተባሉት ሦስት የሱዳን ግድቦች የሚይይዙትን የውሀ መጠን ባምስት እጥፍ እንደሚበልጥ አብራርቶላቸዋል። በዚያን ጊዜ (በ1984 ዓ.ም) ሱዳንና ኢትዮጵያ በምእራቡና በምስራቁ ጐራ የተለያዩና ጨርሶ እማይጣጣሙ ሀገሮች ስለነበሩ፣ የሱዳን ባለስልጣኖችና የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ባንድ ላይ ተወያይተው፣ የተጠናውን የድምበር ግድብ ገድበው፣ በጋራ ተጠቃሚ ለመሆን አልቻሉም/አልበቁም። የዐባይን ወንዝ አጠቃቀም በተመለከተ ሁልጊዜ ከግብጽ ጐን በመሰለፍ የምትታወቀው ሱዳን፣ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ ከግብጽ ተለይታ የሕዳሴ ግድብ ደጋፊ የሆነችበት ዓይነተኛ ምክንያት ይህንኑ (በ1984 ዓ.ም) ያመለጠ እድል ለመጠቀም ፈልጋ ይመስለኛል።
ይህ ግድብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀዘንና ሮሮ ሲያሰማበት በኖረው በዐባይ ተፋሰስ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረ ግድብ ነው። አቅም ከተገኘ ወይም ጊዜያዊ አቅም የሚሰጥ ተገን/ከለላ16 ከተገኘ፣ ኢትዮጵያዊያን ሊቀበሉትና ሊደግፉት የሚገባ ጅምር ይመስለኛል።
16 ተገን/ከለላ ያልኩት ባሁኑ ጊዜ የሚታየውን የምእራባዊያንን በተለይም የአሜሪካንና የኢትዮጵያን መልካም ግንኙነት በማየት ነው። የዐባይ ተፋሰስ ከ1958 ዓ.ም እስከ 1963 ዓ.ም በአሜሪካኖች የተጠናው፣ በገማል አብደል ናስር መሪነት ምስራቅ-ዘመም የነበረቺውን ግብጽን ለማስደንገጥ ተብሎ ነው። ከ1960ዎቹ አጋማሽ እስከ 1970ዎቹ ድረስ የፊንጫ-አማሪቲ የውሀ ኃይልና የመስኖ ጥናት ተግባራዊ የሆነው በአሜሪካኖች ተገንነትና ከለላነት ነው። በፊንጫ ግድብ ግብጽ ከፍተኛ ተቃውሞ አንስታ ነበር፣ ግን ባዶ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን ከአሜሪካ በከፊል የገንዘብ ድጋፍ ተገኝቶ፣ ምናልባት በአሜሪካ አግባቢነት ከዓለም ባንክም ብድር ተገኝቶ ግድቡ በ1972 ዓ.ም ሊጠናቀቅ ችሏል። የአዋሽ ሸለቆ ሁለ-ገብ ልማት የአሜሪካኖቹን የቴኒሲ ሸለቆ ልማት (Tennessee Valley Development) በሞዴልነት በመጠቀም፣ በአሜሪካ አማካሪዎች የተጀመረና የተካሄደ የልማት ስራ ነው።
ይህ ግድብ ለኢትዮጵያዊያ የኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ ያደርጋል በሚል እምነት የተጀመረ ግድብ ነው። ኢትዮጵያዊያንን ይጠቅማል ተብሎ የታሰበ የልማት ስራ ስለሆነ፣ ሀሳቡን በበጐ ዓይን ማየቱ የሚበጅ ይመስለኛል።
በዚህ ጽሑፍ ሰፋ አድርጌ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በዐባይ ተፋሰስ ላይ የሚጀመርን ፕሮጀክት የምትጠላ፣ የምትቃወምና የምታደናቅፍ ግብጽ ብቻ ናት። በዚሁ ተፋሰስ ላይ የተጀመረውን የልማት ፕሮጀክት (የሕዳሴን ግድብ) ብንቃወም፣ ተቃውሟችን የግብጽ አጋር እሚያደርገን ይመስለኛል።
ምንጊዜም አቅመ ደካሞች ነንና (ለአቅመ ደካማነታችንም ዋናዎቹ ተጠያቂዎች፣ ካለፈው ትውልድ ጭምር፣ ራሳችን ነን) በገንዘብ አቅም የተነሳም ሆነ በሌላ ምክንያት የግድቡ ስራ ሊጠናቀቅም ላይጠናቀቅም ይችላል። ፍጻሜውንና ወደፊት የሚሆነውን ማናችንም በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ሀሳቡና ጅምሩ ግን ለተራው ጦም-አዳሪ ኢትዮጵያዊ ለእለት ችግሩ አይደርስም እንጂ፣ በሀገር ደረጃ ረዘምና ሰፋ አድርጐ ለሚያስብ ሰው፣ ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ያቅም ግምባታ ጉዳይ ለሚያስብ ሰው፣ የግድቡ በጐ ጐን ጐልቶ እንደሚታየው እገምታለሁ።
በመግቢያዬ ላይ እንደገለጽኩት ዐባይን ጥቅም ላይ ማዋል የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲናፍቅ ኖሯልና፣ ለሕዳሴ ግድብ ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጥ አምናለሁ። ይህ እምነቴ እውነት ወይም ትክክል ከሆነ፣ የሕዳሴን ግድብ የምንቃወም ሁሉ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየንና የተገነጠልን እንሆናለን ማለት ነው። አንዳንድ የኢሕአዴግ ተቃዋሚ ፓለቲከኞች ሲናገሩ እንደምሰማው “ግድቡን ኢሕአዴግ የጀመረው በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን/ድጋፍን ለማትረፍ ነው” ይላሉ። ይህንን ጅምር ሕዝብ እንደሚወደው ተረድተዋል ማለት ነው።
የሕዳሴን ግድብ አንደግፍም ወይም እንቃወማለን ከሚሉ (በጽሑፍም ሆነ በገጽ ካጋጠሙኝ) ፖለቲከኞች መካከል፣ እስካሁን ድረስ አንድም አጥጋቢ የሆነ ፍሬ ነገር አላገኘሁም። ካጋጠሙኝ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።
7.1. የሕዳሴን አካባቢያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጽእኖ በሚመለከት፣
ግድቡ የሚያስከትለው አካባቢያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጽእኖ “በቂ ጥናት አልተደረገበትም” የሚል ትችት ይሰንዝራሉ። በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ ያካባቢ እንክብካቤ ጉዳይ (environmental conservation) አሳሳቢ ሁኖ አይቆጠርም ነበርና፣ ያሜሪካኖቹ የጥናት ቡድን፣ ግድቡ ባካባቢው ላይ የሚያስከትለውን ተጽእኖ በጥናቱ ውስጥ ሳያስገባው ቢቀር አያስደንቅም። ባሁኑ ጊዜ ግን እንኳን ይህን ያህል የብዙ ቢሊዮን ዶላር ትልቅ ፕሮጀክት፣ የትኛውም ዓይነት አንስተኛ ፕሮጀክት ሲሰራ ባካባቢውና በነዋሪው ሕዝብ ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ ሳይጠና አይጀመርም። ይህን ያህል ግዙፍ ግድብ ሲገደብ በነዋሪው ሕዝብ፣ በእጽዋቱና በእንስሳቱ፣ እንዲሁም በተፈጥሮ መኖሪያቸው ላይ ለውጥ እንደሚያስከትል የሚያጠያይቅ አይደለም። ግን ግድቡ ያስገኛል ተብሎ ከታሰበው ጥቅምና ከሚያስከትለው ጉዳት የትኛው ይበልጣል? ይህን ዓይነቱን ጥያቄ ለመመለስ ነው፣ ግድብ ሲታሰብ ከሚጠኑት ብዙ ጥናቶች መካከል አንዱ የሆነው “cost-benefit analyses” የሚባለው ጥናት የሚካሄደው።
ይህ ግድብ በተጀመረበት አካባቢ ይከሰታል ተብሎ የተፈራውን ያካባቢ ቀውስ የግድቡ ተቃዋሚዎች ተጨባጭ በሆነ መልክ ቢገልጹልን ኖሮ ሁላችንም ትምህርት እናገኝበት ነበር። ግድቡም ይቅርብን ለማለት ያስችለን ነበር። ግን አልገለጹልንም።
ይህ ግድብ የተጀመረው በቤኒ-ሻንጉል-ጉሙዝ ክልል፣ በድሮው አጠራር በመተከል አውራጃ ውስጥ ነው። የቤኒ-ሻንጉል-ጉሙዝ ክልል የሕዝብ ብዛት ባማካይ በየኪሎ ሜትር ካሬው ከ10 እስከ 13 ሰው የሚገኝበት ነው። ተራርቆና ተበታትኖ የሚኖር ሕዝብ ነው። ወደ መተከል ደርግ አዝምቷችሁ የነበራችሁ ሁሉ ያካባቢው አጠቃላይ ስዕል እስካሁን ባእምሯችሁ ውስጥ እንደተቀረጸ ይገኝ ይሆናል ብየ እገምታለሁ። ምን ያህል መንደር አይታችኋል? እያንዳንዱ ያያችሁት መንደር ምን ያህል ሕዝብ የሚኖርበት ነበር? መንደሮቹ ምን ያህል ይራራቁ ነበር? የሕዳሴ ግድብ ይሰራበታል የሚባለው አጠቃላይ ገጽታው እናንተ በዐይናችሁ ካያችሁት የተለየ አይደለም።
ያ ያያችሁት ደልዳላ መሬት እስከ ሱዳን ነጭ ዐባይ፣ ካርቱም ድረስ የሚደርስ ሰፊ ደልዳላ መሬት ነው። የቤኒ-ሻንጉል-ጉሙዝ ሕዝብ ባመዛኙ አዳኝና ከብት አርቢ በመሆኑ፣ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወር ነው። መንደሩም ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኛው ጊዜያዊ ነው። እንደ ደገኛው ሕዝብ ጠንካራና እድሜያማ ቤት አይሰራም። ስለዚህ በግድቡ የተነሳ ከቀየው/ከመንደሩ የሚፈናቀለው የሰው ቁጥር ብዙ አይሆንም።
በተፈናቃዩ ሕዝብ ላይ ይደርሳል ተብሎ የሚገመተው ጉዳትና ግድቡ ለሀገር ያስገኛል ተብሎ የታመነበትን ጥቅም አነጻጽሮ ማየት ያስፈልጋል። ያም ሆነ ይህ የከብት ማሰማሪያ መሬቱና የአደን መሬቱ ግድቡ በሚፈጥረው ሀይቅ ስለሚዋጥበት፣ የለመደው የአኗኗር ዘይቤ መዛባቱ የማይቀር ነውና ላካባቢው ሕዝብ ተገቢው ካሳ ሊከፈለው ይገባል። በግድቡ የሚነካው ሕዝብ ብዛት ስለማይኖረው፣ የሚከፈለው ካሳ ካቅም በላይ የሚሆን አይመስለኝም። በሕዝብ መፈናቀል ሰበብ ግድቡን ከመቃወም ይልቅ፣ ለነዚህ በግድቡ የተነሳ ኑሯቸው ለሚዛባባቸው ሰዎች መንግሥት ተገቢውን ካሳ መክፈል አለመክፈሉን መከታተልና በተፈናቃዮቹ ጐን መሰለፍ ያስፈልጋል።
የተፈጥሮ ሚዛንን በመለወጥ በኩል፣ ግድቡ የሚፈጥረው ባሕር በቅርብ የሚገኘውን የባሕሩን አካባቢ የማቀዝቀዝ ጸባይ ይኖረዋል። ሙቀት የለመዱ እጽዋትና እንስሳት (አዲሱን አካባቢ የመቋቋም ችሎታ ካልኖራቸው በስተቀር) ግድቡ
ከሚያቀዘቅዘው አካባቢ ይጠፉና/ይሸሹና አዲሱን የአየር ንብረት የሚወዱ ሌሎች እጽዋትና እንስሳት ይተኩ ይሆናል። ይህ ግን ከቁጥር የማይገባ ጥቃቅን ለውጥ ነው። ግድቡ በተፈጥሮ ሚዛን ላይ የሚያስከትለው አስጊ ተጽእኖ ቢኖርማ ኑሮ ከኢትዮጵያ ይልቅ ስጋት ላይ የምትወድቀው፣ ከግድቡ በታች ሰፋፊ የመስኖ እርሻ መሬት እያለማች የምትኖረውና በርካታ ከብት አርቢ ሕዝብ ያላት ሱዳን ነበረች። ሱዳን ግን ከግድቡ የምታገኘውን ጥቅምና ጉዳት አመዛዝና ግድቡን ደግፋለች።
7.2. የግድቡን ትልቅነት በሚመለከት የሚቀርቡ ተቃውሞዎች
የሕዳሴን ግድብ ከሚቃወሙ ፓለቲከኞች የምሰማው ሌላው ነቀፋ፣ “ግድቡ ትልቅ ነው፣ በአፍሪካ የተገደቡ ትልልቅ ግድቦች ለተራው ሕዝብ አልጠቀሙም። ይህ ትልቅ ግድብም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጠቀሜታ አይኖረውም። ለኢሕአዴግ ስም መጠሪያ ብቻ የሚሆን ነው” የሚል ነው። ይህ አባባል ታላላቅ ግድቦች የሚወቀሱበትን ምክንያት በደምብ ሳያጤኑ የሚሰነዘር የጅምላ አባባል ሆነ እንጂ እውነትነት አለው። አባባላቸውንም ባንዳንድ ማስረጃዎች መደገፍ ይችላሉ። ትክክለኛው የአፍሪካ ታላላቅ ግድቦች ታሪክ ባጭሩ የሚከተለውን ይመስላል።
አንዳንድ የሕዳሴ ግድብ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት ሁሉ፣ በአፍሪካ ውስጥ የታላላቅ ግድቦች ታሪክ አብዛኛው አኩሪ አይደለም። በ1950ዎቹ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጠናቀቀበትና አሜሪካ የምእራባዊው ዓለም መሪ ሁና የወጣችበት ዘመን ነበር። ያ ዘመን (ከ1950ዎቹ እስከ 1960ዎቹ) ባልሳሳት ፓርቱጋል ከገዛቻቸው ከሞዛምቢክና ከአንጐላ በስተቀር፣ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገሮች ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጡበት ዘመን ነበር። እነዚህን ነፃ የወጡ ሀገሮች በጐናቸው ለማሰለፍ (to bring them under their sphere of influence) የምስራቁ ዓለም (በተለይም ሶቪየት ዩኒዬን) እና የምእራቡ ዓለም (በአሜሪካ መሪነት) የሚፎካከሩበት፣ ቀዝቃዛው ጦርነት የተጧጧፈበት ዘመን ነበር።
በዚህ የምስራቁ ዓለምና የምእራቡ ዓለም ውድድር ወይም በቀዝቃዛው ጦርነት የተነሳ፣ ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡት ሀገሮች ገንዘብ እንደልብ ይፈ(ስ)ስላቸው ነበር። ያንን (በእርዳታም በብድርም) እንደልብ ያገኙት የነበረውን የማባበያ ገንዘብ፣ የመስኖ እርሻን በማስፋፋት ርሀብንና ድህነትን እናጠፋበታለን በሚል ትልልቅ ግድብ ለመገደብ ቆርጠው ተነሱ። ከ1950ዎቹ እስከ 1960ዎቹ ድረስ ይገደቡ የነበሩት ታላላቅ ግድቦች “አረንጓዴው አቢዮት” (Green Revolution) በመባል የሚታወቀው እንቅስቃሴ አካል ናቸው። ከእርሻው መስክ በተጨማሪ ለፋብሪካዎች ማንቀሳቀሻ ፔትሮሊየም በውድ ከመግዛት ይልቅ፣ ግድቦቹ በሚያመነጩት ርካሽ የውሀ ኃይል (hydro-electric power) ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት ይቻላል የሚል እምነት ነበር።
እነዚያ ታላላቅ ግድቦች ሲገደቡ ብዙ ሕዝብ ከሰፈረበት መንደር ተፈናቅሏል17። የተራ ገበሬዎች እርሻዎች በግድቡ ውሀ ተውጠዋል/ተጥለቅልቀዋል። የተፈናቀለው ሕዝብ ካሳ ተቀብሎ እንዲሰፍርበት በተሰጠው አዲስ አካባቢ ሊለምድ ባለመቻሉ ከመቶ ሃምሳ እጁ (50%) ያህል ወደ ከተማ እየተሰደደ ባዝኖ ቀርቷል። በግድቡ አካባቢ እንዲሰፍር የተደረገውም ሕዝብ የሰፋፊዎቹ የመስኖ እርሻዎች የቀን ወዛደር ሁኗል።
ታዲያ ተራው ሕዝብ ያን ያህል ከፍተኛ ዋጋ/መስዋእትነት ከከፈለ በኋላ፣ የመስኖው እርሻ በተራው ገበሬ የማይታረስ፣ ለጥቃቅን እርሻዎች የማይመች ሆነ። የተንጣለለ ሰፊ መሬት ሊያርሱ የሚችሉ ቱጃር ግለሰቦች፣ ቡድኖች ወይም ኩባንያዎች ብቻ በዘመናዊ መሳሪያ የሚያርሱት ሆነ። ያም አልበቃ ብሎ (ለሀገር ውስጥ የምግብ እህል ማምረቱ ለቱጃሮቹ ብዙ ትርፍ ስለማያስገኝላቸው) ወደውጭ የሚላኩ ምርቶች (export crops) የሚመረቱበት፣ የተራውን ሕዝብ ርሀብና ችግር የማይቀርፍ ሆነ። የሕዝቡን ርሀብና ችግር ለማስወገድ የታቀደው የታላላቅ ግድብ ፕሮጀክት ዓላማውን ሳተ። ሕዝቡ ከድህነትና ከጦም አዳሪነት ሳይላቀቅ ቀረ። ከዚህም በተጨማሪ ሰፊ የመስኖ እርሻ ሊያካሂዱ የሚችሉ ሀብታም አፍሪካዊያን ጥቂት ስለነበሩ፣ አብዛኛው ሰፋፊ የመስኖ እርሻ የውጭ ቱጃሮችና ኩባንያዎች መዋእለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ የሚያካሂዱትና የሚጠቀሙበት የእጅ-አዙር ቅኝ አገዛዝ የሚንጸባረቅበት ሆነ።
ከታላላቆቹ ግድቦች በርካሽ ይገኛል የተባለውም (ከውሀ የሚመነጭ) የኤሌትሪክ ኃይል በከተሞች ለሚገኙ (ባመዛኙ) በውጭ ዜጐች ለተያዙ ፋብሪካዎች መጠቀሚያ ሆነ። አፍሪካዊያን እነዚያን ግድቦች በመስኖም ሆነ በኢንዱስትሪ ልማት ለመጠቀም (በገንዘብ፣ በዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ወ.ዘ.ተ.) ዝግጁ ስላልነበሩ ግድቦቹ የጥቂት ሀብታሞችና የውጭ ዜጐች መጠቀሚያ ሆኑ።
ያም ሆኖ ግን እነዚያ ግድቦች ለተራው ዜጋ አልጠቀሙም እንጂ፣ ለመንግሥት በሚያስገቡት ግብርና ቀረጥ ለአጠቃላይ የሀገር ገቢ አስተዋጽኦ አላደረጉም አይባልም። በጋና(አኮሶምቦ ግድብ)፣ በናይጀሪያ(ካይንጂ ግድብ)፣ በኮንጐ(ኢንጋ ግድብ)፣ በዚምባቡዬና በዛምቢያ (ካሪባ ግድብ) እስካሁን ድረስ በመብራትና በኃይል አመንጭነት፣ በፋብሪካና በመጠጥ ውሀ አቅርቦት፣ በመስኖ አገልግሎት፣ በአሳ ማጥመጃነትና በመጓጓዣነት ለየሀገራቸው ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጡ ነው። እሚወቀሱበት ምክንያት መጀመሪያ የታቀዱበትን (የሕዝቡን ድህነት የመቅረፍ) ዓላማ በመሳታቸው ነው። ስለዚህ ነው
17 አንዳንድ ምሳሌዎችን ለመጥቀስ ያህል፣ ጋና ውስጥ በአኮሶምቦ ግድብ የተነሳ 80 ሺህ ሕዝብ ተፈናቅሎ ሌላ አካባቢ እንዲሰፍር ተደርጓል። ናይጀሪያ ውስጥ ካይንጂ ግድብ ሲገደብ 50 ሺህ ሕዝብ ተፈናቅሎ ወደሌላ ቦታ እንዲሰፍር ተደርጓል። ዛምቢያና ዚምባቡዬ ውስጥ ዛምቤዚ ወንዝ ላይ ካሪባ ግድብ ሲገደብ 57 ሺህ ሕዝብ ተፈናቅሎ ሌላ አካባቢ እንዲሰፍር ተደርጓል።
እነዚያ ታላላቅ ግድቦች የታሰበላቸውን (ሕዝብን ከድህነት የማላቀቅ) ግብ የሳቱ፣ የሀገር መሪዎች ስም መጠሪያ ብቻ ሁነው የቀሩ ናቸው እየተባሉ ሲተቹ እሚኖሩት።
የሕዳሴ ግድብ ግን ትልቅ ከመሆኑ በስተቀር ለየት ላለ ዓላማ የታቀደ ግድብ ነው። የግድቡ ዓላማ በመስኖ አርሶ የሕዝቡን የምግብ ፍላጐት ለማርካት ሳይሆን፣ የውሀ ኤሌትሪክ ኃይል አመንጭቶ፣ ኃይሉን ለሌሎች ሀገሮች ሽጦ ለሀገር ገቢ ለማስገኘት ነው። የሕዳሴ ግድብ የተራውን ሕዝብ ያጭር ጊዜ (የምግብ) ችግር ለመፍታት እንዳልተወጠነ በግልጽ የተነገረና የታወቀ ነው። ጥቅሙ (ወደፊት) ለሀገር በሚያስገኘው ገቢ የሚለካ ነው የሚሆነው።
የሕዳሴ ግድብ ገቢ አስገኝቶ የሀገራችን አቅም (ኢኮኖሚይዊ፣ ወታደራዊ፣ የተማረና የሰለጠነ የሰው ኃይል) ለመገንባት የሚጠቅም ከሆነ፣ ትልቅ በመሆኑ ብቻ ልንቃወመው አይገባም። በትልቅነት ብቻ ግድብን የምንቃወም ከሆነማ ለግብጾች ሁለንተናቸው የሆነውን የአስዋን ግድብም መቃወም ሊኖርብን ነው ማለት ነው። አናቶሊያ የተሰኘው በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከሚደነቁት ታላላቅ ግድቦች አንዱ የሆነው የቱርኮች ግድብም መወገዝ አለበት ማለት ነው። ታላላቅ ግድቦች ጠቃሚ በመሆናቸው እስካሁን በመሰራት ላይ ናቸው። የቻይናዎቹን ታላቅ ግድብ (the Three Gorges Dam) እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።
አንዳንድ ተቺዎች፣ ብዙ ቢሊዮን ብር አውጥቶ አንድ ትልቅ ግድብ ከመስራት ይልቅ፣ በዚያው ገንዘብ ከተለያየ ቦታ ላይ አንስተኛ የሆኑ ግድቦች ቢገደቡ ይሻላል፣ ‘ለሕዝብም የሚጠቅሙት አንስተኞቹ ግድቦች ናቸው’ ይላሉ። ይህ አባባል የመነጨው ከላይ የጠቃቀስኳቸው ታላላቅ ግድቦች የተገደቡበትን (የሕዝቡን ርሀብና ችግር የመፍታት) ኢላማ በመሳታቸው ነው። “ትልልቁ ግድብ ለሕዝቡ ችግር መፍትሄ ካልሰጠ፣ መለስተኛና አንስተኛ ግድቦች ይገደቡና ይሞከሩ” ከሚል አስተሳሰብ የመነጨ ነው። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ግለሰቦች ተጨባጭ ማስረጃ ሳይኖራቸው “ለሕዝብ የሚጠቅሙት መለስተኞቹና አንስተኞቹ ግድቦች ናቸው” በማለት የትልልቅ ግድብ ተቃዋሚ ይሆናሉ።
ግድቦች መለስተኞችና ትንንሾች ስለሆኑ ብቻ ለሕዝብ ይጠቅማሉ ማለት ስህተት ነው። በነፊንጫ፣ በነመልካ ዋከና፣ በነቆቃ የትኛው ሕዝብ ሲጠቀም አይታችኋል? በነዚህ መለስተኛ ግድቦች የተነሳ ችግሩ የተቀረፈለት የትኛው ተራ ኢትዮጵያዊ ነው? እኔ እማውቀው በተቃራኒው ነው። ከ1960 ዓ.ም እስከ 1971 ዓ.ም ድረስ በየተራ በተሰሩት በቆቃ፣ በአዋሽ ሁለትና በአዋሽ ሦስት ግድቦች በሚካሄደው የመስኖ ልማት የተነሳ የአርሲ ኢቱ ከብት አርቢዎች የከብት ማሰማሪያቸው ተወስዶባቸው ተስድደዋል (ካካባቢው ጠፍተዋል)። የአፋርና ኢሳ ከብት አርቢዎች በተንዳሆ የልማት ስራ የተነሳ የግጦሽ መሬታቸውን አጥተዋል። ያውም ያለካሳ።
እነዚህ መለስተኛ ግድቦች በተራው ሕዝብ ላይ ያስከተሉት ችግር መጠኑ ከማነሱ በስተቀር፣ በአፈናቃይነታቸውና ባካባቢያዊ ተጽእኗቸው ከታላላቆቹ ግድቦች በምን ይለያሉ? ስለዚህ ትንንሾቹ ግድቦችም ቢሆኑ ካንዳንድ መሠረታዊ ለውጦች ጋር የተቀናጁ ካልሆኑ በስተቀር ለተራው ሕዝብ እርባና የላቸውም። አይጠቅሙም። ለተራው ሕዝብ አልጠቀሙም ተብሎ ግን ባጠቃላይ ለሀገር የሚሰጡት አገልግሎት ሊካድ አይችልም። እነዚህ መለስተኛ ግድቦች የሚሰጡትን ጥቅም ስለምታውቁት ከኔ መስማቱ እሚያስፈልጋችሁ አይመስለኝም። ስለዚህ ባጭር ጊዜ የተራውን ሕዝብ አለመጠቀም ምክንያት አድርገን የሕዳሴን ግድብ በትልቅነቱ ብቻ ልንቃወመው አይገባም እላለሁ።
ይህ ግዙፍ ግድብ የግብጽን ዓይን ይስባል፣ ስለዚህ መለስተኛና አንስተኛ ግድቦች ቢሰሩ ይሻላል የሚሉ ካሉ፣ ግብጽ ግድቡን የምትቃወመው በትልቅነቱ አለመሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል። ግድቦቹ አንስተኛም ቢሆኑ በዐባይ ተፋሰስ ውስጥ የሚገደቡ እሰከሆኑ ድረስ ግብጽ ከመቃወም አትታቀብም። ግብጽ በዐባይ ተፋሰስ ላይ ምንም ዓይነት ልማት አትፈቅድም። ቀደም ብዬ እንደ ገለጽኩላችሁ አቶ መለስ በ1993 ዓ.ም ከግብጽ ጋር የወዳጅነት ውል ተፈራርሜያለሁ ብለው፣ በ1996 ዓ.ም በተከዜና በዐባይ ተፋሰስ ለማሰፍረው ሰፋሪ ወደ 3,333 ሄክታር መሬት በመስኖ እንዳለማ እወቁልኝ ሲሏቸው፣ ተጨማሪ መረጃና ተጨማሪ ጥናት እየጠየቁ ፈቃደኝነታቸውን ሳይገልጹ ቀርተዋል። ከዚህ ያነሰ ፕሮጀክት ምን አለ?
7.3. ታላላቅ ግድቦች የመሪዎች ስም መጠሪያ ስለመሆናቸው፣
ታላላቅ ግድቦች የመሪዎች መጠሪያ ናቸው የሚለው ትክክል ነው። የሕዳሴ ግድብ የአቶ መለስ ወይም የኢሕአዴግ መጠሪያ ሆነ አልሆነ በኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር ላይ እሚጨምረውም እሚቀንሰውም ነገር የለም። አንድ መንግስት አንድ ትልቅ ስራ ሲሰራ፣ ስራው መጠሪያው እንደሚሆን እሙን ነው። ኢሕአዴግ ስሙን እሚያስጠራበት ስራ አልገደደውም።
 ኢትዮጵያን በር-አልባ አድርጓልና ሲጠራበት ይኖራል።
 የልማት ስራን (መንገድን፣ ሕንጻን) በተመለከተ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከጣሊያን ቀጥሎ ተወዳዳሪ የለውምና ሲጠራበት ይኖራል።
 ኢትዮጵያን በቋንቋና በጐሳ አስተዳደር ለያይቶ የገዛ ነውና ሲጠራበት ይኖራል።
 ሕዳሴንም ከገደበ ስራው ነውና ሲጠራበት ይኖራል።
ስራ የሰሪው መጠሪያ ነውና አዲስ ሊሆንብን አይገባም።
8. ማጠቃለያ
በዚህ ጽሑፍ ለማሳየት የሞከርኩት በዐባይ ተፋሰስ ውስጥ በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት እንደልብ ሁኖ ሳለ በአቅመ-ደካማነታችን የተነሳ ልንጠቀምበት አለመቻላችን ነው። ከኛ ተነስቶ በሚሄደው ውሀ ግብጽ በብዙ ሚሊዮን ሄክታር የሚሰፈር መሬት በመስኖ እያለማች የምግብ ፍላጐቷን ስታሟላ፣ እኛ በትንሹ እንኳን እንዳንጠቀም መከልከላችን ጥቃት ሁኖ ይሰማኛል። በጽሑፌ ውስጥ እንዳሳየሁት ስንትና ስንት የልማት ጥናቶች ተጠንተው በተግባር ሳይተረጐሙ መክነው መቅረታቸው፣ የአቅመ-ደካማነታችን፣ የተጠቂነታችን ግዙፍ ማስረጃዎች ናቸው። መሬት ጾሙን እያደረ የእርሻ መሬት የገደደው፣ በመስኖ ጥሩ ምርት ማምረት ሲችል በድርቅ የሚጠቃ፣ መጥገብ ሲገባው የሚራብ፣ እንደ ዐባይ ተፋሰስ ሕዝብ ያለ የለም። ይህ ያሳዝናል።
የውሀ አጠቃቀም ከተፋሰስ በላይ ወይም በታች በኩል በመገኘት አይደለም። በደጋ ወይም በቆላ በመገኘት አይደለም። በጽሁፌ ደጋግሜ እንዳሳየሁት የውሀ አጠቃቀም ከአቅም ወይም ከኃይል ሚዛን ጋር የሚሄድ ነው። ስለዚህ የዐባይን ውሀ ለመጠቀም ከፈለግን የዘለቄታው መፍትሄ (ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊና የተማረ-የሰለጠነ የሰው ኃይል) አቅማችን መገንባትና ከባላጋራዎቻችን ጋር አቻ ሁነን መገኘት ነው። ዓለም አቀፍ ያገር-አቋራጭ ወንዞች አጠቃቀም ሕግጋት ሊረዱን/ሊደግፉን የሚችሉት አቅም/ኃይል/ጡንቻ ለማሳየት ስንችል ብቻ ነው። በየትኛውም መድረክ እየተገኘን ያለ የሌለ ተቃውሞ ብናሰማ ያላቅም አድማጭ አይኖረንም። ዐባይን ያላቅም ልንጠቀምበት አንችልም።
በዐባይ ተፋሰስ ውስጥ የሚወጠን የልማት ውጥን፣ ትርፍና ኪሳራ፣ ጥቅምና ጉዳት የሚሰላበት ብቻ ሳይሆን፣ የጥቃት መወጫና የመብት ማረጋገጫ ሁኖ መታየት ያለበት ይመስለኛል። ስለዚህም ነው በዐባይ ተፋሰስ ውስጥ የተጀመረውን “ሕዳሴን” የምደግፈው። የሕዳሴ ጥቅም ገና ወደፊት የሚታይ ይሆናል። የጥቃት መወጫና የመብት ማስከበሪያ ምልክትነቱን ግን እወደዋለሁ።
ዐባይ ከጭቃና ከፖለቲካ አይጠራም። ዐባይ ከፖለቲካ እማይጠራ መሆኑ የሚታመንበት ከሆነ፣ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አቋሟን ማጠናከር ይኖርባታል። በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ መድረኮች የሚወክሏት፣ የሚከራከሩላት፣ እንደ ግብጾች ተደማጭነትና ክብደት ያላቸው ፖለቲከኞች/ዲፕሎማቶች ያስፈልጓታል። እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ ሰዎች ለማፍራት አሁንም የኢኮኖሚ ጥንካሬ/አቅም ወሳኝ ነው። በደካማ ኢኮኖሚ የነጠረና ልምድ ያካበተ የሰው ኃይል ማፍራት አይቻልም።
የሕዳሴ ግድብ መነጋገሪያ ከሆነ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ በተለያዩ የሕዝብ መገናኛ ዘዴዎች አልፎ አልፎ እንደዋዛ የሚሰነዘሩ አነጋገሮች ይሰማሉ። እነዚህ አነጋገሮች፣ አንደኛው “ውሀው እሚያመነጨው የኤሌትሪክ ኃይል ለኢትዮጵያ፣ ውሀው ለግብጽ” የሚል ነው። ሁለተኛው ደግሞ “ኢትዮጵያ የዐባይ ወንዝ ባለመብትነቴ ይከበርልኝ ስትል፣ በወንዙ ላይ አንድ ወይም ሁለት ግድብ ልገድብ ማለቷ ነው” የሚል ነው። ይህ ወጥመድ ውስጥ እሚያስገባ አባባል ስለሆነ፣ ከወዲሁ መጠንቀቅ ይገባል። ኢትዮጵያ ከውሀ የሚመነጭ ኃይል ብቻ ሳይሆን፣ ለመስኖ ልማት የሚውል ከዐባይ የውሀ ድርሻ እንዲኖራት ትፈልጋለችና ይህን ግልጽ አድርጐ በሚገኘው መድረክ ሁሉ ማሳወቅ የሚጠቅም ይመስለኛል።
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
አንባቢዎች፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ያሉ መረጃዎች ሁሉ የተወሰዱት ከሚከተለው መጽሐፍ ነው። ዐባይን በሚመለከት ብዙ ቁምነገሮችን ያካተተ መጽሐፍ ነው። ጽሐፊው ግብጽ ውስጥ ብዙ የቆዩ፣ ካይሮ ዩኒቨርሲቲ ያስተማሩ፣ የተፋሰሱን ሀገሮች ተዘዋውረው ያዩና ባለስልጣኖችን ያነጋገሩ አሜሪካዊ ናቸው። አንብቡት።
John Waterbury (2002) The Nile Basin: National Determinants of Collective Action; Yale University Press, London.
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com – May 23, 2014