Saturday, March 5, 2016

ከድጡ ወደ ማጡ፣ አሰብ በአረቦች እጅ ገባች


በዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማሪያም

የአገራችን አንድነትና ብሎም ሕልውና በቋፍ ባለችበት በዚህ ቀውጢ ወቅት ውይይቱ ሁሉ ማተኮር ያለበት ለሥጋቶቹ ምንጭና ምክንያት ስለሆኑት ስለ ዴሞክራሲ ደብዛ መጥፋት፣ ስለፍትህ መቅጨጭ. በብሔረሰቦች መካከል ስለሚታዩት ጥላቻና ግጭቶች እነዚህን የወለደው ሥርዓት ስለመለወጥ ብቻ መሆን አለበት ሌላው ሁሉ ገብስ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውጭ በሆኑ ጉዳዮች መነጋገር ሥርዓቱን ለውጦ ዴሞክራሲና ፍትህ ለማስፈን በሚደረገው ትግል ላይ ቀዝቃዛ ውሃ እንደመቸለስ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ 

ሆኖም ዘላቂ የአገር ጥቅሞችን መዘንጋት የኋላ ኋላ ሕልውናን ወደ መፈታተን ደረጃ ሊደርሱ ይችላሉ አገር ከሌለ ዴሞክራሲ ምን ሊፈይድ ፍትህስ ምን ሊረባ ምናልባት የአገር ሕልውናን እስከመፈታተን ሊደርሱ ከሚችሉ ከዋነኛ የአገር እሴቶች አንዱ የባህር በር አለመኖር ነው፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ሁኔታ በማይጨው ጦርነት ለሽንፈታችን ምክንያት ከሆኑ ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ኢትዮጵያ የገዛችው የጦር መሳሪያ በጅቡቲ በኩል ወደ አገር እንዳይገባ ፈረንሳይ መከልከልዋ እንደነበር መዘንጋት የለብንም፡፡

ኢትዮጵያ በምትገኝበት አደገኛ አካባቢ ሲሆን ጂኦፖለቲካውና ሃይማኖት ከስሌት ሲገባ የባህር በር በተለይም የኢትዮጵያ የአሰብ ባለቤትነት ጥያቄ ከሸቀጥ ማስተላለፍ በዘለለ የሕልውና ጥያቄ ሆኖአል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት ወሳኝነት እንዳለው እያወቁ “አሰብ አሰብ የምትሉት ምንድን ነው” እያሉ ይህንን ትልቅ ሕዝብን ያስጨነቀና እንቅልፍ የነሳ ጉዳይ ሲያጥላሉ ተደምጠዋል፡፡ በዚህ ላይ ብዙ ማለት ቢቻልም በተቃዋሚዎች መሃከል ሌላ አዲስ የጭቅጭቅ ርእስ ላለመክፈት ሲባል ጉዳዩን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትዝብት እንተዋለን፡፡ ጥቅሙን ከሕዝብ በላይ የሚያውቅ የለምና፡፡

ኤርትራና ኢትዮጵያ በ1983 ዓ.ም የዓለም የሃይል አሰላለፍ ባልተገነዘቡ፤ የአካባቢው ጂኑፓለቲካና ሃይማኖታዊ ሁኔታዎችን ማገናዘብ ባልቻሉ ከዘር ወይንም ከጎሳ ውጭ ሌላ ነገር ለሚታያቸው የሁለቱ አገራት ሕዝቦች ሁለዘርፍ ቁርኝትና መስተጋብር ከመጤፍ ባልቆጠሩ መሪ ተብዮች አመራር ስር ወደቁ ከዚያም ወንድም እህት የሆነው ሕዝብ

በጦርነት ተላለቀ:: ኢትዮጵያ በታሪኳ በፍፁም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከቀይ ባህር አካባቢ ተገልላ በዓለም ትልቁ ወደብ አልባ ዝግ አገር ሆነች፡፡ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካም ታሪክ ወደ ተከታታይ ትውልድ ሲንቁረቁር ኢሕአደግ በተለይም አቶ መለስ ዜናዊ የሚታወሱበት ዋነኛ ቅርስ (ሌጋሲ) ኤርትራን አስገንጥለው ኢትዮጵያን በእግር መንገድ እርቀት ወደብ አልባ ማድረጋቸው ይሆናል፡፡
እ.አ.አ በ2000 ዓ.ም በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃከል የተደረገው አሳዛኝና ዓላማ ቢስ ጦርነት እንደ ተደመደመ ሁለቱም አገራት ድርድር ወደ አልጄሪያ ከማቅናታቸው ቀደም ብሎ በአገርም በውጭም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ወደብ አልባ ከመሆን ጋር በተጓዳኝነት የኤኮኖሚ የስኩሪቲና የፖለቲካ ክስረቶች ለኢሕአደግ ለማስገንዘብ ኒው ዮርክ በተባበሩት መንግስታት ጽህፈት ቤት ደጃፍ ከተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ጀምሮ ያልፈነቀሉት ድንጋይ ያልማሱት ሳር የለም ማለሰት ይቻላል፡፡ ምናልባትም የአስብ ኢትዮጵያዊነትና የቀይ ባህር አፈሮች አንድነት ያህል የተተነተነ ኢትዮጵያዊ ጉዳይ የለም ማለት ይቻላል፡፡ አሰብን ወደ ኢትዮጵያ የሚያጥፍ የወሰን ሽግሽግ እንዲደረግ ይኸ ባይሆን ለሰላም ሲባል አሰብ በሁለቱም አገሮች የጋራ ባቤትነት (goint sovereignty) ስር ሆኖ ራስ ገዝ እንዲሆን ኢትዮጵያውያን ከአቀረቡአቸው አሳቦች ጥቂቶቹ ነበሩ፡፡

ለዚህ ሁሉ ጥረቶች በአቶ መለስ አማካኝነት ኢሕአደግ የሰጠው መልስ ወይንም አስተያየት የዚህ ሐሳብ አቀንቃኞች ኋላ ቀር ነፍጠኞች ከጊዜው ጋር የማይራመዱ ጊዜ የማይለውጣቸው መሃይማን የሚል ስድብ ነፍጠኞች ነበር፡፡ አስብ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የጭንቀት ምክንያት የሆነችው አገሪቷ ለወደብ አገልግሎት ለቀረጥና ለደሜራዥ ለመሳሰሉት ኢሕአደግ ሕዝቡን ሳያማክር በነፃ ለጅቡቲ የሰጠው ውሃ እንኳን ቅናሽ ሳያደረግ በዓመት ወደ ስድስት ቢልዮን ደላር የሚጠጋ ገንዘብ ለጅቡቲ በመክፈላችን ብቻም አይደለም፡፡ እንዲሁም ኢትዮጵያ እጅግ ስተራተጂክ ከሆነው ከቀይ ባህር ባትገለል ሊኖራት ይችል የነበረው ጀኦ ፓለቲካ አቅም ዜሮ በማግባቱም ብቻ አይደለም፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ጉዳታቸው የላቀ ቢሆንም የኢትዮጵያውያን ዋናው ጭንቀት የሚመነጨው አስብ በኤርትራ እጅ ከገባች አቶ ኢሳያስ ምናልባትም ለኢትዮጵያ በጎ ለማይመኙና ለማያስቡ ሀይላት ወይን አገራት አሳልፈው ሰጥተዋት የኢትዮጵያ ደህንነትና ሉአላዊነት ለአደጋ ይጋጥል ከሚል ፍራቻ ነው፡፡

ይኸው እንግዲህ የተፈራው ደርሶ የኤርትራ ሕዝብ ሳያውቅና ሳይመክርበት አቶ ኢሳያስ አሳብን በራይ ስም ለሳውዲ አረቢያና ለዮናትድ አረብ ኤምሬት አስረከቡት፡፡ ቀደም ሲል አቶ መለስ ዜናዊ አሰብ ኢትዮጵያ ካተጠቀመችበት የግመል ውሀ ማጠጫ ይሆናል የሚል ራዕይ ታይቶት ይህንኑ ለሕዝብ አሳምቶ ነበር፡፡ ከአቶ መለስ አባባል ቀደም ብሎ "ኢትዮጵያውያ በአሁኑ ጊዜ ለኤርትራ ምንም ጥቅም የማይሰጥው አሳብ እራስዋ ኤርትራ ባትጠቀምበትም ለለየላቸው የኢትዮጵያ ጠላቶች አሳልፋ መስጠትዋ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ብለው ነበር"፡፡ አሰብ የማን ናት! የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ 2003 ገጽ 190) አቶ መለስ ዜናዊ 70% የዓለም ነዳጅ በሚተላለፍበት ስትራተጂክ አካባቢና የሚገኝ ወደብ ኢትዮጵያ ካተጠቀመችበት የግመል ውሀ ማጠጫ ይሆናል ማለቱ ካንጀቱ ሳይሆን በጉዳዩ እጅግ ይቆጩ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ለማዘናጋት ነበር፡፡

አቶ ኢሳያስ አሰብን ለአረቦች ያስረከቡት ለአረቦች ከማከራየት ውጭ ለሌላ ጥቅም ሊውል አይችልም ከሚል አይደለም፡፡ አቶ ኢሳያስ አሰብን ለአረቦች አስረክበው አገራቸውን ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጡት የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆን በኢትዮጵያውያን በኩል ምን ያህል ቁጭት እንደስከተለ ስለሚያውቁ ኢትዮጵያ አንድ ቀን ወደቡን በኃይል ለመያዝ ትሞክራለች ከሚል ፍራቻ ሊሆን ይችላል ሆኖም ግን በኢሕአደግ የአገዛዝ ዘመን ይህ የማይታሰብ ነው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር በዚህ ላይ የነበረው አቋም ከላይ የተጠቀሰውን ሲሆን የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ደግሞ የአቶ መለስን አቋም በማስተጋባት የካቲት 24 ቀን በ2002 ዓ.ም ለሪፖርተር በሰጡት ቃለ ምልልስ ኢሕአደግ ኢትዮጵያን የወደብ ባለቤት ለማድረግ ፍላጎት እንደሌለውና እንደማያምንበትም አረጋግጠው ነበር (አሰብ የማን ናት? ዝኒ ከማሁ ገፅ 60) የእነዚህ የሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስተሮች አቋም አንድ ገጣሚ በውስጥ ወይራ አገላለጽ አስቀምጦታል ፡፡

 ከጫካ ሰው ጋራ ቁማር ተጫውቼ ወና ወጥቻለሁ አገር ተበልቼ እኔም ስጠባበቅ ምርት እህሌን ላፍሰው ከጫካ የወጣ ዝንጀሮ ጨረሰው ይህ የአሰብ በአረቦች እጅ መግባት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ብሎም ሕልውና ሊፈታተን ቢችልም የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ከቶም ጉዳት ሆኖ የማያውቀው ኢሕአደግ ድርጊቱን ይቃወማል ብለን አንጠብቅም " ውሀ ሲጎድል ተሻገር፣ ዳኛ ቢኖር ተናገር" እንደሚባለው የኢትዮጵያ ሉዓታዊነት የሚቆረቆር ዳኛ (አስተዳዳሪ) ሲመጣ አቤት እንላለን፡፡

የአሰብ በአረቦች ቁጥጥር ስር መሆን ብዙ ለውጦችን አስከትሎአል፡፡ ቀይ ባህርን በምስራቅም በምዕራብም ዳርቻ ከመቆጣጠራቸውም በላይ ለዘመናት ሲያልሙትና ሲመኙት የነበረው የቀይ ባህር የአረብ ሀይቅነት እውን ሆኖላቸዋል፡፡ "የጎረቤት ሌባ ባያዩት ይሰርቃል ቢያዩት ይስቃል" እንደሚባለው እኛም ለኢትዮጵያን ኩታ ገጠም ጎረቤቶች መሆኑን በቀረብን፡፡ ምክንያቱም ከጉርብትናቸው ጋር ተያይዞ የሚመጡ ብዙ መዘዞችም አሉ፡፡ ከመካከለኛው ምስራቅ ለሚፈልቁ አሸባሪዎች ቀላልና በቅርብ እርቀት የምንገኝ ኢላማ ሆነናል፡፡ ባህር ማቋረጥ የሌለባቸው አክራሪ ወሀቢዎች በኢትዮጵያ በወንድምነትና በመፈቃቀር የኖሩ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታዮች ግንኙነት በአክራሪ ዋሃቢዎች ሊደፈርስ ይችላል፡፡

በኤርትራውያን ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ከኢትዮጵያውም በብዙ እጅ የበለጠና የከፋ ነው፡፡ በሳውዲ ንዳድ ይቃጠሉ የነበሩ ሼኮች ቱጃሮችና ልፁላን በነፋሻው አስመራ እየተሽሞነሞኑ ሕዝቡን ወደ ሁለተኛ ዜግነት ዝቅ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ከዚይም አልፎ በሂደት የጥንቱ የአክሱም ስልጣኔ አካል የነበረችው ኤርትራ ደብዛዋ ጠፍቶ አረባዊ ማንነት ሊጫናባት ይችላል፡፡ ከአርባና ከአምሳ ዓመታት በኋላ ሳውዲ አረቢያ የሚኖረው ሙቀት የሰው ልጅ ሊቋቋመው አይችልም ስለሚባል የውሉ ጊዜ ሲጠናቀቅ ተደላድለው ለዘመናት የኖሩ አረቦች ጓዛቸውን ጠቅላለው ለመውጣት ፈቃደኛ ይሆናሉ ወይ? ከመነሻው መለያየት የማይገባቸው የነበሩ ወንድማማች ሕዝቦች ኤርትራውያን ኢትዮጵያውያንና በስልጣን ጥመኞችና አርቆ ማሰብ በተሳናቸው መሪዎች ውሳኔ ቢለያዩም ተመልሶ የመተሳሰር ዕድል ይህ የአረቦች ጣልቃ ገብነት አጥብቦታል፡፡

አቶ ኢሳያስ ከአረቦች ጋር የተፈራረሙበት ውል የኤርትራን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ሕዝብ ወይንም የሕዝቡ ተወካዮች ያልመከረበት የአቶ ኢሳያስ የግል ውሳኔ በመሆኑ ጊዜው ሲያመች ኤርትራውያን ውሉን መሰረዝ እንደሚችሉ የኤርትራ ምሁራን አይጡትም፡፡ ኤርትራውያን ይህንን ውል የሚቃወሙ ቢሆን የኢትዮጵያውያን ሕዝብ እገዛ እንደማይለያቸው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

በመጨረሻም ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በማይበጠስ የዘር፣ የቋንቋ የባህል፣ የሀይማኖት ወዘተ ሀረግ ተሳስረዋል፡፡ የሁለቱ አገራት መሪዎች የፈጠሩት እንጂ ሕዝቡ ዘንድ ዘልቆ የገባ ስሜት አይደለም፡፡ ተራው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለኤርትራ ሕዝብ ከፍተኛ ፍቅር እንዳለው ኤርትራውያን ከኢትዮጵያውያን በተባበሩ ጊዜ ሕዝቡ ሲችል እየደበቃቸው ሳይችል ስንቅ እየሰጠ በእምባ እንደሸኛቸው ሰው ያወቀው ጸሐይ የሞቀው ሃቅ ነው፡፡ ስለዚህ የአካባቢውን ጂኦ-ፓለቲካ በጥልቀት የገባቺው ህብረት ኃይል መሆኑን የተረዱ በዘረኝነትና በጎሰኝነት ደዌ ያልተለከፉ መሪዎች በሁለቱም አገር በሕዝብ ተመርጠው ስልጣን ሲጨብጡ በጠላት የማትደፈር፣ በልማት የዳበረች፣ በዓለምና በአፍሪቃ ጫና ልትፈጥር የምትችል አንድ የተዋሃደች በፌዴሬሽን የተሳሰረች አገር ሊፈጥሩ መቻላቸው ሲታሰብ በራሱ ያማልባል፡፡

የኢትዮጵያ ሰፊ ገበያ፣ ሰፊና ለም መሬት በአፍሪቃ በሁለተኛነት የሚመደብ የውሀ ሀብት ሁለቱም አገራት የታቀፉአቸው ብዙ ዓይነት ማድናት፣ በዓለም ተወዳዳሪ የማይገኝለት ተስማሚ አየር፣ እጅግ ስትራተጂክ የሆኑ ሁለት ወደቦች ያለው አገር በጥቂት ጊዜ የበለጸገና የታፈረ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ከግብ ለማድረስ በሁለቱም ሕዝቦች በኩል ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ጉጉትም አለ፡፡ ጥያቄው እንግዲህ እንዲህ ዓይነት ራዕይ የሰነቁ እሩቅ አሳቢ ራሳቸውን እርሳቸው ለአገር ያደሩ መሪዎች ይኖራሉ ወደ …… ነው እንዲህ ዓይነት መሪዎች በሁለቱም አገራት ብቅ ካሉ ይህ በምድረ ገነት የተመሰለው አገር ዕውን ማድረግ ይቻላል፡፡

ለዚህ ለዘለቄታ ግብ የሁለቱም አገራት ሕዝቦች በተለይም ወጣቱ መነጋገር መተዋወቅ መግባባት ስለሚኖርበት ይህንን ዓላማ አንግበው የተነሱት እንደነቪዥን ኢትዮጵያና ኢትዮ ኤርትራ ሶሊደሪቲ ግሩፕ ሌሎችም ተመሳሳይ አላፊነት ለሚወጡ ቡድኖችና ግለሰቦች የሚያደርጉት ጥረት ይበል የሚያሰኝ ሲሆን ያበርታችሁ እንላለን፡፡




Wednesday, March 2, 2016

ሞረሾችን ከልብ አመሰግናችኋለሁ::

(Aynadis Tesema)

ጸረ ኢትዮጵያ ሀይሎች ኢትዮጵያን: አማራውንና የኦርቶዶክስ ሀይማኖትን ለማጥፋት ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ማድረግ የሚችሉትን ያህል አድርገው ማውደም የሚችሉትን ያህል ውድመት አድርሰዋል:: በዚህ በሰለጠነው በ21ኝው ክፍለዘመን ላይ በኢትዮጵያ የነገሱት ወያኔወችና ጀሌወቻቸው በሀገራችንና በአማራው ላይ የፈጸሙት በደል እጅግ ዘግናኝ መሆኑን ማንም ያውቀዋል:: ይህን ሀቅ በጥናት ማረጋገጥ ለሶስተኛ ወገን ግንዛቤ የሚረዳ በመሆኑ ሞረሾች ላደረጋችሁት ብርቱ ጥረት ልትመሰገኑ ይገባል:: "ውሀ እርኩስ - ውሀ ቅዱስ" እንደሚባለው ሁሉ የሰውም እርኩስና ቅዱስ አለው:: አንዱ የወገኖቹ ስቃይ አንሰፍስፎት ምርር ብሎ ያለቅሳል: ሌላው ደግሞ የራሱን ወገን ከጠላት ጋር አብሮ ፍዳ ያስቆጥራል::

ሴማውያን (እስራኤላውያን) ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በፊትም ይሁን በኋላ የዘር ፍጅት ተፈጽሞባቸዋል:: እኒህን ህዝቦች ያላሳደደና እጁን ያላነሳባቸው የአውሮፓ ሀገር የለም ማለት ይቻላል:: ያም ሆኖ እስራኤላውያን እንደታለመው ሊጠፉ አልቻለም:: ፈጣሪ ህዝቡን የሚጠብቅበት የራሱ መንገድ አለው:: እኒህ ከምድረአውሮፓ እንዲጠፉ የዘር ማጽዳት ዘመቻ የተከፈተባቸው እስራኤላውያን ዛሬ ላይ የታሪካቸው መነሻ ከሆነው መሬት ላይ ተሰባስበው ነጻ መንግስት መስርተው ታላቅ ሀይል ሆነው ብቅ ብለዋል:: 

አማሮች አማራ በመሆናቸው ብቻ የራሳቸውን ክልል ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ ውስጥ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል:: ያም ብቻ አይደለም በአጎራባች ሀገሮችም ቢሆን አማራ የተጠላና የጥላቻ በትር የሚያርፍበት ሆኗል:: ይህን የአማራ ቅስም መሰበርና የዘር ጥፋት ያቀነባበሩት ኢትዮጵያ እንደሀገር እንዳትቀጥል የሚፈልጉ በሀገራችን ላይ የተለየ ፍላጎት ያላቸው ታሪካዊ ጠላቶች ናቸው:: እኒህ ሀይሎች ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ካልሆነም ራሷን ችላ ለመቆም እንዳትችል አድርጎ ለማሽመድመድ የተለያዩ ስልቶችን ሞክረዋል:: ይሁንና ኢትዮጵያውያን በአንድነት የሀገር ዋልታና ማገር በመሆን በደምና በአጥንት አንጸው ይህችን የምንሳሳላትን ሀገር እስከ እኛ ትውልድ ድረስ አድርሰዋል:: 

የአማራና የኦርቶዶክስ ሀይማኖት አቅም ማጣት የኢትዮጵያን ክንድ ያዝላል ብለው ያመኑ ኢትዮጵያችን እንደሀገር ጠንካራና የበለጸገች ሆና እንዳትወጣ የሚፈልጉ ጠላቶቻችን ህዝባችን በዘርና በሀይማኖት እንዲከፋፈል ባደረጉት የዘመናት ጥረት የጎጥና የሀይማኖት ድርጅቶች ሊመሰረቱ ችለዋል:: ጀብሀ: ሻእቢያ: ኦነግ: ኦብነግ: --- ወዘተ የተመሰረቱት ጸረ አንድነት ትግል በማካሄድ የጋራ ቤታችንን ለማፍረስ ነበር::

ተገንጣይ የጎጥ ድርጅቶች ተሳክቶላቸው ነጻ መንግስት ቢመሰርቱ አመራሮች ቀደም ሲል ያልነበራቸውን ስልጣን ሊጎናጸፉ እንደሚችሉ እሙን ነው:: እኒህ የነጻ አውጭ አመራሮች ከነጻነት በኋላ በሀገሪቱ ላይ ባለስልጣን ሆነው ክብርን ሲጎናጸፉ ህዝባቸው ግን መኖሪያውን አጥብቦ ያለመው ሳይሳካ ለከፋ ኑሮና ለብስጭት ይዳረጋል::

 በኤርትራ ላይ የደረሰው ነገር ይኸው ነው:: የሻእቢያ አመራሮች በሀገሪቱ ላይ አድራጊ ፈጣሪ ሲሆኑ ህዝባቸው ግን ከጀርባው እየተተኮሰበት ድንበር አቋርጦ የሚሄድ ስደተኛ ሆኗል:: ያም ሆኖ ሻእቢያ የአይዞህ ባዮቹን አላማ አሳክቶ የአመራሩን የበላይነት አረጋግጧል:: ሌሎች የጎሳ ድርጅቶች አላማም ከዚህ የተለየ አይደለም:: 

በህዝብ ስም አልቅሰው: ህዝብን አሳምጸው: ሀገር መበተንና በዚያች በሚመሰርቷት ሀገር ላይ አዛዥ ናዛዥ መሆን:: ከብዙ ነጻነታቸውን ተጎናጸፉ ከተባሉት ሀገሮች (ደቡብ ሱዳን: ኤርትራ: ዩክሬይን: ---) ተጨባጥ ሁኔታ እንደተረዳነው ህዝቡ መቸም አይቶት የማያውቀው የስቃይ ኑሮ እየኖረ እንደሆነ ነው::  

የጎሳ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ሲጀምሩ የትግል ማሰባሰቢያ አጀንዳ መቅረጽ ይኖርባቸዋል:: በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ሀገሮች የሚነሱ የነጻነት እንቅስቃሴወች ዋና ምክንያቶች ተብለው የሚጠቀሱት የነጻነት: የዴሞክራሲ የፍትህና: የእኩልነት መነፈግ የሚሉ ናቸው:: ከነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ጀርባ ግን አንድ አቢይ ጉዳይ ይኖራል: የሌላ ሦስተኛ ወገን ፍላጎት:: የጎሳ ድርጅቶች እንወክለዋለን የሚሉትን ህዝብ መብትና ጥቅም ለማስከበር ነው የምንታገለው የሚል ሽፋን ይስጡ እንጅ ዋናው ነጥብ ግን ጥቅም ነው (በትግል ጊዜ ከሦስተኛ ወገን የሚፈስላቸው ገንዘብ እና ከነጻነት በኋላ የሚጎናጸፉት ገደብ አልባ ስልጣን):: 

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የዘር ፖለቲካ አማሮችንና የኦርቶዶክስ ሄይማኖትን በማጥፋት ላይ ያነጣጠረ ነው:: ሻእቢያ: ወያኔ: ኦነግ: --- ትግላቸው በደል ፈጽሞብናል ብለው የሚሉትን አማራን በማጥፋት ላይ ያነጣጠረ ነው:: እነዚህ ድርጅቶች አማራን ለማጥፋት የተነሱት በሁለት ምክንያት ነው:: አንደኛው አማራው የአንድነት ጠበቃ ስለሆነ አማራው እስካለ ድረስ ነጻ መንግስት ለመመስረት ያዳግተናል ከሚል እሳቤ የተነሳ ሲሆን ሌላው ደግሞ ቀደምት አማሮች አካባቢያችንን ወረው ሳንፈልግ ኢትዮጵያዊ አድርገውናል: ህዝባችንንም ፈጅተዋ በሚል የአሁኑን አማሮች ለመበቀል ነው::

እርግጥ ነው የሰውም እርኩስና ቅዱስ ስላለው መጥፎወቹ ሰዎች የጥፋት ጦራቸውን ሲሰብቁ ደጎቹ ደግሞ "ተው አይሆንም" ብለው ተቃርነው በመቆማቸው ዘራቸው ይጥፋ ተብለው ከተወሰነባቸው ጋር ተዳብለው የጥፋቱ ሰለባ ይሆናሉ:: ለዚህም ማስረጃ ይሆን ዘንድ በሞረሽ ጥናት ላይ ከአማሮች ጋር የተገደሉት ኦሮሞወችንና ሌሎች ኢትዮጵያዊያንን መጥቀስ ይቻላል::

 የአዲሳበባን የተቀናጀ ማስተር ፕላን በመቃወም ኦሮሞወች ተቃውሞ ማሰማት እንደጀመሩ አንድ ጓደኛየ (የደቡብ ሰው) ደውሎ ስለወቅቱ የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ስንጨዋወት "እንዲያው አማራው ምን ሆኖ ነው ስንት ነገር ሲፈጸምበት ምንም እንዳልተነካ ሆኖ ጸጥ ብሎ የተቀመጠው? ይሄ ብአዴን የሚባለው የአማራው ድርጅትስ ምን ነካው? በጠቅላላ ሀገሪቱ ማለት ይቻላል አማሮች እየተፈናቀሉ: ንብረታቸው እየተቀሙ: እየተዋረዱና እየተገደሉ ነው:: 

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ድርጅታችሁ አንድም ተቃውሞ ሲያሰማ አልተደመጠም:: አማራውም እንዴት ህዝባችን እንዲህ አይነት ግፍ ይፈጸምበታል ብሎ ሲያምጽ አልታየም:: ---ኦሮሞ እያደረገ ያለውን ተመልከች! የኦሮሞው ድርጅት ኦህዴድ እያደረገ ያለውንም ተመልከች! ሕዝቡ ዳር እስከዳር እየተንቀሳቀሰ ተቃውሞውን እያሰማ እየተዋደቀ ነው:: ኦህዴድም የመንግስትን ታጣቂ ሀይል አውግዞ የህዝቡን ትግል ደግፎ መግለጫ እስከማውጣት ደርሷል:: በዚህም ምክንያት መንግስት አድርጎት የማያውቀውን እቅዱን እስከመሰረዝ ደርሷል:: ያም ሆኖ ኦሮሞወች አሁንም ተቃውሟቸውን አላቋረጡም:: እርግጠኛ ነኝ ይኸ መንግስት ከእንግዲህ በኋላ በኦሮሞ መሬት ላይ ህዝብ ያልፈቀደውን እቅድ ሊያቅድ አይደፍርም:: ይህ ሁሉ የኦሮሞ አመጽ አዲስ አበባ አካባቢ ያሉት ገበሬወች እንዳይፈናቀሉ በሚል የተፈጸመ ነው:: 

--የአማሮች ታሪክ ከታሪክ እንደምናውቀው ሌላ አሁን እያየን ያለነው ደግሞ ሌላ ነው:: በቤቶችና በህዝብ ቆጠራ ሪፖርት ሳይቀር በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝባችሁ 'ያርግ ወይ ይስጠም' ሳይታወቅ እንደጠፋ ነው የተገለጸው:: በዚያ ላይ የአለም ሜዲያ ያወሩለት የአማሮች መፈናቀል: ንብረት መወረስ: መታሰር: መደብድደብ: በገፍ መገደል: በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢወች በስውርና በገሀድ ተፈጽሟል: እየተፈጸመም ነው::

 ታዲያ ዝምታችሁ በሕዝባችሁ ላይ የሚደርሰው ግፍ የት እስከሚደርስ ነው? ምንም ሊገባኝ አልቻለም:: እስቲ አስረጅኝ" ሲል አንዱን በአንዱ ላይ እያነባበረ ጠየቀኝ:: ምን ልበለው! ብቻ አፌ እንዳመጣ "ጥያቄውን እኮ አንተው መልሰኸዋል:: ወያኔና ሻእቢያ የዘሩት ጸረ አማራ ዘመቻ በተግባር እየተተረጎመ ነው:: በብአዴን ውስጥ በአመራርነት የተቀመጡት ወሳኝ ሰወች አማሮች አይደሉም: ድርጅቱን ለመቆጣጠርና አማራውን ለማፈን የተቀመጡ የሌላ አካባቢ ሰዎች ናቸው:: ከታች ያሉት አማሮች ደግሞ ነፍስ የማያውቁ ናቸው:: ትልቅ ስራ

የሰሩ የሚመስላቸው ለህዝባቸው ሳይሆን ለድርጅታቸው ታማኝ ሆነው ማገልገል በመቻላቸው ነው:: ሀገርና ህዝብ የሚል አማራ አይደለም በድርጅቱ በክልሉም በሰላም አይኖርም:: ታዲያ ህዝብ አደራጅና መሪ ሳይኖረው እንዴት ሆኖ ለተቃውሞ መውጣት ይችላል? ---በሌላ በኩል አማራው ወያኔን ተቃውሞ ቢቆም 'ነፍጠኛው አንገቱን እያቀና ነው: : ስለዚህ በሉት' ተብሎ መመሪያ ይወርድና የከፋ ጥፋት ይደርሳል በሚል ስጋት የተነሳ ሊሆን ይችላል:: በርግጥ ይህ የእኔ መላ ምት ነው::

 ዕውነቱ ሊታወቅ የሚችለው በጥናት ነው::" አልሁት:: ጓደኛየ ከት ብሎ ከልቡ ሲስቅ ቆየና " ያልሽው ሁሉ የማይረባ ነው:: የብአዴን አመራሮች: እሽ አንች እንዳልሽው አማሮች አይሁኑ- ታዲያ ከታች ያለውስ አማራ ምን ይሰራል? እየተሰደደ እየተገደለ ያለው ወገኑ አይደለም እንዴ? አንድ ነገር ደግሞ መርሳት የለብሽም:: ማንኛውም ሰው ለመለያው እንደሚጫወት! በዚህ ስሌት መሰረት አማራ ያልሆነ የብአዴን አባል ቢኖርም ሊጫወት የሚችለው ለለበሰው መለያ ማለት ለአማራው ነው::

 ምንም ይሁን ምን የሚጫወትለት ቡድን ተሸናፊ ሆኖ ማየት አይፈልግም: ምክንያቱም በቡድኑ ውስጥ እራሱ ስላለ:: ---ሌላው ያነሳሽው ውሀ የማይቋጥር ምክንያትሽ ደግሞ 'አማራው ለተቃውሞ ቢወጣ የከፋ ነገር ይደርስበታል---* ምናምን ያልሽው ነገር ነው:: በእውነት እንዲህ ያለ የተጎሳቆለ ምክንያት ካንች አልጠብቅም:: አማራው አንገቱን ደፍቶ ቢቀመጥና መከራው ቢያበቃለት ጥሩ ነበር:: 

ዝም በማለቱ የቀረለት ክፉ ነገር እኮ የለም:: አንገቱን እንደደፋ አንገት አንገቱን እየተቀነጠሰ እየወደቀ እንደሆነ አይታይሽም? ነው ከተጎጅወች ውስጥ ያንች የቤተሰብ አባል ስለሌለ ጉዳቱ ቀሎ ታየሽ! ---ሰማሽ እህቴ የከፋ ነገር ሲገጥምሽ እየታገልሽ መጮህ ይኖርብሻል:: እንዲያ ካደረግሽ ጉልበትሽ ፈቅዶ ማሸነፍ ባትችይም ጩኸትሽ አጋር ወይም ገላጋይ ይጠራልሻል:: 'ዝምታ ለበግም አልበጃት' ሲባል አልሰማሽም? ---እንደሚባለው ከሆነ ግን የናንተ ጀግንነት እዚያው በዚያው ነው:: ሃ-ሃ-ሃ በቤተሰብ: በጎረቤት: በአካባቢ ነው አሉ ጀግንነታችሁ የሚታየው:: መሬት ነክሶ መዋጋትና አላማን ለማሳካት መጽናት ዞሮም አያያችሁ ሲባል ሰምቻለሁ:: በፊትም ቢሆን በብልሀታችሁ ሌላውን ህዝብ ከፊት እያስቀደማችሁ እናንተ ግን ጥይት ከማይደርስበት አካባቢ ሆናችሁ 'በል ግፋ' ማለት ነበር የምታውቁት አሉ::

 ---አሁን ሁሉም በየራሱ ክልል ሲሰባሰብ ማን ከፊት ሆኖ ይዋጋ! ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚሉት የሌሎችን ድጋፍ ለማግኘት እንጅ እነርሱማ እንኳን ለሀገር ሊተርፉ ለራሳቸውስ መች ሆኑ እየተባላችሁ ነው:: መቸም እንዲህ እያሉ ይሰድቧችኋል ልልሽ አልፈልግም:: 'ከሰዳቢየ ነጋሪየ' እንደሚባለው እንዳትቀየሚኝ ስል:: ለማንኛውም ግን የአማራ የሀሰት የጀግንነት ካባ ተገለጠ እየተባለ እየተወራ ነው:: ለማንኛውም ልብ ይስጣችሁ! ንግግሬን በክፋት እንዳትወስጅው! አይደለም ኢትዮጵያዊ ወገኔ የትኛውም ሰው ቢሆን ካለሀጢያቱና ካለፍርድ ሲቀጣ ማየትም ሆነ መስማት ስለሚያመኝ የተሰማኝን ስሜት ለመግለጽ ነው:: ሰላም ሁኝ አለና ስልኩን ዘጋው::

 ከጓደኛየ ጋር ያደረኩት የስልክ ቆይታ በዐዕምሮየ እየተመላለሰ ሲረብሸኝ እስካሁን አለ:: ጓደኛየ ላይ የተፈጠረብኝ መጥፎ ስሜት የለም:: የተናገራቸው ነገሮች ሁሉ ከመቆርቆር የተነሳ እንደሆነ የተናገራቸው ነገሮች ሳይሆኑ ሲናገር የነበረው የንግግር ቅላጼና ስሜት ገላጮች ነበሩ:: ይሁንና ከአንደበቱ የወጡትን አረፍተነገሮች ደግሜ ደጋግሜ ማመንዠኬን ግን አላቋረጥሁም::

 ችግራችን ምንድን ነው? የምን አፍዝ አደንግዝ ተደገመብን? ዕውነት እንደሚባለው አማራ ፈሪ ነው? የብአዴንን ነገር ከህሊናየ አውጥቸዋለሁ:: ማለቴ -ለአማራው የሚቆረቆር ሳይሆን ራሱ ጸረ አማራ እንደሆነ አመራሮች ከተናገሯቸውና በአማራው ላይ እየደረሰ ባለው አስከፊ ጥፋት ላይ ምንም የተቃውሞ ድምጽ ባለማሰማቱ: -"ምነው ለጅብ ሰጣችሁን- እኛ እኮ ወገኖቻችሁ ነን - አማሮች ነን - እባካችሁ ድረሱልን" እያሉ የሚጮሁትን የወልቃይት አማሮች አልሰማ ያለ ድርጅት በመሆኑ: -እወክለዋለሁ በሚለው ህዝብ ላይ እልቂት የሚያውጅና እወክለዋለሁ የሚለውን ሕዝብ የሚያዋርድ አመራር ያለው ድርጅት በመሆኑ: በአጠቃላይ የወያኔ ዱላ ሆኖ አማራውን ለማሰቃየትና በክልሉና በህዝቡ ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም ህገወጥ ድርጊት ሽፋን እንዲሰጥ የተቀመጠ የህሊና ቢሶች ስብስብ በመሆኑ ብአዴን ጠላት እንጅ የአማራ ድርጅት ሊባል ከቶም አይችልም የሚል ዕምነት አለኝ:: 

ሌሎች በተቃዋሚነት ስም የሚታወቁ ድርጅቶችስ ምን አደረጉ? ከታች ያለው አካል ከላይ ያለውን አድብቶ ለመጣል የሚያደርገው ደባና ክፍፍል በትግሉ ላይ ያሳረፈው አፍራሽ ተጽእኖ ይኖር ይሆን? ለምን ሕዝቡ ተቃዋሚወችን ደግፎ አደባባይ ወጥቶ ድብልቅልቅ ያለና እልህ አስጨራሽ ተቃውሞ አላደረገም? ድንገት የተናገርኋት ነገር የዐዕምሮየን ጓዳ እያንኳኳች ነው:: በአማሮች ላይ የደረሰው ጥፋት ብቻ ሳይሆን የአማራው ዝምታ ምክንያትም መጠናት ይኖርበታል:: ለማንኛውም ለሞረሾች ያለኝን 

ክብር እንደገና ልገልጽ እፈልጋለሁ::