Tuesday, September 8, 2015

በጥርሳችን መሃል አሾልከን እየዋሸን ይሆን ....... ?

ደምስ በለጠ ከጋዜጠኛ ደምስ በለጠ ቀጥሎ ያለው የንግሊዝኛ ፅሁፍ ፤ ኤልያስ ክፍሌ ከኤርትራ ጋር ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል ባለበት ጊዜ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ኤልያስን የተቹበት ፅሁፍ ነው ። 

“I wonder what in the "Hell" Asmara has to do with the likely outcome of political events in Ethiopia. Isn't Asmara the home of Esayas Afewerke, a man who never sleeps before he makes sure that Ethiopia is reduced to multiple mini states? Had there been an inch thick of a heart that worries for Ethiopia under the chest of Essays, Asmara wouldn't have opened its door for separatist elements that fight to dismantle Ethiopia, and for EPPF; an organization that firmly stands for the unity of Ethiopia. If there is anything that the opposition gets from Asmara today, it will definitely be paid back at an exorbitantly high price tomorrow. The question of Assab, Bademe, Tsorena, and other border areas that I can’t even name are issues that face the current opposition in the future when it assumes power. If we believe that Esayas is willing to raise a lion that may ultimately devour him, we’re not just lying through our teeth, but we are also simplifying very complex national issues.” 

ትርጉሙን በአማርኛ ቀጥዬ አስቀምጨዋለሁና ይዝናኑበት ። “በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚደረጉ ማናቸውም ፖለቲካዊ ክንዋኔዎች አስመራ ምን ጥልቅ እንደሚያደርጋት ሳስበው ያስደንቀኛል ። ኢትዮጵያ በጥቃቅን መንግስታት መበጣጠሷ እስኪረጋገጥ ድረስ በአይኑ እንቅልፍ ዝር የማይለው የኢሳኢያስ አፈወርቂ አገር አይደለችም እንዴ አስመራ ? ለመሆኑ በኢሳኢያስ ደረት ውስጥ ለኢትዮጵያ የሚጨነቅ አንድ ኢንች እንኳ ውፍረት ያለው ልብ አለን ? ይህ ባይሆን ኖሮማ ፤ አስመራ ለኢትዮጵያ አንድነት በፅናት ለቆመው የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባርን ጨምሮ ፤ ኢትዮጵያን ለመገነጣጠል ለተሰለፉ ለተገንጣይ ቡድኖች በሯን ባልከፈተች ነበር ። ዛሬ ተቃዋሚው ከአስመራ ሊያገኘው የሚችለው ቢኖር እንኳ ፤ ነገ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍለው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል ። የአሰብ ፤ የባድሜ ፤ የፆረና እንዲሁም ዘርዝሬ የማልጨርሳቸው ሌሎች የድንበር አካባቢዎች ጉዳይ ስልጣን የሚያልሙ የዛሬ ተቃዋሚዎች የሚጋፈጧቸው የወደፊት ጥያቄዎች ይሆናሉ ። ኢሳኢያስ ራሱን ሊበላው የሚችል “አንበሳ ለማሳደግ ፍላጎቱ አለው ብላችሁ የምታምኑ ከሆነ ፤ በጥርሳችን መሃል አሾልከን እየዋሸን ብቻ ሳይሆን ፤ እጅግ ውስብስብ የሆነውን ብሄራዊ ጥያቄ እያቃለልነው እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ።........” ይህን የጻፉት አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ነዎት ። ምነው ይህ አቋምዎ እንደፀና ቢቆይ ብየ መመኘቴ አልቀረም ። የፅሁፍዎ ማስረጃም በሚቀጥለው ሊንክ ላይ ይገኛል ። ሊንኩን ይጫኑ ።

 http://www.ethiomedia.com/all/6113.html

 በዚህ ላይ ጥቂት ጥያቄዎችን ከራስዎ ፅሁፍ ላይ ላንሳ ነው ። ጥያቄ አንድ- አቶ ኤፍሬም ዛሬ ኢሳኢያስ ደረት ወስጥ ለኢትዮያ የሚጨነቅ አለሎ የሚያህል ልብ አገኙበት ? ጥያቄ ሁለት- የአሰብ ፤ የባድሜ ፤ የፆረና እንዲሁም ዘርዝሬ የማልጨርሳቸው ሌሎች የድንበር አካባቢዎች ሲሉ ለጠቀሷቸው ዝርዝሮች ፤ የተረጋገጠ መልስ ከሻእቢያ አገኙ ወይ ? ጥያቄ ሶስት- ኢሳኢያስ ራሱን ሊበላው የሚችል አንበሳ ለማሳደግ ፍላጎቱ እንደሌለው ገልፀውልናል ። እርስዎስ ካንበሳ በታች ኢሳኢያስን ሊበላ በማይችል ፤ በየትኛው እንሰሳ ደረጃ ራስዋን አስቀምጠው ነው የገቡት ? ጥያቄ አራት- ኢትዮጵያ በጥቃቅን መንግስታት መበጣጠሷ እስኪረጋገጥ ድረስ በአይኑ እንቅልፍ ዝር የማይለው የኢሳኢያስ አፈወርቂ አገር አይደለችም እንዴ አስመራ ? ብለው ነበር ። አሁን እናንተ የግንቦት አመራሮች አስመራ ከገባችሁ በኋላ ፤ ኢሳኢያስ አፈወርቂ ሃሳባቸውን እናንተ ላይ ጥለው ፤ ኢትዮጵያን መበጣጠሳቸውን ትተው ፤ እፎይ ብለው በጀርባቸው ተንጋለው ተኙን ? አቶ ኤፍሬም ይህን ከመለሱልኝ ደግ ።

 ካልመለሱልኝ ግን “በጥርስዎ በኩል አሾልከው እየዋሹ ነበር” ማለት ነው ? ስነ-ፅሁፍ ሆኖብኝና ከላይኛው አባባልዎ ሁሉ “በጥርስ መሃል አሾልከን እየዋሸን ነው” የምትለዋ አባባልዎ ተመችታኛለችና በዛሬው ፅሁፌ እመላለስባታለሁ ። አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ለክፉም ለደጉም መጀመሪያ ሰላምታየን ላስቀድም ። አስመራ ፤ ሃሬና ፤ ኦምሃጀር ፤ እና ዊአ በሰላም መግባትዎን ስሰማ ደስ አለኝ ። የጀግና ፤ የተዋጊ አምላክ ፤ እንዲከተልዎና ወገኔ ስለሆኑም ፤ የሻእቢያ አዙሪት ውስጥ ፤ ሰምጠው እንዳይቀሩ ፤ የዘወትር ፀሎቴ ነው ። አቶ ኤፍሬም ለፅሁፍዎ የሰጡት ርእስ “ከዊሃ እስከ ኦምሃጀር – አንድ ሰሞን ከአርበኞች ጋር” የሚል ነው ። ምን ማለት ነው ሰውየው ይህን ሰሞን ከአርበኞች ጋር አይደሉም እንዴ ብዬ እራሴን ጠየቅሁት ። 

“አንድ ሰሞን” የሚለው ሃረግ ፤ ረዘም ያለ ሃላፊ ጊዜን (Past tense) ስለሚያሳይ ፤ ምንልባት ይህን ሲሉ ምን ለማለት ፈልገው ነው ብዬ ፤ ግር ብሎኝ ነበር ። ፅሁፍዎን እስከመጨረሻው ሳነበው ግን ሁሉንም ተረዳሁት ። የፅሁፍዎ ጅምር በመለኮታዊ ሃይለ-ቃል ላይ ስለሚጀምር ፤ የቅዱሳንና የነቢያትንም ስም ደጋግመው ስለሚጠሩ ፤ ምነው እዚሁ አሜሪካ ቀርተው ፤ (በራስዎ አባባል) ለዚህ ቱሪናፋ ዲያስፖራ ሁሉ ፤ ትምህርት በሰጡት ብዬ ተመኘሁ ። እርስዎ ወደአስመራ በተጓዙ በሁለተኛው ቀን ፤ በፓልቶክ ፤ አንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ፤ አቶ ኤፍሬም ሳልፈልግ ነው የምሄደው ብለው ፤ እያለቀሱ ነው ወደ አውሮፕላን የገቡት ብለው ሲያሙዎ ሰምቼ ነበር ። እርስዎም ይህንኑ በፅሁፍዎ ላይ አረጋግጠዋል ። እንደ ባህላችን ወደ ጦር ሜዳ ለመሄድ የቆረጠ ሰው ፤ ሃሞቱን ኮስተር ፤ ግንባሩን ቆፍጠን ፤ ደርቱን ነፋ አድርጎ እያቅራራ ነበር የሚሸኝ ። ቀረረቶው እንኳ ይቅር ፤ ዳላስ ኤርፖርት ላይ ሌላም ጣጣ ሊያመጣ ይችላል ። ልጅዎም ቢሆን ከዳላስ ኤርፖርት ሲሸኝዎ ቆፍጠንጠን ያለ ኮስተር ያለ ሃሞት ፤ ቢያይ ፤ የተገባ ነበር እላለሁ ። ይህን ማለቴ ፡ የጦር ሜዳ ሰው ስለሆኑ እንጂ ፤ ለልጅዎ ፍቅር ያፈሰሱትን እንባ ሳላደንቅ ቀርቼ እንዳይመስልዎ ። ቆይ! ቆይ! ግን አቶ ኤፍሬም ! ከዳላስ የተነሱት ረቡዕ ምሽት ላይ ነው ፤ ቢያንስ በመንገድ ላይ ከነትራንዚቱ 12 ሰአታት ያሳልፋሉ ። እንዴት ተደርጎ ነው እንደገና ረቡዕ ከቀኑ አንድ ሰአት አስመራ ሊነቁ የቻሉት ? እኔ ሳልሰማ ምድር ወደ ምእራብ መዞር ጀመረች ወይስ ፤ አስመራ እናንተ ከገባችሁ በኋላ በሳምንት ሁለት ሁለት ረቡዕ ታወጀላት ? ግራ ስለገባኝ ነው። ጉደኞችዎ ሲቀሰቅሱዎና ከእንቅልፍዎ ሲነሱ መነሳት ባይፈልጉም በልብዎ “ትግሉ ተጀመረ” ማለትዎን ሲገልፁ ፤ አልዋሽዎትም “ድንቄም ትግል” ብየ አሹፊአለሁ ። እኔ ብቻ እንዳልመስልዎ ሌሎችም ፤ ሲያሸሙሩ ሰምቻለሁ ። 

ክፅሁፍዎ ላይ ካነበብኳቸው ምእራፎች ሁሉ ያዝናናኝንና ቀኔን ደስ የሚል ቀን አድርጎት የዋለው ፅሁፍ ፤ ከዚህ በታች ያስቀመጧቸው ምእራፎች ናቸው ። ከኤፍሬሞ ማዴቦ ፅሁፍ የተጠቀሰ ። “አላማ የሌለዉ፤ ሆዱ ያልቆረጠ፤ ፈሪ፤ ወኔ የከዳዉና አይኑን ተራራዎቹ ላይ ብቻ ያሳረፈ ሰዉ ከአስመራ ተነስቶ በከረን በኩል አቆርደትን አቋርጦ የጀግኖቹ መንደር ሀሬና የሚደርስ አይመስለዉም። ለዚህ ነዉ ሁሉን የሚችል እግዚአብሄር አይዞህ ብሎ የላከዉ የብሉይ ኪዳኑ ነቢዩ ኤልያስ ኤልዛቤልን ፈርቶ እንደሸሸ ሁሉ የኛም ዘመን ጋዜጠኛ ነን ባዮች፤ ዘፋኞችና አርበኛ ነን ባይ የሀሰት ነቢያት ገና ከረን ሳይደርሱ ተራራዉን እየፈሩ በኤርትራ በኩል ምንም ነገር መስራት አይቻልም እያሉ እንደ ግመል ሽንት የኋሊት የሚጓዙት። ድንቄም ጋዜጠኛ! ጋዜጠኛ ታሪክ ሸራርፎ በሰጠዉ ግዜ እየኖረ ያየዉንና የሰማዉን ለትዉልድ እያስተላለፈ ለራሱ የማይኖር ልዩ ፍጡር ነዉ። የኛዎቹ “ጋዜጠኛ” ነን ባዮች ግን እራሳቸዉ ለራሳቸዉ በሰጡት ግዜ እየኖሩ የራሳቸዉን ግሳንግስ የፈጠራ ታሪክ የሚነግሩን ከህያዉ በታችና ከሙታን በላይ ባለዉ ባዶ ቦታ የሚኖሩ ባዶዎች ናቸዉ። አምላክ በምህረቱ ወደ ላይ ይሳባቸዉና ከህያዋን ጋር ይቀላቅላቸዉ። ምድረ የወሬ ቋቶች ይግባችሁ! የኢትዮጵያ ህዝብ ዉኃ ዉኃ የሚያሰኝ የእሳት ጉድጓድ ዉስጥ ነዉ ያለዉ፤እሱ ከጉድጓዱ ባስቸኳይ መዉጣት እንጂ እንደናንተ በኤርትራ በኩል ከሆነ ይቅርብኝ ብሎ የሚጃጃልበት ግዜዉም ትዕግስቱም የለዉም። ለነገሩ እነዚህ የወሬ አርበኞች ተራራ ወጥተዉ፤ በረሃ አቋርጠዉና ወንዝ ተሻግረዉ ከወያኔ ጋር ሳንጃ ሊማዘዙ ቀርቶ የገዛ ልጆቻቸውን የልደት ኬክ ደፍረዉ በቢላዋ የማይቆርጡ የ”ዳዉን ታዉን” ቅምጦልች ናቸዉና ከነወሬያቸዉ እዚያዉ “ዳዉን ታወን” ብንተዋቸዉ የሚበጅ ይመስለኛል። አይደል?” አቶ ኤፍሬም ማዴቦ በነዚህ ምእራፎችዎ ላይ ብዙ ነገሮች ተቀላቅለው ታዩኝ

 እርስዎ ፀሃፊው ስለሆኑ የፃፉትን ያውቁታል ። ጉዳዮቹን ማሳየት የምፈልገው ግን ለአንባቢዎቼ ነው ። የብሉይ ዘመን ቅኔ ፤ ተራ ስድብ ፤ የከረረ ጥላቻ ፤ የምሬት ርግማን ፤ በመጨረሻም ሞት ተመኙልን ። እርስዎና ቡድንዎን ግንቦት ሰባትን በምናቤ ለአፍታ ምኒሊክ ቤተ-መንግስት ስልጣን ላይ አውጥቼ አየኋችሁ ። ያለ ፍርድ በናንተ አብዮታዊ ውሳኔ መሰረት ፤ መረሸኛው ግርግግዳ ላይ ቀዳሚ ተሰላፊዎች የምንሆነው ፤ አንደኛ በብሉይ ዘመን ቅኔ ስሙ የተጠቀሰውና ኤልዛቤልን ፈርቶ የሸሸው ኤልያስ ክፍሌ ፤ ሁለተኛ በጋዜጠኛ የተገለፅኩት እኔ ደምስ በለጠ ነበርን ። ግንቦት ሰባትን የሚያህል ድርጅት ፤የስራ አስፈጻሚ አባል ፤ ፅሁፍ በሚፅፉ ሰዎች ላይ ፤ ይህን የመሰለ የከረረ ጥላቻ ካደረብዎ ፤ በስልጣን ባለቤትነት ሲተረጎም ምን ሊያመጡ እንደሚችሉ መገመት ቀላል ነው ። እዚህ ላይ በአደባባይ ምስክር እየጠራሁ ልሞግትዎ ነው ። 
የኛም ዘመን ጋዜጠኛ ነን ባዮች፤ ዘፋኞችና አርበኛ ነን ባይ የሀሰት ነቢያት ከረን ሳይደርሱ በኤርትራ በኩል ምንም መስራት አይቻልም ይላሉ ብለው ወቀሱን ። እድሜ ለቴክኒዎሎጂ ዩ ትዩብ የሚባል የታሪክ መዝገብ ቤት ስላለ እሱን ምስክርነት እጠራብዎታለሁ ። ሊንኩን ይጫኑ ።

 https://www.youtube.com/watch?v=B8L7pFvKzIs

ይህ ምስክርነት ካልበቃዎ ፤ የራስዎን ሰዎች ፤ አንደኛ የግንቦት 7 የስራ አስፈጻሚ አባላችሁን አቶ ብዙነህ ፅጌንና ፡ የለንደን ቀንደኛ ደጋፊያችሁንና የአባይ ሜዲያ አዘጋጁን አቶ ግሩም ዘገዬን ምስክር እጠራብዎታለሁ ። 

ሁለቱም ከኔው ጋር ሃሬና የፊልም ማህደሬ ላይ ስላሉ አይክዱም በማለት ነው ። ቀጥለውም የልጆቻቸውን የልደት ኬክ እንኳ ደፍረው መቁረጥ የማይችሉ ብለው ፈሪነታችንን በአደባባይ ገለጡብን ። አቶ ኤፍሬም እርስዎ እንዳሉት ፈሪ ብንሆንስ ምን አለበት ? እኛ በጋዜጠኝነት ብዕር ይዘን ሄድን እንጂ ጦር ሜዳ ገብተን ልንዋጋ ነው ብለን አውጀን አልሄድን ? እርስዎስ ቢሆኑ ከአሜሪካ ትግሉን ለመቀላቀል ወረድኩ ብለው ሃሬና ሲደርሱ ባረጉት ንግግር ላይ ፤ ልዋጋ ሳይሆን ፤ የመጣሁት “ውኃ ላቀብላችሁ” ነው ያሉት ። አቶ ኤፍሬም ገና ሳይተኩሱ እንዲህ እሽኮለሌን ምን አመጣው ። እኛን ፈሪዎች ናቸው ካሉን ፤ ጀግና ከፈሪ የሚለየው ፤ በቀወጠው ውጊያ ምኻል ተኩሶ ሲጥል እንጂ (በራስዎ አፃፃፍ) አፉን ስላሾለም አይደለም ። ቃታ ስበው ተኩሰው ሲጥሉ ደግሞ ፤ እንዲህ ነን እኛ !! ብለው በኛ በፈሪዎቹ ላይ ይሳለቁብን ። 

ከከረን በታች አልወረዱም ብለው በጥርስዎ ቀዳዳ አሾልከው ሲዋሹ ፤ እኔ ደግሞ ከላይ የጠቀስኳቸውን የራስዎን ሰዎች ምስክር ጠርቼ በጥርሴ ቀዳዳ አሾልኬ ከትከት ብየ ስቄበዎታለሁ ። በሚከተለው አባባልዎ “የምወደዉን አንድ ልጄንና ጥሩ ስራዬን ደህና ሁኑ ብዬ በረሃ የገባሁት እናት አገሬ ዉስጥ ፍትህ፤ ነጻነት፤ እኩልነትና ዲሞክራሲ አብበዉ ለማየት ነዉ።” ሲሉን ፤ ደግመን ደጋግመን ሰማንዎ ፤ ደጋፊዎችዎም ይህንኑ ነው ፊሽካ የሚነፉበት ( ወይ ፊሽካ ! እንዲሁ በከንቱ ተነፍታ ቀረች አይደል ?) ። ስለዚህ እንደገና እናጨብጭብልዎ ? !! ጨብ…ጨብ…ጨብ ። እርስዎ የተመኙት ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲያብብ ደግሞ እጥፍ በእጥፍ እናጨበጭብልዎታለን ። ለከፈሉት መስዋእትነት ክሬዲት ያዙልኝ ከሆነም በወርቅ ቀለም መዝግበን ይዘንልዎታል ።

ሆኖም ግን አንድ የሰማሁት ነገር አለና ፤ ምክሬን ላካፍልዎ ። የወልቃይት ጠገዴ ሰው እንዲህ እያለ እየፎከረ ነውና በቶሎ ጦር ሜዳ ግቡ ። “ወይ እነሱ አይመጡ ወይ እኛ አንሻገር ፤ ቦታው ጦም አደረ የኒያ ሰዎች አገር ።” ሳቄ በጣብኝ !!! አፌን ይዣለሁ !! ም…ን….ም ፡ አ …ልልም !! ከተናግሮ አናጋሪ ሰውረኝ ነው የሚባለው ። እንዲያው በጥርሴ ቀዳዳ አሾልኬ ልሳቅ እንጂ ? ወይ ዘመን ? አቶ ኤፍሬም እርስዎ በጥርስዎ አሾልከው ሲዋሹ ፤ እኔም በጥርሴ አሾልኬ ስስቅ ፤ ከረምናታ ነው የሚባለው ። “ትራክተሩ ያርሳል፤ ግረደሩ ይዳምጣል፤ እንደኔ አይነቱ ጠመዝማዛዉ መንገድ ቀልቡን የሰለበዉና ፀሐዩ ያቀለጠዉ ምስኪን ደግሞ ወላዲት አምላክ ምን በደልኩሽ እያለ ያምጣል ። ምጥን እዚህ ላይ ምን አመጣው ?…….ግድቡ፤ እርሻዉ፤ የጤና ተቋሙና ሌላም ሌላ የመሠረተ ልማት ምልክቶች በጉልህ የሚታዩት ገጠሪቱ ኤርትራ ዉስጥ ነዉ።” አሉን ።

 እውን ትራክተሩ ያርሳል ? ኤርትራ ውስጥ እርሻ በነሐሴ ሆነ እንዴ ? ግሬደሩስ ምን እየዳመጠ ነበር ? ለመሆኑ ግሬደር ይዳምጣል እንዴ ? ሌላ ትርጉም አይስጥብኝ እንጂ ወላዲት አምላክንስ ቢሆን በአማላጅነቷ ያውቋታልን ? ወይስ ለወሬ ማጣፈጫነት ሊጠቀሙባት ነው ? ያን መንገድ የምናውቀው ፤ ብዙ ሰዎች በዚያ በኩል ተመላልሰናል ።

እንዴት ነው ወንዝ ሳይኖር ግድብ የሚኖረው? በበረኻ መንገድ ላይ እየተጓዙስ ፤ እንዴት የጤና ተቋማቱ ፤ መሰረተ-ልማቶቹ የታዩዎ ? ልዩ መነፀር አስመራ እንደገቡ ሻእቢያ ካላስገጠመልዎ በቀር ያሉት ሁሉ በዛ መንገድ ላይ የለም ። ሊኖርም አይችልም ። ከአስመራ ተነስቶ እስከ ተሰነይ ባለው መንገድ ላይ ፤ ከሃይኮታ ጀምሮ እስከ ተሰነይ ድረስ ያለው ፤ ወደ 50 ኪ.ሜ የሚጠጋ መንገድ ፤ ለአይን የሚስብ ፤ ቀልብ የሚሰቅል ፤ ምንም ነገር የሌለበት አሰልቺ መንገድ ነው ። እርስዎስ ቢሆኑ ለመሰረተ ልማት ግምገማ ነው እንዴ ኤርትራ የሄዱት ? ወይስ በጥርስዎ መኻል አሾልከው እየዋሹን ነው ? ወረድ ብለው ደግሞ እንዲህ ይሉናል ። “. . . ደረስን እንዴ አልኩ … የመኪናችንን ሾፌር። ገና ነዉ ትንሽ ይቀራል አሉ ወደኋላ ዞር ብለዉ።

እንዳዉ ለነገሩ ነዉ እንጂ ሰዉዬዉ ዬት እንሄዳለን፤ መቼ አንሄዳለን ወይም መቼ እንመለሳለን ለሚሉ ጥያቄዎች በፍጹም መልስ አይሰጡም። ወያኔ የማይሰማን ሁሉንም ነገር ሆዳችን ዉስጥ ከያዝነዉ ብቻ ነዉ የሚል ፈሊጥ አላቸዉ።” እግዜር ይስጥልኝ አቶ ኤፍሬም ። እንዲህ እውነት ሲናገሩ ደግሞ እውነት ተናግረዋል ብዬ እመሰክራለሁ ። የት እንሄዳለን ፤ መቼ እንሄዳለን ፤ መቼ እንመለሳለን ለሚሉ ጥያቄዎች በፍፁም መልስ አይሰጡም ፤- ያሉት እውነት ነው ። የናንተ እቅድ እንኳ የራሳችሁ እንዳልሆነ እዚህ ላይ ራስዎ መሰከሩ ። ሁሉንም ነገር ሻእቢያ ቀድሞ አቅዶላችኋል ። ሾፌሩ መንዳት !! እናንተ መነዳት !! ። የገረመኝ ግን ፤ ወዳጅ ብላችሁ የሄዳችሁበት ሻእቢያ ገና ካሁኑ በወያኔነት ጠርጥሯችሁ ይሆን እንዴ ሁሉን ነገር በሆድ መያዝ ነው የሚል ፈሊጥ የጀመረው ። ምስኪን ። እውነት ከተናገሩባት ነጥቦች አንዷ ደግሞ የምትከተለው ናት ። “የነፍስ ወከፍ ጠመንጃዉን እንዳቀፈ ሰላም ሊለኝ ሲመጣ ትኩር ብዬ አየሁት።

ወጣት ነዉ፤ ጽናቱና ቁርጠኝነቱ ፊቱ ላይ ይነበባል። በፈገግታ የታጀበዉ የዋህ ፊቱ ልጅነቱን በአዋጅ ይናገራል። ዕድሜዉ ከሃያ አይበልጥም። ………..ድንኳን ዉስጥ ገብተን ቁጭ እንዳልን . . . . እዚህ አካባቢ ችግራቸሁ ምንድነዉ አልኩት። ይምጡ አለኝና ከድንኳኑ ይዞኝ ወጥቶ ገዢ መሬት ይዘዉ የመሸጉትን የተለያዩ ካምፖች አሳየኝና የእያንዳንዳቸዉን ስም ነገረኝ። ሁላችንም የመጣነዉ ከኢትዮጵያ ነዉ፤ ሁላችንም የምንታገለዉ ወያኔን ነዉ፤ ደግሞም የሁላችንም ጥያቄ ፍትህ፤ ነጻነት፤ እኩልነትና ዲሞክራሲ ነዉ. . . .. ግን አንድ ላይ አንታገልም። እስከመቼ ነዉ የአንድ አገር አርበኞች ከአገራችን ወጥተን፤ የተለያየ ድንኳን ተክለን፤ በተናጠል የጋራ ጠላታችንን የምንዋጋዉ? እባካችሁ ገላግሉን ብሎኝ ቀና ሲል አይኑ ካይኔ ገጠመ። “እዚህ አካባቢ ችግራቸሁ ምንድነዉ አልኩት ፤” ይላሉ ። ጥያቄዋ የትልቅ የመንግስት ባለስልጣን ጥያቄ ነች ። በተለይ ኮለኔል መንግስቱ የሚታወቁባት ጥያቄ ነች ። የቀይ ኮከብ ዘመቻ ጊዜ ከኮለኔል መንግስቱ የኮረጇት ትሆናለች ። በኋላ እመለስባታለሁ ። የካምፖቹን ስሞች ዝርዝር ወጣቱ ሲነግርዎ ፤ የአንድ አገር ልጆች በተለያዬ ድንኳን ውስጥ መቀመጣቸው አስገረመዎ አይደል ? እኛንም አስገርሞን አስገርሞን ይህ ነገር ይብቃ ሲሉ የነበሩ ሰዎችን አይተናል ። በተለይ ኤልያስ ክፍሌና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ፤ ይህ በኮለኔል ፍፁም አማካይነት ብቻ እንደማይፈፀም ሲረዱ ፤ ጉዳዩን እስከ ኢሳኢያስ አፈወርቂ ድረስ አድርሰውት ነበር ። የተለወጠ ነገር ግን አልነበረም ። ይህ እንግዲህ ጉዳዩን በአገራዊ ደረጃ ኮስተር አድርገን ከተመለከትነው ነው ። አገራዊ ካልሆነ ደግሞ ፤ እርስዎ የመጡባትን ጉዳይ እኛ “የዳውን ታውን ቅምጥሎች” በኤርትራ ከነበርው ልምዳችን በመነሳት ፤ ቀድመን ነቄ ብለን ስለነበር ፤“አዎ የኤርትራው ፎቶ ይናገራል” በሚለው ፅሁፋችን ፤ እንዲህ ብለን ተንብዬን ነበር ።

 ትንቢታችንን ቀጥለው ይመልከቱ፦ “ሁለተኛው ሴናሪዎ ደግሞ ከብርሃኑ ነጋ መምጣት ጋር የአርበኞች ግንቦት 7 ውህደት ከሌሎች ድርጅቶች በተለይም ከድምህት ጋር አሊያንስ ፈጠረ ተብሎ አዋጅ ይነገራል ፤ መግለጫዎች ይወጣሉ ፤ ከበሮ ይደለቃል ። ለዚህ ትያትር ማዳመቂያ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት በምርኮ ከተያዙ የደቡብ ተወላጆች በሆኑ ሰዎች ሻእቢያ ያቋቋማቸው ሁለት ወይም ግፋ ቢል ሶስት አባላት ያላቸው የደቡብና የቤንሻንጉል ድርጅቶችም ተሳታፊ ናቸው ተብለው የአሊያንሱ ማጫፈሪያ ይሆናሉ ።”-ብለን ነበር ። ይህንንም የተማርነው እዚያው ከሻእቢያ በተግባር ነው ። የሻእቢያ ፎርሙላ ሁልጊዜ አንድ አይነት ነው ። አንዳርጋቸው ፅጌ አስመራ ከገባ እንኳ 8 ጊዜ ትብብሮች ተፈርመዋል ።

 እነዚያ ትብብሮች ዛሬ የታሉ ? ጠይቃችኋል ? ወይስ ስለነበሩት ትብብሮች ማወቅ አያስፈልጋችሁም ። አሁንም ያ ወጣት ተዋጊ ፤ “ተመልከቱ በየድንኳኑ ተነጣጥለን ብሎ ስለነገረዎ ” በሻእቢያ ፈቃድ ፤ ልታስተባብሩና አልያንስ ልትፈጥሩ እየተዘጋጃችሁ መሆኑን ነው ሊነግሩን የፈለጉት ። ምስኪኑ ተዋጊ ወጣት አስተባብሩን ሲላችሁ ፤ እርስዎ ወደ ድንኳኖቹ ለመሄድ ጠየቁ ። ምንም እንኳ ሰአቱ ከቀኑ 9 ሰአት ቢሆንም ልጁ እራሱ አሁን መሽቷል አለዎ ። ልጁ የተሰጠው የፉገራ ስራ ፤ እናንተ የመጣችሁት ለታልቅ አገር አድን ተልእኮ መሆኑን ማሳየት ነው ። ሆኖም ግን ፤ የሻእቢያ እቅድ እስኪነገራችሁ ድረስ ፤ ከነበራችሁበት ቦታ ፤ እስከ ድንኳኗ ድረስ እንኳ ፤ መንቀሳቀስ አትችሉም ። እኛም ስንናገርና ስንፅፍ የነበረው ይህንኑ ነበር ። መሪዎች ባሻችሁ ጊዜ ሰራዊቱ ውስጥ መንቀሳቀስ ካልቻላችሁ ፤ ስራዎቻችሁን እንዴት ነው ማከናወን የምትችሉት ? የኮለኔል ፍፁምን ፈቃድ እየጠየቁ መስራት ምን ያህልስ ያስኬዳል ? ከራስዎ ፅሁፍ ላይም ይኸንኑ ምልክት እያየንበት ነው ። ኮለኔል ፍፁም የዋዛ ሰው እንዳይመስላችሁ ። በምትሄዱበት ቦታ ሁሉ በቀጥታም ሆነ ፤ በእጅ አዙር እንደጥላ ይከተላችኋል ። የስራ ችግሮቻችሁ ፤ በገንዘብ ተቀይሮ ኪሱ እስኪገባ ድረስም ያዳክማችኋል ። ከዚያ በኋላ እየከፈላችሁ መስራት ትማራልችሁ ። አሁንም አስተውሉ ብለን እንመክራለን ።

ኮለኔል ታደሰ ሙሉነህ ከመጀመሪያ ጀምሮ ከሻእቢያ ጋር የነበረው ትልቁ ችግሩ ፤ እነዚህ ተበታትነው የተቀመጡ ፤ ጥቃቅን ድርጅቶች ያለንን የሰው ኃይልም ሆነ ወታደራዊ ብቃት ፤ የሚበታትኑ በመሆናቸው ፤ ከዚያም አልፎ በወታደራዊ ስነ ልቡና ረገድ ፤ በዘር ተደራጅቶ አንድ አካባቢ ላይ መስፈር ችግር የሚያመጣ ክስተት ነው ። በመሆኑም በአንድነት መታገላችን የተሻለ ውጤት ያመጣል የሚል አቋም በመያዙ ፤ መከራ በመክፈል ላይ ያለ ኢትዮጵያዊ መሆኑን እዚህ ላይ ሳልገልፅ ማለፍ አልፈልግም ። ይህን አይነት ትግል ያደረጉ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይም አንስቶ መነጋገር ተገቢ ነው ፤ ራሳችሁን በእኩል ደረጃ ከተመለከታችሁ ማለቴ ነው ። ወጣቱ ተዋጊ አስተባብሩን ብሎናል ብለው ፤ አቶ ኤፍሬም ፤ በጥርስዎ በኩል አሾልከው ስለዋሹን ፤እኛም በጥርሳችን በኩል አሾልከን እየሳቅንብዎ ነው !! ስለ ኢትዮጵያዊነት የተናገሯትን እንዲያው ትንሽ ልዳስሣት ፈለኩና ተውኳት ። ነገር ግን ችግር በመጣ ቁጥር ኢትዮጵያዊነትዎን ጥያቄ ውስጥ ያስገቡ ነበር እንዴ ? ይህ ነገር በአሳብዎ ለምን ሽው እንዳለ ስላልገባኝ ፤ እንዲያብራሩልኝ ለመጠየቅ ነው ። አይ ግንቦት 7 !! ቀጥለውም እንዲህ አሉ ።

 “ሐሙስ ነኃሴ 13 ቀን ጎህ ሳይቀድ ከእንቅልፌ ተነሳሁና ትንሽ ዞር ዞር ብዬ አልጋዬ ላይ ተመልሼ መጽሐፌን ማንበብ ጀመርኩ። ሁለት ምዕራፍ ጨርሼ ሦስተኛዉን ልጀምር ስል ከሩቁ ቡና ቡና ሸተተኝ። ቀና ብዬ ስመለከት ፍረወይኒ የቆላችዉን ቡና እስከነማንከሽከሻዉ ተሸክማ ልታስሸትተኝ ስትመጣ አየኋት፤ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ቁርስ ደረሰ እንዴ ብዬ ማንከሽከሺያዉ ላይ የሚንቦገቦገዉን ጭስ በእጄ ደጋግሜ ወደ አፍንጫዬ ሳብኩት። ‘ኡወ ቁርሲ ደሪሱ’ በፂሁ ብላ ፍረወይኒ የተቆላዉን ቡና ይዛ ወደ መጣችበት ተመለሰች።” ወይ ፍረወይኒ ? ወይ “ኡወ ቁርሲ ደሪሱ” አንባቢ ሆይ ! ቡና በማንከሽከሻ መኝታ ድረስ !! ዘመናዊ ትግል ማለት ይቺ ናት ። አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ተናግረው ጨርሰውት ፤ በዚህ ላይ እኔ ምን ማለት እችላለሁ ። በጥርሴ አሾልኬ ከመሳቅ በስተቀር !! አቶ ኤፍሬም ይህን ሲሉ ደግሞ አንዳርጋቸው ፅጌ ትዝ አለኝ ። እመለስበታለሁ ። ከዚያም በፅሁፍዎ ላይ “ዬት እንደምንሄድ ወይም ለምን እንደምንሄድ የጠየቀም የተናገረም አልነበረም። . . . ዋ! ትንፍንሽ ብትሉ የተባለ ይመስል ሁሉም አፉን ዘግቶ ወደማያዉቀዉ ቦታ ጉዞዉን ቀጠለ።” ሲሉ ነገሩን ። እረ ይሄ ሰውዬ ደገሙት አልኩኝ ። እንደገና አሁንም ሻእቢያ እየነዳችሁ እናንተም የምትሄዱበትን ቦታ ሳታውቁ እየተነዳችሁ ሄዳችሁ ። እኔ መቼም ስለ ኦምሃጀርና ስለተከዜ የተናገሩት ቢያስቀኝም ምንም ለማለት አልፈልግም ። ግን ይቺን የዩ ትዩብ ሊንክ ሳልጋብዝዎ ማለፍ አልፈለኩም ።


 http://www.ethiomedia.com/all/6113.html

 ትልቅ ነገር ሆኖ ሳይሆን አቶ ኤፍሬም እርስዎ ስላነሱት ብቻ ላነሳው ፈለኩ ። በ2011 እ.ኤ.አ. የአርበኞች ግንባር ጉባኤ ይደረጋል ተብሎ ከከረረን ጥቂት ኪ ሜትሮች ርቀት ላይ ይገኝ ወደነበረ ወታደራዊ ካምፕ ተወሰድን ። ገና አስመራ እያለን ethiopianreview ዌብ-ሳይት ሃክ እየተደረገ ኤልያስ ክፍሌ ተቸግሮ ነበር ። ጉባኤው በተካሄዱባቸው ቀናት ሁሉ ፤ ዌብ ሳይቱን ቼክ ለማድረግ ፤ ጠዋትና ማታ በተከራየው መኪና ፤ ወደ አስመራ የተመላለሰበት መንገድ ነው ። ስለዚህ ያቺን እርስዎ በሾፌር እየተነዱ ፤ ምጥ ያመጣብዎን የከረን መንገድ ፤ ኤልያስ ክፍሌ ያለሾፌር ደጋግሞ የተመላለስበት ስለሆነ እየተስተዋለ ለማለት ነው ። ይህም ከጀግንነት ከተቆጠረ ብዬ ነው ።

በቃ አንሂድ አለ ይዞን የመጣዉ የበላይ መኮንን . . . አዎ እንሂድ እንጂ ከዚህ በላይ መቆየት ለወያኔ ካልሆነ ለሌላ አይጠቅምም አሉ ሌላዉ በዕድሜ ጠና ያሉ የበላይ መኮንን። እኚህ ሰዉ የወያኔ ስም ሲነሳ ደማቸዉ ይፈላል ፤ እሳቸዉ እራሳቸዉ እንደ ዳዊት ሲደጋግሙት ግን ምንም አይሰማቸዉም ። ከሰዐት በኋላ ረፋዱ ላይ ሁላችንም ወደየመኪናችን ገብተን ኦምሀጀርን ለቅቀን ወደ ጀግኖቹ አገር ወደ ሀሬና አቀናን። አሉ ። ከነማን ጋር እንደነበሩ ግምቴን ልስጥ ። ወደ ኦምንሃጀር ይዞአችሁ የሄደው ኮለኔል ፍፁም ነው ። በዛ አካባቢ ከውጪ የመጡ ሰዎችን ፤ ይዞ ወደ ድንበሩ አካባቢ ሊጠጋ የሚችል ፤ ከኮለኔል ፍፁም ሌላ የበላይ መኮንን የለም ። ብሎም ከኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ወደ ኤርትራ በኩል ገባ ብሎ ያለውን ወታደራዊ ቀጠና የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው ። በአለም አቀፉ ስምምነት መሰረት ለወታደሮች የማይፈቀደውን መስመርም የሚያውቀውም እሱ ነው ። ሌላው በእድሜ ጠና ያሉት መኮንን በማለት አቶ ኤፍሬም የገለጿቸው ሰው ፤ ከዚህ በፊት ከውጬ ከመጡ እንግዶች ጋር ተመሳሳይ ጉዞ ሲያደርጉ አይቼ ባላውቅም ፤ የስሪት አሃደ ዋና አዛዥ ጀነራል ተክሌ ማንጁስ እንደሚሆኑ ጠርጥሬአለሁ ።

 እናንተን የሚያካክል ሶስት ሙዳ ሙዳ የግንቦት ሰባት ሹማምንት በቦታው ሲገኝ ፤ ተክሌ ማንጁስ ከናንተ ጋር ቢገኙ ለክብራችሁ አያንሳችሁም ።………. “ እኚህ ሰዉ የወያኔ ስም ሲነሳ ደማቸዉ ይፈላል ፤ እሳቸዉ እራሳቸዉ እንደ ዳዊት ሲደጋግሙት ግን ምንም አይሰማቸዉም።” ሲሉ ስለገለፁልን አቶ ኤፍሬም ፤ ከገለጡልን ባህሪያቸው በመነሳት ነው ተክሌ ማንጁስ መሆናቸውን የጠረጠርኩት ። አቶ ኤፍሬም ፤ ጀነራል ተክሌ እንጣጥ እንጣጥ ማለት የሚወዱ ሰው ናቸው ። አንድ ቦታ መቆም እንኳ አይችሉም ። መረጋጋት የሚባል ነገር አልሰራባቸውም ። ቆጣ ቆጣ እያሉ መናገር ፤ ኖርማል የአነጋገር ባህርያቸው ነው እንጂ ፤ እርስዎ እንደገመቱት ብቻም አይደለም ። እኔም መጀመሪያ ሳገኛቸው እንዲሁ እንደርስዎ ምን ያስቆጣቸዋል ስል ታዝቤአቸው ነበር ። ፅሁፍዎ ከኤርትራ ምእራባዊ ጫፍ ፤ ባንዴ ወደ ምስራቃዊው ጫፍ ስለተወነጨፈ ፤ እኔንም ይዘውኝ ተወነጨፉ ። እንዲህም አሉ፦ “ምፅዋ ልንደርስ ትንሽ ሲቀረን ሆዴን ባር ባር አለዉ ። የደስታ ይሁን የሀዘን ወይም የሲቃ አላዉቅም ብቻ ልቤ ሌላ ሌላዉን ሰዉነቴን ትቶ ደረቴ ዉስጥ ብቻዉን ይዘላል።” የኤርትራ ሁለ-ገብ አብዮታዊ ዘመቻ ። በዓሉ ግርማ “በኦሮማይ” መፅሃፉ ላይ ፤ ማንም ሊገልፀው ከሚችለው በላይ ፤ “የቀይ ኮከብ ሁለገብ አብዮታዊ ዘመቻ”ን የምፅዋ ስብሰባዎች ፤ ጥሩ አድርጎ ገልፆአቸዋል ። ልብዎ ቢዘል ምን ሃጢያት አለበት ።

ምነው አይዘል ፤ ይዝለል እንጂ ! እርስዎም እዚያው ነበሩ ።፤ ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ (የደርጉ) ኤርትራን ስያስተዳድሩ ፤ ወጣቱ ኤፍሬም ማዴቦ ፤ በኢሠፓ አባልነት ፤ የ(ሁገአዘ) የኤርትራ ክ/ሃገር የኤኮኖሚ ጉዳይ ሹም ነበሩ ። ለዚህም ይሆናል ለውጊያ የሄዱት ሰው ፤ ገና ኤርትራ እንደገቡ መሰረተ ልማት ግምገማ ውስጥ ዘው ያሉት ። አይ ቀይ ኮከብ ሁለ-ገብ አብዮታዊ ዘመቻ ስንቱን ህይወት ፤ ስንቱን የአገሪቱን ንብረት ፤ ስንቱን ተስፋ ፤ መና አግብቶት ቀረ ። ሃገራችን ኢትዮጵያ ስንቱን አይነት ዘመቻ አስተናገደች ? አቶ ኤፍሬም ፤ ቀጥሎ ባለው ሊንክ ላይ የሚያደርጉት ንግግርዎ የሚያረጋግጠውም ያን ሁሉ የኤርትራ አውራጃዎች ሊጎበኙ የቻሉት ፤ በደርጉ ጊዜ በነበረዎት ስልጣን አማካይነት እንደሆነ ነው ።
https://www.youtube.com/watch?v=pW1mopFgf2k

   
ኮለኔል መንግስቱን ጨምሮ ፤ የአገሪቱ መሪ ፓርቲ የኢሠፓ መኳንንት ፤ ሚኒስትሮችና የጊዜው ታላላቅ የጦር መኮንኖች ፤ በተገኙበት የምፅዋ የ(ሁገአዘ) ስብሰባዎች መኻል ፤ ወጣቱ ኤፍሬም ማዴቦ ፤ የአዋሳው የፒያሳ ልጅ ፤ የአገሪቱን መፃኢ እድል ከሚወስኑት ተሰብሳቢዎቹ መኻከል ተኮፍሶ ፤ የዛን ጊዜው ግልገል ባለስልጣን ፤ የወደፊት ተስፋው እየታየው ፤ ሊሰማው የሚችለውን ስሜት አስብኩት ። እኔ በማንም አልፈርድም ፤ ማንም አበሻ ፤ ያን አይነት አጋጣሚ ቢኖረው ፤ ሊሰማው የሚችለው ስሜት ነው ። ይህን የመሰለ ትዝታ ያሳለፉባት ምፅዋ አጠገብ ፤ ልብዎ ቢዘልል ምንም ሃጢያት የለበትም ። የታሰበው ሳይሆን ያልታሰበው ሆነ እንጂ !! ምፅዋ ዛሬ ከስሟ በስተቀር ምንም የሌላት ከተማ ናት ። ሁለት ቀን በቂ ነው ። ምፅዌዎቹ እንደነገሩኝ ፤ ምፅዋ በንጉሱ ጊዜ የሰው ዘር ሁሉ የሚታይባት ደማቅ የባህር ላይ ንግድና ፤ የባህር ኃይል ከተማ ነበረች ። ከአስመራ ቃኘው ሻለቃ በየሳምንቱ መጨረሻ የሚመጡት የአሜሪካ ወታደሮ ፤ ሌላው የምፅዋ ውበቶች ነበሩ ። በወታደራዊው አስተዳደር ዘመን የባህር ኃይልና የእግረኛ ወታደር ከተማ ነበረች ፤ እንደበፊቱ ባይሆንም የህይወት እንቅስቃሴ በጥቂቱ ነበራት ። የዛሬውን መሰረተ ልማቷን አቶ ኤፍሬም በነካ አፍዎ እባክዎ !! እኔም ሆንኩ ሌሎች ወደ ኤርትራ የሄድን ሰዎች ዊአ ላይ ፤ የአርበኞች ማሰልጠኛ መኖሩን ሰምተን አናውቅም ። አዲስ ተቋቁሞላችሁ ከሆነም ፤ እንኳን ደስ አላችሁ ። ስለ ዊአ የሚታወቀው ፤ የቅጣት ስፍራ መሆኑ ነው ። አቶ ኤፍሬም እንዳሉት ፤ ጭው ያለ በረኻ ነው ። 

ዊአ ላይ ከደጋ አገር የመጡ ውኃ ውኃ እያሉ ሊያስቸግሩ የሚችሉ ወታደሮችን ማሰልጠን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል ። ለጦሩ ውኃ በቦቴ ማመላለሱ ራሱ ትልቅ ወጪ ነው ። ኤርትራን ለቀው ወደ ኢትዮጵያ ወይ ወደሱዳን እየኮበለሉ ያሉ ወጣቶች ድንበር ላይ ከተያዙ ፤ ለቅጣት የሚላኩት ወደ ዊአ ነው ። ስለዚህ አርበኞቹም ለቅጣት ተልከው ይሆን ? ወይስ...............ዊአ ፤ ምፅዋ ያሳለፋችሁት የመዝናናት ቀናት መሸፈኛ ናት ። የፅሁፍዎ መደምደሚያ ምፅዋ ላይ የሚያሳየው ዘና ዘና ማለታችሁን ነው ። ከዛ በፊት ግን አንድ ጥያቄ ? ከነሞላ አስገዶም ጋር እንዲህ ተቃቅፋችሁ በጥላሁን ገሠሠ ዘፈን ስትማማሉ ፤ የአርበኞች ግንባር መሪዎች እነመአዛው ጌጡ የት ደረሱ ? በሻእቢያ ፕላን መሰረት ፤ ዙፋን ለንጉሱ አስረክበው ወደጦር ካምፓቸው ተመለሱ እንዴ ? ከዴምህት ጋርም ሳትነግሩን ተዋሃዳችሁ እንዴ ? እንግዲህ ነገሩ ሁሉ ጥላሁን ገሠሠ ከሆነ እኛም እንዝፈን !! “ፍቅሬ ፍቅሬ በዛ እኔ አላማረኝም” ያለው ማን ነበር ? በመጨረሻም አንድ ነጥብ ። 

ከላይ አንዳርጋቸው ፅጌ ፤ ትዝ አለኝ ብዬ ነበር ። ሻእቢያ ለኢትዮጵያ ታጋዮች የFive Star ደረጃውን የጠበቀ ፤ መስተንግዶ እያደረገላቸው መሆኑን ፤ በኢሳት ቲቪ መስኮት ፤ ብቅ ብሎ የነገረን ትዝ ስላለኝ ፤ እርስዎም ትዝ ይልዎታል ብዬ እገምታለሁ ። እንግዲህ Five Star ትግሉ ይመቻችሁ ። እዚህ ላይ እኔም እንደእናንተ ፤ ዘፈን አማረኝና እንደ እርስዎ ዘፈን የምጋብዝበት ቲቪና ጋዜጠኞች ስለሌሉኝ ንድድ አለኝ ። የድሐ ነገር እንግዲህ ፤ እኔው ልፎክር ነው ። የጥላሁን ዲጄ ነአምን ከኢሳት ፤ ጭፈራው ፤ የአመራር ግንቦት ወዴምህት ፤ ሰአት ከፕላን ውጪ እስካፍንጫ እስከፑንት ። እንዲህ ጨሶ ጨሶ የነደደ እንደሆን የአመዱ ማፍሰሻ ቦታው ውዴት ይሆን? ወዴት ይሆን? እትትትትትት ዘራፍ ! ከንባብ በኋላ ፤ የፍረወይኒ ቡና ፤ ቤተ-መንግስቱ ጋ የጉርጉሱም ዋና ። ከሻእቢያ ጋር ፤ በዚያ ዳፋታ ፤ ጅው ጂው ሲል የግንቦት ጌታ ፤ በአንድ እጁ ቡና በአንድ እጁ ቃታ ፤ እትትትትትትት ዘራፍ ! እንዲህ ያለ ጊዜ ዘመነ ግርቢጥ ፤ ውሻው ወደሰሮዶ አህያው ወደሊጥ ፤ ወደ ሊጥ ፤ ወደ ሊጥ ፤ እረ ጎራው እትትትትት ዛሬስ በርዶኛል ፤ ከመፃፍ ሌላ ሞት አስቦኛል ፤ እርግማኑንም ተቀብያለሁ ፤ ፈሪነቱንም ተቀብያለሁ ፤ ተራ ስድቡንም ተቀብያለሁ ፤ ጥላችውንም ተቀብያለሁ ፤ የጦቢያን ነገር እምቢ ብያለሁ ፡ እትትትትትትት ሻእቢያ ጋልቦኝ ፤ ከምሆን ፈረስ ፤ እምቢ ብያለሁ ለኢሳኢያስ ።

 እረ ጎራው...... እረ ጎራው የነብሩን ጉሮሮ ፍየል ገብቶ ላሰው ይኼ ዘመን ታሟል መዳኒት አቅምሰው ፤ እረ ጎራው ፤ ጎራው ትግሉ (Five Star) ፤ በሬው የተውሶ ፤ እንጀራው ሊበላ እንዲህ ሆኖ ታርሶ ። እረ ጎራው.... ጎራው...... ጎራው ሴፕቴምበር 4 ቀን 2015 እ.ኤ.አ ላስ ቬጋስ ኒቫዳ 

No comments:

Post a Comment