ያለፉትን 50 እና 60 ዓመታት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታሪክ በአንክሮ የተከታተለ ሰው በውል እንደሚረዳው፣ 'የኢትዮጵያ አውራ ችግር መደባዊና ብሔራዊ ጭቆናዎች ናቸው፣' የሚለውና ድምፅ ያልተቆጠረበት ፣ ነገር ግን አብዛኛውን ቀለም-ቀመስ ትውልድ የገዛ አስተሳሰብ እንደነበር ይረዳል። ገዥው መደብና ጨቋኙ ብሔርም 'ዐማራ' እንደሆነ ያላንዳች ማመንታት እንደ ደረቅ ሃቅ የተወሰደ መሆኑን ያጤናል። ይህን አባባል ከመቀበል አልፈው ፣ ዐማራውን ለማደን በመጀመሪያው ረድፍ ተሰልፈው ፣ መሣሪያ መልጠው ፣ ጎራዴ መዝዘው ፣ 'ዱርቤቴ' ፣ ያሉት እኒሁ አባቶቻቸው 'በገዥነትና በጨቋኝ ብሔርነት' የተፈረጁት የዐማራው ልጆች እንደነበሩም ይገነዘባል። ዐማራን ለማጥፋት በታቀደው ዘመቻ ግንባር ቀደም ሆኖ 'ዐማራን የማጥላላት' ዘመቻውን 'ሀ' ብሎ ያስጀመረው 'ዋለልኝ መኮንን' የተባለው ወጣት የያኔው የቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበር። ዋለልኝ መኮንን ከዐማራው ልጆች መካከል ‘እንደ ጠማማ የመጥረቢያ እጀታ ሆኖ በማገልገል’ ሆኖ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የገዛ ወገኖቹ በዘረኞች እንዲጨፈጨፉ ጥርጊያ መንገዱን ከፍቷል። በመሆኑም የዐማራው የመጀመሪያ ጠላቱ ራሱ ዐማራው መሆኑንም ከድርጊቱ ይረዳል። ይህ 'ማንነትን የመሸሽ እና የሌሎች ጀሌ የመሆን አባዜ' ዛሬም የዐማራው ቀለም-ቀመስ ትውልድ ‘ባለህበት ሂድ’ ከመሆን ያልወጣ የዝንጉነት ደዌ እንደሆነም ልብ ይላል። በአንፃሩ ደግሞ አክራሪ ብሔርተኞች 'ዐማራው ጨቋኝ ብሔር ነው፤ የኢትዮጵያ አንድነት የተመሠረተው በዐማራው የበላይነት በኃይል ነው፤ ዐማራው የሌሎች ነገዶችንና ጎሣዎችን ባህል ፣ ቋንቋ ፣ ታሪክ ፣ እምነትና ማንነት አጥፍቷል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት እየተባለ የሚነገረው ውሸት ነው፤ ሕዝቡ የታሪክ ፣ የባህል ፣ የቋንቋና የሥነ-ልቦና አንድነት የለውም፤ ኢትዮጵያ የምትባል አገር "የብሔረሰቦች እስር ቤት ናት፤" ኢትዮጵያዊነት ዐማራው በሌሎች ላይ የጫነው ዕዳ ነው፤' በማለት የራሳቸውን ማንነት በአፍ መፍቻ ቋንቋ ልዩነት ላይ መሥርተውና ተደራጅተው፤ ‘የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት መሠረት ነው’ ባሉት የዐማራ ነገድ ላይ በትጥቅ የታገዘ የፕሮፓጋንዳ ቅስቀሣ የዘር ማጥፋት ጦርነት ከከፈቱበት በትንሹ ከአርባ ዓመታት በላይ እንደሆነ በግልጽ ይታወቃል።
ከእኒህ ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት በዘር ከተደራጁት ድርጅቶች መካከል ሻዕቢያ ፣ ሕወሓት ፣ ኦነግና በኦሮሞ ስም የተቋቋሙት ከስምንት የማያንሱ ድርጅቶች ፤ እንዲሁም በሶማሌ ፣ በአፋር ፣ በጉራጌ ፣ በሐዲያ ፣ በከንባታ ፣ በሲዳማ እና በሌሎችም ነገዶችና ጎሣዎች 'ነፃ አውጪነት' ስም የተደራጁት ከአንድ መቶ በላይ የሆኑ ደርጅቶች ፣ ሁሉም ማለት ይቻላል 'ጠላታችን ዐማራው ነው ' ብለው የተነሱ መሆኑ የታወቀና በተግባርም እየታዬ ያለ ሕያው እንቅስቃሴ እንደሆነ ማንም ያጣዋል አይባልም። የፖለቲካ ፕሮግራማቸውና ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው ሳይዛነፍ የሚናገረው ይኸንኑ ዕውነታ ነው። ስለዚህ የሌሎች ነገዶች ልሂቃን ዐማራን ለማጥፋት ሲያሤሩ ከግማሽ ምዕተ-ዓመት የማያንስ ጊዜ አስቆጥረዋል ቢባል ከሃቁ አይርቅም። የብሔርተኛ ድርጅቶች መሪዎች ዐማራውን 'በጨቋኝ ብሔርተኝነት' ፈርጀው ብቻውን አቁመው ለመቅጣት የዐቅም ውሱንነት እንዳለባቸው ሲረዱ ሌላ አጋዥ ኃይል ማግኘት እንዳለባቸው ተገነዘቡ። ስለሆነም አጋዥ ኃይሉን ለማግኘት የሚያበረክቱት ገጸ-በረከትና ሊያሣምኑበት የሚችሉበት ምክንያት ማቅረብ እንዳለባቸው አመኑ። በዚህም መሠረት የሚሰጡት ገጸ-በረከት የኢትዮጵያን ቅምጥ የተፈጥሮ ኃብትና የሰው ጉልበት እንዳሻው ለመበዝበና ለመጠቀም ፍላጎት ያለው የውጭ ኃይል መሆን አለበት። ይህንን ካደረጉ የአገሪቱን የግዛት አንድነት ባፈተቱት መልኩ መሸንሸን እንደሚችሉ ተማመኑ። ነገር ግን ከውጭ ኃይሎች ጋር ለመሞዳሞድ ይህንን በገጸ-በረከትነት መልክ የሚያቀርቡትን የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ኃብትና የዜጎቿን ጉልበት በቁጭትና በእልክ እምቢ ብሎ የሚሟገታቸው ማን እንደሆነ ሲያጠኑ፦
1. የኢትዮጵያዊነት ብሔርተኝነት ዋናው ኃይል ዐማራው ነው ፣ ስለዚህ መመታትና ዘሩ ከምድረ-ገፅ መጥፋት ይኖርበታል፤
2. ዐማራው የነጮችን የበላይነት አይቀበልም፣ ምክንያቱም በራሱ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ይመካል፤
3. በየካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ዐድዋ ላይ የአውሮፓን ቅኝ ገዥ ኃይል ቅስም ሰብሮ የመለሰ ዐማራው ነው፤
ስለዚህ በሚከተሉት የሐሰት መርሆዎች ላይ ተመርኩዘው የዐማራውን ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት ለማኮላሸት የዋሃንን የማነሁለያ ሥልቶችን ነደፉ ፦
1. "ኢትዮጵያዊነት ዐማራው በሌሎች ነገዶችና ጎሣዎች ላይ የጫነው ዕዳ እንጂ የቀሩት ጎሣዎችና ነገዶች የሚጋሩት የወል ዕሴት አይደለም፤
2. በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩት ነገዶችና ጎሣዎች (በእነርሱ አገላለፅ ብሔር/ብሔረሰቦች) የዐማራው ነገድ እስረኞች ፣ አገሪቱም የብሔረሰቦቹ እስር ቤት ናት ፤ በአገሪቱ ሕዝብም መካከል የታሪክ ፣ የባህል ፣ የሥነ-ልቦና ፣ የደምና የጋብቻ መተሣሠር የላቸውም፤
3. ኢትዮጵያ የምትባለዋ አገር በመጀመሪያ ሙሉ በሙሉ ፈርሣ ከዚያ በእኒህ ነገዶችና ጎሣዎች መልካም ፈቃድ እንደገና መሠራት አለባት፤" የሚሉ ናቸው።
MORESH WEGENIE AMARA ORGANIZATION ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት
8221 Georgia Avenue, Silver Spring, MD. 20910
Tel: (202) 230 - 9423 Fax:
2
“ላለቅስ ሲሻኝ መታኝ” ወይም “ሲሻኝ ጢስ ወጋኝ” የሆነላቸው ምዕራባውያንም ፣ በተለይም በዘመነ-አብዮት ፣ አገሪቱ
የሶቪዬት ኅብረት ጥገኛ ፣ የሶሳሊስቱ ዓለም ጎራ አባል በመሆኗ ፣ የኮሙኒዝምን መስፋፋት አጥብቀው የሚቃወሙ አገሮች በተለይም ዩ.ኤስ. አሜሪካ ከፀረ-ዐማራና ፀረ-ኢትዮጵያ ከሆኑት ቡድኖች ጎን እንዲቆሙ ሁኔታዎች የበለጠ አመቻቸላቸው። በመሆኑም በውስጥ በሻዕቢያ ፣ በሕወሓት እና በኦነግ የጋራ ቅንብር የተንቀሳቀሱ ፀረ-ዐማራ ድርጅቶች በምዕራባውያን ሁለንተናዊ ዕርዳታና ድጋፍ ኢትዮጵያንና የዐማራው ነገድ ዛሬ ለሚገኙበት ከችግር ያለፈ የሕልውና ጥያቄ ውስጥ እንደከተቷቸው ይስተዋላል። የኢትዮጵያዊነት የወል መገለጫ ዕሴቶችና ተቋሞችም ልክ እንደ ዐማራ የግል ዕሴቶች ተቆጥረው እንዲወገዙና አልፎ ተርፎም እንዲፈራርሱ ተደርገዋል። “የጨው ክምር ሲናድ ሞኝ ይስቃል ፣ ብልኅ ያለቅሳል፤” ሆኖ ፣ ሞኞቹ የጋራ ቤታቸው ሲፈርስ “የአባትህ ቤት ሲወረር አብረህ ውረር፤” ዓይነት የሆነባቸው ኃሣበ-ድውያን ወይም “ትኋን በላኝ ብሎ ቤቱን በእሳት እንዳቃጠለው” የዋህ ሰው የማፍረሱ ፊታውራሪዎች ሆነዋል። ኢትዮጵያዊነትን ለመበተን ብቸኛ መንገድ ሆኖ ያገኙትም እስከምንገኝበት ወቅት ድረስ በኢትዮጵያዊነት እንጂ በቋንቋ ትሥሥር ተደራጅቶ የማያውቀውንና ለመደራጀትም እንግዳና ገደል የሆነበትን የዐማራውን ነገድ ማጥፋት ቀዳሚው ተግባር አድርገው ይዘውታል። ከላይ እንደተጠቆመው እርሱን ለማጥፋትም መነሻ ምክንያት አድርገው የሚደረድሯቸው ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፦
1. ዐማራ ገዥና ጨቋኝ ብሔር ነው፤
2. ዐማራ ማንነታችን ያስካደ ፣ ቋንቋችን ፣ ባህላችንን ፣ እምነታችንና ታሪካችን ያጠፋ ነው የሚሉ ናቸው፡፡
የዐማራው ምሁራን እነዚህ ምክንያቶች ውሸትና ፈጠራ መሆናቸውን ችላ ብለው በአንድ በኩል ባለመደራጀታቸው ፣ በሌላም
በኩል የማርክሲዝምን አስተምህሮ የዐማራው ምሁራን እንደ ደረቅ ሃቅ ሲቀበሉት የሌሎች ነገድ ልጆች ግን የሥውርና ዘረኛ ዓላማቸው ማራመጃ ሽፋን አድርገው በመያዛቸው ዐማራውን በተበታተነ መልኩ ለጥቃት እንዲጋለጥ እንዳደረገው ሁኔታዎች ያረጋግጣሉ። ዐማራው የወላድ መካን ሆኖ ፤ ወይም “ወይራ ዶግ ይወልዳል” ሆኖበት በተናጠልና በወል ከመገደል ፣ ከመታሰር ፣ ከሥራ ከመባረር ፣ ከመሰቃየት ሊታደጉት አልፈለጉም። አልፎ ተርፎም ሕይወቱን ገብሮ ፣ አጥንቱን ከስክሶና ደሙን አፍስሶ ዘብ ሆኖ ባስከበራት በአገሩ በኢትዮጵያ በነፃነት በፈለገው ሥፍራ እንዳይኖር ከደቡብ ፣ ከምሥራቅና ከምዕራብ "መኖር አትችልም ፣ አገርህ አይደለም ፣ ወደ ክልልህ ሂድ፣' እየተባለ በቋንቋውና በዘሩ ምክንያት ተለቅሞ በመባረር ላይ ይገኛል። የዐማራው ምሁራን ይህንን ድርጊት እያዩ እንዳላዩ ሆነው ፣ ‘የአገሪቱ ዋነኛ ችግር ዐማራ ነው’ ተብሎ የዘር ማጽዳት ዘመቻ ተከፍቶበት እያለ ፤ በመሬት ላይ በማይታይ ፣ ነገር ግን በእነርሱ አዕምሮ ውስጥ ከፍተኛ ግንብ በሠራ 'ተምኔታዊ ኢትዮጵያዊነት' ስም ተሸብበው በአገሪቱ ላይ አሉ የሚባሉትን ችግሮች ሊፈቱ የሚፈልጉት የብሔረተኛ ድርጅቶች የፖለቲካ መሪዎች 'የአገሪቱ ቁልፍ ችግር ነው' ብለው ባመኑበት መንገድ ብቻ ነው። በሌላ አባባል ፣ የአማራ ምሁራን ችግሩን ለመፍታት የሚፈልጉት ፣ ችግሩን ፈጠረው በተባለው አስተሳሰብ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ ነው። የሌሎች ነገዶችና ጎሣዎች ልጆች 'የነገዳችንና ጎሣችን ዓይነተኛ የችግር ምንጭ ዐማራ የተሰኘው ነገድ ነው፤' ብለው በነቂስ አምነው በፀረ-ዐማራነት ተሰልፈው የዘር ጥቃት እያደረሱበት እያለ ፤ 'ኢትዮጵያዊነት የእኛ አይደለም ፤ የዐማራው ብቻ የግል ዕሴት ነው፤' እያሉ በዓለም አደባባይ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በሚጮኹበት ወቅት፤ የአገሪቱ የችግር ቋጠሮ ነው በተባለው መንገድ ችግሩን ለመፍታት መሞከር አስተሳሰቡ በራሱ ዕንቆቅልሽ የሆነ የችግር ቋጠሮ መሆኑን አለመገንዘብ ነው።
የሌሎቹ ነገዶች ልሂቃን 'የእኛ ችግር ዐማራ ነው' ካሉ ዐማራን በደመኛ ጠላትነት ፈርጀውታል ማለት ነው። ዐማራውን በደመኛ
ጠላትነት ፈርጀው ሊያጠፉት ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ደግሞ ቁጭ ብሎ ለችግሩ መፍትሔ ማፈላላግ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ለችግሩ
መፍትሔ የሚገኘው ፣ ሌሎች 'ችግራችን ነው' ብለው የፈረጁት ወገን ሰብሰብ ብሎ፣ 'በምን እና እንዴት ሆኖ ነው ዐማራው የሌሎች ነገድና ጎሣዎች ችግር የሆነው?' የሚባለው 'ዕውነት ነው ወይስ ውሸት?' ብሎ በመጠየቅ ተገቢውን መልስ ማግኘት ሲቻልና ለመፍትሔውም አዲስ አስተሳሰብና ወደፊት የሚያራምድ ገንቢ አመለካከት ስንላበስ ነው። ይህ ሳይሆን እንዲያውም 'ችግሩን ፈጠረው' በተባለው የኢትዮጵያዊነት አመለካከትና አስተሳሰብ መርሆነት የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ የሚያስጠብቅልን አይሆንም። ለዚህም ዐማራው የሚፈልገው 'ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት' እንዲጠበቁ ከፈለገ ፣ የማስጠበቂያ መንገዱ ያለውን ሁለንተናዊ ኃብት ሰብሰብ አድርጎ ፣ ኢትዮጵያዊነትን ከሚፈታተኑ ኃይሎች በአደረጃጃት ቢቻል ልቆ አልያም ቢያንስ አቻ ሆኖ መገኘት ሲቻል ብቻ ነው። ኢትዮጵያ የምትባል አገር እና ኢትዮጵያዊ የሚባል ዜጋ መኖር የሚችሉት አንዱ አጥቂ ፣ ሌላው ተጠቂ፤ አንዱ አባራሪ ፣ ሌላው ተባራሪ፤ አንዱ አሣዳጅ ፣ ሌላው ተሣዳጅ ሆኖ አይደለም። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት መኖር የሚችሉት ፣ የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭየሆነው በግለሰቦች ፈላጭ ቆራጭነት የሚዘወር የአገዛዝ ሥርዓት ሲወገድ ብቻ ነው። በግለሰቦች አምባገነናዊ አገዛዝ ከመማቀቅ ተላቅቀን ሥልጣን በሕዝብ ነፃ ፍላጎትና ተሣትፎ ከሚደረግ ምርጫ ሲመነጭ፤ ሰዎች በዘራቸው ሳይሆን በሰብዓዊነታቸው አስፈላጊው አክብሮት ሲቸራው፤ መንግሥታዊ ኃላፊነት በፖለቲካ ሽርክና ሳይሆን በችሎታና በውድድር ሲያዝ፤ አንዱ የሌላውን ኅልውና ፣ የመኖር መብትና ነፃነት አውቆ ሲቀበል፤ ግለሰባዊ ነፃነትና የግል ኃብት ባለቤትነት መብቶች ሕጋዊ ጥበቃ ሲያገኙ፤ ዜጎች በአገራቸው በየትኛውም ሥፍራ ተዘዋውረው የመኖርና የመሥራት መብታቸው ያላንዳች ገደብ ሲከበር፤ ለኢትጵያ አንድነትና ነፃነት ዋጋ የከፈሉ ዜጎች ተገቢ የሆነ እንክብካቤና ክብር ሲያገኙ ፤ ያኔ 'ኢትዮጵያ የምትባል አገር እና ኢትዮጵያዊ የሚባል ዜጋ አሉ' ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን። ዛሬ ይህ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ እያለንና ከጥንታዊ የጎሣ አኗኗር እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን አስከፊ ዘረኛ አገዛዞች (ናዚዝም ፣ ፋሽዝም ፣ አፓርታይድ) የሚያስንቅ አስከፊ የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ ሠፍኖ እያለ ፣ ስለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት መኖር መናገር የችግራችንን ክብደት ካለመገንዘብ የመነጨ ነው።
3
ዛሬ 'ኢትዮጵያ አለች ' እያሉ የሚናገሩ ሰዎች ፣ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባል አገር ሆና ያስመዘገበችውን የግዛት ስፋትና አዋሳኞችን የዘነጉ ፤ እንደ እነ አፄ ዐምደጽዮን ፣ እነ አፄ ሠርጸድንግል እና መሰሎቻቸው የነበሩት ራዕየ-ሠፊ መሪዎቻችን ያስረከቡንን የኢትዮጵያ ወርድና ቁመት የማያውቁ ፤ በጥቅሉ የታሪክ እና የጂኦግራፊ ማይምነት የጋረዳቸው ብቻ ናቸው። የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያዊነት መሠረቱ ባሕረ-ነጋሽ ተገንጥሎ ፤ አገራችን የ1 ሺ ኪሎሜትር ርዝማኔ ያለውን የቀይ ባሕር ምዕራባዊ ዳርቻ ባለቤትነት መብቷን ባጣችበት ፤ ከአምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ ለምና ድንግል የእርሻ መሬቷ ከዜጎቿ ተነጥቆ ለቱርክ ፣ ለሕንድ ፣ ለቻይና ፣ ለግብፅ ፣ ለሣዑዲ ዐረቢያ እና ለጅቡቲ ለ 99 ዓመታት በሊዝ በተሸጠበት፤ ከ80 ሺ ስኩየር ኪሎሜትር ስፋት የማያንስ የአገሪቱ ምዕራባዊ የወሠን ዳርቻ ለሱዳን በተሰጠበት፤ የኢትዮጵያዊነት መታወቂያ የሆነችው አረንጓዴ ፣ ቢጫ እና ቀይ ሠንደቅ ዓላማችን በላይዋ ላይ 'የሠይጣን አማኞች ምልክት በሆነው የፔንታግራም ምሥል ' በተበረዘችበት ፤ አልፎም ተርፎም አንድ የነበረው የአገራችን ሠንደቅ በዘጠኝ በተተካበት ሁኔታ ፣ 'ኢትዮጵያ አለች' ማለት የነበረንን ከመናገር ያለፈ የአሁኑን ነባራዊ ሃቅ የሚገልጽ አይደለም፤ ኢትዮጵያም የለችም። አለመኖሯንም ሟቹ የወያኔዎች መሪ መለስ ዜናዊ እንዲህ ሲል አስረግጦ ነግሮናል፦ "ኢንዱስትሪው በቱርኮች ፣ በሕንዶች እና በቻይናዎች በተያዘበት አገር አገር አለን ማለት አይቻልም። በዚህ ከቀጥልን ከጥቂት ዓመታት በኋላ አገር አልባ እንሆናለን።" በማለት በሕይወቱ የበመጨረሻ ቀናት ሃቁን ተናዝዟል፡፡
በግልጽ እንደሚታወቀው ዐማራው ኢትዮጵያዊ መሆኑ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። 'ኢትጵያዊ አይደለህም' ያለውም የለም። ሆኖም የሌሎች ነገዶችና ጎሣዎች ልሂቃን የሚሉት፦ "ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የዐማራው ዕሴቶች ናቸው፤ ኢትዮጵያዊነትን በእኛ (ሌሎች ነገዶች) ላይ የጫነብን ዐማራው ነው፤" ነው። በሌላ አባባል ብሔርተኞቹ ድርጅቶች የሚያራምዱት ግልፅ አቋማቸው፦ "ኢትዮጵያዊ ለመሆን ለመደራደር ዝግጁ የምንሆነው ዐማራው በእኛ ላይ ያደረሠውን ሁለንተናዊ ኪሣራ አሜን ብሎ ሲቀበልና ከእኛ በታች ሆኖ ሲገዛልን ብቻ ነው። ያለበለዚያ እስከዛሬ ዐማራ ያስጠበቃት አገር ለእኛ ምናችንም አይደለችም። እኛ ትግራዋይ ፣ ኦሮሞያዊ ፣ ኤርትራዊ ፣ ሲዳማዊ ፣ ሐዲያዊ ፣ ጉራጌያዊ፣ ከምባታዊ፣ ወዘተርፈ ነን፤” ነው። ይህንን ማለት ብቻ ሣይሆን የየራሰቸውን ሠንደቅ ዓላማ ሠቅለው ኢትዮጵያዊነትን ክደዋል። ስለሆነም 'ዐማራው በዐማራነቱ መደራጀት የለበትም’ የሚሉ 'ኢትዮጵያዊ እንጂ ዐማራ አይደለንም’ ባይ ምሁራን አመለካካታቸው እኒህን ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግንዛቤ ያላስገባ መሆኑን ሊያጤኑት ይገባል። ይህ ዓይነቱ የየዋሃን አቋም በኢትጵያዊነት ፍቅር የተመላ ሆኖ ከመታየት ውጪ፣ ለዐማራ ጥቃት የማይደርስ ፣ በአንፃሩ ዐማራውን ለከፍተኛ ጥቃትና ፍጅት የሚያጋልጥ በመሆኑ ፣ ከቻሉ በዐማራው ስም የተደራጁ ወገኖችን ቢረዱ፤ ካልቻሉና ካልፈለጉ ደግሞ ቢያንስ ተደራጅተው ለዐማራው መብት የቆሙ ኃይሎችን እንቅፋት ባይሆኑባቸው ይመረጣል። “ሊነጋ ሲል ይጨልማልና” ዛሬ በዐማራው ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ላይ ያጠላው ድቅድቅ ጨለማ ፣ ነገ በዕውነተኛ የዐማራው ልጆች ትግል ጨለማው ሲገፈፍ ለትዝብት እንዳንጋለጥ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን መሆኑን ማስገንዘብ አጉል ድፍረት አይደለም።
ስለዚህ ዐማራነትን ክዶ እና አዋርዶ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት የቆሙበትን መሬት አለማወቅ ብቻ ሳይሆን ፣ ‘ችግር ነው’ በተባለው መንገድ ችግሩን ለመፍታት ከመሞከር የማያልፍ ፣ ከዚያም በላይ ችግሩን ማባባስ መሆኑን አለመረዳትም ነው። የኢትዮጵያ ችግሮች የሚፈቱት ዐማራው ራሱን ዐውቆ ኅልውናውን ለማስጠበቅ የበቃ እና የማይገፋ ኃይል ሆኖ መውጣት ሲችል እንዲሁም ሌሎች እርሱን ለማጥፋት የተነሱ ኃይሎች ሊያጠፉት እንደማይችሉ እንዲገነዘቡ ሲያደርግ ብቻ ነው። ይህ ገሃድ ዕውነታ ደግም የዐማራውን መደራጀት የግድ አስፈላጊ ያደርገዋል። ዓለማችን የምትገዛው በተደራጀ ኃይል ነው። መደራጀት ማለት ደግሞ ከኃሣብ አንድነት የሚነሣ ሆኖ የመረጃ ፣ የዕውቀት ፣ የገንዘብ ፣ የሰው ኃይልና የድርጊት እንቅስቃሴን በተቀናጀ መልኩ ለውጤት የሚያሰለፉበት የብቃት መገለጫ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ዐማራው ሁለንተናዊ ዐቅምና ችሎታው እንዳለው ይታወቃል። ያጣው መሠረታዊ ነገር የአብዛኞቹን የዐማራውን ልሂቃን ፖለቲካዊ ፈቃደኝነትን ነው። ሆኖም በጥቂቶችም የዐማራው ልጆችም ቢሆን የመደራጀቱ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የተጀመረ ነገር ከዳር መድረሱ የማይቀር ነው። ዐማራው ተደራጅቶ በቅድሚያ ኅልውናውን ያስጠብቃል ፤ ቀጥሎም የኢትዮጵያን ዳግም ትንሣዔ ዕውን ያደርጋል።
http://www.moreshwegenie.org/
http://www.moreshwegenie.org/
ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደግ !
ፈለገ አሥራት የትውልዳችን ቃል ኪዳን ነው !
No comments:
Post a Comment