ግልጽ ደብዳቤ
ጥቅምት 17, 2008 / November 28, 2015
የገላጋይ ቤተሰብ
ዴንበር፡
ኮሎራዶ
ሳን ሆዜ፡ ካሊፎርኒያ
ለአርበኞች ግንቦት ሰባት መሪዎች
ለኢሳት ተሌቪዥን አዘጋጅዎች
ግልባጭ: ለተለያዩ የሚድያ ሴነተሮች
ጉዳዩ። የተወገዘ ወንጀለኛ፡ የነጻነት አርበኛ አይሆንም
ሰሞኑን በአርበኞች ግንቦት ሰባት መሪዎችና የኢሳት ተሌቪዢን አዘጋጆች በኩል አምሳሉ ተሾመ የተባለ የተወገዘ ወንጀለኛ
ግለሰብ በተመለከተ የተሳሳተ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ሲሰራጭ ሰንብቶአል። ይህ ዜና ከአርበኞች ግንቦት ሰባት እና ከኢሳት
አልፎ በማህበራዊ ድረ-ገጾችም ላይ በስፋት ሲሰራች ሰንብቷል። ማን ያውራ የነበረ፡ ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ፡ ይህን
ወንጀል አደግ ግለሰብ በቀጥታ የምናወቀው ውድ ሀገራችን ለማየት ከአሜሪካ በሄድንበት ወቅት መንገድ ጠብቆ፡ ተወዳጅ
አባታችንን በግፍ የተገደለብን፡ በአፈሙዝ በሰደፍ የተደበድብን የተዘርፍን፡ እንዲሁን 10 አመት ህጻን እያስለቀሱ ከአያቷ
አስከሬን አጠገብ የዘረፈ ስለሆነ፡ ይህን ወንጀለኛ ስለዚህ ገልሰብ የምናውቀውን እውነት ለወገኖቻችን ማካፈል
እንፈልጋለን።
በፈርንጆች አቆጣጠር በ1995 አ/ም አራት ሆነን ቤተሰብ ለመጠይቅ ወደ ኢትዮጳያ ጉዞ ጀመርን። እስከ ባህር ዳር
በአይሮፕላን ሄደን ወደ ጎንደር ደግሞ ሀገር ማየት እንድንችል፡ በመኪና ለመሄድ ታቀደ። አባታችን ልጆቻቸውንና 10 አመት
የልጅ ልጃቸውን ለመቀበል መኪና ተከራይተው ባህር ዳር ጠበቁን። ከኛ ቤተሰብ ተጨማሪ ሌሎች ሰዎች ስለነበሩ
የተከራዩልን መኪና ሰፋ ያለ ነበርና ሰባት ራሳችን ተሳፍረን ወደ ጎንደር ማምራት ጀመርን። አባታችን ከፊት ለፊት የልጅ
ልጃቸውን አቅፈው የቦታዎን ስም እየነገሩን እኛም የሀገራችንን ውበት በጉጉት እያየን በጎዞ ላይ እንዳለን፡ ጨለማን ተገን
አድርገው፡ ሳይታሰብ በኢራቅና ሶሪያ እንደምናያቸው አሸባሪዎች ፊታቸው የተሸፈኑ አራት የታጠቁ ወታደሮች እጅግ
በሚያስፈራ ድምጽ መኪናው እንዲቆመ አዘዙ። መኪናው ድንገት ቆመ። ድንገት ያላሰብነው ስለነበር ሁላችንም ተደናገጥን።
አባታችንም ወደ እኛ ዞር ብለው አይዟችሁ አሉንና ወደ ሽፍቶቹ ወጣ ብለው ምነው ደግሞ አገራችን ላይ ልትዘርፉን ነው
እንዴ? እኔ ደማሴ ገላጋይ ነኛ። እነዚህም የኔ ልጆች ናቸው በማለት ለወታደሮቹ ከተናገሩ በኋ ወደኛ ዘውር ብለው
እግራቸውን ይዛ የምታለቅሰውን የልጅ ልጃቸውን አይዦሽ እያሉ ለመከላከል ወጣ ብለው መነጋገር ሲጀምሩ በጭካኔ
ከፊታቸን በጥይት ገደሏቸው። ሁላችንም በያለንበት በደንጋጤ ወድቀን፡ ተራችንን ስንጠብቅ እንደ አበደ ውሻ እየተራወጡ
በአሙዝና በሰደፍ እያጋጩ የያዝነውን ንብረት ሁሉ ከተለበሰ ጫማ እስከ ህጻን ዳይፐር ለቃቅመው ዘርፈው ወሰዱ። ከነዚህ
ሰዎች አንዱ የሰሞኑ “አርበኛ” ነበር። ታዲያ የጻነት አርበኛ እንደዚህ ነው እንዴ?
በቤተሰባችን ላይ በደረሰው አደጋ በጥልቅ ያዘውነው የጎንደር ህዝብ ዳር እስከዳር ተንቀሳቅሶ ወንጀለኞችን መከታተል
ጀመረ። እነዚህ ወንጀለኞች ከኛ የዘረፉትን ሀብት እየተከፋፈሉ፡ በውስኪ እየተሳከሩ አንታወቅም ብለው ሲንቀሳቀሱ
በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ ሴራው ተጋለጠና የአባትችን አስክሬን አፈር ሳይለብስ ወንጀለኞች አምበል የነበረው መሀል ጎንደር
ከተማ ላይ ተገደለ። የሰሞኑ “አርበኛ” ደግሞ ለማምለጥ ሲሞክር ወጣትና ሴቶች ነብሰ ገዳይ ነብሰ ገዳይ እያሉ እያራወጡ
ይዘው ከወንጀል ግብረ አበሩ ጋር ለፍርድ ቀርበው ወንጀላቸውን አምነው ተፈርዶባቸው ነበር። እንደነዚህ አይነት የተደራጁ
ወንጀለኛ ቡድኖች አማካኝነት በጎንደር ከተማና በምዕራብ ጎንደር ገጠሮች ከፍተኛ የወንጀል መስፋፋት በርክቶአል።
ባለንብረቶችን በሌሊት መዝረፍ፡ ሴተኛ አዳሪዎችን ማስገደድ፡ በተንቀሳቃሽ መኪናዎች ላይ አደጋ መጣል፡ ህጻናትን ጠልፎ
ገንዘብ መጠየቅ። የሚያሳዝነው ግን ይህ ወንጀለኛ ለፈጸመው ወንጀል ተመጣጣኝ ቅጣት ሳይገኝ፡ እንደገና መሳሪያ ታጥቆ
ወንጀል በሰራበት፡ ደም ባፈሰሰበት፡ ንብረት በዘረፍት፡ ቤተሰብ ባስለቀሰበት ከተማ ታጥቆ ሌላ ሽብር፡ ሌላ ነብስ ግዲያ
ለመፈጽም እድል ማግኘቱ ነው።
በተለይም ደግሞ፡ አርበኞች ግንቦት ሰባትና የኢሳት አዘጋጅዎች እንደነዚህ አይነት በወገን ላይ ኢሰባዊ ወንጀል የፈጽሙ
ግለሰቦችና የተወገዙ ወንጀለኞችን “አርበኞች” የሚል ስያሜ ለጥፎ የሚያስራጩት ፕሮፖጋንዳ ለህብረተሰባችን አደገኛ ነው
እንላለን። ለጊዝያዊ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ወንጀለኞችን ማሞገስ፡ ለነጻነት የሚካሄደውን ትግልም ሆነ ነጻ ሚዲያ
ለመገባት ለሚካሂደው ጥረት አይበጀም። ስለዚህ፡ የአርበኞች ግንቦት ሰባት መሪዎችና የኢሳት ቴሌቪዢን አዘጋጅዎች፡
ማሳሰቢያችንን ተገቢ ትኩረት ሰጥተው ግምገማና ማስተካከያ እንዲያደርጉ እናሳስባለን።
የገላጋይ ቤተሰብ
ዴንበር፡
ኮሎራዶ
ሳን ሆዜ፡ ካሊፎርኒያ
No comments:
Post a Comment