Monday, March 23, 2015

የፕረዝደንቱ የአዞ እንባ


ከዳግማዊ ተፈራ

ጓደኛዬ ደዉሎ አቶ ኢሳያስ ቃለ ምልልስ እያደርጉ ነዉና አዳምጥ አለኝ።እዉነት ሲናገሩ ሰምቼ ስለማላዉቅ አናንቄ ተዉኩት። ሌላ ቀን ደዉሎ እባክህን አዳምጥ አለኝ ! ምን አዲስ ነገር ቢኖር ነዉ ብዬ መጎርጎር ጀመርኩ ። በተከታታይም አዳመጥኩት።አልተሳሳትኩም ። ለእሳያስ አፈወርቂ “እዉነት ማለት ለእርሳቸዉ ትክክል የሆነና የሚሰራ ብቻ ነዉ”

ከዓለም በተቃራኒ ብቻቸዉን ቆመዉም ዛሬም እዉነት የሚናገሩትና ትክከል የሚሰሩት እሳቸዉ ብቻ ናቸዉ። ለዚህም ነበር ያንን ቀልድ መስማት የጠላሁት። ሳልወድ በግድ ግን መራራ ክህደትን እንዳዳምጥ ተገድድኩ።

የኢትዮጲያ ህዝብ በቅጡ ያልተረዳዉ ዓለምም ያላወቀዉ አስከፊ ሰቆቃ በኤርትራ ምድር ተፈጽሟል። ርሃብም እርዛትም ጦርነትም አይደለም። ነገር ግን ከዚህ ሁሉ የከፋዉና የሰዉ ልጅ በሰዉ ዘር ላይ ጭካኔ የፈጸመበት ሁኔታ ነዉ። ግንቦት 16 1981 ሻቢያ በአሸናፊነት አስመራን ሲቆጣጠር አብዛኛዉ የኢትዮጲያ ሰራዊት የተሰደደዉ ወደ ሱዳን ነዉ ። ለሱዳን መንግስት ምስጋና ይግባዉና ተሽንፎ እየተሰደደ የነበረዉን ሰራዊት ድንበር ላይ እየያዘ ከሻቢያ ጋር በመሆን ትጥቁን አስፈታ። በዉሃ ጥምና በርሃብ የተንገላታዉ ሰራዊት እነሱ ያሉትን ከማድረግ ዉጭ ምርጫ አልነበረዉም። በዚህ መካከል አንድ ወታደር በዉሃ ጥም የደረቀዉን ጉሮሮዉን ሊያርስ ሲዳክር ከሻቢያ ወታደሮች ሞራሉንም ሆነ ስበናዉን የሚንካ ድርጊት ስለተፈጸመበት ከመኖር መሞትን መርጦ በኪሱ የያዘዉን ቦንብ በመወርወር አንድ የሻቢያ ወታደር ይገድላል። ምክኒያት የሚፈልጉት የሻቢያ መሪዎች ወታደሩን ወዲያው ቢገሉትም የበቀል ጥማቸዉ አልረካም ነበረና ዉሃ ይታደላችኋል በማለት ባዶ እጁን የነበረዉን ሰራዊት አንድ ረባዳ ቦታ ላይ እንዲሰባሰብ አደረጉ። ከሰዓታት በኋላ ዶልተዉ በመመለስ ዙ -23 በሚባል መሳሪያ በጭካኔ ረሸኑ። ከሶስት ሺህ ያላነሰ ወታደርና መኮንን በዚህ ጭፍጨፋ አለቀ። ይኸ አንድ ስፍራ ላይ የሆነ ሲሆን ሰራዊቱ ተሸንፈናል ብሎ በየቦታዉ እጁን ወዳላይ ቀስሮ እያሳየ በጭካኔ እንዲረሸኑ ተደርጓል።

በተለይም መሪ መኮንኖችን ከተሸሸጉበት ሱዳን ጭምር ከሱዳን መንግስት ጋር በመመሳጠር ወደ ኤርትር በመዉሰድ ረሽነዋቸዋል።ያ አልበቃ ብሏቸዉ ከፍተኛ መኮንኖችን ከአዲስ አበባ ጭምር በሻቢያ አፋኞች በማሳፈን ኤርትራ በመዉሰድ ደብዛቸዉን አጥፍተዋል።

እንግዲህ እነዚህንና ሌሎችንም እራሳቸው ኢሳያስ የሚያዉቋቸዉን ጭምር ነዉ “ሌላዉ ቀርቶ ምርኮኞችን በእንከብካቤ ነዉ የያዝነዉ” ብለዉ ድጋሚ የተሳለቁብን። አዕምሮአቸው ማሰብና ማገናዘብ ሲያቅተዉና ስጋቸው ከአጥንቻቸዉ ተላቆ ሳይሞቱ ከአስርና -አስራምስት ዓመታት እስር በኋላ የተፈቱትን ወታደሮች እድል ገጥሟችሁ ብታናግሯቸዉ የፕረዝደንት ኢሳያስን ደግነትና ጭዋነት ትገናዘባላችሁ።

በኢትዮጲያ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበዉ የወለቀዉን የወርቅ ጥርሳቸዉን እያሳዩ የተወሰደባቸዉን ንብረት እያልቀሱ ታሪካቸዉን የተረኩትንና በይፋ በአደባባይ የተናገሩትን የካዱ ሰዉ በጦሩ ላይ በድብቅ የፈጸሙትን ጭካኔ ይናገራሉ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ብቻ ሳይሆን ስንት ጊዜ ለመሞትና ስንት ጊዜ ለመታለል እንደታዘጋጀን ነዉ የሚገርመኝ።

ምንስ መድረክ ተገኝቶ የትስ ሆኖ ይጮሃል ሆኖ እንጂ የኢሳያስና የቡድናቸዉ ግፍ በኔ መመዘኛ በየትኛዉም ዓለም በተካሄዱት የእርስ በርስ ይሁን አገራዊ ጦርነቶች ያልተፈጸመ ጭካኔ ነዉ። ያ ተርስቷል ብለዉ ነዉ መልካቸዉን ለዉጠዉ ስለሰላም ይሰብኩ የነበሩት።

ስብከታቸዉን ከሠማሁ በኋላ ሁለት ነገሮች ወደአዕምሮዬ መጡ። ኢሳያስ አንዳች ጸጸት የማይሰማቸዉ ዛሬም በአዛዉንት እድሜቸዉ ክፋት ያልራቃቸዉ ጭካኔ የሚያረካቸዉ(እኔ በመልካቸዉም ይሁን በግብራቸዉ ሳዳም ሁሴንን ነዉ የሚመስሉኝ) ተቆርቋውሪ በመስል ሌላ ደም ለማፍሰስ ያሰፈሰፉ መሆናቸዉን።

ሁለተኛዉ ዛሬም ጭምር በእርሳቸዉ የበረሃ እስርቤቶች የኢትዮጵያ ሰራዊትአባላት በእስር እየማቀቁ ሞታቸዉን የሚጠባበቁ መሆኑን እያወቁ የትናቱን ክፍ ስራቸዉን ጽድቅና መልካም ነገር አድርገዉ ሲስብኩን ለእኛ ለኢትዮጲያዊያን ምን ያህል ንቀት እንዳላቸዉ ነበር ያሳየኝ።

የሚለማመጥ በሚመስል ገጽታ ቃለመጠይቅ ያደረጓቸዉ የእሳት ጋዜጠኞች ምስጋና ይድረሳቸዉና ኢሳያስን እንደገና ለህዝብ አቅርበዉ ምን ያህል ዛሬም ከህሊናቸዉ ያልታረቁ ሰዉ መሆናቸዉን አሳይተዉናል።

ቃለ መጠይቁን ከሰማሁ ቀን ጀምሮ ቁስሌን ያመረቀዙት ኢሳያስ በታሪክ ዉስጥ የሚኖራቸዉን ቦታ እያሰላሰልኩ ሳለሁ ራስ ምታት የጨመሩብኝ ደግሞ ለኢትዮጲያ አዲስ ራእይ ያላቸዉ የኢትዮጲያን ትንሳኤ ሊያዉጁ የተነሱ መሲህ አድርገዉ በማቅረብ “እባካችሁ እሳቸዉን አትንኩ” የሚሉ ኢትዮጵያዊያን እዉቀት ገርሞኛል።(እዉቀት ስል ስለኢሳያስ ያላቸዉን ማለቴ ነዉ)

አንድ ግምታዊ አስተሳሰብ ልሰንዝርና ሃሳቤን ልቋጭ።


ሂትለር በሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት ከወረራቸው አገሮች ሁሉ በአላይድ (Allied forces) ጦር ተሸንፎ ከለቀቀ በኋላ የራሱን አገር ጀርመንን ብቻ ሳይለቅ ቆየ እንበል። በአሜሪካና በሶቬየት ህብረት በሚመሩ ሃያላን መንግስታት መካከል ያለዉ ፍጥጫ ቀጥሎ ካፒታሊዝም ኮሚኒዝምን ለመመታት እንዲያስችለዉ ሂትለርን መጠቀም ፈለገና እሥካሁን በመላዉ ዓለም ላይ የፈጸምከዉን በደልና በአይሁዳዊያን ላይ የፈጸምከዉን ጭፍጨፋም ይቅር ተብሎልሃል። ስለዚህ ከእኛ ጎን ተሰልፈህ ኮሚኒዝምን በግንባር ቀደምትነት ትዋጋልናለህ ይሉታል። ይኸንን “መልካም ዜና” የሰማዉ ሂትለር በሃሳቡ ተስማምቶ ለካፒታሊዝም ያለዉን በጎ አስተያየት ፤ ለነጻ ገበያና ለህዝቦች እኩልነትና ነጻነት እንዲሁም ለዲሞክራሲ እንደሚቆም መስበክ ቢጀምር የሰዉ ዘር በሙሉ ምን ምላሽ ይሰጠው ይሆን ?በተለይም አይሁዳዊያን ምላሻቸዉ ምን ይሆን? እንዴት ይቀበሉት ይሆን? ያለፈዉንና የወደፊቱን የሚመዝኑትስ በምን መመዘኛ ይሆን?

አጋንነሃል ካላችሁ መብታችሁ ነዉ ። ኢሳያስ ለሚያነቡት የአዞ እንባ ግን ያለኝ ስሜት ከላይ የገለጽኩት ግምታዊ አስተሳሰብ ጋር የሚመሳሰል ነዉ። በራሳቸዉ ህዝብ ላይ የሚፈጽሙትን ሰቆቃ በዉዳሴ የሚናገሩትና ዛሬም ብቻቸዉን መቅረታቸዉን ማየት ያልቻሉ ብቸኛዉ የክፍለዘመናችን ሃሙራቢ ናቸዉና ( conqueror and lawgiver)።


የዚህ መልዕክት ዓላማ የተጀመረ ስራ ለማጣጣል የታቀደ እቅድ ለማክጨናገፍ ወይም አንዱን ወይም ሌላዉን ለመወገን ያላነጣጠረ ነገር ግን በኢሳያስ አፈወርቂ ንግግርና “እዉነት” ቁስሉ ያመረቀዘበት የቀድሞ ሰራዊት አባል ህመም ትንፋሽ ነዉ።

ተልዕኮ ካለዉ ብቸኛ ተልዕኮ የሚሆነዉም ክቡር አቶ ኢሳያስ ሆይ!!! ስላደረሱብን ሰቆቃ የአይን ምስክሮች ዛሬም አለን። ስለ እግዚአብሄር (እግዚአብሄርን የሚያዉቁ እንኳ አይመለኝም) ስለ ህሊና ፤ ስለ ህግ (ህግም እራሳቸዉ ናቸዉ) ስለሰብዊነት ፤ ስለታላቅነቶና ስለምስራቅ አፍሪካ መሪነቶ! ለክብርዎ!ሲሉ አይዋሹ ።እዉነት የእርስዎ ብቻ ሳይሆን ሌላዉም ሰባዊ ፍጡርም እዉነት አለዉና! እንኳን እኛ በህይወት ያለነዉ ቀርቶ ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻቸን ጭምር እርስዎ ያደረሱብንን ግፍ እንዲያውቁ አድርገናል። ቁሳላችን የሚድነዉ እርስዎ ጨምድደዉ ከያዙት ወንበር ወርደዉ ለኤርትራ ህዝብ ስልጣኑን ሲያስረክቡ የኢትዮጲያና የኤርትራ ህዝብ ይቅር ለእግዚአብሄር ብሎ ወንድማማችነቱን ወደ ነበረበት ይመልሳል የሚል ነዉ።

በመጨረሻ ወንድሜ ታዲዮስ ዳንኤል በማርች 16፣2015 ኢትዮሚዲያ ላይ በእንግሊዘኛ የጻፈዉን አንብቤዋለሁ። በጹሁፉ ዉስጥ ዉስጣችንንና ህመማችንን የሚገልጽ ነገር ስለተናገረ ወታደር ወይም የወታደር ቤተሰብ ይሆን ብዬ ገመትኩ። ለነገሩማ የዛሬን አያድርገዉና የህዝብ ሰራዊት ነን ብለን ነዉ የአቶ ኢሳያስን የሃገር ግንጠላ ዓላማ ለሰላሳ ዓመታት የተዋጋነዉ። ለኛ ለመቆርቆር የግድ ወታደር መሆን አያስፈልግም።

ለወንድሜ ግን ምስጋንዬ የላቀ ነዉ።