Wednesday, December 3, 2014

ፕ/ር መስፍን " ከባለቤቱ ያወቀ ምንትስ ነው" ሲባል አልሰሙ ይሆን?

ሠሞኑን በአማራ ተወላጆች ዙሪያ ብዙ እየተባለ ነው። አማራ አለ፣የለም እና የመሳሰሉት። እኔም በግሌ የሚሰማኅኝን ለማለት ካሰብኩ የሰነባበትኩ ቢሆንም እስከአሁን የቆየሁት በዚሁ አወዛርጋቢ በሆነው የአማራ ጉዳይ በዋናነት የሚጠቀሱት ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም እኔ ወደምኖርበት ምእራብ አውስትራሊያ ፐርዝ እንደሚመጡ በመስማቴ እና ስለሁኔታው በይበልጥ ለመረዳት ከዚህ የበለጠም አጋጣሚም ሥላልነበረ ነው። ወደዝርዝሩ ከመግባቴ በፊት ግን አንባቢያን ሁለት ነገሮችን እንዲገነዘቡልኝ በልዑል እግዚአብሔር ስም እጠይቃለሁ። ይሄውም አንደኛ እውነታውን ውድ ኢትዮጵያውያን እንዲያውቁት ከሚል ቀና መንፈስ እንጅ እኔ አንድ ተራ ሰው የእሳቸውን አመለካከትም ሆነ ንግግር የመተቸት ብቃቱም ሆነ ፍላግጎቱ የሌለንኝ መሆኑን ሲሆን ሌላው ደግሞ ከዚህ በታች እሳቸው እንደተናገሩት አድርጌ የምጠቅሰው ነገር ተራ የአሉባልታ ወሬ ሳይሆን ለታሪክም በሚል በድምጽ ተቀድቶ የሚገኝ መሆኑን ነው።

1፦ቀደም ብለው ከተናገሩት በመነሳት ለምን በደፈናው ኢትዮጽያውያን በብዛት እና በግዳጅ ከኖሩበት አካባቢ ይፈናቀላሉ ይላሉ?የዘር ግንዳቸው እየተጠና የሚፈናቀሉት አብዛኛዎቹ አማራዎች ናቸው።ስለሆነም የኢትዮጵያ ምሁራን እውነታውን የመጋፈጥ ድፍረቱ ሊኖራችሁ ይገባል የሚል መንፈስ ያዘለ ጥያቄ ከአንድ የስብሰባው ታዳሚ ሲጠየቁ፦ "በኢትዮጵያ ውስጥአማራውም፣ኦሮሞውም፣ጋምቤላውም፣አፋሩም....ይፈናቀላል።ስለዚህ ለሁሉም አዝናለሁ እንጂ ለአንድ ወገን ብቻ ለይቼ አላዝንም " የሚል ነው።
እዚህ ላይ ግን መታወቅ ያለበት አንድ መሰረታዊ ሃቅ " ከባልሽ ባሌ ይበልጣል " እንዳለችው ዘመናይ ሳይሆን በአማራውና በሌሎች ነገድ ላይ የሚደርሰውን በደል አንድ አድርጎ ማየት ለእኔ ሚዛናዊ የሆነ የህሊና ዳኝነትን ትዝብት ውስጥ የሚጥል ከመሆኑም በላይ የወያኔን ታሪካዊ ማንነትንም ጠንቅቆ ካለማወቅ ወይም ማወቅ ካለመፈለግ የመነጨ ይመስስለኛል። ወያኔ ገና ጫካ ሲገባ ጀምሮ የትግራይ ህዝብ ጠላት አማራ ነው ብለው በግልፅ በሰነድ አስቀምጠዋል ። ሥለዚህ ሀብትን ብቻ ዒላማ ያደረገ ዘረፋንና በተራ ቂም በቀል በመነሳሳት ሆን ብሎ በመግደል ንብረቱን መዝረፉ ጉዳቱ አንድ አይነት ነው ብሎ መናገር በጣም ያስተዛዝባል። የህወሃት ወንበዴ የማፍያ ቡድን በአማራ ላይ ያለውን ጥላቻ ያስጠኑት የውጭ ባዕዳን ኃይሎች እና ለጊዚያዊ ፍርፋሪ ብለው ለጣሊያን ያደሩ ባንዳ የወያኔዎቹ ወላጆቻቸው ናቸው። ይህንን ደግሞ እነታማኝ በየነ ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ከመውረራቸው በፊት በትግራይ ክልል ከአውሮፕላን ላይ የበተኑትን ፀረ አማራ የሆነ የቅስቀሳ በራሪ ወረቀት በማስረጃ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።

ስለሆነም ለም መሬትንና ማዕድንን ስለፈለጉ ብቻ ማፈናቀልን እና ታሪካዊ ጠላታችን ነው ብለው በአደባባይ ያለይሉኝታ የሚገልፁትን ነገድ በአገሪቱ በአራቱም አቅጣጫ ሲመቻቸው በመግደል፣ሳይመቻቸው በሌሎች ነገድ በማስገደል እና የተረፈውን በብዛት ማፈናቀል በጣም የተለያዮ ናቸው። ሥለእውነት እንነጋገር ከተባለ ከአማራ ውጭ የትኛው ነገድ ነው ሆን ተብሎ ኤችአይቪ(HIV) እየተወጋ እንደቅጠል የሚረግፈው? ከበሽታው የተረፉትን የአማራ ሴቶች እህቶቻችን እስከወዲያኛው እንዳይወልዱ ያለፈቃዳቸው ክትባት እተሰጣቸው መውለድ ያልቻሉ እስኪ ንገሩን እነማን ናቸው? የሚወለዱ ህፃናት ሥለሌሉ ትምህርት ቤቶች የሚዘጉበት ክልል የቱ ይሆን? እንደነ ዶ/ር አሰፋ ነጋሽ ጥናት የአማራውን ቁጥር ለመቀነስ ከየትኛውም ክልል በይበልጥ እንደሜሪ ስቶፕስ(Mary stops) የመሳሰሉ ስለቤተሰብ እቅድ የሚያስተምሩ ድርጅቶች በአማራው ክልል በየሰፈሩ የበዙበት ምክንያት ከቶ ለምን ይሆን? ወያኔ በራሱ የመገናኛ ብዙሀን በህዝብ ቆጠራ ሪፓርት ላይ እንዳመነው 2.5 ሚሊዮን አማራ የት እንደደረሱ አልታወቀም የተባለለት ነገድ ከቶ የትኛው ይሆን? እራሱን እንደ እንጨት እየማገደ በደምና በአጥንቱ የአገሩን ዳር ድንበር አስከብሮ ሌሎችንምእንዳላስከበረ፣ከሌሎች ነገዶች ጋር እየተጋባ እንዳልተዋለደ በፈጠራ የውሸት ታሪክ በተለያዮ ክልሎች " አማራ ያየህ ጠላት አየህ " እየተባለ የሚዘመትበት ሌላ የትኛው ነገድ ነው? ፍርዱን ለእነፕሮፌሰር ሳይሄን በአለም መጨረሻ ሥለእውነት ለሚፈርደው ብቻ ሳይሆን እራሱም እውነት ለሆነው ለአብ ልጅ፣ ለድንግል ማርያም ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ እተዋለሁ።

2፦የአማራን ጉዳይ በሚመለከት በተደጋጋሚ ለቀረበላቸው ጥያቄ በተለያዮ የኢትዮጵያ ቦታዎች እየተዘዋወሩ በቂ ጥናት እንዳካሄዲና ወሎ አካባቢ አንዱን የእስልምና እምነት ተከታይ አማራ ነህ ወይ? ብትሉት አይደለሁም ብሎ ይሸሻል። በተለያየ አካባቢም ያገኙት መልስም ተመሳሳይ ስለሆነ አማራ ማለት ክርስትያን ማለት ነው ካሉ በኃላ ይህንን በሚመለከት ያልተረጋገጠ ወሬ ይዞ ከመሮጥ " የክህደት ቁልቁለት " የሚለው መጽሐፋቸውን ህዝቡ ቢያነበው በቂ መልስ ያገኝ ነበር ብለዋል።

በመጀመሪያ መጽሐፉን የማንበቡ እድል ላልገጠመን " የክህደት ቁልቁለት "በሚለው መጽሐፋቸው ላይ አማራን በሚመለከት ምን እንዳሉ ሲጠየቁ ቢነግሩን ኖሮ በቂ መልስ በሆነ ነበር። ሆኖም ፈልጉና አንብቡት ከማለት ውጭ ሊነግሩን ፈቃደኛ አልነበሩም። ሌላው አሁን ላይ ሆኖ " ድሮ አማራ ማለት ክርስትያን ማለት ነበር " ማለት ለእኔ ለተፈጠረው ወይም ለሚፈጠረው ችግር እራስን ለመሸንገል ካልሆነ በስተቀር ለችግሩ መፍትሄም አይሆንም ባይ ነኝ። ዛሬ የበሬን ቆዳ ሸጠን ዶሮ እንክዋን መግዛት በማንችልበት ዘመን ላይ ተቀምጠን " ድሮ እኮ በግ በአንድ ብር ገዝተን፤ መልሰን ቆዳውን በአንድ ብር በመሸጥ ስጋ በነፃ እንበላ ነበር " እንደማለት ነው። እውነታው አማራ ምንም ይሁን ምን፣ ነበረም ተባለ አለ በወረንጦ እየተለቀመ እየታደነ በመገደል ላይ ይገኛልና ገዳዮቹ ፈልገው ያላጡትን ነገድ፤ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ግድያን እቃወማለሁ የሚለው ወገን የሚገደለውን አጣሁት ማለቱ ከቶ ሚስጢሩ ምን ይሆን? ለዚያውም የሚገደለው ወገን አለቅን እያለ እየተጣራ። ከዚህበተጨማሪ እኔ በእድሜዬ ትግራይ ውስጥ ያለን ክርስትያን አማራ ነው ሲባል ሰምቼአላውቅም።ኦሮሞውም፣ጉራጌውም፣ሌላው ሌላውም በነገዱ ስም ይጠራል እንጂ ክርስትያን ስለሆኑ ብቻ አማራ ተብለው ሲጠሩ አልሰማንም። በይበልጥ ግልፅ ለማድረግ እንዲረዳን ትግራይ ውሰጥ ያለ ክርስትያን አፉን የሚፈታው በትግርኛ ሲሆን በተጨማሪ አማርኛ ይናገራል። በሌሎችም አካባቢ የሚገኙ ክርስትያኖችም የሚናገሩት የራሳቸውን ነገድ እና አማርኛም ጭምር ነው። አሁን ግን በግንባር ቀደምትነት ዒላማ እየሆነ ያለው አማርኛ የአፉ መፍቻ ተናጋሪ የሆኑት ላይ ነው። ይህ እውነታ እንዳለ ሆኖ እነ መለስ ዜናዊ፣አቦይ ሥብሃት፣ተፈራ ዋልዋ፣ታምራት ላይኔ.....ወዘተ ለአማራ ያላቸውን ጥላቻ ከልባቸው ሞልቶ ስለተትረፈረፈ መቆጣጠር አቅቶአቸው በመገናኛ ብዙሃን ሳይቀር ሲደነፉ እየሰማን አማራ ማለት ክርስትያን ማለት ነው ማለት በተለዬ መልኩ በዚህ ነገድ ላይ የሚደርስን ግፍ ለማዳፈን የሚደረግ ጥረት ያስመስላል።

3፦በጣም የገረመኝና እስካሁንም ድረስ ለማመን የከበደኝ ነገር ከኢትዮጵያ ተቆርሶ ለሱዳን ስለተሰጠው ለም መሬት የሚያውቁት ነገር እንዳለ ፕሮፌሰሩ ተጠይቀው የሰጡት አስደንጋጭ መልስ ነው " ይሄን በሚመለከት አሜሪካን አገር የሚኖሩ ጎንደሬዋች እኔን ስለጉዳዮ ጥናት ስላደረክ ማስረጃ ካለህ ብለውኝ ነበር ግን ያደረጉት ነገር የለም። አሁንም ይሄ ለጎንደሬዎቹ ቀላል ነው። ቁጭ ብሎ ድንበሩ ለሱዳን ተሰጥቶዋል ወይስ አልተሰጠም ከማለት እያንዳንዱ ጎንደሬ አምስት፣አምስት ዶላር አዋጥተው አንድ ሰው ቢልኩ ማረጋገጥ ይቻሉ ነበር " ሲሉን የተወሰንን ሰዎች ስሜታችንን መቆጣጠር ስላቃተን "በመሠረቱ ድንበሩ የኢትዮጵያ ነው፣ የተወሰደውም ከጎንደር ብቻ ሳይሆን ከጎጃምና ከጋምቤላም ጭምር ነው፣ ግን እርስዎ እንዳሉት ለምን ጎንደሬው ብቻ ያዋጣል?ለምን እርስዎም ጭምር አያዋጡም?ለምን ጉራጌው፣ ኦሮሞው.....ወዘተ አያዋጣም? "ሲባሉ "ከረጠበው ላይ ሸናችበት" እንዲሉ እንደቀልድ አሁንም እደግመዋለሁ ብለው ያንኑ ቃል በቃል ደግመውታል።
እዚህ ላይ ሳልገልፅ የማላልፈው ነገር ይህን ድንበር በሚመለከት በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜም ንጉሱ ድንበሩን ለሱዳን ሰጡ እየተባለ ይወራ ስለነበር አንድ የቡልጋ አካባቢ ሰው መጥተው ስለጉዳዮ ሲጠይቁኝ " እርስዎ የቡልጋ ሰው ታዲያ ምን አሳሰበዎ "እንዳልዋቸውና እሳቸውም " ዳሩ ሲነካ መሃሉ ዳር ይሆናል " ብለው እንደመለሱላቸው ለተሰብሳቢው ገልፀውልናል። እንደእኔ አስተያየት ይሄንን ንግግር የተናገሩት ሳያስቡት ነው። ምክንያቱም ፕሮፌሰር መስፍን ለቡልጋው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የመለሱላቸው መልስ ፤ ፕሮፌሰሩ ዛሬ ለእኛ የነገሩን እቅዋማቸው የዛሬ አርባ አመት ጀምሮ በልባቸው ተቀብሮ አብሮዋቸው እንደነበረ የሚያመለክት ስለሆነ ነው። እንደፕሮፌሰሩ አባባል የጎንደሬው የድንበርም ሆነ ሌላ ችግር የሌላውም ሁሉ ኢትዮጵያዊ ችግር ካልሆነ፤ ከሞተው የወያኔ ጠቅላይ ሚ/ር መልስ ዜናዊ "የአክሱም ሀውልት ለወላይታው ምኑ ነው?......" ንግግር ፕሮፌሰሩ በምን ተለዮ? በባድሜ የድንበር ቸግር ሆን ተብሎ ፈንጅ ጠራጊ እንዲሆኑ ከፊት ግንባር ያሰለፉዋቸው 80,000 ኢትዮጵያውያን የኦሮሞ፣አማራ እና የሌሎች አካባቢ ተወላጆች መሆናቸውን እውን ፕሮፌሰሩ ሳያውቁ ቀርተው ነው? እኔ እንደራሴ አመለካከት ፕ/ር መስፍን ከአማራ ነገድ ጋር በተያያዘ የፈጠራቸው አምላክና እራሳቸው ብቻ ወይም ደግሞ በአስተዳዳጋቸው ዙሪያ አብረው የነበሩም ጭምር የሚያውቁት የሆነ ነገር እንዳለ ይሰማኛል።
በአጠቃላይ የፕ/ር መስፍን የፐርዝ ጉብኝት ሲገመገም የመጡበት አላማ ያልታወቀበት እና ከመድረክ ለሚነሱ ጥያቄዎችም አጥጋቢ መልስ ያልተሰጠበት ነበር ስል በርግጠኝነት ነው።ሌላው ቀርቶ የጋምቤላ ተወላጅ የሆነች እህት ተንስታ " የኢትዩጵያ ሁኔታ ስለሚያስፈራ ወደፊት ስለኢትዮጵያ ምን ቪዥን(vision) አለዎት? ስትላቸው ምንም የለኝም ብለው የሌሎቹን ባላውቅም እኔን ግን በጣም ስላስገረሙኝ " የጉዞዎት እላማ ምንድን ነው? ቢባሉ መልስዎት ምን ይሆናል? በውጭ አገር የምንገኘውን ኢትዮጵያውያንን ተስፋ ለማስቆረጥ ነው ወይ የሚል አንድምታ አያሰጥቦዎትም ወይ?"ብዬ ጠይቂያቸው ነበር ግን እንደተለመደው መልስ አልሰጡኝም። ማጠቃሊያ በኢትዮጵያ እንድነት ለምታምኑ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፤ አማራ እንደማንኛውም ሌሎች ነገዶች ሁሉ ነበረ፤ እስከአለም ፍፃሜም እግዚአብሔር እንደፈቀደለት እንደሌሎች ወንድሞቹ ይኖራል። ሌሎቹ ውንድሞቹ እንዳይደርሱለት ወይም የሚደርስበትን ችግር ለማደብዘዝ እያለ የለህም፤ በተለዬ መልኩ እየተገደለ ችግርህ እኩል ነው እየተባለ እየሰማን ነው። አንድ ሰው በተሰጠው የዘመኑ ህገመንግስታዊ መብቱ ተጠቅሞ እኔ ስለሌለሁ ከዛሬ ጀምሮ እንዳሌለሁ ቁጠሩኝ ማለት እየቻለ፤ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠርን አንድ ባለታሪክ ህዝብ ፈፅሞ የለህም ማለት የአመቱ ብቻ ሳይሆን የሚሊኒዮሙም ታላቅ ድፍረት ይመስለኛል። በኮሚኒዝም ማቆጥቆጥ ዋዜማ የራሺያ ኦርቶዶክስ ካህናት ነጭ እና ቀይ ለባሽ በሚል ተለያይተው ሲናቆሩ በስተመጨረሻ ሌኒን ከነተከታዮቹ መጣና አንተም ነጭ እትለብስም፤አንተም ቀይ አትለብስም ብሎ ቤተክርስትይንን እስከማዘጋት ደርሰው እንደነበር አንድ ሰባኪ ያስተማረውን አስታወሰኝ። ዛሬ ያለን ነገር አለ ፤ የለም እያባባሉን ስያጨቃጭቁን ጠላቶቻችን ግን እኩይ ሥራቸውን ለሰክንድ እንኩዋን አላቆሙም። የተከበሩ ውድ ፕ/ር እርስዎ የማይወዱት ነገር ካለ አልወድም ይባላል እንጂ የለም አይባልም። እየተገደልኩና እየተፈናቀልኩ ነው እባካችሁ ድረሱልኝ እያለ የለህም ማለዎ" ከባለቤቱ ያወቀ ምንትስ ነው " የተባለውን ያስመስልብዎታልና አንድ እና ሁለት የወሎ እስላም ብቻ ጠይቀው
በእርግጠኝነት ከመናገር ይልቅ ወይ በሰፊው እየተዘዋወሩ በድጋሚ ጥናት ያልድርጉ፤ ወይም ደግሞ ንግግሮዎት ብዙዎችን ስላስቀየመን ደፍረው እንኩዋን ይቅርታ ባይጠይቁን ዝምታም እኮ ወርቅ ነው ። እንደአባቶቻችን ዘወትር ስምህን የምንጠራው ፤ አልፋና ኦሜጋ የሆንክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እንደኛ ሃጢያት ሳይሆን ስለቅዱሳን አባቶቻችን ብለህ፤ከሁሉም በላይ ከሰው ወገን ሁሉ መርጠህ ስላከበርካት ስለእናትህ ስለቅድስት ፤ድንግል ማርያም ብለህ ከዚህ ሁሉ መዓት ታደገን፤ አሜን መላከፀሐይ ኃይሌ ከምዕራብ አውስትራሊያ ፐርዝ

No comments:

Post a Comment