Thursday, February 19, 2015

ሻዕቢያ አፈር ልሶ ተነሳ

ከአበበ ከበደ፣ ሐሙስ የካቲት ፲፫ ቀን ፪ሺህ፯ ዓም (Thursday, February 19th, 2015 ) Posted by ዘ-ሐበሻ
ምንጭ፦ http://www.zehabesha.com/amharic/archives/39131
ደርግ ወገቡን እየደበደበ ያቆሳሰለው በመጨረሻም በጾረናና ዛላንበሳ ጦር ሜዳ ላይ ራሱን ክፉኛ የተቀጠቀጠው እባብ አፈር ልሶ ተነሳ። እባብ ራሱን ተቀጥቅጦ ሞቶ እንኳን ቢሆን ሊነሳ ይችላልና መፍትሄው የዛፍ ቅርንቻፍ ላይ ወይም ገመድ ላይ ሰቅሎ መተው እንደሆነ ይታወቃል። ይህ እላይ የተሰቀለ እባብ ድንገት ቢነቃ እንኳን መላወስ ስለሚያቅተው እዚያው ሞቶ ደርቆ ይቀራል። እባብን ሞቷል ብሎ ሜዳ ላይ፣ ያውም በረሃ ላይ ጥሎ መሄድ ራስን ማታለል ነው።

ሻዕቢያ ለኢትዮጵያ መጎሳቆል ዋነኛው ተጠያቂ ነው። ገና ከጠዋት የኢትዮጵያ ተማሪዎች የትግል እንቅስቃሴን አቅጣጫ በማወላገድና ኋላም ተራማጁን ክፍል እርስ በእርስ በማጋደል ለኤርትራ ግንጠላ ያዋለው ሻዕቢያ ነበር። ደርግ የሚወጥናቸው ዘመቻዎች ሁሉ እርባና ቢስ የሆኑት ሻዕቢያ እውስጥ በሰገሰጋቸው ሰላዮቹ አማካኝነት ነበር። ኦነግን፣ ኦብነግን ወያኔን ጠፍጥፎ የሠራው ሻዕቢያ ነው። ሻዕቢያ በመጨረሻ
እንደ አጋንንት ራሱን ገንጥሎ በረሃ ላይ በረሃብ ይቆዝም ጀመር። ወያኔ መንትያውን ሻዕቢያን አበጥሮ ያውቅ ስለነበር የባድመውን ጦርነት የመጀመርያዋን ጥይት ከመተኮሱ በፊት ሰላዩንና ሰላይ ያልሆነውንም ጭምር አብዛኛውን ኤርትራዊ ከኢትዮጵያ ምድር አባረረ። ጾረናና ዛላንበሳ ግንባር ላይ በቀድሞው ሠራዊትና በወያኔ ሠራዊት ቅንጅት ውጊያ ድል የሆነው፣ ራሱን ክፉኛ የተቀጠቀጠውን እባቡን ሻዕቢያን ሞቷል ብለው ጥለውት ሄዱ። ሻዕቢያ በአስራ አምስተኛው ዓመቱ ግንቦት ሰባት-ኢሳትን ልሶ አሮጌ ቆዳውን ለውጦ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት በቴሌቪዥን ቀረበ። ወገኖቼ እባካችሁ እንደገና አንሳሳት። በዚህች ዓለም ፍቅረ ገመድ ታስረን፣ በፍቅረ ሥልጣንና፣ ፍቅረ ንዋይ ተጠምደን ሃገራችንን መከራዋን አናብዛ። እባካችሁ ማስተዋላችንን ለኢትዮጵያ ሃገራችን ትንሳዔ እናውለው። ብዙ መጻፍ አልፈልግም ነገር ግን ይህን፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካን ያልገባውን፣ ይህን ኢትዮጵያን አዋራጅ፣ ግንቦት ሰባት-ኢሳትን ማስተማር ስላለንብ ነው ይህችን ትንሺቱን ሃሳቤን የምወረውረው። ዛሬ ለአቶ ኢሳያስ ቃለ መጠይቅ አቅርቦ የይስሙላ ይቅርታ በማስጠየቅ ሻዕቢያ ኢትዮጵያን እንደገና እንዲያፈርስ መንገድ የሚያበጃጀውን ግንቦት ሰባት-ኢሳትን በጽኑ ልንወቅሰው ይገባል።

ለኢትዮጵያ ፖለቲካ መፍትሄው ራሱ የኢትዮጵያ ሕዝብና ከጠላቶቿ ጋር የማያብሩት የፖለቲካ ድርጅቶቿ ብቻ ናቸው። ወያኔንና ግብረአበሮቹን ከሥር መንግለው ኢትዮጵያን ነጻ የሚያወጧት ቆራጦቹ ልጆቿ ናቸው። ሻዕቢያ በኢትዮጵያውያን እግሮች ሥር ተደፍቶ ይቅርታ መጠየቅ ሲገባው እንደ ኦነግና ኦብነግ ጠፍጥፎ በሠራው በሮቦቱ ግንቦት ሰባት-ኢሳት አማላጅነት አይደለም ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት በቴሌቪዥን የሚቀርበው። “ኢትዮጵያን ከጽንፈኞቹ እስላማዊ እንቅስቃሴ ለመጠበቅ ተቃዋሚዎች ከአቶ ኢሳያስ ጋር መናበብና አካባቢውን ማዳን አለባቸው” የሚለው ማደናገርያ የኢትዮጵያ ሕዝብ “ዶሮን ሲያታልሏት” ብሎ ያልፈዋል። የእስላማዊ ጽንፈኝነትን አጀንዳ የሚያራምደው ማን ሆነና ነው አቶ ኢሳያስ የአፍሪካ ቀንዱ ቀጠና ሰላም አስጠባቂ ተደርገው የሚሞካሹት። “እስላማዊ ጽንፈኝነት መጥቶብሃል አቶ ኢሳያስ ጉያ ሥር ተሸሸግ” እያለ የሚያጃጅለው ግንቦት ሰባት-ኢሳት ራሱ ከሕዝብ ቁጣ የሚሸሸግበትን መላ ቢፈልግ ይሻላል።

የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደገና በማስተኛትና በማሞኘት በኢትዮጵያ ኪሳራ የኤርትራን በረሃ ውሃ ለማጠጣት ብሎም በአቶ ኢሳያስ የተገደለችውን ኤርትራ ዳግም ነፍስ ለመዝራት መሞከር በቅድስት ኢትዮጵያ ላይ ዳግም የሚሰራ ግፍ ነው። ዋሺንግተን ተራራ ላይ ሆኖ መዋጋቱ አልሆን ቢለው ወደፊት ሊከሰት ይችላል ብሎ የሚመኘውን የሥልጣን ክፍተት ለመሙላት ሻዕቢያን ተገን አድርጎ በመጠባበቅ ላይ ያለው ግንቦት ሰባት-ኢሳት እንደ ቋመጠ ይቀራል እንጂ ከእንግዲህ ሥልጣን ከሕዝብ እጅ አይወጣም። ትግሉ እንኳን ቢዘገይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጸሎት እንደነ አጼ ልብነድንግልና አጼ ገላውድዮስን የመሳሰሉ መሪዎችን ያስነሳል።
ወገኖቼ በአቶ ኢሳያስ መሠርያዊ አነጋገር ዳግም መታለል ለአንድነታችን የታገሉትን ኃይላይ መናቅ ነው። ሻዕቢያን እንደገና ማመን ማለት እምነታችንን መካድ ማለት ነው። ሻዕቢያንና አቶ ኢሳያስን ማዳመጥ ቅኝ ገዥዎችን ያርበደበዱትን የአድዋውን ጀግኖች መዘንጋት ማለት ነው። ሌላው ቀርቶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንዳትገነጠል ውድ ደማቸውን በኤርትራ በረሃ ላይ ያፈሰሱትን ክቡር አጥንታቸውን በሳህል ምድረ በዳ፣ በናቅፋ ተራሮች፣ በአፋቤት ሜዳዎች ላይ የከሰከሱትን እኚያን ጀግኖች
2
አለማስታወስ እግዚአብሄር የማይወደው የክፋት ሥራ ነውና ዛሬ በግንቦት ሰባት ኢሳት የተቀነባበረውን መሠሪ ሥራ ማውገዝ ይጠበቅብናል።
ፖለቲካ ፌዝ አይደለም። ፖለቲካ ማለት ወያኔን ለማናደድ ሻዕቢያን መጠጋት አይደለም። ፖለቲካ ትላንት አቶ አንዳርጋቸውን ያፈነውን ወያኔን ለማብሸቅ አቶ ኢሳያስን መጨበጥ፣ አስመራ መጓዝ፣ ቃለ ምልልስ ማድረግ፣ ቴምር መመገብ አይደለም። ፖለቲካ በጥበብ የሚደገፍ ትግል ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሃገራችንን ሉዓላዊነቷን ለመመለስ፣ ወያኔ ለባዕዳን የቸረውን መሬቶችና የባህር በር ለማስመለስ፣ ወያኔ በዘር የከፋፈለውን ሕዝቧን ለመታደግ የሚደረግ በሳልና ቆራጥ ትግል ነው። ሃገርን መጠበቅ ጀግኖች አባቶቻችን እንዳስተማሩን ስሜትን ተቆጣጥሮ ብልሃትንና ማስተዋልን መጨበጥ ሃቅን መልበስ ማለት ነው እንጂ የሚላስ የሚቀመስ እሌለበት ሃገር በመመላለስ “የራሱን ምቾቱን ትቶ ቤተሰቡን በትኖ በርሃ ተጓዘ”የሚለውን ተራ ወሬ መንዛት፣ ማስነዛት አይደለም። የተባበሩት መንግስትታ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ሆኑ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን ለመስክ ሥራ በረሃ ይልካሉ። ሊታገሉ አይደለም የሚሄዱት። ትግል፣ ለሥልጣን ሳይሆን ለሕዝብ ሲባል ቆራጥ መስዋዕትነት በመክፈል የሚተገበር እንጂ በረሃ መጓዝ ወይም አለመጓዝ አይደለም። በተጋድሏቸውና በድፍረቶቻቸው አርዓያነት ለሕዝብ ነጻነት ፀዳል የሆኑት እነ እስክንድር፣ አንዷዓለም፣ ርዕዮት፣ ኃብታሙ፣ በቀለ ገርባ፣ ዘጠኙ ብሎገሮች፣ ተመስገን፣ ወዘተ የመሳሰሉት የነብር ጣቶች በሠላማዊ መንገድና በአንዲት የብዕር ጠብታ ትግል ምን እንደሚመስል አሳይተዋል።

ይህን ሁሉ ችግር፣ ይህን ሁሉ የኢትዮጵያ አበሳ የፈጠርው ራሱ ወያኔ ነው። ትላንትና እባቡን ሻዕቢያን ራሱን እንደቀጠቀጥነው የሞተ ገላው ዛፍ ላይ ተሰቅሎ ቢቀር ኖሮ ዛሬ ግንቦት ሰባት-ኢሳትን ልሶ አይነሳም ነበር። የእባቡን ሻዕቢያ የተቀጠቀጠ ራስ ሜዳ ላይ ትተነው እንድንሄድ ያደረገን ነገ አፈር ልሶ እንደሚነሳ የሚያውቀው ወንድሙ ወያኔ ነው። ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን መድሃኔ “ይኸውና ኤርትራ ሞተች” በሚለው ጥናታዊ ፕሮፖዛላቸው “ወያኔና ሻዕቢያ ተጣብቀው የተወለዱ መንትዬዎች ናቸው” ብለዋል። ግንቦት ሰባት-ኢሳት በሻዕቢያና ወያኔ ማህል ሊገባ አይችልም። መሃላቸው የገባ ከመሰለው ተላላ ነው። ተጣብቀው የተወለዱት ሻዕቢያና ወያኔ አንዱ ከሞተ ያንደኛው ኅልውና ያከትማልና ሁሌም ይጠባበቃሉ። ግንቦት ሰባት-ኢሳት ውስጥ የመሸጋችሁ ተላላ ኢትዮጵያውያን ይህንን ሃቅ ተረድታችሁ ዛሬውኑ “እግሬ አውጭኝ” ብላችሁ ፈርጥጡ።

ኢትዮጵያን በዲሞክራሲ ለማነጽ፣ የወያኔን የተበላሸ የዘር ፖለቲካ ለመገርሰስ አቅሙ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ለኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝብ ዳግም ትስስርም ባለቤቶቹ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ናቸው እንጂ ሻዕቢያ፣ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ አልሻባብ አይደሉም። በፕሮፖጋንዳ የሚያግዛቸው ግንቦት ሰባት-ኢሳት በርሃ ላይ ለቆዘመው እባቡ ሻዕቢያ ዳግም እስትንፋስ ሆኗል። ይህ በቀላሉ የሚታይ ስህተት አይደለም። ከዚህ በኋላ ሌላ ሃገርን የሚጎዳ ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት ግንቦት ሰባት-ኢሳት ወደ ትክክለኛው የትግል አቅጣጫ እንዲመለስ ምክሬን እለግሳለሁ።
ወያኔና ሻዕቢያ የኢትዮጵያን ትንሳዔ በቅርብ ይመለከታሉ። አ.ከ. abebekebede321@gmail.com

Wednesday, February 18, 2015

ለመሆኑ ለወደፊቱ የየካቲት ፲፪ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. ሠማዕታትን የሚዘክር ተተኪ ትውልድ ይኖረን ይሆን?

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት             ረቡዕ የካቲት ፲፪ ቀን ፪ሺህ፯  ዓ.ም.             ቅፅ ፫ ፣ ቁጥር ፲፪
ኢትዮጵያውያን በታሪክ በተለያዩ ዘመኖች ከውጭ ወራሪዎች ጋር ተፋልመዋል። ሁሉም የውጭ ወራሪዎች ዘለቄታዊ ግባቸው ተመሣሣይ ነበር፦ ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛታቸው አድርገው ሕዝቧን በባርነት ቀንበር ሥር መግዛት። በዚህ ረገድ አረቦች ከ፰ኛው (ስምንተኛው) መቶ ክፍለዘመን ጀምሮ በእስልምና ኃይማኖት ማስፋፋት ሽፋን ተደጋጋሚ ወረራ ፈፅመዋል። ቱርኮችም በአረቦች እግር ተተክተው ከ፲፮ኛው (አሥራ ስድስተኛው) መቶ ክፍለ-ዘመን መግቢያ ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ ከሰሜን-ምዕራብ እና ከሰሜን አቅጣጫ በሱዳን፣ ከሰሜን-ምሥራቅ አቅጣጫ በቀይባሕር፣ እንዲሁም ከምሥራቅ እና ደቡብምሥራቅ አቅጣጫ ግራኝ አሕመድን በጦር ኃይል ድጋፍ እየሰጡ በግማሽ ቀለበት ኢትዮጵያን የከበበ ወረራ አካሂደው ነበር። የቱርኮች ወረራ ያከተመው አዳዲሶቹ ቅኝ ገዢዎች እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ እና ጣሊያን በ፲፱ኛው (አሥራ ዘጠነኛው) መቶ ክፍለዘመን አጋማሽ ጀምሮ ሲተኩ ነበር። ሆኖም ቱርኮች በኢትዮጵያውያን ላይ ትተውት የሄዱት የጥፋት ጠባሣ እስካሁን ድረስ አልጠፋም። በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ዘመን በ፲፰፻፷ (1860) ዓ.ም. እንግሊዞች «የታሠሩብንን እስረኞች እናስፈታለን» በሚል ሠበብ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አወጁ። በወቅቱ ከኢትዮጵያ መሣፍንት መካከል ለእንግሊዞች ወረራ ቀጥተኛ ድጋፍ ያደረጉት ጥሶ ጎበዜ (በኋላ አፄ ተክለጊዮርጊስ) እና ካሣ ምርጫ (በኋላ አፄ ዮሐንስ ፬ኛ) ነበሩ። የእንግሊዞች ወረራ ዓላማ እሥረኛ ማስፈታት ስላልነበረ፣ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በብዙ ድካም ያሰባሰቡትን ልዩ ልዩ ቅርስ የዘረፉትን ዘርፈው፣ አብዛኛውን አቃጥለው እና አውድመው ተመለሱ። እንግሊዞች ቆዬት ብለውም በአፄ ዮሐንስ ፬ኛ ዘመን ጣሊያኖች በቀይ ባሕር ዳርቻ ግዛት እንዲያገኙ እና ምፅዋን እንዲቆጣጠሩ አደረጉ፤ በኢትዮጵያም ላይ መሠሪ ጠላት ተከሉባት። እስከዛሬም ድረስ እንግሊዞች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን የጠላትነት ፖሊሲ አልሰረዙም።
ኢትዮጵያውያን ከጣሊያኖች ጋር ሁለት ጊዜ ተዋግተዋል፦ በመጀመሪያ በ፲፰፻፹፰ (1888) ዓ.ም. በአድዋ ሲሆን ከዚያም ከ፵(አርባ) ዓመታት በኋላ ለ፭(አምሥት) ዓመታት ከ፲፱፻፳፰ - ፲፱፻፴፫ (1928 – 1933) ዓ.ም.። ጣሊያኖችን በአድዋ ድል የነሣቸው በታላቁ የኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥት በዳግማዊ አፄ ምኒልክ የተመራው የኢትዮጵያ ጀግኖች ሠራዊት ነበር። ጣሊያኖች፣ እና በአጠቃላይም ቅኝ ገዢዎች፣ የአድዋን ድል ጠባሣ ለመፋቅ ለ፵(አርባ) ዓመታት ቂም ቋጥረው፣ አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ አድርገው ሲያበቁ በቤኔቶ ሙሶሎኒ በሚመራው የፋሽስት ጦር ኢትዮጵያን ፲፱፻፳፰ (1928) ዓ.ም. ዳግም ወረሩ። በ፭(አምስቱ) ዓመት ወረራ ፋሽስቶች ከአንድ ሚሊዮን የማያንሱ ኢትዮጵያውያንን ጨፍጭፈዋል። በተለይም በየካቲት ፲፪/፲፱፻፳፱ (12/1929) ዓ.ም. በአዲስ አበባ እና በአካባቢዋ ያደረሱት የግፍ ግድያ በታሪካችን ካጋጠሙን ዘግናኝ የጭፍጨፋ ድርጊቶች የሚስተካከሉት በግራኝ ዘመን እና አሁን በትግሬ-ወያኔ የአገዛዝ ዘመኖች የተፈጸሙት እና የሚፈጸሙት ናቸው።
የውጪ ወራሪ ኃይሎች በጣሊያኖች ፊታውራሪነት ሁለት ጊዜ ሲወርሩን ከመጀመሪያው በሁለተኛው የበለጠ ጉዳት እንዳደረሱብን ግልፅ ነው። ሆኖም የውጭ ኃይሎች በቀጥታ ወረራ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ቅኝ ለማድረግ እንዳልቻሉ ተገንዝበዋል። ስለዚህ በፋሽስት ዘመን በመለመሏቸው ባንዳ ሎሌዎቻቸው አማካይነት ኢትዮጵያን ለዘለቄታው ለማፈራረስ የሚስችላቸውን ተተኪ ዕቅድ ነድፈው ተግባራዊ ማድረግ ቀጠሉ። ለ፶(ሃምሣ) ዓመታት በአገር-በቀል ባንዶች በእነ ሻቢያ፣ ትግሬ-ወያኔ፣ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ሲዳማ አርነት ንቅናቄ፣ ወዘተርፈ አማካይነት በመጠቀም በአዲስ ዘይቤ ኢትዮጵያን ገዝግዘው፣ በ፲፱፻፹፫ (1983) ዓ.ም. አገራችንን ለመቆጣጠር በቅተዋል። ስለሆነም ላለፉት ፳፬(ሃያ አራት) ዓመታት ኢትዮጵያን ለሁለት ከፍለው የሚገዟት ሻቢያ እና የትግሬ-ወያኔ የሚያከናውኗቸው ተግባሮች ሁሉ ጌቶቻቸው የውጭ ኃይሎች የሠጧቸውን መመሪያ ተከትለው እንደሆነ ለአፍታም ሊዘነጋ አይገባም።
ልክ የዛሬ ዓመት በዚህ ዕለት ሞረሽ ወገኔ አንድ ወቅታዊ መግለጫ አውጥቶ ነበር፦ «የየካቲት ፲፪ ሠማዕታትን ስናስብ» የሚል። ከአንድ ዓመት በኋላ ሁኔታው ሲታይ፣ ኢትዮጵያውያን እንኳን ለእንደዚህ ዓይነቱ ጥሪ ተግባራዊ ምላሽ ሊሠጡ ቀርቶ፣ በተቃራኒው የትግሬ-ወያኔዎች የጥፋት ድርጊት ይበልጥ ተስፋፍቶ ይታያል። የእኛ የኢትዮጵያውያኑ ዝምታ እና ምንቸገረኝነት እንኳን ሕያዋንን ሙታንን ያስደነግጣል። ለመሆኑ በዚህ ዓይነት ቸልተኝነት ለተተኪው ትውልድ ምን እያወረስነው ነው? በዚህ ከቀጠልንስ ከተተኪው ትውልድ መካከል የየካቲት ፲፪ ቀን ፲፱፻፳፱ .ሠማዕታትንየሚዘክር ይኖረን ይሆንብሎ መጠየቅ አግባብነት ይኖረዋል። ስለሆነም ቸልተኝነቱ ይብቃ! ሠማዕቶቻችንን እናስብ፣ ለእነርሱም ተገቢውን ክብር እንስጥ!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

New Ethiopian music 2015

Tuesday, February 17, 2015

ምን እየጠበቅን ነው? «የትግራይ ሪፑብሊክ ድንበር አል-ወሃ ድረስ ነው»

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት    ማክሰኞ የካቲት ፲፩ ቀን ፪ሺህ፯  ዓ.ም.    ቅፅ ፫ ፣ ቁጥር ፲፩


የትግሬ ወያኔ በኃሣብ፣ በዕቅድ እና በተግባር ፀረ-ዐማራ፣ ፀረ-ኢትዮጵያ እና ፀረ-ኢትዮጵያዊ የሆነ ድርጅት መሆኑን ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ያረጋገጠው ሃቅ ነው። ሠሞኑንም ከመገናኛ ብዙሃን የሚደመጠው «የትግራይ ድንበር አል-ውሃ ድረስ ነው» የሚለው ወሬ የዚሁ የሚጠበቀው የትግሬ-ወያኔ ተከታይ እርምጃ እንደሆነ አያጠያይቅም።
ኢትዮጵያን የማፈራረሱ የንድፈ-ኃሣብ መሠረት የተጣለው በተለያዩ የውጭ ኃይሎች እንደሆነ ይታወቃል። ከእነዚህ መካከል ሮማን ፕሮቻዝካ የተባለው የኦስትርያ-ሐንጋሪ መሥፍን (Baron Roman Prochazka) ወጥነት ባለው መንገድ አዘጋጅቶ ያሠራጨው መጽሐፍ ዋና ተጠቃሽ ነው። የሮማን ፕሮቻዝካ መጽሐፍ ኢትዮጵያ በፋሽስት ጣሊያን በተወረረችበት በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. (1935 G.C.) በጀርመንኛ ቋንቋ «Abessinien: die schwarze Gefahr» በሚል ርዕስ፣ በኋላም በ1935 G.C. ወደ እንግሊዘኛ ተተርጉሞ «Abyssinia: The Powder Barrel» ተብሎ ወጥቷል። መጽሐፉ፣ በተለይም ዐማራውን፣ «የነጮችን የበላይነት የማይቀበል፣ ሌሎችን ነገዶች እና ጎሣዎች ጨቁኖ እና ረግጦ የሚገዛ» እና አልፎ ተርፎም «ኢትዮጵያን በአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ሥር እንዳትውል የሚያደርግ ቀንደኛ ጠላታቸው» እንደሆነ ያትታል። ሮማን ፕሮቻዝካ ባቀረበው የመፍትሔ ኃሣብ በግልጽ እንዳሠፈረው፣ ኢትዮጵያን ለማዳከም እና ለማፈራረስ በቅድሚያ የሥልጣን ምንጭ እና የአንድነት ምልክት የሆነውን ዘውዳዊ ሥርዓት መገርሰስ፤ የሕዝቡ መንፈሣዊ ሕይዎት የበላይ እና የዘውዳዊ ሥርዓቱ ርዕዮተ ዓለማዊ ክንድ የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ማዳከም እና ማጥፋት፣ እንዲሁም ራሱን በቋንቋ ክልል ያላደራጀ፣ በሠፊዋ ኢትዮጵያ ተሰራጭቶ የሚኖር የኢትዮጵያዊነት ብሔርተኝነት አቀንቃኝ የሆነውን የዐማራው ነገድ መጥፋት እንዳለባቸው ለፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ምክር ይለግሣል። የፋሽስት ጣሊያን መሪ የነበረው ሞሶሎኒም ሆነ የትግሬ-ወያኔ ያስፈጸሙት እና የሚያስፈጽሙት ይህንኑ ነው።
ፋሽስት ሞሶሎኒ ለ፭(አምስት) ዓመታት ከኢትዮጵያ አርበኞች የሚደርስበትን ጥቃት እየተከላከለ፣ በኢትዮጵያ ከተሞች ዙሪያ በቆየበት ወቅት ያከናወናቸው ተግባሮች የሮማን ፕሮቻዝካን ምክር ተከትሎ ነበር። በቅድሚያ ለ፫(ሦሥት) ሺህ ዘመናት የዘለቀውን ዘውዳዊ ሥርዓት አፍርሶ ኢትዮጵያን በይፋ የኢጣሊያው ንጉሥ ኢምቤርቶ ግዛት ተቀጥላ አደረጋት። የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኃይማኖትን በልዩ ልዩ መንገዶች አዳከመ። የአገሪቱን አስተዳደራዊ ክልል ቋንቋን መሠረት ባደረገ በ፮(ስድስት) ከፋፍሎ አደራጀ። «ዐማራ» ብሎ ከከለለው ግዛቱ ውጭ የሚኖሩ ዐማሮችን ዛሬ የትግሬ-ወያኔ እንደሚያደርገው አባረረ። «ጋላ ሲዳማ» ብሎ ዋና ከተማውን ጅማ ላይ አድርጎት በነበረው ግዛት ከ80,000 (ሰማኒያ ሺ) በላይ ዐማሮችን አባሯል። ልክ ዛሬ የትግሬ-ወያኔ በሚያደርገው መልኩ የአማርኛ ቋንቋ ከዐማራ ክልል ውጭ እንዳይነገር አድርጎ ነበር፣ ወዘተርፈ። በተመሣሣይ ሁኔታም የትግሬ-ወያኔ በቁጥር ከ፭(አምሥት) ሚሊዮን የማያንሱ ዐማሮች ገድሏል። «የዐማራ ክልል» ብሎ ከከለለው ግዛት ሣይቀር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዐማሮችን «አገራችሁ አይደለም» ብሎ አባሯል። የዐማርኛ ቋንቋን ለማጥፋት ሠፊ ዘመቻ ከፍቷል።
የትግሬ-ወያኔ ኢትዮጵያን የማፈራረሱ ዓላማው የሠከነ እንዲሆን ከሠራቸው መሠሪ ዋና ዋናዎቹ ሥራዎች መካከል «ሕገ መንግሥት» ብሎ ባዘጋጀው ሕገ-አራዊት በአንቀፅ 1፣ 2፣ 39 እና50-52 ያሠፈራቸው ናቸው።
አንቀጽ 1፦ «እኛ የኢትዮጵያ ብሔር/ብሔረሰቦች ሕዝቦች ….» ሲል ነው የሚጀምረው። ይህም አንድ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ዜጋ ወይም ሕዝብ እንዳይኖር፣ ሁሉም በነገዱ ዙሪያ ብቻ ተሰባስቦ ኢትዮጵያዊነትን አውልቆ እንዲጥል ከታለመ የሩቅ ግብ አኳያ የተቀመረ ለመሆኑ ማንም አይስተውም። ቀመሩም የኢትዮጵያ ማፍረሻ መሆኑን አንድ በሉ። በዓለም ላይ የሚገኙት ነገዶች እና ጎሣዎች ሁሉ  ተቀላቅለው በሚኖሩባት አሜሪካ፣ በርካታ ጎሣዎችን ባቀፉት ቻይና እና ሕንድ፣ ወዘተርፈ በሕገ-መንግሥታቸው «ሕዝብ» እንጂ «ሕዝቦች» አይሉም። በአንድ ሕገ-መንግሥት ሥር የሚተዳደር ሕዝብ፣ «ሕዝብ» እንጂ «ሕዝቦች» ተብሎ አይጠራም።
አንቀጽ 2፦ «የኢትዮጵያ ወሰን የብሔር /ብሔረሰቦቿ ወሰን ነው» ይላል። የኢትዮጵያ ዳር ድንበር በታወቁትና ዓለም በተቀበላቸው ቋሚ የድንበር መለያዎች የተቀመጠ አይደለም። የትግሬ-ወያኔ «ኢትዮጵያዊ መንግሥት» ሆኖ ለመዝለቅ ቢያስብና ፍላጎቱ ቢኖረው ኖሮ ይህን አንቀጽ በዚህ መልክ አያስቀምጠውም ነበር። በምትኩ በአንቀጹ ሊቀመጥ የሚገባው፦ «የኢትዮጵያ ወሰን በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት ዕውቅና ባገኘውና በካርታ ላይም ከምድር ወገብ በስተሰሜን ከ-እስከ ዲግሪ፣ ከግሪንዊች ሜሪዲያን ወደ ምሥራቅ ከ-እስከ ዲግሪ» ተብሎ መሆን ነበረበት። ይህን ግን እንዲሆን አልተፈለገም። ምክንያቱም እነዚህ ቋሚ መስፈርቶች ከተቀመጡ ሕዝቡ የአገሩን ወርድና ቁመት ሊያውቅ ነው። ወያኔ እየሸራረፈ ለፈለገው አካል የሚሰጠው መሬት «ለምን?» ሊባል ነው።
አንቀፅ 39 (1)፦ «ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው።» ይላል። ይህ ምን ማለት ነው? ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊ፣ ጋምቤላ፣ ወዘተርፈ ተብለው የተፈጠሩት አዳዲስ የባንቱስታን ግዛቶች በሕገ አራዊቱ አንቀጽ 39 በተሰጣቸው መብት መሠረት «በኢትዮጵያ ሥር አንቀጥልም፣ አብሮነት አንሻም፣ እንገነጠላለን» ካሉ የእነዚህ ክልሎች «ዜጋ» ከሚባለው ውጪ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በጉዳዩ ላይ ድምፅ የማሰማት መብት የለውም ማለት ነው። በእርግጥ የዚህ አንቀጽ በሕገ-አራዊቱ መካተት ተጠቃሚ ማንም ሣይሆን የትግሬ-ወያኔ ብቻ ነው። ምክንያቱም የመገንጠል ጥያቄ የሚያነሱ ሌሎች ኃይሎች ለግንጠላው ማሟላት የሚገባቸውን ጉዳዮች በቀላሉ ማሟላት አይችሉም። እያንዳንዱ ክልልም ለይስሙላ በራሱ ክልል ተወላጅ የሚገዛ ቢሆንም፣ እኒህ አሻንጉሊት ገዢዎች ከትግሬ-ወያኔ ፍላጎት ውጭ ምንም ነገር ማድረግ አይችሉም። ስለዚህ የዚህ አንቀጽ ዋና ዓላማ ወደፊት የምትመሠረተዋን የትግራይ-ትግሪኝ ሪፑብሊክን ለመመሥረት «ሕጋዊ መሠረት» ለመስጠት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
ከአንቀጽ 50-52፦ የሥልጣን መዋቅሩን የሚያመለክቱ አንቀጾች ናቸው። በእኒህ አንቀጾች እንደተጠቀሰው ከፍተኛ የሆነው እና በአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ላይ የመወሰን ሥልጣን ባለቤት ያለው «ፓርላማ» ተብዬው ነው። ሆኖም በተግባር የሚታየው ሃቅ ግን በኢትዮጵያ ከፍተኛውን ሥልጣን የያዘው «ፓርላማው» ሣይሆን፣ በሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች በአምባገነንነት ተጨምድዶ የተያዘ መሆኑን ነው። ስለሆነም፥ ፓርላማ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እና ኢሕአዴግ የሚባሉት መዋቅሮች የተሞሉት የትግሬ-ወያኔ ፖሊት ቢሮ አባላት ወስነው የሰጡዋቸውን «ለምን? እንዴት?» ሣይሉ በሚያስፈጽሙ ታዛዥ አሽከሮች ነው።
በሌላ በኩል የትግራይ ግንጠላ የማይቀር እና የትግራይ-ትግሪኝ ሪፑብሊክ ምሥረታ ሁኔታ እየተመቻቸ እና የማይቀር መሆኑን በቅርቡ ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን መድኃኔ የተባሉ « ይኸውና! ኤርትራ ሞተች። ትግል ለሀገር ትንሣዔ!» በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ አያሌ ማስረጃዎችን በመዘርዘር ግልጽ ኣድርገውታል። ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን የትግሬ-ወያኔ የትግራይ-ትግሪኝ ምሥረታ ዕውን ለማድረግ እየሠራ እንደሆነ የሚከተሉትን ማስረጃዎች ይጠቅሳሉ።
1.      ሜንሆት ወልደማርያምን በመጥቀስ «ሕወሓት የትግራይ ነፃ ሀገር ኅልውና ለማመቻቸት ሲል የብሔር ብሔረሰቦች የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚል መሠረት ድንጋይ አስቀምጧል። ይህም በሀገሪቱ የጸደቀውን (ኤትኒክ ፌዴራሊዝም) መሠረት ባደረገው ሕገመንግሥት የተደገፈና የታቀፈ እንዲሆን ተደርጓል። ትልቁ ዓላማም ሀገረ ትግራይን ለማቋቋም አንዳንድ የኤርትራ ቦታዎችን ቆርሶ ወደ ትግራይ ማካለል ነው።»( ገጽ 12)
2.     «አቶ ስብሐት የባድመ ቀውስ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ፣ ኢሣያስ ሰላማዊ መፍትሔ አልቀበልም ብሎ አፈንግጦ በነበረበት ጊዜ፣ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ የኃይል ርምጃ እንዳትወስድ የሚቻለውን ያህል አድርጎ ነበር። አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር መዋጋት አልነበረባትም ባይ ነው። የአቶ ስብሐት ነጋ አቋም መነሻው የኤርትራና የትግራይ ዝምድና ሕያው ነው የሚል አመለካከት ነው። አቶ ስብሐት «ትግራይ እኮ ካለ ኤርትራ አትኖርም፣ ኤርትራም እንደዚሁ» (ገጽ 13) የሚለው አክራሪ እምነቱ የትግራይ መገንጠል አይቀሬነት የሚያመልክት አቋም እንደሆነ ጸሐፊው ያምናሉ። ይህ የስብሐት አቋም ወይም አባባል ደግሞ ዝም ብሎ ለማለት ያህል የተባለ ሳይሆን፣ ከመለስ ሞት በኋላ በወያኔ መሪዎች አካባቢ የትግራይ መገንጠል እና ከኤርትራ ጋር ሊኖራት የሚችል ዝምድናን በሚመለከት ውስጥ ለውስጥ እየተካሄደ ያለው መመሣጠር መገለጫ መሆኑን ያስረዳል።
3.     «ወያኔ ወይም አመዛኙ የአመራር ክፍል በኢትዮጵያ ሥልጣን ለመቆጣጠር ካልተሳካለት ለብቻው ተገንጥሎ ነጻ ሪፑብሊክ ለመመሥረት ዕቅድ ያለው ነው።» (ገጽ 20)
4.     «ሪፈረንደም በሚል ስም የተካሄደው የይስሙላ ሂደት ትግራይ ከኢትዮጵያ መገንጠል ለሚችል የረጅም ጊዜ ዕቅድ መንገድ የሚያመቻችና የሚጠርግ እንጂ፣ የኤርትራን ሕዝብ መብትና ጥቅም ለማስከበር ተብሎ በቅንነት የተቀናጀና የተደራጀ አልነበረም።» (ገጽ 27)
5.     ተስፋጽዮን እንደጠቆሙት የትግሬ-ወያኔዎች «ሥልጣን ላይ ከሌሉ የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚፈቅደውን ሕገ መንግሥታቸውን ተጠቅመው ትግራይ ከኢትዮጵያ በኃይል ለመገንጠል ሊሞክሩ ነው። ይህንን ዕውን ለማድረግ ደግሞ አስቀድመው የቀረችውን ኢትዮጵያ በረቀቀ መንገድ መበታተን፣ አለያም የሕዝቧን እና የግዛቷን አንድነት የሚያዳክምና የሚያላላ ተግባር ከመፈጸም ወደኋላ አይሉም።» በማለት የትግራይ ሪፑብሊክን የመመሥረቱ ሁኔታ በከፍተኛ ሚስጢር ተይዞ እየተሠራበት መሆኑን ሰሚ ካለ ነግረውናል።
የትግሬ-ወያኔዎች ቀደም ብለው ከ፲፱፻፹፫ ዓም ጀምሮ፣ ከሰሜን ጎንደር እና ሰሜን ወሎ አውራጃዎች የዐማራ ተወላጆችን ገድለው፣ አፈናቅለው እና ማንነታቸውን በግድ አስቀይረው ሠፊ የትግራይ ግዛት መስርተዋል። ሠሞኑን ደግሞ ከተለያዩ የብዙሃን መገናኛ ተቋሞች የተሠራጩ ይፋ መግለጫዎች እንደሚያመለክቱት የትግራይ ግዛት እስከ አል-ውሃ (ወሎ) የሚዘልቅ እንደሆነ ተገልጿል። ወደፊት ደግሞ አሰብን ያካተተ ግዛት ያለው የትግራይ-ትግሪኝ ሪፑብሊክ ለመመሥረት በሠከነ ሁኔታ እየሠሩ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። የትግሬ-ወያኔ አገር ለማፍረስ ይህን ያህል ርቀት ሲጓዝ፣ «ኢትዮጵያዊ ነኝ» የሚለው ኃይል ግን ይህንን እንቅስቃሴ የሚገታ አንዳችም ተጨባጭ ሥራ ካለመሠራቱም በላይ፤ የአገሪቱን የአፈራረስ ሂደት በቅጡ የተረዳም ሆነ ሊረዳ የሚሻ ወገን ያለ አይመስልም። እነዚህ ሁሉ በአንድነት ተጠቃለው ሲመዘኑ ኢትዮጵያ እንደ አገር መኖሯን የሚያመለክቱ አይደሉም። ዕውነታው አገሪቱ በ፳፬(ሃያ አራት) ዓመታት አዝጋሚ የመፈራረስ ሂደት፣ በሰመመን መልክ እየተበታተነች መሆኑን ነው። ይህ ደግሞ በዕቅድ እና በሰከነ መልኩ በኢትዮጵያ ጠላቶች የተቀነባበረ ረጅም ጊዜ የወሰደ ሂደትን የተከተለ መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለበትም።
ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን የሚወዱና የሚያፈቅሩ ዕውነተኛ ዜጎች፣ «ምኗን ሰዳ ምኗን ጨበጠች» እንዳይሆን ነገሩ፣ ከአሁኑ ተቻችሎ እና ልብ ለልብ ተዋውጦ ይህ ዘረኛ ቡድን የፈለውን ሣያደርግ፣ ኢትዮጵያን የምንታደግበትን መንገድ በጋራ መላ እንድንል ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት የተለመደ ጥሪውን ያቀርባል። ከሁሉም በላይ የጥፋት ዘመቻ የተከፈተበት የዐማራው ነገድ ተወላጆች ለዚህ ጥሪ የሚያቀርቡት አሉታዊ ምክንያት ሊኖር አይገባም። ጥሪው የሞት፣ የሽረት ነውና ኅልውናችን በማስጠበቅ የኢትዮጵያን ትንሣዔ ዕውን የማድረግ ትውልዳዊ ኃላፊነታችን ልንወጣ ይገባል።
ዐማራውን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደግ!
ፈለገ አሥራት የትውልዳችን ቃል ኪዳን ነው!
ኢትዮጵያ በጀግና እና ቆራጥ ልጆቿ መስዋዕትነት አንድነቷ እና ነፃነቷ ተከብሮ ለዘለዓለም ትኖራለች!

Wednesday, February 11, 2015

ተሂዶበት ከሚፈለገው ቦታ ባላደረሰ መንገድ ተመላልሶ መጓዝ ችግሩ የመንገዱ ሣይሆን የተጓዡ ነው

ሰሞኑን የትግሬ-ወያኔ እጀታ የሆነው የምርጫ ቦርድ፣ በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና በአንድነት ለፍትሕና ዲሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) ላይ «ከምርጫ ውድድር የማገድ» ውሣኔ ማሣለፉን ሰምተናል። ይህም ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊስ፣ አቃቢ ሕግ፣ መከላከያ ሠራዊቱ እና መሰል በ«ሕገ-መንግሥቱ ተቋቋሙ» የተባሉት ተቋሞች በሞላ የወያኔ ሕዝባዊ ድርጅቶች መሆናቸውን በይፋ እና በማያሻማ መንገድ ከታዩባቸው አያሌ ተግባሮች መካከል አንዱ ሆኖ የሚጠቀስ ነው። የምርጫ ቦርዱ ውሣኔ በራሱ ምርጫ ቦርድ የወያኔ ሕዝባዊ ድርጅትና እጀታ ከመሆኑ የመነጨ ብቻ ሣይሆን፣ የተቃዋሚው ጎራ ደጋግሞ በሄደበት እና ምንም ዓይነት ውጤት ባላስመዘገበበት መንገድ መጓዙ ጭምር እንደሆነ ሊስተዋል ይገባል።

የትግሬ-ወያኔ በምርጫ ተሸንፎ ሥልጣን እንደማይለቅ ያለፉት አራት የይስሙላ ምርጫዎች ከበቂ በላይ ነቃሾች ናቸው። ይህን በተመለከተ የ1997ቱን የምርጫ ውጤት ተከትሎ የትግሬ-ወያኔ በወሰደው የድምፅ ነጠቃ፣ ታዛቢ የነበሩት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር አቶ መለስን ለማለስለስ ባደረጉት የማግባባት ሙከራ ያረጋገጡት ሃቅ ነው። አቶ መለስ በወቅቱ የሰጣቸው መልስ፦ «ኢሕአዴግ በምርጫም ሆነ በኃይል ሥልጣን ከለቀቀ የሚጠብቀን አንድ እና አንድ ብቻ ነው። ይኸውም በአገር ክህደት ተከሰን ወህኒ መውረድ ነው። በመሆኑም ለ፲፯(አሥራ ሰባት) ዓመታት አፈር ግጠን የጨበጥነውን ሥልጣን በሕዝብ ድምፅ አንለቅም።» ሲል ነበር እቅጩን እና የማይለወጠውን የትግሬ-ወያኔን ዓላማ የገለጸው። በተመሣሣይ ሁኔታ የሕወሓት እና የኢሕአዴግ የፖሊት ቢሮ አባል የነበረው አቶ ገብሩ አሥራትም «ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ» በሚለው መጽሐፉ የሚነግረን ይህንኑ ነው። ስለዚህ ምርጫ ቦርድ ሰሞኑን የሰጠውም ውሣኔ የዚሁ ተከታይ አካል በመሆኑ፣ ድርጊቱ አስገራሚም፣ አስደንጋጭም አይሆንም። ባለፉት ፳፬(ሃያ አራት) ዓመታት የኖርንበት ዓለም የታዘበው ዕውነታ ነውና። አስገራሚና አስደንጋጭ የሆነው ተቃዋሚው በወያኔ ሁለንተናዊ ፍላጎት ቁጥጥር ሥር መሆኑን አለመገንዘቡ ነው። እኒህ ተቃዋሚዎች ጉዟቸው ያልተለወጠ እና በየአምስት ዓመቱ በሚደረግ የምርጫ ዘመቻ የተገዛ ነው። ይህ ጉዞ ለውጤት ያላበቃ መሆኑ ተደጋግሞ እየታዬ፣ ውጤት እንደማያስገኝ በታወቀ መንገድ መጓዙ፣ ችግሩ ከመንገዱ ሣይሆን፣ ከተጓዡ እንደሆነ ትግሉ የሚገኝበት ሁኔታ ያሣያል። ስለሆነም ተቃዋሚ ኃይሎች ከ1997ቱ የምርጫ ሂደት እና ውጤት ከታዩት አዎንታዊ እና አሉታዊ የጉዞ አቅጣጫዎች ትምህር የቀሰሙ አይመስልም።

ሁለተኛው የተቃዋሚ ድርጅቶች መሠረታዊ ችግር በአደረጃጀታቸው ላይ ያጠነጠነ ነው። የትግሬ-ወያኔ በማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ብቻ ሣይሆን በዕድሮች ሣይቀር የራሱን ሥውር መዋቅር አስርጎ አደራጅቷል። ሰሞኑን በመኢአድ እና በአንድነት ላይ የተከሰተው ችግር ግን፣ ተቃዋሚ ድርጅቶች የትግሬ-ወያኔን የሤራ ስልት ባለመገንዘብ ከነ አየለ ጫሚሶ ዓይነት ሠጎ ገቦች ድርጅቶቻቸውን ማጽዳት አለመቻላቸውን ቁልጭ አድርጎ ያሣያል። ሰለዚህ የአደረጃጀት ሥልታቸው የወያኔን ሠርጎ ገቦች ሊያንተረትር በሚችል መልክ እስካልተቃኘ ድረስ፣ በምንም ሁኔታ የትግል ጉዞ አቅጣጫቸው በወያኔ እና በአጋሮቹ ላይ ተጽዕኖ ሊያሣድር አይችልም። ይህም ብቻ አይደለም፤ ተቃዋሚው የሙጥኝ ብሎ የያዘው «በሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ ብቻ የትግሬ-ወያኔን በምርጫ አሸንፈን ሥልጣን እንይዛለን» የሚለውን ብቸኛ የትግል መሣሪያው አድርጎ መያዙ፣ ለትግሬ-ወያኔ ሠርጎ መግባት የተመቻቸ ሁኔታ ከመፍጠሩ ባሻገር፣ የነቁትን የኅብረተሰብ ክፍሎች በቀላሉ የአገዛዙ ዒላማ እንዲሆኑ አድርጓል። ይህም ትግሉን ተተኪ መሪዎች በማሣጣት መሪ አልባ በማድረጉ፣ የሕዝቡን የወኔ ሥንቅ እንዳሟጠጠ በድርጅቶቹ ውስጥ በቂ ትኩረት የተሰጠው ያለመሆኑን ያመለክታል።

ተሂዶበት ከሚፈለገው ቦታ ባላደረሰ መንገድ ተመላልሶ መጓዝ ችግሩ የመንገዱ ሣይሆን የተጓዡ ነው
ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ረቡዕ የካቲት ፭ ቀን ፪ሺህ፯ ዓ.ም. ቅፅ ፫ ፣ ቁጥር ፲
የተቃዋሚው ኃይል የትግሬ-ወያኔን ባሕሪ የሚመጥን የትግል ሥልት መከተል ባለመቻላቸው፣ ወያኔ «ግሞ» ሲል «ጥንቦ» ማለት አልቻሉም። በተደጋጋሚ በአገር ቤት ካሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚደመጠው የትግል ስልት፦ «በሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ ብቻ የትግሬ-ወያኔን በምርጫ አሸንፈን ሥልጣን እንይዛለን» የሚል ነው። ሆኖም የሰላማዊ ትግል ሥልት በምርጫ ዘመቻ ብቻ የተገደበ አይደለም። የምርጫ ዘመቻ ለሰላማዊ ትግል ጠቃሚ የሚሆነው ዲሞክራሲያዊ ተቋሞች የሚባሉት ማለትም፦ ነፃ እና ገለልተኛ የሆነ የምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶች፣ አቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ፣ የመከላከያ ሠራዊት እና ወገንተኛ ያልሆኑ የብዙኃን መገናኛ ተቋሞች መኖር፣ ወዘተርፈ፣ በአጠቃላይ የሕግ የበላይነት ሰፍኖ ከማንም ተፅዕኖ ውጭ በነፃ የመሥራት የዜግነት መብት ሲረጋገጥ ነው። እነዚህ ተቋሞች በሌሉበት ሁኔታ ግን፣ በምርጫ ፖለቲካ ወያኔን ከሥልጣን እናወርዳለን ብሎ ምርጫን በብቸኛ የትግል መሣሪያነት የሙጢኝ ብሎ መያዝ፣ ታጋዩ ሕዝብ ሥቃይን እና በደልን ተለማምዶ የ፵(አርባ) ቀን ዕድሌ ነው ብሎ እንዲያምን እና ለወያኔ አገዛዝ ምቹ እንዲሆን ሠፊ በር የሚከፍት መሆኑ በግልፅ ሊታመንበት ይገባል። በተግባርም የሚታየው ይኼው ነው። የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ መዋቅር፣ የፍትህ አካሎች እና የብዙሃን መገናኛ ተቋሞች በአንድ ዘረኛ ቡድን ፍላጎት እና ቁጥጥር ሥር በዋሉበት ሀገር፣ በምርጫ ሥልጣን እረከባለሁ ማለት ሸንበቆ ያፈራል፣ በቅሎ ትወልዳለች፣ ዝንብ ማር ትጋግራለች፣ ፀሐይ በምሥራቅ ትጠልቃለች እንደማለት ይቆጠራል። እንደሞረሽ-ወገኔ እምነት፣ ሰላማዊ ትግሉ የተለየ መንገድ መከተል ይኖርበታል። ወቅታዊ የትግሉ መፈክር «ለዲሞክራሲ፣ ለዕኩልነት እና ለብልጽግና» ሣይሆን ቅድሚያ ለነፃነት ትግል መሆን አለበት። አገር እና ሕዝብ ሳይኖሩ፣ ዲሞክራሲ እና ዕኩልነት ሊታሰቡ የሚችሉ ጉዳዮች አይደሉምና!

በመሆኑም፣ የተቃዋሚው ጎራ፣ የትግሬ-ወያኔን እንደተኩላ ከብቦ የሚቦጫጭቅበትን፣ አጠቃላይ ሕዝባዊ እንቢተኝነትን የትግሉ መርህ አድርጎ ሊንቀሣቀስ ይገባዋል። ስለዚህ ቀዳሚው የትኩረት አቅጣጫ መሆን ያለበት በየአካባቢው ያለውን የትግሬ-ወያኔን የስለላ መዋቅር በመበጣጠስ፣ ሕዝቡ የራሱ አለቃ የሚሆንበትን ዘዴ በመሻት፣ የትግሬ-ወያኔን እና አጋሮቹን ለነፋስ በመስጠት፣ የአገዛዝ ዕድሜያቸውን ለማሳጠር መንቀሣቀስ ነው። ይህ ደግሞ ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከመሀል እስከዳር ሕዝቡን በማደራጀት በእንቢተኝነት ስሜት እንዲነሣ ማነቃነቅ ያስፈልጋል። የትግሬ-ወያኔ አፋኝ ቡድን የኃይል መከፋፈል የሚፈጠርበት፣ ለቅልብ ጦሩ ሆድ መሙያ የሚከፍለው በጄት የሚያጣበት፣ በገዥው ቡድን መካከል የኃሣብ መከፋፈል የሚፈጠርበት፣ የማስፈጸም አቅሙ የሚሟሽሽበት፣ እርስ በርሳቸው የሚጠራጠሩበት ሁኔታን የሚፈጥር ሥራ መሠራት አለበት። ለዚህም በደህንነቱ፣ በሠራዊቱ፣ በፖሊሱ፣ በቢሮክራሲው መሀል ሠርጎ በመግባት ዓላማ እና ዕቅዳቸውን ማክሸፍ ያስፈልጋል። ሕዝቡም «ላልወከልነው አካል ግብር አንከፍልም፣ የእኛ ባልሆኑ ተቋሞች አንገዛም፣» የሚለውን ስሜት እና እምነቱን ሊያጎለብት ይገባል። በትግሬ-ወያኔ የተለያዩ የንግድ እና የአገልግሎት ተቋሞች፣ ማለትም፥ የትራንስፖርት፣ የሆቴል፣ የንግድ ቤቶች እንዳይጠቀም በልዩ ልዩ መንገዶች በማስተማር ወያኔ እና አባሎቹን ከማናቸውም ማህበራዊ እና ባህላዊ እንቅስቃሴዎች በማግለል ብቻቸው እንዲቆሙ መደረግ አለበት። «መጡብን» ሳይሆን፣ «መጣንባችሁ» ሊባሉ ይገባል። ከእንግዲህ ተቃዋሚው ጎራ ሙሾ ማውረዱን ማቆም አለበት። መርዶ የሽንፈት እንጂ፣ የድል ምልክት ባለመሆኑ፣ «እንዲህ ሆን፣ እንዲ,ህ ተደረገን» የሚሉት እሮሮዎች ሊገቱ ይገባል።

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት የትግሬ-ወያኔ በሁለቱ የሰላማዊ ትግል አራማጅ ድርጅቶች ላይ የወሰደውን እርምጃ የተመለከተው ከትግሬ-ወያኔ ጉዞ እና ዓላማ አንፃር የሚጠበቅ እንጂ፣ ዱብ ዕዳ እና እንግዳ ነገር አድርጎ አይደለም። በአንፃሩ «ማሽላ ሲያር ይስቃል» እንዲሉ፣ ይህ እርምጃ ለፀረ-ወያኔ ትግል እልህ፣ ቁጭትና የመጠቃት ስሜትን የሚፈጥር ነው ብለን እናምናለን። ስለሆነም የተቃዋሚው ጎራ በአንድ ብሔራዊ ዓላማ ዙሪያ እንኳን መሰባሰብ ባይችል፣ በፀረ-ወያኔ አቋሙ በአንድ ግንባር ወይም ኅብረት ሥር እንዲሰለፍ ሠፊ በር የከፈተ ያህል ይቆጥረዋል። ስለዚህ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ የሚገኘው ተቃዋሚ ኃይል ከምንጊዜውም በበለጠ ተቀራርቦ በመነጋገር በትግሬ-ወያኔ አገዛዝ ላይ የተጠናከረ እና ሁሉን- አቀፍ ትግል እንዲያደርግ በኢትዮጵያ እና
በኢትዮጵያዊነት ስም ጥሪያችንን እ,ናቀርባለን።


ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደጋለን!
ፈለገ አሥራት የትውልዳችን ቃል ኪዳን ነው!
የትግሬ-ወያኔ ዘረኛ ቡድን ነው፤ በመሆኑም መወገድ አለበት!