Wednesday, October 5, 2016

ምን ስም ይሰጠዋል?

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት             ማክሰኞ መስከረም ፳፬ ቀን ፪ሺህ፱  ..              ቅፅ   ቁጥር 

በዓለም ላይ የነበሩና ያሉ ዘረኞች፣ ግፈኞችና አምባገነኖች የተለያዩ ምክንያቶች እየፈለጉ ሕዝብ ገድለዋል፣ አስረዋል፣ አሰቃይተዋል። በዚህም ተግባራቸው፣ « ናዚ፣ ፋሽስት፣ ጨፍጫፊ፣ አረመኔ» ወዘተርፈ ተብለዋል። ከእነዚህ እጅግ በከፋ ሁኔታ የዘረኛው የትግሬ ወያኔ ቡድን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በአጠቃላይ፣ በተናጠል ደግሞ በዐማራው፣ በኦሮሞው፣ በአኙዋኩ፣ በኑኤሩ፣ በሶማሊው፣ በአፋሩ፣ በሲዳማው ወዘተርፈ ነገዶች ላይ የሚፈጽመው ሁለንታናዊ ግፍ በምን ቃላት ሊገለጽ እንደሚችል የቋንቋ ሊቃውንት ሊያስቡበት የሚገባ ነው። ከላይ የተገለጹት የጭካኔ እና የአረመኔነት ስያሜዎች በፍፁም የወያኔን ማንነትና ዕውነተኛ ባሕሪ አይገልጹትም። ይገልጹታል ከተባለም ተለምዶአዊ በመሆኑ፣ የቃሎቹ የያዟቸው ጽንሰ ሀሳቦችና ድርጊቶቹ የሚጣጣሙ አይደሉም። በምንም ታምር ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የኖረ በዓልን ለማክበር ቄጤማ ይዘው በተቀመጡ ሽማግሌዎች፣ ሕፃናት፣ ሴቶችና ወንዶች ላይ ከሰማይ በአውሮፕላን፣ ከምድር በመትረየስ የሞት ዶፍ ማውረድ በምንም መመዘኛ ምክንያታዊነት የለውም። እገዛዋለሁ የሚለውን ሕዝብ፣ ያውም «ለብሔር/ብሔረሰቦች እኩልነት» ቆሜአለሁ እየለ ጧት ማታ በሚምል የገዛ ወገኑን የደበደበ አረመኔ የሚባል ቡድን በዓለም ታሪክ ስለመኖሩ በእርግጠኝነት ለመናገር አይቻልም።
የትግሬ ወያኔ ፣ በሀሰት ያሰራቸውን የኅሊና እስረኞች በራሱ የፍርድ ሂደት ቢያቀርባቸው አደረጉ ያላቸውን ስለማድረጋቸው ማስረጃ ማቅረብ አልቻለም። ስለሆነም እስካሁንም የሚሠራው ትያትር ሕዝቡ ያወቀበት መሆኑን በመረዳቱ፣ በቂልንጦ፣ በጎንደርና በደብረታቦር እስር ቤቶች በቁጥጥሩ ሥር ያሉትን እስረኞች በእሳት ለኩሶ፣ ንፁሐን ዜጎችን አጠቃ፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ጨረሰ። እስረኞችን የወባ መድኃኒት ነው ብሎ፣ ማላታይን አጠጥቶ ፈጀ። ኤች አይ ቪ ቫይረስን በመርፌ እየወጋ ሕዝብ ጨረሰ። የዐማራውን ነገድ ቁጥር ለመቀነስና ፈጽሞ ለማጥፋት ባለው ዕቅድ፣ ዐማራ ሴቶችን ለይቶ በወሊድ ቁጥጥር ስም ታማሚና መካን አደረገ። የዐማራ ወንዶችን የመራቢያ አካላቸውን እየቀጠቀጠ፣ ሰዎችን በቁማቸው ጉድጓድ ውስጥ ከቶ አሰቃየ። እንዲህ ዓይነት ፍፁም አረመኔና ፋሽስት የተባለ ቡድን ከወያኔ በቀር የኢትዮጵያ ታሪክ አያውቅም።
ግፈኛውና ዘረኛው የትግሬ ወያኔ ቡድን ባለፈው እሑድ ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓም በደብረ ዘይት ከተማ የእሬቻን የኦሮሞ ባህላዊ በዓል ለማክበር ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተሰበሰቡ ንፁሐን ዜጎች ላይ የፈጸመው ቃላት ሊገልጹት የማይችሉት የጅምላ ግድያና ፍጅት ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት በጽኑ ያወግዛል።
ግድያው ወያኔ ለ25 ዓመታት ካደረጋቸው የሚለየው፣ ላለፉት ዘጠኝና አሥር ወራት በተከታታይ በሐረርጌ፣ በወለጋ፣ በጅማ፣ በአርሲ፣ በኢሉባቡር፣ በሸዋ፣ በጎንደር፣ በጎጃምና መሰል ክፍለሀገሮች የዘለቀው ሕዝባዊ እንቢተኝነትና የዐማራው የማንነት ትግል ገዝፎና ገፍቶ ምኒልክ ቤተመንግሥት በራፍ ላይ በመድረሱ፣ በወያኔና አሽከሮቹ ላይ የፈጠረው የፍራት መጠን ከፍተኛ መሆን በአልሞት ባይ ፍርግጫ ያላቸውን የመጨረሻ ኃይል ያሳዩበት መሆኑ ነው። ነፃነትን የተጠማ፣ ማንነቱን ለማስከበር ቆርጦ የተነሳን ሕዝብ፣ ይህ ዓይነቱ የፈሪ በትር የታጋዩን ሕዝብ ወኔ ያጎለብታል እንጂ፣ እንደማይቀንሰው የኢትዮያ ሕዝብ ደጋግሞ ለዓለም ማኅበረሰብ አሳይቷል። በመሆኑም የትግሬ ወያኔ ፍርሀት በወለደው ስሜት በእሬቻ በዓል ተሳታፊዎቹ ላይ የወሰደው ዘግናኝና ሰቅጣጭ የጅምላ ፍጅት፣ የወያኔን በቃላት ሊገለጽ የማይችል ጭካኔ ከማሳየት በቀር፣ የሥልጣን ዕድሜውን ያራዝማል ተብሎ አይታሰብም። በአንፃሩ የወያኔን ዕድሜ በእጅጉ የሚያሳጥር፣ የሕዝቡን ነባር አንድነት ወደነበረበት ደረጃ የሚመልስ ነው። እንዲያውም የትግሬ ወያኔ ጠባብና አናሳ ቡድን ለሥልጣን ዕድሜው ማራዘሚያ በኦሮሞውና በዐማራው ነገዶች መካከል በሀሰት ገንብቶት የነበረው የጥላቻ፣ የመጠራጠርና የመገፋፋት ድልድይ ይሰብራል።
ሰሞኑን ደብረዘይት ላይ የፈሰሰው የኦሮሞው፣ የዐማራውና መሰል ነገዶች ልጆች ደም፣ ትናንት ጎንደር፣ ባሕርዳር፣ ደብረታቦር፣ ደብረማርቆስ፣ ነፋስ መውጫ፣ ወረታ፣ አምባ ጊዮርጊስ፣ ደባርቅ፣ ዳንግላ፣ ኮሶ በር፣ ቡሬ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ወዘተርፈ ላይ ከፈሰሰው የዐማሮች ደም የሚለየው አንዳችም ነገር የለም።  በሁሉም አካባቢዎች በወያኔ ነፍሰ ገዳዮች የፈሰሰው ደም የኢትዮጵያውያን ደም ነው። ወያኔ ከሁሉም በላይ የዐማራውንና የኦሮሞውን ልዩነት ሊያሰፋው የሚፈልገው ሁለቱ ነገዶች አንድ ከሆኑ ኢትዮጵያን ሊገዛና ሊዘርፋት እንደማይችል ስለሚያውቅ ነው። ይህንን የትግሬ-ወያኔን መሰሪ ሴራ፣ የኦሮሞውና የዐማራው ልጆች «አውቀንባችኋል» በማለት ወደ ነባሩ አንድነታችን በፍጥነት መመለስ ወያኔን አይሞቱ ሞት የሚገድለው እንደሆነ አይጠረጠርም። ስለሆነም የመከራ ጊዜአችን ለማሳጠር የሁለቱ ነገዶች አንድነት ፍቱን የወያኔ አገዛዝ ማርከሻ እንደሚሆን ተረድተን፣ ፍትሕ የተነፈጉ ፍትሕን እንዲያገኙ፣ በአረመኔዎች የተገደሉ ደማቸው ደመከልብ ሆኖ እንዳይቀር፣ ኢትዮጵያውያን በነገድ ሳይሆን፣ በዕኩልነት ላይ በተመሠረተ ኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ እንድናተኩር ያሻል።

ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደጋለን!

የኢትዮጵያ ትንሣዔ በትግላችን ዕውን ይሆናል!