እንደ - መግቢያ
በኢትዮጵያ ታሪክ አፃፃፍ ላይ ብዙ ልዩነቶች ይስተዋላሉ፡፡
የልዩነቶቹ ሥረ- ምክንያት እንደ ጸሐፊው ማንነትና የሥርዓታቱን
ባህሪ መነሻ ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ የኢትዮጵያን የቀደመ ታሪክ
የሚቃኙ የተለያዩ ኃይለ-ሐሳቦች በየጊዜዉ እንዲጸባረቁ ግድ ብሏል፡፡
የታሪክ ትንቅንቁ በአጥቂነትና በተከላካይነት የሚበየን ነው፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ ፍልሰት ፣ መስፋፋት፣ ብሔራዊ ጭቆና ፣
ቅኝ ግዛትና መሰል ቃላት ላለፉት አርባ ዓመታት ፤ በተለየ መልኩ
ደግሞ ላለፉት ሃያ አራት ዓመታት የታሪክ ሙግት አጀንዳ አስቀማጭ
ቃላት ሆነዋል፡፡ ባሳለፍነው የሩብ ክፍለ ዘመን ጉዟችን የታሪክ ጉዳይ
እጅግ አብሰልሳይና ውርክብ የበዛበት ሊሆን የቻለው አገዛዙ ለኢትዮጵያ የቀደመ ታሪክ
በጎ እይታ የሌለው በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የታሪክ ነክ ሙግቶች ታይቶ
በማይታወቅ መልኩ ዱላ ቀረሽ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡
በአንድ ወቅት በኢዮጵያ ታሪክ አፃፃፍ ላይ አስተያየቱን የሰጠው የዘመኑ አዳሽ
ምሁር ገብረህይወት ባይከዳኝ ይህን ብሎ ነበር ‹‹ታሪክን መማር ለሁሉ ስው ይበጃል፡፡ …
እውነተኛውንም ታሪክ ለመፃፍ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ …. መጀመሪያ ተመልካች ልቦና
የተደረገውን ለማስተዋል፣ ሁለተኛ የማያዳላ አእምሮ በተደረገው ለመፍረድ፣ ሦስተኛ
የጠራ የቋንቋ አገባብ የተመለከቱትንና የፊረዱትን ለማስታወቅ›› እንደሚረዳ አፅኖት
ስጥቶ ተናግሯል፡፡ ገብረህይወት ልክ ነበር፡፡ የገብረህይወት ምክረ-ሀሳብ የሚሰራው ግን
ታሪክ የፖለቲካ እስረኛ መሆን ስታቆም ብቻ ነው፡፡ በዘመናችን ታሪክ የአሸናፊዎች
ደንገ-ጡር ናት፡፡
ከገብረህይወት አስተያየት በፊትም ሆነ በኋላ ታሪክ በጸሐፊው ማንነት /ኃይማኖታዊ
ማንነቱንም ያካተተ/ እና በስርዓታቱ ባህሪ ሲከተብ ኖሯል፡፡ (አልፎ አልፎ የነገስታቱን
ጉልህ ጥፋቶች የፃፉ ደብተራዎችና ሊቃውንት እንዳሉ ሳዘነጋ) ከዚህ የተጣባዉ ባህሪያችን
ዛሬም ተከትሎን ዘልቋል፡፡ እናም በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ ክርክሮች ሲፈጠሩ
ማጠንጠኛቸው ከላይ በተገለጹት ቃላት (ፍልሰት፣ መስፋፋት፣ ብሔራዊ ጭቆና፣ ቅኝ
ግዛት……) የትርጉም ልዩነት ዙሪያ ሊሆን ግድ ብሏል፡፡ ለዚህም ይመስላል በተፎካካሪ
የኢትዮጵያ ታሪክ ትርጉም አቀንቃኞች መካከል የታሪክ ገመድ ጉተታው ሊቋጭ
ያልቻለው፡፡
ፖለቲካን የታከከ የታሪክ ትርጉም ጮክ ባለ መልኩ የሚያራግበው ኢህአዴግ፣
ታሪክን ከፕሮፌሽናል ባለሙያዎች መዳፍ ነጥቆ የካድሬዎቹ መጫወቻ ካደረገው በኋላ
ደግሞ የአብሮነታችን ጠንቅ የሆኑ፣ በሰነድም ሆነ በሥነ-ቃል ደረጃ ያልተዋረሱ
(ያልተደገፉ) ትርክቶች ኃውልትን መሰረት ያደረገ የጥላቻ ርዕዩተ ዓለም ይዘው ብቅ
ማለት ጀምረዋል፡፡ ታሪክ በጊዜ ምጣኔ እየተከፈለ፣ እንደ ዘመኑ የህብረተሰብ አስተሳሰብ
ዕድገትና የባህል ይዞታ እንዲሁም አካባቢያዊ (regional) ቅኝትን በንፅፅር እያሳየ
እስካልተፃፈ ድረስ የታሪክ ትርጉም ቅርቃር ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ መሀል
ስለ ቡድን ፍላጎታቸው ሲሉ መሓኑን ታሪክ ለማዋለድ ጥረት የሚያደርጉ የታሪክ
አዋላጆች ይፈጠራሉ፡፡ ታሪክን ከብሔራዊነት ግንባታ አኳያ ሳይሆን ከቡድን ፍላጎት
አንጻር አጣመው የሚፅፉና የሚተረጉሙ አካላት በመስመር መሀል ትግላቸው ለተራዛሚ
ስልጣንና ለኪስ አብዮት መሆኑን ያላስተዋለ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ይኖር ይሆን? እጅግ
የበዛ የመርማሪነት ልቦናን የሚሻው የታሪክ ምርምርና ዘገባ ስራ አርበኝነት ባጠቃቸው
‹ፀሐፍት› በመወርሩ ከረጅሙ የታሪክ ጉዟችን እንደ አገር የሚያስማማ ገዥ-ሐሳብ
ለማግኘት አልታደልንም፡፡ የአንዱ ጀግና የሌላው ሒትለር የሚሆንበት አጋጣሚ በአንድና
በሁለት ነገስታት ብቻ አይታይም፡፡ የመቻቻል ትርጓሜ እና የአንድነት ሐሳብ ላይ ያሉን
ብያኔዎች በጠርዝ የተወጠሩ ናቸው፡፡ የታሪክ ወቀሳና ሮሮ ዛሬም እንደ አዲስ ሲነሳ
መስማት የተለመደ ነው፡፡ በጥቀሉ የታሪክ ተከላካይነትና አጥቂነት ግብግቡ የሰሜን Vs
ደቡብ ምዕራብና ምስራቅ ኢትዮጵያ መገለጫ ሆኗል፡፡ ሙሉውን ለማንበብ ይህንን ይጫኑ
http://www.ethiomedia.com/1010ideas/sarcastic_poet_bewqetu_seyoum.pdf
No comments:
Post a Comment