ጌታቸው ኃይሌ
እንደምሰማውና እንደማነበው ከሆነ፥ ከአንድ ዓመት በኋላ በሚደረገው ምርጫ የወያኔ ተቃዋሚ ፓርቲዎች
በምርጫው ይሳተፋሉ። ይኸ እንዴት እውነት ሊሆን ይችላል? ባለፉት ምርጫዎች ምን እንደሆነ
ረሥተነዋል እንዳንል፥ ለመርሣት የሚያበቃ ጊዜ የለንም። ምርጫ 97 ላይ ቅንጅቶች፥ “አንዳንድ ቦታ
ተጭበርብረናል፤ ይመርመርልን፥ ወይም እነዚያ ቦታዎች ምርጫው ይደገምልም” ሲሉ፥ ወያኔዎችም፥
“እኛም ተጭበርብረናል፤ መመርመሩንና ድጋሚውን ምርጫ እኛም የምንመኘው ነው” ብለው፥ ሁሉም
ተመረመረ፤ ምርጫውም ተደገመ። በሁሉም ቦታ፥ የነሱ ተወዳዳሪ የተሸነፈበትንና ቅንጂት ያሸነፈበትን
አውራጃ ሳይቀር፥ ወያኔዎች ወሰዱት። ሕዝቡም ቢቆጣ፥ ከቁም ነገር የቈጠረው አልነበረምና የማታ
ማታ ቁጣውን ዋጥ አድርጎ ተኛ።
የተቃዋሚ ቡድኖች በሚቀጥለው ምርጫ ለምን ለመሳተፍ እንደወሰኑ ከመሪዎቻቸው የሰማሁት ነገር
የለም። ስገምተው ግን፥ እርግጥ ለመሳተፍ ከወሰኑ ምክንያታቸው ከሁለት አንዱ ወይም ሁለቱም መሆን
አለበት፤ ወይ እንዲሳተፉ የሚያስገድዳቸው ወያኔያዊ ተጽዕኖ አለባቸው፥ ወይም ወያኔዎቹ ምርጫውን
ነፃና ፍትሐዊ ሊያደርጉት ይችላሉ የሚል ተስፋ አድሮባቸዋል። እኔ ግን ለውጥ አለ ብዬ ለማመን
እቸገራለሁ። ምክንያቱም መለስ ዜናዊ የሞተው ፖሊሲው እንዳይለወጥ ኀይለ ማርያም ደሳለኝን አደራ
ብሎ ነው። እንደሰማሁት ኀይለ ማርያም ደሳለኝ ክርስቲያን ስለ ሆነ፥ በአደራ-በላነት አይጠረጠርም።
ለማንኛውም፥ በምርጫው የሚሳተፉ ከሆነና በምርጫው ተስፋ ከጣሉበት፥ ተመሳሳይ ራእይ ያለቸው
ቡድኖች በአንድነት ለመሥራት ፈጠን ብለው መስማማት ይኖርባቸዋል። እስካሁን አዲስ አሳብ
አላቀረብኩም። እንዲያውም ቅንጅት የተወለደው በዚህ ምክንያት ነበር። አሁንም የመላው ኢትዮጵያ
አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና እንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) አንድ አማራጭ
ኀይል ሆነው ለመገኘት የሚያስማማቸው የቅድመ ውሕደት የመግባቢያ ሰነድ በይፋ ወጥቷል። የሰማያዊ
ፓርቲ ራእይ መሪ ያሰማቸውን ቃለ ምልልሶች እንዳዳመጥኩት ከሆነ፥ ከነዚህ ሁለት ፓርቲዎች
ለኢትዮጵያ የተለየ ፍላጎት የለውም። ሁሉም በኢትዮጵያ አንድነትና በሙሉ የዲሞክራሲ መዋቅሮችና
መቆሚያዎች ያምናሉ። የጎሳዎች የባህል መብት መከበርን ተቀብለው፥ የጎሳ ፖለቲካን ያወግዛሉ። እነዚህ
ቡድኖች በሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ ለማስወገድ የተዘጋጁት በእነዚህ ባነሣኋቸው መሠረታዊ ነጥቦች
ስለሚለያዩ ነው።
የምተቻቸው ተቃዋሚ ቡድኖች ከወያኔዎች ጋር በሌላም ነገር እንደሚለዩ ተስፋ አለኝ። ወያኔዎች
የመጡት ሲገዙ ለመኖርና ራሳቸውን ለመጥቀም ነው። የተቃዋሚዎቹ ጥረት ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ
ለመጥቀም ነው። ነፃና ፍትሐዊ በሆነ ምርጫ ወያኔዎች ቢሸነፉ፥ ሽንፈቱን አይቀበሉም፤ እነዚህ ቡድኖች
ግን ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ መሆቱ በገለልተኛ አስመራጭ ድርጅት ከተረጋገጠላቸው ሽንፈታቸውን
በደስታም ባይሆን በጸጋ ይቀበሉታል።
2
የተቃዋሚዎቹ ራእይ እንደ እምነቴ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመጥቀም ከሆነ፥ በፍጥነት አንድ ግምባር ለመፍጠር ቢነሡ፥ ብዙ ችግር ሊገጥማቸው አይችልም። ከልብ ካለቀሱ ዕንባ አይገድም እንዲሉ፥ ከልብ ከጣሩ የአንድነት መንገድ አይገድም። ለምሳሌ፤
1. አባሉ ሕዝብ መሪውን ስለሚከት መሪዎቹ ብቻ የዝግ ስብሰባ አድርገው አንድ አመራርና አንድ የፓርቲ ስም ሊፈጥሩ ይችላሉ፤ ሕዝቡም በውሳኔያቸው የማይስማማበት ምክንያት አይኖረውም። ለኢትዮጵያ የሚያስብና ውገናን የሚኮንን “የእኛ እገሌ ይምራን” አይልም። ዲሞክራሲ በሰፈነበት ሀገር የሚደረገውን ስናይ፥ ፓርቲዎች በመሪ ፍለጋ ላይ ብዙ ይጥራሉ።
2. ይኼ ካልሆነ፥ መሪዎቹ የዝግ ስብሰባ አድርገው፥ ወደ አንዱ ፓርቲ ይጠቃለሉ። ለኢትዮጵያ የሚያስብና ውገናን የሚኮንን ድርጅት “ወደእኛ ፓርቲ እንጠቃለል” ብሎ አያስቸግርም። “በሥሩ ብንጠቃለል የበለጠ ኀይል ያገኛል የሚሉትን” አለዚያ በዕጣም ቢሆን አንዱን ይምረጡ። ዲሞክራሲ በሰፈነበት ሀገር የሚደረገውን ስናይ፥ አንድ ተወዳዳሪ መዳከሙን ሲያይ፥ ተከታዩን ሕዝብ “ወደ እገሌ ሂዱ ብሎ” አስናብቷቸው ይወጣል። እርግጥ፥ እምቢ የሚልም አለ፤ ግን እሱ መሰሉን ፓርቲ ይጐዳና ሲወቀስ ይኖራል።
3. ይኼም ካልሆነ፥ ፓርቲዎች እርስ በርሳቸው የሚወዳደሩበት ቀዳሚ ምርጫ ያድርጉ። ይኸንን አሜሪካ “Primary election” ይሉታል። ቡድኖች በየምርጫው ቦታ የራሳቸውን ተወዳዳሪ አቁመው ያወዳድሯቸው። አንዱ ማሸነፉ አይቀርም። በጠቅላላው ምርጫ ጊዜ የፓርቲዎቹ ሁሉ ተወዳዳሪ ያ በቀዳሚ ምርጫ ያሸነፈው ይሁንና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁሉ ይደግፉት።
ለኢትዮጵያ ተመሳሳይ ራእይ ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአድነታቸውን ዐዋጅ ሲያሰሙ የሚደርሳቸው የሞራልና የገንዘብ ድጋፍ ፥ የአባልነት ማመልከቻን ጨምሮ ሲጎርፍ ይታየኛል።
No comments:
Post a Comment